የኢት. ኦር.ተዋ.ቤተ. አባቶች ከመንፈሳዊ እና ቀኖናዊ ተልእኳቸው ይልቅ ለዓለማዊ ሃይልና ጥቅም እያጎበደዱ ነው
ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ኢትዮጵያን እንደሃገር በማቆም ረገድ ሁለት ታሪካዊ እና ጥንታዊ ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ መወጣታቸውን የታሪክ ድርሳናት በስፋት ዘግበውታል፡፡ እነሱም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሠትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት በሪፐብሊክ ከተተካ በኋላ እና በተለይ ከደርግ አገዛዝ ውድቀት በኋላ፣ የነገድ ፖለቲካ በሃገራችን ተንሰራፍቶ መዋቅራዊ ህልውና ካገኘ ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ስነ ልቦናዊ መገለጫ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀገረስብከት መልካምድራዊ አደረጃጀት ነው፡፡
የጎሳ ፖለቲካ በሀገራችን ከተተገበረበት ካለፉት ሰላሣ ዓመት ጀምሮ በተለይም ካለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት ወዲህ ቤተ ክርስትያንዋ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ የኦህዴድ/ ኦነግ ብልፅግና ስርዓት ጥር 14 ቀን 2015ዓ.ም. ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ አዳዲስ ጳጳሳትን አይን ባወጣ መንገድ ለመሾም ያደረገው ጥረት በወቅቱ አባቶች ይዘውት በነበሩት ጠንካራ አቋም፣ የአባቶችን ጥሪ በመቀበል የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናን እና ተቆርቋሪዎች ባካሄዱት መጠነ ሰፊ ተቃውሞ አገዛዙን ስላስደነገጠ ጣልቃ ገብነቱ በወቅቱ ሊከሽፍ ችሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዳሩ ግን የኦህዴድ/ብልፅግና ስርዓት ቤተ ክርስቲያንዋን እና ሀገርን የማፍረስ ክፉ መንፈስ ስለተጣባው፤ በምዕመኑ ተጋድሎ የከሸፈበትን ዓላማ ለማሳካት ዛሬም እንደ ትናንቱ ስልቱን ቀይሮ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሲኖዶሱ አባላትና ዋናዋናዎቹ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች የቤተ ክርስትያን ሊቃውንትን፤ መምህራንን፣ ካህናትን እና ምዕመናኑ እንዲመክሩበት ሳይደረግ፣ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ዘመን ጠገብ የጳጳሳት ሲመት መመዘኛዎች ውጭ በአገዛዙ ግፊት ሹመት ለማጽደቅ ሀምሌ 09/2015ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ካህናትና ሕዝብ በኤጲስ ቆጶስ ሹመት ላይ ያላቸውን ተሳትፎና ሓላፊነት ፍትሃ ነገሥት አንቀጽ 5 ረስጠብ 52 ፣ ‹‹ካህናቱና ሕዝቡ እንዲሾምላቸው ኤጲስ ቆጶስ የሚሆነውን ቆሞስ መርጠው ሲያቀርቡ፣ ስለደግነቱና ስለትሩፋቱ ስለንጽሕናውና ከነውር የራቀ ስለመሆኑ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ 3 ጊዜ እየመላለሰ ማረጋገጫ ይጠይቃቸዋል፤ ሕዝቡም አረጋግጠው ‹የሚገባው ነው› ብለው 3 ጊዜ መልስ ይሰጣሉ፤ በ3ኛው ሕዝቡ መልስ ሲሰጡ እጃቸውን አንስተው ‹ይገባዋል› እያሉ ያጨበጭባሉ››ይላል፡፡ በፍተሃ ነገስቱ በግልፅ እንደተመለከተው በቤተ ክርስቲያኗ የጵጵስና ሲመት መመዘኛዎች የመንፈሳዊ ህይዎት ንጽህና፣ የቤተክህነት ትምህርት ብቃት እና ለቤተክህነት የተሰጠ የአገልግሎት ዘመን እርዝማኔ ናቸዉ። አሁን እንዳሚሰማው ግን ጠቅላይ ሲኖዶሱ እነዚህን የመንፈሳዊ ተክህኖ መመዘኛዎች ወደ ጎን አድርጎ ዘመን አመጣሽ የነገድ ፖለቲካ ዉልድ የሆኑ ቋንቋን እና ክልልን ለጳጳሳት ሲመት በመመዘኛነት ሊጠቀምባቸዉ ወሰኗል። ይህ ዉሳኔ የቤተ ከርስቲያኗን መሰረታዊ አስተመህሮ የሚያናጋ እና እስካሁን የተከፈለላትን መስዋእትነት መና የሚያስቀር ነዉ።
የቤተክርስቲያኒቷ አባቶች በፋሽስት ኢጣሊያ ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የአቡነ ጴጥሮስን እምነት እና ለሃገር ፍቅር የመስዋዕት ተምሳሌት መከተል ተስኗቸዋል፡፡ ከመንፈሳዊ ተልዕኳቸው ይልቅ ዓለማዊ ጥቅማቸውን በማስቀደም ጠቅላይ ሲኖዶሱን ወደ ጳጳሳት የአክሲዮን ኩባንያነት እየቀየሩት ይመስላል፡፡ የቤተክርስቲያኒቷን ቀኖና በመጣስ ለኦሮሙማ ሀገር አፍራሽ ፖለቲካ እያጎበደዱ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አባቶች ሊገነዘቡ የሚገባው ቁምነገር ሊያስፈፅሙ የተዘጋጁት የፖለቲካ ሹመት ከቤተክርስቲያኒቷ መሠረታዊ እምነት በተፃራሪነት የቆመ መሆኑን ነው፡፡
የኦሮሙማ ዓይነተኛ የሆነው የፖለቲካ ተልዕኦ በኢትዮጵያ ነባር የሆኑ የኦርቶዶክስ እና የእስልምና እምነቶችን በመቦርቦርና በቁጥጥሩ ስር እንዲሆኑ በማድረግ በኢትዮጵያ ኪሣራ ኦሮምያ የሚባል ነፃ ሃገርን ማወለድ ነው፡፡ በ2015 ዓ.ም የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ወይም መጅሊሱን ከእስልምና እምነት ይልቅ የኦሮሙማ ፖለቲካን እምነታቸው ያደረጉ ሰዎች አመራሩን እንዲይዙ መደረጉ ይታወቃል፡፡
ለየት ባለ መልኩ ይኸው ሁኔታ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እየተደገመ ነው፡፡ የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና የቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ለጊዜው ባይችልም፣ አስርጎ ያስገባቸው ጎጠኞች ካድሬዎች በሲኖዶሱ እውቅና ተሰጥቷቸው በየጎጣቸው እንዲመደቡ መደረጋቸው እየተሰማ ነው፡፡ ይህ አመዳደብ ለዘመናት የቆየውን የቤተክርስቲያኒቷን መልካምድራዊ/ ሀገራዊ አወቃቀር በቋንቋዊ ክልላዊ አወቃቀር በመቀየር የኦሮሙማን የፖለቲካ ግብ በሂደት በቤተክርስተያኒቷ ጠቅላይ ሲኖዶስ ውስጥ የበላይነት አግኝቶ በመጅሊሱ እንደተደረገው ሲኖዶሱን በሂደት የኦሮሙማ የፖለቲካ ተልእኮ አስፈፃሚ እንዲሆን የሚያደርገው ነው፡፡
የኦህዴድ/ብልፅግና ስርዓት ሀገረ ኦሮምያን ለማዋለድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ይህችን ጥንታዊት ቤተ-ክርስተያን ተግዳሮት እንዳትሆንበት እና የኦሮሚያን ቤተ ክህነት ለማቋቋም ስለተፈለገ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የጳጳሳትን ቁጥር መጨመር ለእኩይ ዓላማው መሳካት አስፈላጊ ሁኖ አግኝቶታል፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና ስርዓት አክራሪ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን የሚያራምዱትን የጎጠኝነት ሀሳብ ተቀብለው ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል የሚተጉ ጳጳሳት፣ በመንፈሳዊውም ዓለም ሆነ በታሪክ ተወቃሻ እንደሚሆኑ እያሳሰብን፣ የሚደረገውን ከቀኖና ያፈነገጠ የጳጳሳት ሲመት ፓርቲያችን ባልድራስ በፅኑ እያወገዘ፣ ይህ የሲኖዶሱ ውሳኔ በቤተክርስቲያኗ ምዕመናን መካከል መከፋፈልን እና ብጥብጥን እንዳይፈጥር ስጋታችንን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ከላይ በተጠቀሱ እሳቤዎች ላይ በመንተራስ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፣ ኦሕዲድ/ኦነግ ብልጽግና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየፈጸመ ያለው ጣልቃ ገብነት ከቤተክርስቲያ አልፎ የሃገርም ጉዳት በመሆኑ፣ የሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጣቸው ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጥሪውን ያቀርባል።
➢የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ፣ ሲኖዱሱ አሁን የሄደበት የጳጳሳት ምርጫ በአገሪቱ፣ በቤተክርስቲያንና በልጆቿ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ መሆኑን አጢነው ሀምሌ 9/2015 ዓ.ም. በሚደረገው በአዲስ ተሿሚዎች ጳጳሳት ላይ እጃቸውን እንዳይጭኑ እንጠይቃለን፡፡
➢እስከ ሀምሌ 9/2015 ዓ.ም. ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እውነተኛና ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ የሆኑ የሲኖዶስ አባላት የተካሄደው የጳጳሳት ምርጫ ትክክል አለመሆኑን በማስመልከት እንዲያወግዙ እንጠይቃለን፡፡
➢የቤተ ክርስትያን ሊቃውንትን፣ መምህራን፣ ካህናት እና ምዕመናን ቁርጠኛ የሲኖዶስ አባላት የሚያቀርቡላችሁን ጥሪ ተቀብላችሁ ከጎናቸው እንድትቆሙ እንጠይቃለን፡፡
➢በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ውስጥ የተካሄደውን መንፈሳዊ ያልሆነ የኦሮሙማን የፖለቲካ መፈንቅለ መጅሊስ መደረጉን በጥብቅ እናወግዛለን፡፡ የተወሰደውን ህገ ወጥ ውሳኔ በሙስሊሙ ምእመን ነፃ ፍላጎት መሰረት እንዲስተካከል እንጠይቃለን፡፡
➢የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና መንግሥት በቤተ እምነቶች አሠራር ውስጥ እያካሄደ ያለውን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
ሀምሌ 05/2015
አዲስ አበባ