>

"አስከሬን ፣ እባብ ፣ ዓይጦችና እንሽላሊቶች በሚርመሰመሱበት፣ አስረው አሰቃይተውኝ ከግድያ ዛቻ ጋር ጫካ ጥለውኝ ሄዱ‼

አስከሬን ፣ እባብ ፣ ዓይጦችና እንሽላሊቶች በሚርመሰመሱበት፣    አስረው አሰቃይተውኝ  ከግድያ ዛቻ ጋር ጫካ ጥለውኝ ሄዱ

ጋዜጠኛ ያየህሰው ሽመልስ

ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

አሻራ ሚዲያ ፣

ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ካለቀበትና ሞት መንግሥታዊ አዋጅ ሆኖ በየደቂቃው ከሚከሰትበት አገር መውጣት መታደል ሊመስል ይችላል፡፡ ሰዎቹ የጭካኔያቸውን አጽናፍ ለማሳየት ሁሉንም ዓይነት ክፋት አሳይተዋል፡፡ የፈፀሙት ክፉ ነገር ዕልፍ ነው፤ የተነገረው ግን ጥቂት ነው፡፡ በጣም ጥቂት!

ለምሳሌ ሌሊት የቤቴን በር ሰብረው ገብተው በጭምብል ሸፍነው የሆነ የማላውቀው ቦታ ውስጥ ወስደው ከአስከሬን ጋር እስኪያስሩኝ ድረስ እንዲህ እንደሚያደርጉ አላውቅም ነበር፡፡ እባብ ገድለው በማስገባት፣ ዓይጦችና እንሽላሊቶች በሚርመሰመሱበት፣ የምንጭ ውሃ በሚፈልቅበት ቀዝቃዛ ቤት ውስጥ አስገብተው እስከሚዘጉብኝ ድረስ እንዲህ ያሉ መሆናቸውን አላውቅም ነበር፡፡ ከእኔ የሚፈልጉትን ለማግኘት አጠገቤ አምጥተው የሰው አካል እያጎደሉ ሲመረምሩ እስከማይ ድረስ እንዲህ ያለውን ታሪክ የማውቀው በመፃሕፍት ብቻ ነበር ፡፡ ይህንን ሁሉ አድርገው ‹‹ያደረግንህን አንዷን እንኳን ብትናገር ገድለን ለጅብ እንሰጥሃለን›› ብለው በሌሊት ጫካ ውስጥ ጥለውኝ ሲሄዱም አውሬነታቸውን አላውቅም ነበር፡፡ 

በርግጥ እንዲህ ብሎ ማውራት ቅንጦት ነው፡፡ ሰዎችን ከተራራ አናት ላይ ሆኖ እየገደለ ወደ ሸለቆ የሚጨምር  ሠራዊት በተሰማራበት፣ ሰዎችን ከነነፍሳቸው አቃጥሎ ቪዲዮ የሚቀርጽ መንግሥታዊ ጦር ባለበት፣ ንፁሃንን ገድሎ በግሬደር የሚቀብር አገዛዝ ባለበት፣በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች እንዲደፈሩ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ‹‹በወንድ አካል እኮ ነው የተደፈሩት›› የሚል ጠቅላይሚኒስትር ባለበት፣ ‹‹ኧረ ሕዝብ አለቀ፤አትግደለን›› ተብሎ ሲጠየቅ፣‹‹ሞት አታዳንቁ፤ሞት የሌለበት አገር የለም›› የሚል ደመቀዝቃዛ መሪ ባለበት፣ ሚሊዮኖችን ለመጨፍጨፍ ‹‹ወጣቶች ያልቃሉ፣እናቶች ያለቅሳሉ›› ብሎ የጦርነት ነጋሪት የሚጎስም ጠቅላይሚኒስትር ባለበት አገር… በግል ይሄን ተበደልሁ፣እንዲህ ተደረግሁ ማለት ነውርም፤ቅንጦትም ነው፡፡

ከአስከሬን ጋር ያሰሩኝ ሰዎች እኔንም ሬሳ ማድረግ እንደሚችሉ እየነገሩኝ ነበር፤አካል እያጎደሉ ሲመረምሩኝ እኔንም እንደዛው  እንደሚያደርጉኝ እየጠቆሙኝ ነበር፡፡ ስለዚህ እኔ አስከሬንም ሳልሆን፣ አካሌም ሳይጎድል፣ ከነተሟላ ጤንነቴ ነው የወጣሁት፡፡ የእኔ ነፍስ የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ከጨፈጨፋቸውና ካስጨፈጨፋቸው ሚሊዮኖች አይበልጥም፡፡ ዜጎችን የእምነት ቤታቸውንም የመኖሪያ ጎጇቸውንም አፍርሶ ‹‹ሕጋዊ ድሃ አደረግኋችሁ›› እያለ በመመፃደቅ የራሱን ቤተመንግሥት ግን በትሪሊዮን ብር ለመገንባት ዓይኑን የማያሽ፣ የሙያ አጋሮቼን በሥራቸው ምክንያት አጉሮ ሰበር ዜና የሚያስነግር፣ ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከት እያፈነ የሚሰውር፣ ሚሊዮኖችን ከሚሊየነርነት ወደ ለማኝነት ቀይሮ ኑሮን ሰማይ ጠቀስ ያደረገ  አገዛዝ  120 ሚሊዮኖችን አስሮ ባለበት ሁኔታ በግሌ የደረሰብኝን ሁሉ መዘርዘር አልፈልግም፡፡ ከሞቱትና አካላቸውን ካጡት፣ ደብዛቸው ከጠፋና ታግተው ከተሰወሩት፣ ከተገደሉትና ለአእምሮ ሕመም ከተዳረጉት አንፃር እኔ ምን ሆንኩና!  

ስደት እንዳያጋጥመኝ ስፀልይባቸው ከነበሩት የሕይወት ምዕራፎች አንዱ ነው፡፡ 

በአገሬ ሰርቼ  ኑሮዬን ማሸነፍ እንደምችል አውቃለሁ፡፡ተሳክቶልኝም ለራሴ ሳላንስ አይቼዋለሁ፡፡  መንግስትን ግን ማሸነፍ አቃተኝ። እናም በምወዳት አገሬ ከምወዳቸው ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ጋር መኖርን እንጂ መሰደድን ተመኝቼ አላውቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ ስድስት ጊዜ እየታሰርሁ ስፈታ አንድም ጊዜ ስለመሰደድ አስቤ አላውቅም፡፡ በሰባተኛው ግን ወሰንሁ፡፡ ያንን ሁሉ ነገር እያደረጉ ሲያሳዩኝ ከርመው ጫካ ውስጥ አምጥተው ሲጥሉኝ ‹‹ካየኸው ሁሉ አንዷን ብትናገር ገድለን ለጅብ እንሰጥሃለን›› ሲሉኝ ወሰንኩ!  በናዚ መፃሕፍት ላይ እንኳን ያላነበብሁትን ግፍ ሲፈጽሙ ካየሁ በኋላ መሰደድን መረጥሁ፡፡  ሰዎቹ በድለውህም በደልህን እንድትናገር አይፈቅዱልህም! 

ሚሊዮኖችን በሁሉም ዓይነት የአገዳደል ዓይነት እያረገፈ ያለ መንግሥት፣የራሱ አልበቃ ብሎት በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች የአገርን ሕዝብ ያስጨረሰና እያሰጨረሰ ያለ አገዛዝ ካለበት አገር መውጣት ከአንድ ግዙፍ እስር ቤት ወይም የግድያ ማዕከል አምልጦ እንደመውጣት ነው፡፡ 

በርግጥም  አምልጦ መውጣት ነው፡፡ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደየትኛውም የዓለምም ሆነ የኢትዮጵያ ክፍል እንዳልጓዝ ሲከለክሉኝ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠሩትን የዐቢይ አሕመድ አጋቾች አምልጩ ሞምባሳ ለመግባት ሰኔ 4/2015 ተነሳሁ፡፡ የመጣው ይምጣ ብዬ ኤርፖርት ደረስሁ፡፡ የፈራሁት አልቀረም፡፡ ‹‹ሞምባሳ ለመሄድ የተነሳኸው ለዘገባ ነው፤አትሔድም›› አሉኝ፡፡ ‹‹የምሔደው ለሰርግ ነው፤ሥራ ካስቆማችሁኝ አንድ ዓመት ሆነኝኮ፤እንዴት ለዘገባ እሄዳለሁ›› ብዬ ድርቅ አልኩ፡፡ አልተሳካም፡፡ ፓስፖርቴንም፣ሞባይሌንም፣በጠቅላላ የጉዞ ሰነዴን ነጠቁኝ፡፡ ሞምባሳን የመረጥሁት ለሰርግ እሄዳለሁ ብዬ ለመሸወድ እንዲያግዘኝና እነሱን ለማሳመን ነበር፡፡ 

ከረዥም ቆይታ በኋላ እንደገና ተመልሰው መጥተው፣የምሄደበት ሰርግ የማን እንደሆነ፣ሙሽሮቹን የማውቃቸው የትና መቼ እንደነበር፣ መቼ እንደምመለስ፣ የሰርግ ጥሪ ካርድ ስለመያዜ ወዘተ ጠይቀው ከአድካሚ ጭቅጭቅ በኋላ ‹‹ባትመለስ ግን ወዮልህ›› ብለው ሸኙኝ፡፡ 

አውሮፕላኑ ሞምባሳ እስከሚያርፍ ድረስ አላመንኩም ነበር፡፡ ሆነ! ከኬኒያ ሞምባሳ በናይሮቢ አድርጌ በየብስና በአየር ተጉዤ ቢያንስ የዐቢይ አሕመድና ታዛዦቹ ጥርሶች ከማይደርሱበት ቦታ ደርሻለሁ፡፡ አሁንም ጉዞው ይቀጥላል፡፡ከምወዳቸው ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ የነጠሉኝ ጉዶች አሁን የማፈቅረውን ሥራዬን መንጠቅ አይችሉም፡፡  በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ስራዬ እመለሳለሁ።

Filed in: Amharic