>

<< አርበኛን መሞት ማን አስተማረው ..... (ታሪክን ወደ ኋላ)

<< አርበኛ መሞት ማን አስተማረው 

 ታላቁ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው >>

ታሪክን ወደ ኋላ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በ 1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ማይጨው ድረስ ዘምተው ነበር። አርበኞች አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ጥቃት ሲያደርጉ ከሰላሴ ጦር ጋር ወደ አዲስ አበባ መጡ። ጥቃቱን ከሽፎ አርበኞቹ ሲያፈገፍጉ አቡነ ጴጥሮስ አዲስ አበባ ቀርተው ተማረኩ።

በእስር ላይ ሆነው ህዝቡ ለኢጣሊያ እንዲገዛ እንዲሰብኩ ተጠይቀው ነበር እርሳቸው ግን እንኳንስ ህዝቡ መሬቱን እንዳይገዛ በመግዘታቸው በቀድሞ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አጥር ስር የፋሽስት ጣሊያን ጦር በመትረየስ ጥይት ተደብድበው የተሠውት ከ 87 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነበር። የብፁዕ አቡን ጴጥሮስ ሞት ለአርበኞቹ የትግል እንቅስቃሴ በይበልጥ አቀጣጥለው።

<<< ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ >>>

…ጸሐፊው ሲገልጥ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር። በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ። ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣልያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው። የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር።

የቀረበባቸውም ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም ዐምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል የሚል ነበር። ዳኛውም «ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?» ሲል ጠየቃቸው።

አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መለሱ።….

 «አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለአገሬና ስለቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ» አሉ።

ኢጣልያዊው ጋዜጠኛ ቺሮ ፓጃሊ «እኒህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣልያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጐም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሐቀኛ ንግግር አላስተረጐመም። እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበባ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ኃላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቤ ተቀምጦ ስለነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለገለጠልኝ ነው። እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተሰበሰቡት ጣልያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰሙ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር» ይላል።

ሆኖም አስተርጓሚው በጳጳሱ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው እውነተኛ ንግግራቸው ሳይገለጥ እንደ ቀረ ይጽፋል። ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለእርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣልያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ይታይ ነበር።

«ይሙት በቃ» የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉና ደክሟቸው ስለነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡም ፈቀደላቸው። በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው። ብፁዕነታቸው እስከመቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ የሆነ ፍጹም የክብር ትሕትና ይታይባቸው ነበር።

የአገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ ለመገደል ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይጐዳ ግንብ ይፈለግ ጀመር። ሩቅ ባለመሔድ ከመካነ ፍትሑ 10 ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ። ከገዳዮቹም አንዱ «ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?» ሲል ጠየቃቸው። «ይህ የአንተ ሥራ ነው» ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ።

ከመግደያውም ቦታ እንደ ደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ።

ከዚያ በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው።

የብፁዕነታቸው አስከሬን ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር ተደረገ። በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ልቅሶና ዋይታ ሆነ» ሲል ጽሑፉን ይደመድማል።….

በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ልቅሶና ዋይታ ሆነ» ሲል ጽሑፉን ይደመድማል። ይህም ጠላት የሰጠው ምስክርነት በካቶሊካዊው ፓፓ ቡራኬ አገራችንን የወረረውን የፋሺስት ኢጣልያን ጦር አረመኔነትና በአንጻሩ የታየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጀግንነት ሲያረጋግጥ ይኖራል።

በተጨማሪም ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ «አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?» ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውም የሚከተለውን ተናግረዋል። «አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም የያዙትን መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በእሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው። ይህ እንደ ሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ።

ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት «በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል» አለኝ። «እንዴት?» ብለው «አላየህም ሲያጨበጭብ?» አለኝ። እኔም «ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል» አልኩት።«እንዴት?» ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት።

እሱም አሳየኝ። «ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ» ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኪስ ሰዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተሰንጥቋል። መስቀሉም ልክ በመሐከሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል። የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንደዚሁ ጥይት በስቶታል» ብለው ያዩትን መስክረዋል።»

/ትንሣኤ፣ቁጥር 58፣1978 ዓ.ም/

ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ግንቦት/ሰኔ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም

youtube.com/@TariknWedehuala

Filed in: Amharic