>

የዐምሐራ ሕዝባዊ ግምባርና የተፈጠሩ ብዥታዎች (ከይኄይስ እውነቱ)

የዐምሐራ ሕዝባዊ ግምባርና የተፈጠሩ ብዥታዎች

ከይኄይስ እውነቱ

የዐምሐራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ላይ ላለፉት 32 የግፍና የሰቈቃ ዓመታት በተለይም በቅርቡ 5 ዓመታት የዘር ማጥፋት፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የጦር ወንጀሎች፣ ዘር የማፅዳት ወንጀል፣ በሚሊዮኖች ከቤትና ንብረት መፈናቀል፣ ግዙፍ ዝርፊያዎች፣ በቤተ እምነቶቹ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በማድረግና ባሠማራቸው ቅጥረኞች አማካይነት ሊጠገን የማይችል በታሪክ ተወዳዳሪ የሌላቸው ጥፋቶች፣ በረሃብና በኑሮ ውድነት፣ ነውሮችና ማዋረዶች በጭራቅ ዐቢይና ኦነጋዊ አገዛዙ ሲፈጸምበት ከቆየ በኋላ ጐሣዊው የፋሽስት አገዛዝ የዚህ ኹሉ ጥፋት ማሳረጊያና የዐምሐራን ሕዝብ ከምድረ ገፅ ለማጥፋት አልሞ፣ ሕዝቡን እንደ ‹ብሔራዊ ሥጋት› በመቊጠር በይፋ ጦርነት ካወጀበት ወራት ተቈጥረዋል፡፡ ሕዝባችንም ከተቃጣበት ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ራሱን ለመከላከልና ህልውናውን ለማስከበር የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡ ባጭሩ ሕዝባዊ ፍልሚያው ህልውናዊ የመከላከያ ትግል ነው፡፡ ሰማዩ ከረዳን ደግሞ ወደ ማጥቃት የማይሸጋገርበት አንዳች ምክንያት የለም፡፡

በቅርቡ ደግሞ በእጅጉ ሲጠበቅ የቆየውንና የህልውናውን ተጋድሎ የሚያስተባብርና የሚመራ መነሻችን የዐምሐራ ህልውና፤ መድረሻችን የኢትዮጵያ አንድነት በሚል ‹‹ የዐምሐራ ሕዝባዊ ግምባር›› የሚባል አደረጃጀት መፈጠሩ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህን ወቅት ስለ ግምባሩ መናገር ጊዜው ገና ቢሆንም ዓላማውን በሚመለክት ግን ከግምባሩ መግለጫና በሚመለከታቸው አካላት በሜዲያ ከተሰጠው ማብራሪያ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ይህ ግምባር  በቅድሚያ የዐምሐራን ሕዝብ በሕይወት የመኖር እና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ቀጣይነቱን በአስተማማኝ ሁናቴ ማረጋገጥ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዓላማው ሲሆን፤ በቀጣይም በሁለተኛው ምዕራፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት÷ የአገር ሉዐላዊነትና የግዛት አንድነት ተከብሮ እንዲቀጥል ከሚፈልጉ የኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ አገራችንን ምድራዊ ሲዖል ያደረጓትን ኦነጋዊ አገዛዝና ተባባሪዎቹን ወያኔ ሕወሓትና የዚህ አገራዊ ጥፋት ግበረ አበሮችን በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር በማጥፋትና ለጐሣ አገዛዙ መሠረት የሆነውን የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› በማስወገድ ለሁላችን እኩል የምትሆን ኢትዮጵያን በጋራ ለመመሥረት የሚያስችል መደላድል መፍጠር ነው፡፡ ግምባሩ በታዋቂው ኢትዮጵያዊ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋችና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ጓዶቹ የሚመራ ሲሆን፤ ባገር ውስጥ ለሚደረገው ሁለ ገብ ትግል ሁለንተናዊ ድጋፍ (በዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በገንዘብ፣ በማቴሪያል፣ በሎጂስቲክስ፣ ሙያዊ ምክር ወዘተ.) የሚያደርግ ከኢትዮጵያ  ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን የሚያስተባብር የድጋፍ ሰጭ ኃይል አደራጅቷል፡፡ የድጋፍ ሰጭ ኃይሉን በበላይነት የሚመሩት ደግሞ ስመ ጥሩው ኢትዮጵያዊ ምሁር በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ÷ በተለይም በአፍሪቃ አገሮች የግጭቶች አያያዝ ሥራ አመራር ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ባላቸው÷ ለዚሁ ዓላማ የአፍሪቃ የስትራቴጂ እና ጸጥታ ጥናት ተቋም መሥርተው በአስፈጻሚ ዲሬክተርነት የሚመሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ የግምባሩም መሪ ሆነ በውጭ የሚገኘውን የድጋፍ ሰጭ ኃይሉን የሚያስተባብሩት እኒህ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነታቸውና ባገራዊ አስተዋጽኦቸው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያምንባቸውና የምንኮራባቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ ስለ ግምባሩ ከመግለጫው በተጨማሪ የድጋፍ ሰጪው ኃይል አስተባባሪዎች በተለያዩ ሜዲያዎች ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

ለዐምሐራው ሕዝብ ኢትዮጵያዊነትን መስበክ ምጥ ለእናቷ አስተማረች ይሆንብናል፡፡ ይህ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ስላለው ከደምና አጥንት ጋር የተዋሐደ አቋም እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ነቅዕ የሌለበት መሆኑ ምስክሩ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ስም ለመታለል ዝግጁ በመሆን ህልውናው በቋፍ እስከሚሆን ድረስ ለ32 ዓመታት ያሳየው ትዕግሥት ሕያው ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ሲል የዘር ፍጅት፣ የዘር ማፅዳት፣ የጦር ወንጀል፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ ከቤት ንብረቱ በገፍ በመፈናቀል፣ ለአስከሬኑ እንኳን ክብር አጥቶ የአውሬ ሲሳይ ከመሆን የተረፈው እንደ ቆሻሻ በግሬደር እየተዛቀ በጅምላ መቃብር የተጣለ ተሳዳጅና ተቅበዝባዥ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በመሆኑም በተቃዋሚነት፣ በጋዜጠኝነት፣ በማኅበራዊ አንቂነት ስም፣ በለየለት አድር ባይነት  ከዘረኛው ፋሽስት አገዛዝ ጋር መቀመጫቸውን ገጥመው ይህን ታላቅ ሕዝብ ሲበድሉ የኖሩና በተፈጸመበት ግፍ  ሁሉ ተባባሪ የነበሩ ድርጅቶች፣ የከሸፉ ፖለቲከኞችና ሆድ አደሮች በኢትዮጵያዊነት ስም የተጀመረውን ሕዝባዊ ትግል ለማኮላሸት ወይም ቀዝቃዛ ውኃ ለመቸለስ ዳር ዳር ሲሉ ማስታመም የነሱ ተባባሪ መሆን ነው፡፡ ወገኖቻችን ውድ ሕይወታቸውን እየሰጡ፣ ቤት ንብረታቸው ብቻ ሳይሆን የተቀደሱ የአምልኮ ስፍራዎቻቸው በከባድ መሣሪያ ለውድመት እየተዳረገ ባለበት በዚህ ቀዊጢ ሰዓት እነዚህ እንቶ ፈንቶ ለሚያወሩ የእንቅፋት ድንጋዮች ጆሮውን የሚሰጥ ጤነኛ አይደለም፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ እንደሚለው ‹‹ወዮ ለዓለም… ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፤ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ በእኔ ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ደንጊያ ባንገቱ ታሥሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር፡፡›› ማቴ. 18÷6-7፡፡ ሐሳባችሁ በጎ ከሆነ ከማሰናከያነት ተቆጠቡ፡፡ በሕዝብ ዘንድ መደናገርን አትፍጠሩ፡፡ ላገለገላችሁት ፋሺስታዊ አገዛዝ ዳግም መሣሪያ ከመሆን ተቆጠቡ፡፡

ብዙዎቻችን የዐምሐራው ወገናችን በማንነቱ መደራጀት ጕረሮአችን ላይ እንደተሰነቀረ አጥንት ሆኖብን ሲፈታተነን ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ ለኢትዮጵያዊነቱ ያለን ስሜት እዚህ ድረስ የሚተናነቀን በመሆኑ፡፡ ታዲያ ከክሽፈቱ ያላገገመ ሁላ የኢትዮጵያዊነትን ‹ሀ ሁ› ላስቆጥራችሁ ሲለን ወግድ ሰይጣን ልንለው ይገባል፡፡ ከምር የዐምሐራውን ሕዝብ የህልውና ትግል የሚደግፍ ከሆነ ባለበት ሆኖ በሎሌነት ሲያገለግለው የነበረውን ጐሣዊ የፋሽስት አገዛዝ በሚችለው ዐቅም ይፋለመው፡፡ አሁንም ታላቁ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ርኵስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል÷ አያገኝምም፡፡ በዚያን ጊዜም ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል፡፡ ከዚያ ወዲያ ይሔድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል÷ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል፡፡ ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል፡፡››  ማቴ. 12÷43-45፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፉ ቊራኛዎች ከመሆን ልትጠነቀቁ ይገባል፡፡ 

የዐምሐራ ሕዝባዊ ግምባር የዐምሐራን ሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት ለተረዳ፣ ኢትዮጵያዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ላልገባ፣ ብአዴን÷ ኦነግ-ኦሕዴድ ÷ ወያኔ ቀንደኛ የህልውና ጠላቶቹ እንደሆነ የሚያምን ÷ ሆድ አደር አድር ባይ ላልሆነ የምዐሐራ ተወላጅ ብቻ ነው ክፍት ሊሆን የሚገባው፡፡ ከአገዛዙ ጋር በተቃዋሚ ስም ሲሞዳሞድ ለነበረና ላለ ÷ የአገዛዙን ዓላማ ዐውቄና ተረድቼ ተመልሻለሁ ላለ ዐምሐራ ነኝ ለሚልና በዚህ ሕዝብ ስም ተቋቁሜአለሁ ለሚል ግለሰብ ፖለቲከኛም ሆነ ድርጅት በጭራሽ በጭራሽ በጭራሽ ክፍት መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ በኋላ የዐምሐራው ሕዝብ ተጨማሪ በደል መሸከም አይችልም፡፡ በስም እንጥራ ከተባለ ከአብን እና ከኢዜማ ወጥተናል ካሉ ፖለቲከኞች እንዲሁም ማን ስያሜውን እንደሰጣቸው ባላውቅም ራሳቸውን ‹ኢትዮጵያኒስት› ካሉና በቅርቡ ‹ምን እናድርግ› በሚል በአሜሪቃ ለወሬ ከተሳባሰቡ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑ (አብዛኞቹ አቋም የሌላቸው የአገዛዙ አሸርጋዶች በመሆናቸው) አደገኛ ኃይሎች በእጅጉ ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡ 

በዚህ ጽሑፍ አበክሬ ለማስተላለፍ የምፈልገው መልእከት አፍራሽ ኃይሎች የሚፈጥሩት ውዥንብር ሳያንስ አንዳንድ በውጭ የምትገኙና ዐምሐራው ለጀመረው የህልውና ትግል ደጋፊ የሆናችሁ የዐምሐራ ተወላጆች በመረጃ ቲቪ ላይ ቀርባችሁ በምታደርጉት ውይይት የግል አስተያየታችሁን/አመለካከታችሁን ማንፀበረቅ መብታችሁ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሕዝባችንን ከሚያደናግርና በቂ መረጃና ማስረጃ ከሌላቸው ንግግሮች ብትቆጠቡ መሬት ላይ ሆኖ ዕለት ዕለት የፋሽስታዊው አገዛዝ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆነውን ሕዝብ ባንድ ልብ ሆኖ ጠላቱን እንዲመክት ይረዳዋል፡፡ 

የዐምሐራ ሕዝባዊ ግምባር የተቋቋመው ዐምሐራዊ ጐሠኛነትን ለማቀጣጠል/ለማራገብ አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ዐምሐራ ጐሣ-ዘለል ሕዝብ ነው፡፡ በቅርቡ ‹ማማ› በተባለው ሜዲያ ከቀረቡ የውይይት ተሳታፊዎች መካከልና ከሜዲያው አዘጋጅ ይህንን ዓይነት አስተያየት አድምጬአለሁ፡፡ የጋሽ ዳዊትን እና የመሳይን ቃለ-መጠይቅ ደጋግሜ ተከታትዬአለሁ፡፡ ደጋግመው የተነሡት ጥያቄዎች ከጋዜጠኛነት ሙያ አኳያ በቅንነት የተሠነዘሩ ናቸው ለማለት አልደፍርም፡፡ ጐሠኛ ለማለት ያለ ቦታው ‹ብሔርተኛ› ብለው ዘረኛ ፋሽስቶቹ የሚጠቀሙበትን ቃል ለጋሽ ዳዊትና ለእስክንድር መጠቀም ነውር ነው፡፡ ባጠቃላይ ለዐምሐራ ሕዝባዊ ትግል መጠቀምም ነውረኛነት ነው፡፡ ማንነትን መሠረት ያደረግ ሕዝባዊ ትግል ውስጥ የገባነው ተገደን እና ኢትዮጵያዊነትን በአፍ ብቻ በሚያነበንቡ ሐሳውያን ተክደን መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በኢትዮጵያዊነት ስም በከሸፉ ፖለቲከኞች ይደረግ የነበረ ነፍስ የሌሌው እንቅስቃሴ የዐምሐራን ሕዝብ አስፈጅቶ ከሻፊዎቹንም ለአገዛዙ ሎሌነት ዳርጎና ቀሪዎቹንም በፋሽሰታዊ ጭፍለቃ ከጨዋታ ውጭ አድርጎ ተደምድሟል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለአንድ የፖለቲካ ማኅበር ወይም ራሳቸውን ‹ኢትዮጵያኒስት› ብለው ለሰየሙ ቡድኖች የማይሰጥ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልብና  አእምሮ ውስጥ የታተመ ለጊዜው በዘረኞች ምክንያት የተዳፈነ ፍሕም ነው፡፡ ይህ የተዳፈነ ፍሕም በጊዜው ጊዜ እንደ ተራራ የተከመረበትን የዘረኝነት ዓመድ ጠራርጎ ያመርታል ይጐመራል፡፡ 

ቅጥ ያጣ ስሜታዊነት ለጀመርነው ትግል የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ ዕድሜና ትምህርት ያላለዘበው ስሜታዊነት ተራ ጀብደኝነት ይሆናል፡፡ የዐምሐራውን ትግል ጐሠኛነት ለማድረግ በመጣር የተቆርቋሪነት ስሜት አድርጎ ማየት ወይም ለማሳየት መሞከር ስንፍናና ተላላነት ነው፡፡ ትግሉ ሲጀመርም ጐሠኛነት አይደለም፡፡ ለወደፊቱም አይሆንም፡፡ ትግሉ በጐሠኛነት እንዲሣል የምትፈልጉ ካላችሁ ተደራጅታችሁ ሞክሩት፡፡ የጐሠኞቹና የአድርባዮች ሲሳይ ከመሆን አታመልጡም፡፡ የሕዝቡንም ትግል ይከፋፍላል፡፡ በብዙ ምጥ የተወለደውንና መሬት ላይ ያለውን እውነታ መሠረት አድርጎ የተቋቋመውን ግምባር ባታደናቅፉ የሕዝባችንን መከራ ለማሳጠር ይጠቅማል፡፡ ውስጥ እንዳለና የመከራው ተካፋይ እንደሆነ ወንድም አጥብቄ እመክራችኋለሁ፡፡

ዐምሐራ በይፋ ከታወቁ ጠላቶቹ ይልቅ በሆድ አደር አድርባይ ወገኖቹ የደረሰበት በደል በእጅጉ ያማል፡፡ የተደራጀ ስብስብ በተገኘ ቊጥር ላገዛዙ ግዳይ ለመጣል ወይም በኪሳቸው ይዘው የሚዞሩትን የሥልጣን ፍትወት ባቋራጭ ለማሳካት የሚፈልጉ ተቅበዝባዥ በሽተኞች በበዙበት አገር ውስጥ ነን ያለነውና እንጠንቀቅ፡፡ በቅንነት ለመታገል የሚፈልግ ግለሰብ ወይም ቡድን ካለ በፋሺስታዊው አገዛዝ ዕለት ዕለት እየተፈጸሙ ያሉ በርካታ ለትግል የሚያነሣሡ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባን ሕዝብ አደራጅታችሁ ከተፈጸመበት ፋሺስታዊ ከበባ ታደጉት፡፡ የጉራጌ ወገናችን እና ሌላው የደቡብ ሕዝባችን በአገዛዙ እየተፈጸመበት ካለው ወከባ ታደጉት፡፡ ይህን ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከተነሣችሁ ሕዝቡ ከጎናችሁ ይቆማል፡፡ የሚከፈለውንም መሥዋዕትነትና ጊዜውንም ማሳጠር ይቻላል፡፡ ኹሉንም ካልቻላችሁ ቢያንስ መሰናክል ሳትሆኑና ከክፉዎች ጋር ባለመተባበር አርፋችሁ ከተቀመጣችሁ የዐምሐራውን ሕዝብ ትግል እንደደገፋችሁ እንቆጥረዋለን፡፡

በመጨረሻም ውድ ሕይወቱን እየሰጠ ላለው የዐምሐራው ሕዝባዊ ኃይል ፋኖ እንዲሁም ዓላማውን ተረድተው የተቀላቀሉ የልዩ ኃይል አባላት ራሳቸውንና ሕዝባቸውን መታደግ የሚችሉት በቅድሚያ ብአዴን ከተባለ ጭንጋፍ እና ከዘረኛው ፋሽስት አገዛዝ ሊያጠፋቸው የሚላከውን ኃይል ጠላትነት ሳይጠራጠሩ ያለምንም ርኅራኄ በማጥፋት ሕዝባቸው ነፃ አየር እንዲተነፍስ ሲያደርጉ ነው፡፡ የኛ የሕዝቡ ድርሻ ደግሞ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡ አማራው በሚገኝባቸው በሁሉም ክፍለ ሀገሮች ባንድ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፣ የሥራ ዐድማ በመምታት፣ ግብር መክፈልን በማቆም፣ ቤት ውስጥ በመቀመጥ፣ በጦር ሜዳ ለተሰለፉ ወገኖቻችን ጉበኛ በመሆንና በመሳሰሉት የሰላማዊ ትግል መንገዶች አገዛዙን ዕረፍት መንሣት ይገባል፡፡ በሽምግልና ስም ትግሉን የሚያደናቅፍ ሽማግሌ ወይም የሃይማኖት ሰው የጠላት ተባባሪ መሆኑን በግልጽ ነግራችሁ ዐርፎ እንዲቀመጥ፤ እምቢተኛ ከሆነም ከመካከላችሁ ልትለዩት ይገባል፡፡ 

Filed in: Amharic