በአዲስ አበባ እና በደብረ ኤሊያስ የተፈፀሙትን ጥቃቶች በጥብቅ እናወግዛለን!
የአማራ ሕዝባዊ ግንባር(አሕግ)/ Amhara Popular Front (APF)
(ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም.)በአማራ ጥላቻ እና ጥቃት ላይ የበቀለው ዘረኛው ስርዓት ፣ በአማራው ሕዝብ ላይ ላለፉት 30 ዓመታት ሲያደርሰው የኖረው ሁለንተናዊ ጥቃት ወደለየለት የዘር ጭፍጨፋ እና የኃይማኖት ተቋማት ጥቃት ተሸጋግሯል። ለዚህ በወለጋ ካለው ሁኔታ በተጨማሪ፣ ግንቦት 18 እና 19 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ፣ በደብረ ኤሊያስ (ጎጃም) ደግሞ፣ በስላሴ እና በተክለ ኃይማኖት ገዳማት ላይ በከባድ የጦር መሣሪያዎች የተፈፀሙት “መንግስታዊ” ጥቃቶች ዓይነተኛ ማሳያዎች ናቸው።
ግንቦት 18 እና 19 2015 ዓ.ም በሁለት አቅጣጫ ወደ ደብረ ኤሊያስ የገባው የመከላኪያ ኃይል፣ “ለፋኖ እርዳታ ታደርጋላችሁ” በሚል መነሻ፣ ላለፉት ወራት በ”መንግስት” ታጣቂዎች ተከቦ በቆየው የስላሴ አንድነት ገዳም ላይ የከባድ መሣሪያ ተኩስ በመክፈት የጦር ወንጀል ፈፅሟል። በዚህም መሠረት፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር ይህንን ጉዳይ በአንክሮ እንዲመለከተው እንጠይቃለን። እንዲሁም፣ በዛሬው ዕለት “ፋኖን ይደግፋል” ወደ ተባለው ተክለኃይማኖት ገዳምም ወታደራዊ ኃይል በማስገባት እና መንገድ በመዝጋት መንግሥት ተብዬው ወረራ ፈፅሟል። ይህ መግለጫ እስከወጣበት ግዜ ድረስ፣ የደረሰው ጉዳት በትክክል አልታወቀም።
ይህን ፈርጀ ብዙ የህልውና ጥቃት ተቀምጠን የምናመልጠው፣ ከሌሎች በመጠበቅ የምናስቀረው፣ በአጥቂዎቻችን በጎ ፈቃድ የሚቆም አይደለም። ዛሬ በአማራ፣ በወለጋ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚካሄዱት የዘር እና የኃይማኖት ጥቃቶች፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማጥፋት ግብ የሰነቁ ናቸው። ስለሆነም፣ ይህንን ጥፋት መመከት የዘር ጥቃት እየተፈፀመበት የሚገኘው የአማራ ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ ኃይማኖታቸውን እና ሀገራቸውን የሚወዱ የመላ ኢትዮጰያዊያንም ግዴታ ጭምር ነው። ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት መነሻውን አማራ፣ መዳረሻውን ኢትዮጰያ አድርጎ የተነሳው “የአማራ ሕዝባዊ ግንባር” (አሕግ) የሕልውና ትግል እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም፣ በአማራ ክልል፣ አዲስ አበባ እና በመላው ኢትዮጵያ ያላችሁ ሁሉ፣ በግልና በአደባባይ በሚደረግላችሁ ጥሪ ትግሉን ለመቀላቀል ራሳችሁን እንድታዘጋጁ እናሳስባለን።
ግንቦት 18 እና 19 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና በደብረ ኤሊያስ የተፈፀሙትን “መንግስታዊ” ጥቃቶች በጥብቅ እያወገዝን፣ መንግስት ተብዬው በኃይማኖት ተቋማት ላይ የሚፈፅመውን ጥቃቶች እና በደብረ ኤሊያስ እያካሄደ የሚገኘውን ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያቆም በጥብቅ እናስጠነቅቃለን።
የአማራ ሕዝባዊ ግንባር(አሕግ)/ Amhara Popular Front (APF)