>

በደብረ ኤልያስ ፋኖን በማገዝ የተጠረጠሩ ገዳማት በጥይት ተደበደቡ (ጌጥዬ ያለው)

በደብረ ኤልያስ ፋኖን በማገዝ የተጠረጠሩ ገዳማት በጥይት ተደበደቡ 

ጌጥዬ ያለው

በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ‘ፋኖን  ታግዛላችሁ፣ ለፋኖ ትጸልያላችሁ” የተባሉ ገዳማት በመንግሥት ታጣቂዎች በጥይት ተደብድበዋል። ባለፈው ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የምራተ ብፁዓን አቡነ ተክለ ኃይማኖት አንድነት ገዳም ተኩስ ተከፍቶበት ውሏል። በተኩሱ በምህላ ላይ የነበሩ ገዳማውያን አባቶች የተረበሹና መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው የተስተጓጎለ ሲሆን የሰው ሕይዎት አልጠፋም። የተኩሱ አላማም በገዳማውያኑ እና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ መንግሥታዊ ሽብር መፍጠር እንደነበር የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል። 
የደብረ ኤልያስ ወረዳ ፅህፈት ቤት ያደራጃቸው ወጣቶች ቤተልሄሙን እና የገዳሙ ቅጥር ግቢ አካል የሆነውን ደን በእሳት አቃጥለዋል። ገዳሙ በወረዳው የአባይ ሸለቆ በረሃማ ቦታ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ‘ፋኖን ይደግፋል’ በሚል ሕጋዊ የይዞታ መሬቱን ለመንጠቅና ፈፅሞ ለማፍረስ መንግሥታዊ ሙከራ እየተደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ የመሬት ይዞታውን በተመለከተ ገዳሙ በሕግ ከሶ ከመንግሥት ጋር ሲከራከር የቆየ ሲሆን የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍርድ ቤት አሁን በገዳሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለው መሬት በሙሉ የምራተ ብፁአን አቡነ ተክለ ኃይማኖት አንድነት ገዳም መሆኑን ወስኗል። በወረዳው የሚገኘው የብሄረ ብፁአን አፄ መልክዓ ሥላሤ አንድነት ገዳምም ተመሳሳይ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል። 
የትግሬ ወራሪዎች ማዕከላዊ መንግሥቱን ተቆጣጥረው በነበረበት ጊዜ ዋልድባ ገዳምን አፍርሶ የእርሻ ማሳ የማድረግ ሙከራ እንደነበር ይታወሳል። መነኩሳቱ “ለፋኖ ትፀልያላችሁ” እየተባሉ ሲገረፉ፣ ሲታሰሩና ፍፁም አረመኔያዊ የሆኑ ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙባቸው እንደቆዩ አይዘነጋም።

Filed in: Amharic