የኢኦተቤክ አመራሮች አገርና ቤተ ክርስቲያኒቱን የመታደግ ኃላፊነት በትከሻቸው ላይ ወድቋል!
ከይኄይስ እውነቱ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገጠማት ፈተና ፋሺስታዊው የጐሣ አገዛዝ በአገራችን ላይ ከደቀነው ፈተና ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡
ባለፉት ሠላሳ ኹለት ዓመታት ባጠቃላይ÷ በተለይ ደግሞ ባለፉት 5 ዓመታት የኢኦተቤክ ቤተ ክህነቱም ሆነ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ሲኖዶስ መንፈሳዊ አቋም አጥተው÷ ሲኖዶሱም በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ አካል ሳይሆን ተራ ዓለማዊ ሸንጎ ከመሰለ ከርሟል፡፡ ፋሺስታዊው የጐሣ አገዛዝ የምንይልክን ቤተ መንግሥት ከተቆጣጠረ ወዲህ ግን ቤተ ክርስቲያንን ተቆጣጥሮ የመከፋፈልና ጨርሶ የማጥፋት ዓላማ ይዞ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ የጐሣ ሲኖዶስ ማቋቋም የዚህ ጥፋት ተልእኮ አንድ ደረጃ/ሂደት ነው፡፡
በዚህ የጥፋት ሂደት ፋሺስታዊው አገዛዝ እየፈጸመ ያለው ኢትዮጵያንና እሤቶቿን የማጥፋት ተልእኮ አካል በመሆኑ እምብዛም አይገርመንም፡፡ ወዲህም ቤተ ክርስቲያኗን÷ በይፋ ጦርነት ያወጀበት የዐምሐራው ሕዝብ ብቻ አድርጎ በመቊጠር የጦርነቱም ቀዳሚ ዒላማ አድርጓታል፡፡
ቤተ ክህነቱን በመምራት መንጋውን እንዲጠብቁ ከመንፈስ ቅዱስ አደራ የተቀበሉት ጳጳሳት ፓትርያርኩን ጨምሮ የራሳቸውን ደኅንነት፣ በምእመኑ ሀብት የተገኘውን ምቾት ላለማጣትና ከመንፈስ ቅዱስ በመራቆት ያሉበትን ጥብዐት የተለየው ሕይወት ምክንያት አድርገው አገር የተባለች የኢኦተቤክንን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን/ሥርዓቷን ተላልፈው ቤተ ክርስቲያንን ለዐላውያን አገዛዞች አሳልፈው በመስጠት የፋሺስታዊ አገዛዝ ተባባሪነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ስድሳ አምስት በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአባልነት የያዘች ቤክ ምእመኗን አስተባብራ በመነሻው ላይ እንደታየው ህልውናዋን እና ልዕልናዋን ማስከበር ሲገባ በከፈቱት የስሕተት መንገድ ቀጥለውበታል፡፡ ይህንን ለማስተባበል የሚቀርቡ ምክንያቶች በሙሉ ከንቱና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው፡፡
የኢኦተቤክ አገርንና ቤተክርስቲያንን የማዳን ዕድል በእጇ እያለ በሚያሳዝን ሁናቴ ከአመራሮቿ ‹‹ሰው›› በማጣቷ ኢትዮጵያ እንደ አገር ቤተ ክርስቲያኗም እንደ አገር መሠረትና ዓምድ ዓይናችን እያዩ ሊጠፉ የተቃረቡ ይመስላል፡፡ ስለሆነም ከእስካሁኑ የከፋ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ከጐሣ ፋሺስታዊው አገዛዝ ጋር አብሮ ማበዱን አቁማችሁ፣ ለዓለም ምውት ነን ብላችሁ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፊት የገባችሁትን ቃል ኪዳንና መንፈሳዊ ጥሪ በማስታወስ፣ የግል ክብራችሁን በመተው፣ በሰማዕትነት ስላለፉ ምእመናን፣ ሳይኖራቸው ትዳራቸውን ኹሉ እየሰጡ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚያስቀድሙ ጌጥና ፈርጧ እንዲሁም የናንተ ክብርና ሞገስ ስለሆኑ ምእመናን፣ ብላችሁ ከልዑል እግዚአብሔር ፍርድና ከታሪክ ወቀሳ የምትድኑበትን፣ አገርና ቤተ ክርስቲያን የምትታደጉበትን ተግባር እንድትፈጽሙ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመን በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ጊዜ የለንም፡፡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ለጥፋት በብርሃን ፍጥነት ሲንቀሳቀሱ እኛ አገርንና ቤተ ክርስቲያንን አሁን ላለውና ለመጪው ትውልድ ከነሙሉ ክብራቸውና ልዕልናቸው ለማቆየት ሰማዕትነት ብንከፍልስ በሰማይም በምድርም የምንከብርበት አይደለም ወይ? ስንዱ እመቤት ቤክ መንፈሳዊውንም ሆነ ዓለማዊውን ዕውቀት አስተባብረው የያዙ ልጆቿ አለንልሽ እያሏት – ለተዋሕዶ ይበጃል ያሉትን ኹሉ ዘመኑን በመዋጀት አቅርበው እያለ – በዚህ ዘመን የሚያስተባብሩና የሚመሩ መንፈሳዊ አባቶች ጠፉ ቢባል ለኹላችን ውርደት ነው፡፡ ሲኖዶሳችንን ከመለካውያን ሸንጎነት ወደ ቅድስና እና ወደ መንፈሳዊ ጉባኤነት እንድትመልሱት አደራ በሰማይ አደራ በምድር እላለሁ፡፡ ከወራት በፊት ፋሽስቶችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እንድንኮራባችሁ ያደረገን መንፈስ እንዴት በቅጽበት ብን ብሎ ጠፋ?
ይህንን ኃላፊነት መወጣት ካልቻላችሁ ከምእመኑ ጋር ያላችሁ የአባትና ልጅነት ግንኙነት ያቆማል፡፡ መንጋውን የበተነ እረኛ ማን ይከተለዋል? ለእናንተ ይብላኝ እንጂ ለህልውናውና ለኢትዮጵያ አንድነት መሥዋዕትነት እየከፈለ ያለው የዐምሐራ ሕዝብ ይህንን ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ ሲያስወግድ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንም እንደሚታገሡ እናምናለን፡፡ ከዚያም የውስጡን ችግርና ተግዳሮት መፍታት የምእመኑና የእውነተኛ ካህናትና አባቶች ኃላፊነት ይሆናል፡፡
ደጋግሜ እንደተናገርኹት በዐዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ዐውደ ምሕረተ እየተገኛችሁ ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጋችሁ ምእመኑን አታዘናጉት፡፡ በዳተኝነት፣ በፍራት እና ከንቱ ክብርን በማስቀደም ባገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየፈጸማችሁት ያለውን ጥፋት ለገንዘብ ልመና በታቀደ ስብከት ተደባብሶ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ልመናችሁን አቁሙ፡፡ በየዐውደ ምሕረቱ ከትምህርትና ስብከት ይልቅ ብዙ ጊዜ የሚባክነው በገንዘብ ልመና መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በተለይም በታላላቅ የንግሥ በዓላት፡፡ ቤተ ክርስቲያን እስከ መቼ በልመና ትኖራለች፡፡ ምን አጣች? አሁንም እንደ ከዚህ ቀደሙ እናገራለሁ፡፡ ለ1700 ዘመን በሙሉ እንዴት ከልመና አትወጣም? ዛሬ በየአድባራቱና ገዳማቱ ቅጥር ዙሪያ አፀዶች ተመንጥረው ለመንፈሳዊ ሕይወት የማይስማሙ የንግድ መደብሮች ተከፍተው የጸሎትና የቅድስናው ስፍራ የወንበዶች ዋሻ መስሏል፡፡ ትውልድ የሚታነፅበት መንፈሳዊና ዓለማዊ ትምህርት ቤቶች ሲሠሩ አይታይም፡፡ በመቶ ሺዎች የሚሸጡ ፉካና የንግድ መደብሮች እንጂ፡፡ እንደዛም ሆነ ራስን አለመቻል ምን ይሉታል? ገንዘቡ የት እየገባ ነው? የቤተ ክርስቲያን ራሷ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ተዘንግቶ ገንዘብ ከሆነ ዘመናት ተቈጥረዋል፡፡ ይሄ በገንዘብ መለከፍ ምን የሚሉት ነው?
በነገራችን ላይ በፋሺስታዊው አገዛዝ በኩል ያለው አገርና ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋት ግልጽ ተልእኮ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቤተ ክርስቲያንን በመከፋፈል ለዚህ የመለካውያኑ ተልእኮ መሣሪያ የሆኑ የውስጥ አፈንጋጮች÷ የጐሣ አበጋዞች ግላዊ ፍላጎትና ዓላማ ዝርፊያ መሆኑን አስተውላችኋል? በመንፈስ ቅዱስ ተሹማችሁ ከሆነ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ የሾመው ህልውና ቤተ ክርስቲያንን ከዶግማዋ፣ ቀኖናዋ፣ ሥርዓቷና መንፈሳዊ ትውፊቷ ጋር እንድታስከብሩና ክርስቶስ በደሙ የዋጀውን መንጋ እንድትጠብቁ እንጂ ለገንዘብ ስብሰባ አይደለም፡፡ እምቢ ካላችሁ ምእመኑን ከናቃችሁና አያገባውም ካላችሁ የቤተ ክርስቲያን መሥራቿና ጠባቂዋ ጅራፉን በእናንተ ላይ እንደሚያነሣ አትጠራጠሩ፡፡ ማንነታችሁን በሻሸመኔው ሰማዕታት ታዝበናችኋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሀብታቸውን ብቻ ሳይሆን የማይተካ ሕይወታቸውን የሰጡት ምእመናን ቤተሰቦች እና ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናን ከካዝናዋ ገንዘብ አውጥቶ በፍጥነት በመድረስ ከመታደግ ይልቅ የልመና ጥሪ ማቅረባችሁ የልመና አባዜ ምን ያህል ሥር የሰደደ በሽታ እንደሆነ ታዝበናል፡፡ በዚህ መከራ በበዛበት ዘመን ምእመናንን ባጠቃላይ የፋሽስታዊው ጐሣ አገዛዝ ሰለቦችን በማጽናናት ምሳሌ ስትሆኑ አልታያችሁም፡፡
በመላው አገራችን ፋሺስታዊው አገዛዝ ከቤት ንብረታቸው በግፍ አፈናቅሎ በዚህ ክረምት ሜዳ ላይ ላፈሰሳቸው ምእመናን እና ለሌሎች ወገኖቻችን ምን አደረጋችሁ? የፈረሱ ሕንፃ አብያተክርስቲናትን ከማሠራት ይልቅ የፈረሱ ሕያው ቤተመቅደሶችን (ወገኖቻችንን) መታደግ አይቀድምም ወይ?
ምእመናን፤ እግዚአብሔርን እያገለገልን እየመሰለን፣ የኃጢአት ሥርየት ያገኘን እየመሰለን፣ ‹አባቶች› የተባሉትን እያከበርን እየመሰለን እስከ መቼ ነው አእምሮአችንን መጠቀም አቁመን በደመ ነፍስ የምንከላወሰው? መቼ ነው በራሳችን ተነሳሽነት የቤተ ክርስቲያንን ህልውናና ሉዐላዊነት ለማስከበር ኃላፊነት የምንወስደው? ከትዳራችን ከኑሮአችን ነጥቀን የምንለግሰውን ገንዘብ ለዘራፊዎች አሳልፎ በመስጠት ጽድቅ የምናገኝበት ይመስላችኋል?
የቤተ ክርስቲያን አመራሮችና አስተዳደር ያጡት መንፈሳዊነትና ለዘመኑ የሚመጥን የሰው ኃይል፣ የፋይናንስና የማቴሪያል ሥራ አመራር እንጂ ገንዘብ አይደለም፡፡ ዦሮአችን እውነትን ለማዳመጥ ከመፍጠን ይልቅ አጭበርባሪዎችን በመስማት በንጹሐን ላይ ደንጊያ ለመጫን ሲፋጠን ብዙ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ በስንቱ አድባራትና ገዳማት ነው የምእመናን ገንዘብ እንዳይባክን በረከትንና ጽድቅን ሽተው ሕይወታቸውን የሰጡ ምእመናን የዝርፊያ መንገድ በተዘጋባቸው አገልጋዮች በሐሰት የተከሰሱትና ምእመኑም ሳያጣራ ያወገዛቸውና ያራቃቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የጠቀምን÷ የጽድቅ ሥራ የሠራን እየመሰለን የቤተ ክርስቲያንን አገልጋዮች የምናበላሽ እኛ ምእመናን ነን፡፡ ኹሉ ባግባቡና በሥርዓት ይሁን ተብለናል፡፡ እስከ መቼ እንዝረከረካለን? ቤተ ክርስቲያን የጥቂት አገልጋዮች ወይም ‹አባቶች› ብቸኛ ንብረት አለመሆኑን ጠንቅቃችሁ ልታውቁ ይገባል፡፡
የትግራይ አኅጉረ ስብከት – አጥፊ ርምጃችሁ በወያኔ ፖለቲካና በተሐድሶ እንቅስቃሴ የተጠለፈ መሆኑን ብናውቅም – የኢኦተቤክንን አሁን ለደረሰባት ፈተና ያመቻቻት አገር አጥፊው፣ ቤተ ክርስቲያንን በጠላትነት ፈርጆ የተነሣው እና ቤተ ክህነቱን ለራሱ ዝርፊያና ፖለቲካ መጠቀሚያ ያደረገው ወያኔ ሕወሓት መሆኑን እያወቃችሁ፤ ትግራይን ትርጕም በሌለው ጦርነት ካወደመና የወያኔ የግብር ልጅ ከሆነው ፋሺስታዊና አረማዊ የአጋንንት ኃይል ጋር መተባበራችሁ በእግዚአብሔርም ሆነ በታሪክ ዘንድ አሳፋሪና የሚያሸማቅቅ ጥፋት መሆኑን ተረድታችሁ ብኵርናችሁን እንደ ኤሳው በምስር ባትለውጡ መልካም ይመስለኛል፡፡
ወያኔ ታላቁን የዋልድባ ገዳም በደፈረ ጊዜ በጽድቅ ፈራጅ የሆነ አምላክ ባንድ ጊዜ ቤተ ክህነቱን እና ቤተ መንግሥቱን ሲመታ ብዙዎች ምስክር ሆነናል፡፡ እኛ የኢኦተቤክ ምእመናን እውነተኛና መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ከሃይማኖታዊ መመዘኛ ውጭ ቆሻሻ በሆነ በጐሣ/ዘር መለኪያ አናይም÷ ልናይም አይገባም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የወንበዶች ዋሻ ከሆነች ከርማለች፡፡ እነዚህ ወንበዶች ነገድ/ጐሣ ሳይለይ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባሉ ከታችኛው ክህነት ማዕርግ አናጕንስጢስ እስከ ሊቀ ጳጳስ ይገኛሉ፡፡ የተወሰኑቱም ክህነት የሌላቸው ተራ ካድሬዎችና ጆሮ ጠቢዎች፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው ክህነታቸውን ያፈረሱ ነውረኞች፣ ገሚሶቹም የመንፈስ ድርቀት የመታቸውና ምንኵስናቸውን የዘነጉ የዕውቀት ጦመኞች፣ አንዳንዶችም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ካባ የተሸፈኑ የሌላ እምነት አራማጆች መሆናቸውን ቊጥሩ ቀላል ያልሆነ ምእመን ያውቃል፡፡ ምርቱ ከግርዱ፤ ፍሬው ከገለባው የሚለይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ እውነተኛና መንፈሳዊ የሆኑ የትግራይ አኅጕረ ስብከት አባቶች ባገራችን የሠለጠኑ የጐሣ ፖለቲከኞች በፈጠሩት አገራዊ ምስቅልቅል የተነሣ የትግራይንም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ምእመኖቻቸውን ከድተው አሁን የምንሰማው ነውረኛ ተግባር ውስጥ ይገባሉ ብለን አናምንም፡፡ ያን ክርስትና በተግባር ሲፈጸምበት የኖረ የተቀደሰ ምድር በዘር/ጐሣ ያረክሱታል ብሎ ለማመን በእጅጉ ይከብዳል፡፡ በአገርም ይሁን በቤተ ክርስቲያን ዕጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን አንድነት ብቻ ነው፡፡ ይህንን ዐውቃችሁ ካበዱት ጋር ካላበድን የሚሉትንና ወፈፍ ያደረጋቸውን ወገኖች ብትገሥፁና ብትመክሩ መልካም ይመስለኛል፡፡ እጃቸው በደም የተጨማለቀና ባገር ላይ ክህደት የፈጸሙ የወያኔ አመራሮች አጥፊዎቻችሁ እንጂ ታዳጊዎቻችሁ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ክርስቲያኑን ሕዝብ ደናቊርት ፖለቲከኞች በጠላትነት እንዲተያይ ሲያደርጉት እንደ ክርስትናው አስተምሕሮ አንድ ለማድረግ የፈጸማችሁት ተግባር አለ? ከሠላሳ የጥፋት ዘመናት በኋላ ወደ አእምሮአችን መመለስ ካልቻልን አይደለም ከመንፈሳዊነት ከሰውነትም ተለይተናል ማለት ነው፡፤
በመጨረሻም ለኢኦተቤክ ምእመናን፤ የፋሺስታዊው ጐሣ አገዛዝ ተልእኮ አስፈጻሚ ሆነው በጭራቁ ዐቢይ ትእዛዝ ከቤተ ክርስቲያናችን ዶግማ፣ ቀኖና ሥርዓት ተፃራሪ በሆነ ውሳኔ ከተወገዙ በኋላ አላግባብ የተመለሱትን እነ አቶ አካለ ወልድንም (የቀድሞ 4 ‹‹ጳጳሳት››) እና በእነዚህ አፈንጋጮች ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ጐሣን መሠረት አድርጎ የተመለመሉትን የሐሰት ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሁም በእነ አካለ ወልድ አስተባባሪነት በጐሣ መስፈርት ለእጩ ኤጲስ ቆጶስነት የታጩ ‹‹መነኰሳት›› ባገዛዙ ተጽእኖና በሲኖዶሱ አባላት ዳተኝነትና ይሁንታ ተቀባይነት አግኝተው በየአኅጕረ ስብከቱ የሚሰማሩ ከሆነ፣ የአባትነት ክብር ከመንፈግ ጀምሮ በሚገኙባቸው አብያተ ክርስቲያናት አለመገኘት፣ በእነዚህ ግለሰቦች የሚደረጉ ማናቸውም ጥሪዎችን አለመቀበልና አለመታዘዝ ይኖርብናል፡፡ እነዚህን ጨምሮ የእነ አካለ ወልድ ተከታዮችንም በሙሉ የመንፈስ ቅዱስን ሀብት በገንዘብ ሊገዛ እንደሞከረው ሲሞን መሠሪ ማየት ይገባል፡፡