>

በአማራው ክልልና በሌሎችም ቦታዎች “የማይታወቁ ሰዎች”ን ያብዛልን!! (ይነጋል በላቸው)

በአማራው ክልልና በሌሎችም ቦታዎች “የማይታወቁ ሰዎች”ን ያብዛልን!!

ይነጋል በላቸው

አማራ የፊታችንን ጦርነት (አሁን በቅጡ ተጀምሮ ካልሆነ) በአሸናፊነት የሚወጣበት እልፍ አእላፍ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል፡፡ እሱ አሁን አይጠቅምም፡፡ ዋናው አማራ ፋኖና ሕዝቡ በአጠቃላይ ምን ያድርግ የሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ላይ ትንሽ ልበልና ወደሌሎች አሳሳቢ ነጥቦች አመራለሁ፡፡

አማራ ፋኖ እጎሬው ድረስ የተሠማራበትን የኦሮሙማ ጦር በተበጣጠሰ መልክም ቢሆን በተቻለ አቅሙ እየተጋፈጠ ይገኛል – ይህ ዓይነቱ ያልተናበበ ትግል ግን ቀስ በቀስ ግን ሁሉንም በጊዜ ሂደት ያስበላልና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ኦሮሙማ የኢትዮጵያን ጓዳ ጎድጓዳ በመቆጣጠሩ የሰውም ሆነ የመሣሪያና የስንቅ ችግር እንደማይኖርበት ይገመታል፡፡ የሕዝብ ፍቅርና እውነት ስለሌሉትና በሕዝብ ላይ ግፍና ሰቆቃ ለማድረስ በዕብዶቹ የኦሮሙማ መሪዎች በተለይም በአቢይ አህመድና በሽመልስ አብዲሣ በመገደዱ በመጨረሻው ብዙ አሣር ይወርድበታል፡፡ ይህ ጦርነት ከአማራ ክልል እስኪወጣና ወደሌሎች ክልሎች እስኪዛመት በጉጉት የሚጠባበቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግምት በላይ እንደሆነ ለመገንዘብ የኦሮሙማን ተፈጥሮ ከመረዳት ውጪ ሌላ ዕውቀት አይጠይቅም፡፡ የነዚህ ቅዠታም ጅላንፎዎች አካሄድ አሁን ለሁሉም ግልጽ በመሆኑ አይቻላቸውም እንጂ አማራን ከጨረሱ ወይንም ካንበረከኩ በኋላ ሌሎች ነገዶችን በቀናትና በሰዓታት ውስጥ የለዬላቸው ባሪያዎች እንደሚያደርጓቸው የሞጋሣ ታሪክ በጉልኅ ይመሰክራል፡፡ 

አሁን ፋኖ ማድረግ ያለበት ድርጅታዊ ምሥጢሮችን አለማውጣት፣ አመራሩን መሰየምና በተማረ የሰው ኃይል መገንባት፣ ጠላቶቹ ብዙ እንደመሆናቸው ለሁሉም የጠላት ግንባሮች መዘጋጀት፣ በገጠርና በአንዳንድ ከተሞች በሚገኙ ትናንሽ ድሎች አለመኩራራትና ትልቁን የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት አቅዶ መራመድ፣ ጠላትን ከጉያ ጀምሮ እስከ አደባባይ ድረስ ያለውን ለሆድ ያደረ መዥገር ሁሉ ጥናት ላይ ተመሥርቶ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ፣ “ያልታወቁ ሰዎች” የሚወስዷቸውን በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ የትግል መስክን የማጥራት ሂደት ማበረታታት፣ (እዚህ ላይ “እነገላግሌን ‹ያልታወቁ ሰዎችን› ያብዛልን” ማለትን ወድጄ ነበር፤ ግን ይቅርብኝ)፤ ትግልን ለሚያሰናክሉ ወገኖች – የእናት ልጅም ቢሆን – ምንም ዓይነት ርህራሄ አለማሳየት፣ መሣሪያን ከጠላት በመቀማት እየታጠቁ ስንቅን ደግሞ ከወገን እንዲቀርብ የሰው ኃይልን እየመደቡ በፍጥነት መጓዝ፣ ከጠላት የሚማረክ ምግብንና መጠጥን በእንስሳት ካልሞከሩ በፍጸም አለመጠቀም፣ ከቴክኖሎጂያዊ መሣሪያዎች መራቅ፣ በአንድ ቦታ አለመሰብሰብ፣ የሚማረክን የኦሮሙማና የዪሁዲው ብኣዴን ወታደርን መክሮና ዘክሮ መሣሪያውንም ተረክቦ በድጋሚ ሊዋጋ ቢመጣ ምሕረት እንደማያገኝ በመምከር ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንዲሄድ ማድረግ እንጂ በአፉ ምን ቢቅለበለብ ለጦርነት አለማሰለፍ (እባብ ለመደ ተብሎ አይታቀፍምና ይህ ነገር በእጅጉ ይታሰብበት)፣ሠርጎ ገብን በከፍተኛ ጥንቃቄ መከታተል፣ ትግሉ ረጂም ጊዜ በወሰደ መጠን የሰውና የስንቅ አቅርቦትም እየሳሳ ስለሚሄድ ትግሉ አሰልቺና ውጤት አልባ ይሆናልና በሁሉም የአማራ አካባቢዎች ያላችሁ ፋኖዎች በመናበብ ሕዝቡንም ከእናንተ ጎን በማሰለፍ አፋጣኝ ሀገራዊ ክተት ማወጅ፣ “እንሸነፋለን” የሚልን ሃሳብ ከአእምሮ ማውጣት (ስለማትሸነፉ!)፤ በወንጀልና በገንዘብ ስካር፣ በሦዶማዊ ኃጢኣትና በሚያጃጅል የድንቁርና ዕብሪት የተሞላን የኦሮሙማን ኦነግ-ሸኔ ጦር የተደራጀ ፋኖ ይቅርና አምስት መቶና አንድ ሽህ የመንዝ ውርጋጦች እያሳደዱ አለቆቹ አማራን ለሞተው ወያኔ ወደሸጡበት ፕሪቶሪያ እንደሚያደርሱት ልብ አለማለት ትግሉን እንደሚጎዳ ማጤን፣ በጎጥና በክፍለ ሀገር መከፋፈል ለጠላት እጅግ አመቺ በመሆኑ አንድነትን ማጥበቅ፣ ዛሬ ያልተመታ ነገና ከነገ ወዲያ የመመታት ተራው የርሱ እንደሆነ መረዳት፣ ለጠላት የከፋፍለህ በለውና የበታትነህ ግዛው ሤራ አለመመቸት፣ በተቻለ መጠን ሀገር ለይቶላት ሳትፈራርስና ከዚህም በበለጠ ሳትበታተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ከሌሎች ሃቀኛ ወገኖች ጋር ኅብረት ፈጥሮ ለተጨነቀው ሕዝብ በቶሎ መድረስን የቅርብ ጊዜ ዓላማና ግብ ማድረግ …. ለአሁኑ እነዚህን ምክሮች መሰንዘሩ ብቻ ይበቃኛል፡፡ ወደሌሎች ወቅታዊ ነጥቦች ላምራ፡፡

የዕብዱ መሪ ዓለምን ጉድ ያስባሉ ሁለት ውሸቶች!

ዓለማችን ካስተናገደቻቸው ዕብድ የሀገር መሪዎች መካከል – ስሙን ቄስ ይጥራው ለማለት ባልደፍርም – አቢይ አህመድን የሚስተካከል እንደሌለ በተደጋጋሚ ተገልፆኣል፡፡ በጭካኔም ሆነ በማንኛውም የአእምሮ-የለሽ ሰውን መለኪያ መሣሪያ ቢመዘን አቢይ ወደር የማይገኝለት ዐረመኔና ሰይጣን ራሱ የሚቀናበት ክፉ የክፉ ክፉ ሰው ነው – ስንቶችን እየሣቀ እንዳሳጣን ማሰብ አለብን፡፡ ይህ ሰው ኢትዮጵያን ከያዘ ወዲህ የዋሻቸው ውሸቶች ተቆጥረው የማይዘለቁ ቢሆኑም ሁለቱ ግን የተለዩ ናቸውና እኔም ልጥቀሳቸው፡-

  1. በኢትዮጵያ 25 ቢሊዮን ዛፍ እንደተተከለና በቅርቡ ደግሞ 50 ቢሊዮን ለማድረስ እንደሚፈልግ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከተሰራጨው የፓሪሱ ስብሰባ ተረድተናል፡፡ ሃያ አምስት ሚሊዮን ብሎ ተናግሮም ቢሆን ግነት ነው፡፡ አንድን ችግኝ ለፎቶ ታይታ ለአምስት እየተከሉ እንኳንስ ሃያ አምስት ቢሊዮንና ሃያ አምስት ሚሊዮን ችግኝ ሊተከል ሁለት ሚሊዮን ከተተከለም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከአንድ አንባቢ ልጅ ገለጻ እንደሰማሁት አንድን ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት በደን ለመሸፈን 40 ሽህ ችግኝ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ሳስበው በአምስት ሜትር ርቀት መሆኑ ነው፡፡ እንደኔ ግን የአማራውን ወይራን፣ የኦሮሞውን ዋርካን፣ የትግሬውን ቁልቋልን የመሳሰሉ ዛፎችን ከግምት ውስጥ ካስገባን ዛፎቹ ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ከአምስት ይልቅ በአሥር ሜትር ርቀት ቢተከሉ መልካም ነውና ለአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር 20 ሽህ ብንል ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን 22 ቢሊዮን እንደሚፈጅ ስሌቱ ይነግረናል፡፡ ይህ ሲሆን አሁን ያለውን የደን ሽፋን ጨምሮ መንገዱም፣ ተራራውም፣ ወንዙም፣ በረሃውም፣ ቤቱም፣ ሐይቁም፣ የእርሻ ቦታውም በጠቅላላው የሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ተካትቶ ማለት ነው፡፡ 

(አንድ የደርግ ዘመን እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡ አሳጥሬ ልንገራችሁና በድርበቡም ቢሆን ፈገግ በሉበት፡፡ በአንድ የሚኒስትሮች ካቢኔ ስብሰባ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ስላለው ታራሽ መሬት (አሬብል ላንድ) መጠን ሪፖርት እያቀረበ ነው፡፡ አምባገነኖች ሲባሉ የተጋነነ እስታቲስቲክስ እንደሚወዱ ታዲያ ልብ አድርጉ፡፡ ሚኒስትሩ ሆዬ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ባለሙያዎች ያቀረቡለትን የየክፍለ ሀገሩን ታራሽ መሬት በተናጠል ከተናገረ በኋላ ድምሩን ሲገልጽ የስብሰባ አዳራሹ በሣቅና ሁካታ ተሞላ፡፡ ሚኒስትሩ ደነገጠ፡፡ መንጌም ፈገግ አለ፡፡ ለካንስ ሰውዬው ያቀረበው የታራሽ መሬት ድምር ከሀገሪቱ የወቅቱ የቆዳ ስፋት የበለጠ ኖሯል!! አያድርስ እኮ ነው፡፡ ካልተዘነጋኝ ያኔ ኢትዮጵያ 1.212 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ነበራት፡፡ አጅሬ ‹በጠቅላላው 1.3 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ታራሽ መሬት አለን› ብሎ ይሆናል፡፡ ከአቢይ ግን በጣም ይሻላል፡፡ አቢይ እኮ አፍሪካን የሚሸፍን ችግኝ ለኢትዮጵያ ብቻ አውሎት አረፈው፡፡ ወይ ቀዳዳነት እናንተዬ!!)

  1. በደቡብ ለሚገነባው መናፈሻ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚፈጅ ራሱ አቢይ በመንግሥት ሚዲያዎች ሲያስነግር ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ገንዘብ ወዳማርኛ ሲመታ 110 ትሪሊዮን 330 ቢሊዮን ዶላር ማነው ብር ነው፡፡ ዕብደት ከዚህ የበለጠ የለም፡፡ ይህ የገንዘብ አሃዝ ውሸት መናገርን ከማፍቀርም በላይ ነው፡፡ እንዲህ ብሎ ሲናገር ይህን ሰው ይዞ ወዳማኑኤል ሆስፒታል ወይንም ወደሸንኮራ ጠበል የሚወስድ ሰው መጥፋቱ በርግጥም በመንግሥት መዋቅሩ ውስጥ አንድም ኦርቶዶክሳዊ አለመኖሩን ይጠቁማል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ እያሠራው የሚገኘውን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ይፈጃል የተባለ ቅንጡ ቤተ መንግሥት አስቡት፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ቤት ከሚያድረው በረንዳ የሚያድረው፣ ቀምሶ ከሚተኛው ጦሙን የሚውለው፣ ተረጋቶ ከሚኖረው የሚፈናቀለው በመቶ ሽዎችና በሚሊዮኖች በሆነባት ኢትዮጵያ በባዶ እግሩ ከሚሄድ ዜጋ በግድ በሚነጠቅ ግብር እንደዚህ መቀናጣት በዕብደት ብቻ ሊገለጽ አይችልም፡፡ ለማንኛውም የአዲሱ የገጠር መናፈሻ በጀት ኢትዮጵያና 120 ሚሊዮን የቁም ከብቶቿ ማለቴ ቤርቤረሰቦቿ ብንሸጥ አናወጣም፡፡ የዚህ ሰው ዱላው ብቻ ሳይሆን የሀሰት ንግግሩም ሊገድለን ነው፡፡ ጨርሰን ከማለቃችን በፊት እግዜር ይድረስልን፡፡ የኑሮ ውድነቱን ካየንማ ከማሳበድም በላይ ነው፡፡ እንጀራ ለማየትም ብርቅ ሆኗል፡፡  

አስደንጋጭ መርዶ!

ኦህዲድ ራሱ ከመፍረሱ በፊት ብዙ ነገሮችን እያፈራረሰ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በፒያሣ የሚገኙ ሱቆችን ሊያፈርስ መሆኑ  እየተነገረ ነው፡፡ ሁኔታው እልህ ይመስላል፡፡ እንደማይቆዩ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ በቀረቻቸው አጭር ጊዜ ማፍረስ የቻሉትን ሰብኣዊና ቁሣዊ ሀብት ሁሉ ማውደሙን ተያይዘውታል፡፡ በየትም ቦታ የሚገኙ አርከበ ሱቆቾንና በረንዳን ተመርኩዘው የተቀለሡ የዕለት እንጀራ ማግኛ ሱቆችን ያላንዳች ርህራሄ እያፈረሱ፣ ከኦሮሞዎች በስተቀር ባለባጃጆች የትም እንዳይሠሩ እያሣደዱ፣ ኦሮሞ ያልሆነን ከሥራና ከማንኛውም ጥቅም እያገዱ … በአዲስ አበባና እነሱ ባሉበት ሁሉ  በነሱው አጠራር ህጋዊ ድህነትን በየቀኑ እያስፋፉና በውጤቱም ሀገሪቱን በዕብድና ሰካራም እንዲሁም በበረንዳ አዳሪና ራስን በማጥፋት ቀቢፀ ተስፋ እየሞሏት ነው፡፡ ትልቅ የኅልውና አደጋ ላይ ነን፡፡ ግን ባዞሩብን አንዳች ነገር አብዛኞቻችን ጀዝበን ወይም ፈዘን እንገኛለን፡፡ ሦዶም ወገሞራዊ የመቅሰፍት ዶፍ እየወረደብን መሆኑን የማናውቅ ብዙ ነን፡፡ እየሞትንም ሞታችንን  የማናምን አለን፡፡ መንጋቱ ባይቀርም ጨለማው ከፍቷልና ውጭ ያላችሁ በተለይ ዝም አትበሉ፡፡ ቢያንስ ጩሁልን- ለዓለምም ለፈጣሪም፡፡ ያለንበት ችግር ከቃላት የመግለጽ አቅም በላይ  ነው፡፡ 

ለዚህ መርገማዊ ችግር መፍትሔው የፋኖ በቶሎ ወደ አራት ኪሎ መምጣት ብቻ በመሆኑ በዚህ አቅጣጫ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች በአስቸኳይ ይሠሩ፡፡ በሁዋል እዬዬና ፀፀት ዋጋ የለውም፡፡ ሰዎቹ አምርረዋል፡፡ ጭካኔያቸውም እንኳንስ በእግዚአብሔር በአባታቸው በዲያቢሎስም ቢለመኑ ደንታ አይሰጣቸውም፡፡ ከፋኖ ጋር የግንኙነት መስመር ያላችሁ ወገኖች አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ከመፈራረሷ በፊት ይህን መልእክት አስተላልፉላቸው፡፡ አደራ፡፡

ዐዋጅ! ዐዋጅ! ዐዋጅ!

ከዛሬ ጀምሮ ምርኮኛ አሥር አለቃ ብርሃኑ ጁላን “ኤታ ማጆር”፣ “ፊልድ ማርሻል” ብሎ የሚጠራ ጥቁር ውሻ ይውለድ፡፡ ሹመቱም ሆነ ወታደራዊ ማዕረጉ ኦሮሞን ለማስደሰትና የኦሮሞን የበላይነት ለማንጸባረቅ ሆን ተብሎ በ7ኛ ጨ ደንቆሮ ጠ/ሚንስትር ተብዬ የተሰጠ እንጂ ብርሃኑ ጀላ ማለት አሥር አለቃነትም የሚበዛበት በትምህርትም በሥልጠናም በዲሲፕሊንም እጅግ የወረደ ስብዕና ያለው መናኛ ሰው ነው፡፡ ለምሣሌ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ሆኖ ሣለ መለዮው ግን በዘረኝነት መጨቅየቱን የሚጠቁም የኦሮምያ ኢምፓየር ባንዲራ ነው፡፡ ይህን ከውሻ ያነሠ ዘረኛና ደደብ ሰውዬ ስለፊልድ ማርሻል ማዕረግ አሰጣጥ ይቅርና ማዕረጉን ራሱ የማያቅ አምባገነን ደንቆሮ ስለሰጠው ብቻ አሥር አለቃ ብርሃኑን በዚህ የተከበረ ማዕረግ ልንጠራው አይገባም፤ ሀገርንም ማዋረድ ነው፡፡ እነሱ ባያፍሩ እኛ እንፈርላቸው፡፡

ስለዚህ በትንሣኤያችን ማግሥት በዐዋጅ ሁሉን ነገር እስክናስተካክል ድረስ ይህን  ወራዳ ሰው እንደነገሩም ቢሆን በሚመጥነው ማዕረግ አሥር አለቃ ብለን እንድንጠራው በዕለተ ቀናቸው በሥላሤዎች እማጠናለሁ፡፡ ይህን መልዕክት ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ አሰራጩ(ልኝ)፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Filed in: Amharic