>
5:16 pm - Saturday May 23, 5063

የአምባገነኖች ፀሐይ ጠልቃለች! [አናኒያ ሶሪ]

በእኛ በኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ ለ23 ዓመታት ተመዝኖ ቀሎብናል – ይህ የጥቂት ሽፍታዎች ቡድን! የመንግስትነት ስም ሊመጥነው የማይችል የውንብድናና የማፍያ ተግባር በ’መንግስትነት’ ሽፋን ሲራመድም ቆይቷል – ላለፉት ሁለት አስርታት፡፡ ዛሬ፡- ይህን በገሃድ የሚታይ ጥሬ-ሀቅ ያልተገነዘበ አንድም ኢትዮጵያዊ አይገኝ፡፡
ይህንን የጥቂቶች ‹‹የምዝበራ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ›› ለመሸፈን እና የተለየ ልባስ/ጭንብል ለማልበስ፤ እነዚህ መዝባሪዎች አያሌ ፎቆቻቸውን ከህዝብ በመዘበሩት የህዝብ አንጡራ-ሃብት አማካይነት ህዝብን ባፈናቀሉበትና ከቀዬው-በነቀሉበት በዚያው ስፍራ ላይ ለማቆም ችለዋል፡፡ ፎቆቻቸውን ያነፁት የእነርሱ-ዝርፊያ የሃገር-‘ልማት’ እንዲባልና በዚህም ሰፊው-ህዝብ ተደናግሮ ይህንን በአገር ላይ የሚሠራ ‹‹ጥፋት›› በበጐ ጐኑ እንዲመለከተው ለማድረግ ነው፡፡
‘ልማት’ እና የዘር-ልዩነት ላይ ያተኰረ ‹‹የአፓርታይድ-ፌደራሊዝም››ም በግራና በቀኝ እግር ወደተለያየ አቅጣጫ ለመጓዝ የሚደረግ ዓይነት ከንቱ-መውተርተር መሆኑን በተግባር አይተናል፡፡ ‹‹አንቀጽ-39››ም በእኩልነት ላይ ወደተመሠረተ ‹‹አንድነት›› ሳይሆን፤ በ‹‹አድሎ››ና በተዛባ-መስፈሪያ ከተቃኘው የአሁኑ የብሔሮች-መበላለጥ አስከፊ ሁኔታ መውጫ /መለያያ በር ሆኗል፡፡ የመገንጠል – አሰፍሳፊነትም ከቀድሞው ጊዜ ይልቅ ዛሬ ላይ በርትቷል፡፡ ማንም በማንም መረገጫ – ስር መረገጥ አይፈልግምና!
ይህ ‹‹መዝባሪ-ቡድን›› በነጋ በጠባ የሚምል የሚገዘትባቸው ‹‹ብሔር-ብሔረሰቦች›› እኩል የሚሆኑት ህዳር-29 ብቻ ነው፡፡ ከህዳር 29 በስተቀር በቀሩት 364 (1/4ኛ) ቀናት እነዚህ ብሔሮች ወደዘመናዊው – እስር ቤታቸው ይገባሉና! የእስራት ሠንሰለታቸውም ‘አብዮታዊ-ዴሞክራሲ’ የሚባል ስውር የዕዝ-መዋቅር ነው፡፡ ከየብሔሮቹ የተውጣጡ ቱባ የጭቃ-ሹሞች ከሰሜን ጫፍ ወደደቡብ የሚንቆረቆረውን ቀጭን-ትዕዛዝ ተከትለው እንደ እንዝርት ይሾራሉ፡፡ ለቋንቋ ችሎታቸው ብቻ የተመለመሉት እኒህ ተላላኪና ጉዳይ-አስፈፃሚ የየክልል ጭቃ-ሹሞች በምንም ዓይነት መለኪያ የህዝባቸውን-ጥቅም እና ልዕልና ለማስከበር የሚችሉ አለመሆናቸውን ራሱ ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ማወቅ ብቻም አይደል ንቋቸዋል፡፡ በህዝባቸው ዓይን ውስጥም ሚዛን የማይደፉ ቀሊል ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ይህን፡- በመሠረቱ የምዝበራ-ጥማት እና ‹‹የቁሳቁስ-ሰቀቀን›› ያደረበት ገዢ-ቡድን ቅቡልነት /ተቀባይነት ለማላበስ፤ ላለፉት 23 ዓመታት ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም፡፡ “ደርግንና ጭቆናን ገረሰስኩ!” በሚለው ዲስኩር የትግራይን-ህዝብ ከጐኑ ለማሠለፍ በአፍላ-የሥልጣን ዘመኑ ብዙ ደክሟል፡፡ ቆየት አለና ደግሞ፡- ‘የሃይማኖቶች እኩልነትን አረጋገጥኩ!’ ሲል ሙስሊም የህብረተሰብ ክፍሎችን የመደላደያ መሠረት ለማድረግ ረጅም ርቀት ተጓዘ፡፡ ከ1997ቱ ክፉኛ አወዳደቅ በኋላ ደግሞ፡- ‘በቃ እኔ የልማት-መንግስት ነኝ፤ ስለ ዴሞክራሲ አትጠይቁኝ’ አለና የልማት-ዝማሬውን ቀጠለ፡፡ በዴሞክራሲ-መድረክ ላይ፡- በብሔሮች እኩልነት፣ በሃይማኖት ነፃነት፣ በአገር ሉዓላዊነት በዜግነት መብት ወሳኝ-ነጥቦች ላይ ተፈትኖ የወደቀው ይህ ‹‹መዝባሪ-ቡድን››፤ በልማት መድረክም ላይ በማህበራዊ-ፍትህ፣ በገቢ ክፍፍል፣ በኢኮኖሚ-ብልጽግና፣ በመሠረታዊ-አቅርቦቶች ስርጭት፣ በመሬት ድልድል፣ በምርታማነትና በዜጐች ተጠቃሚነት ዙሪያ ዳግም ታላቅ-አወዳደቅ ወደቀ፡፡
ዛሬም የሞት-ሞቱን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንቧቸር ‹‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን››፣ ‹‹የህዳሴ-ጉዞ››፣ ‹‹የህዳሴ-ግድብ››፣ ‹‹ቀላል-ባቡር››፣ ‹‹ስኳር-ፋብሪካ››፣ ‹‹ቤቶች-ግንባታ››፣ ‹‹የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ››፣ . . .እያለ በህዝብ ልብ ውስጥ ስፍራ ለማግኘት ይታትራል፡፡ ከሚለፍፈው ውስጥ 5%ቱን የተገበረ ሲሆን፤ 95%ቱን ደግሞ በተጣባው ‹‹የምዝበራ-ልክፍት›› የተነሳ ወደ ወሮበላ-ቡድኑ መሪዎች የግል ኪስ ይሸኛል፡፡
እነዚህ ሁሉ ግዙፍ-ፕሮጀክቶች የግዙፍ-ምዝበራ ማካሄጃ ግንባሮች ናቸው፡፡ እነ ኤፈርት፣ መሰቦ፣ ጉና፣ ሜቴክ (መከላከያ-ኢንጂነሪንግ) እና ሌሎች በግለሰብ-ሎሌዎች ስም ጭምር የሚንቀሳቀሱ ኩባንያና ኢንዶውመንቶች የምዝበራ-መሣሪያዎች ሲሆኑ፤ በሚሊዮናት የሚቆጠሩ ምስኪን ወጣት-ኢትዮጵያውያን ግን በድንጋይ-ጠረባና በጥቃቅን የችርቻሮ ስራዎች ተሰማርተው ከእጅ-ወደ-አፍ ኑሯቸውን በመፃጉዕነት ይገፋሉ፡፡
ታዲያ ዛሬ፡- ከኢህአዴግ ጋር ያለው ማነው? ህዝብን በግዙፍ ተስፋ ለመደለል የሚሞክርበት ግዙፍ ቅጥፈቱና፤ የ‹‹ላም አለኝ በሰማይ…›› ግዙፍ ፕሮጀክቶቹ አይደሉምን? ከዚህስ የተረፈው ግዑዝ ጠብ-መንጃ መታቀፍን የዕለት ስራው ያደረገው ምስኪን ወታደር አይደለምን?
እኔም እላለሁ፡- የ‘ስርዓቱ’ ምሰሶዎች በተናጉና ከውስጡ የሚከዱ ሰዎች በተበራከቱ ጊዜ… ያኔ ‹የስርዓቱ› ጀንበር መጥለቋን አስተውሉ!
ስርዓት ያልፋል፤ አገርና ህዝብ ግን ፀንተው ይኖራሉ!

Filed in: Amharic