>
5:21 pm - Thursday July 20, 3758

ብልጽግና ፖርቲ ሚሊዮን ችግኝ ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን ችግር በመትከል የሚስተካከለው የለም...! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መልዕክተ ቅዳሜ፤ ችግኝና ችግር በሚሊዬን፤ 

ብልጽግና ፖርቲ ሚሊዮን ችግኝ ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን ችግር በመትከል የሚስተካከለው የለም…!

ያሬድ ሀይለማርያ

 

ሚሊዮን ችግሮች ቀስፈው በያዟት አገር በዛው ልክ መፍትሔዎችን ማምጣት የግድ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከመፍትሔዎቹ መካከል አንዱ ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ስለሆነ በጠቅላዩ የሚመራውን የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት ሳላደንቅ አላልፍም። አዎ ችግኞችን በብዛት መትከል ከተፈጥሮ መዛባት እና ከከባቢ አየር መለዋወጥ ጋር ተያይዘው የተከሰቱና ቀላል ግምት የማይሰጣቸው ድርቅ፣ እርሃብና መሰል ችግሮችን በዘለቄታ ለመቅረፍ ይረዳልና። ለዛሬና ነገ ባይደርስም ከአሥር አመታት በኋላ ዛሬ ከተተከሉት ችግኞች ግማሹ እንኳ ዛፍ ቢሆኑ መጪውን መከራ መቀነስ ይቻላል። ከችግኝ ተከላው ጋር የተያያዘው የቁጥር ፖለቲካ ላይ በማተኮር ይህን ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያለውን የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ ለማኮሰስ አልፈልግም። ያው ‘ካድሬና ቁጥር’ በሚል አልፈዋለው።

ኢትዮጵያ ዛሬ በሚሊዮን ችግሮች ተከባለች። ብልጽግና ፖርቲ ሚሊዮን ችግኝ ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን ችግር በመትከል የሚስተካከለው ያለ አይመስለኝም። በየቀኑ አዳዲስ ችግሮች በነባሮቹ ላይ እየተደራረቡ አገሪቱን ለመኖር ከባድም፣ አስፈሪም፣ አደገኛም የሚያደርጉ ገጽታዎች እያለበሷት ነው። በቅርቡ ይህ አሳሳቢ ችግር በአንድ የምክር ቤት አባል በጥያቄ መልክ የቀረቡላቸው ጠቅላዩ የሰጡት መልስ ብዙዎችን ያስደመመ ይመስለኛል። ጠቅላዩ ነገሩን ቀለል አድርገውና አጣጥለው ‘እንደውም ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሕዝቦች ‘አገራችሁ የተረጋጋችና ለኑሮም አመቺ ስለሆነች መጥተን እንኑር’ እያሉን ነው’ የሚል የስላቅ የሚመስል ምላሽ ነው የሰጡት። ይችን ጠቅላዩ የገለጿትን ኢትዮጵያን ከወዴት እንዳለች አብረው ቢጠቁሙን ድፍን ጦቢያ ውልቅ ብሎ ተሰዶ ወደዚች ሰላም የሰፈነባትና ለኑሮ አመቺ ወደሆነችው የተስፋይቱ ምድር ይተም ነበር። እኛም እርሶ ወደሚሏት ኢትዮጵያ ሄደን እንኑር ብሎ ጥያቄ ያቀርብ ነበር።

በእርግጥም እሳቸው የምትታያቸው ኢትዮጵያ የት ይሆን ያለችው?

በእርግጥ ችግኝና ችግርን አያይዘው በሰጡት መግለጫ ጠቆም አድርገው ያለፏት አንዲት ነገር ብዙ እሳቤያቸውን ታመላክታለች። ዛሬ የሚተከሉት ዛፎች ሲያድጉ ምግብ ባይሆኑ እንኳ የተራበ ሰው ከዛፎቹ ሥር በሚኖረው ጥላ  ሥር ጋደም ብሎ ርሃቡን ያሳልፋል ብለዋል። ርሃብ ጥላ ስር አረፍ በማለት የሚታለፍባትንም ኢትዮጵያ የምናይበት ዘመን እንደሚኖር ጥቋማ ይሆን? ከዛ ይልቅ ዛፍ በብዛት ካለ የመራብ እድላችን እየቀነሰ ይመጣል የሚለው አገላለጽ በቂና አመክኒዮ ያለው ይሆን ነበር። እንዲህ ያሉ የተፋለሱ የሃሳብ አገላለጾች በብዙ ንግግሮቻቸው ውስጥ የማያጡት ጠቅላዩ ሕዝብ በማንነቱ ወለጋ ውስጥ  ሲገደል ለምን ትኩረትዎን ዛፍ ተከላ ላይ ብቻ ያደርጋሉ የሚል ጥያቄ በምክር ቤት ደረጃ ሲቀርብላቸው “ቢያንስ የምንተክለው ዛፍ ለአስከሬናቸው ጥላ ይሆናል” የሚል ስላቅና ከሰበአዊነት የራቀ የሚመስለው ምላሻቸው ሚሊዮን ዛፍና ሚሊዮን ችግኝ እየተከልን የምንሄድበት ጉዞ እሩቅ እንደሆነ አመላካች ነው።

የዛሬ መልዕክተ ቅዳሜ ዋና ትኩረቴ እነዚህ ከዛፎቹ እኩል እየተተከሉ ያሉ ሚሊዮን ችግሮች ከዛፎቹ ጋር እኩል ተተክለው በላያችን ላይ እኩል እንዱበቅሉ ከተውናቸው አገር ሊያሳጡን፣ እልቂትና መከራን ሊበረቱብን፣ ስደት፣ እርሃብ፣ ሥራ አጥነት፣ አመጽ፣ ዝርፊያና ሙስናን መገለጫችን በሚሆኑበት ደረጃ ያጸኑብናል። ከቁጥጥር ውጭ የወጣው የኑሮ ውድነት፣ መረጋጋት ያልቻለው ፖለቲካችን፣ በየክልሉ የሚታዩት የሰላም እጦቶችና ግጭቶች የሚያሳዩት አገሪተቱ የከፋ ቀውስ ውስጥ መሆኗን ነው። ለቀወሰ ዘመን ደግሞ ቀውሱ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ጨርሶ የወደቀች አገር እንዳያረገን ብቸኛ መቆጣጠሪያ መንገዱ Crisis Management ወይም ቀውስን የመቆጣጠሪያ መንገድ መፈለግ ነው። ለጊዜው እኔ የሚታየኝ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት፤ መንግስት፣ ተቃዋሚ ፖርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራን፣ ሚዲያውና ሕዝብ የሚሳተፍበት፤ ከገዢው መንግስትም ሆነ ከሌሎች ጫናዎች ነጻ የሆነ የቀውስ አጥኝና መፍትሄ አፈላላጊ ብሔራዊ ግብረ ሃይል መቋቋሙ የግድ የሚልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለኛል።

ይህ ምንም አይነት የፖለቲካ ተልዕኮ የሌለው የቀውስ አጥኝና መፍትሄ አፍላቂ ግብረ ሃይል የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት፣ በጀት ተመድቦለት፣ አስፈላጊው ትብብርና ድጋፍ ተደርጎለት አገሪቱ የገባችበትን ቀውስ፣ የቀውሱን መጠንና ስፋት፣ የቀውሶቹን ምንጭ እና የአጭር ጊዜና ዘላቂ የሚሆኑ መፍትሔዎችን በጥናት አስደግፎ እንዲያቀርብ ቢደረግ ለተጀመሩት ቢሔራዊ የምከክር መድረክም ሆነ ተሳክቶልን እንደ ሀገር የሽግግር ፍትህ ማካሄድ ከቻልንም ለሱም ትልቅ ግብአትና አጋዥ ይሆናል። የብሔራዊ ምክክሩም ሆነ የሽግግር ፍትሂ ሂደቶች እጅግ አዝጋሚና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱ ስለሆነ ዛሬ ለገባንበትና አፋጣኝ መፍትሄ ለሚፈልጉት ቀውሶች ቶሎ ይደርሳሉ ብዮ አላምንም። ሁለቱም ሂደቶች ከቀውስ የወጣና የተረጋጋ የፖለቲካ አውድ ይፈልጋሉ።

ሚሊዮን ዛፍ እየተከልን ሚሊዮን ችግሮቻችንን ካልነቀልን ዛፎቹም፣ አገርም በችግሮቹ ይዋጣሉ። ቀውሱም ይበረታል። ለዛፍነትና ለጥላ የተመኘናቸው ችግኞች እርስ በርስ የምንናረትበት ዱላ ሆነው ይቀራሉ።

መልካም ቅዳሜ!

Filed in: Amharic