ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ።
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስትና በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 19 ቁጥር 3 አስቸኳይ ጉዳይ ሲያጋጥም ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያደርግ በተደነገገው መሠረት ሐምሌ 26ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የዶግማ፣ የቀኖናና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡
ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ሕዝብና አሕዛብን፣ ሰውና መላእክትን፣ ፍጡራን እና ፈጣሪን አንድ አድርጋ የሰው ልጆች ሁሉ በቋንቋ፣ በቀለምና በጐሣ ሳይከፋፈሉ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝተው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ የተወለዱ በማየ ገቦ ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመሆን ልዩነት የሌለባትን ዘለዓለማዊት መንግሥተ እግዚአብሔር እንዲወርሱ በደመ ክርስቶስ የተመሠረተች ስትሆን በየዘመናቱ የተነሣባትን ፈተና ሁሉ አልፋ ከእኛ ዘመን ደርሳለች፤
ምንም እንኳ ከኦርቶዶክስ ትምህርተ ሃይማኖት ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በጐሣና በቋንቋ የመለየት ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንግዳ ክስተት ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጠባይዋ በተለየ፣ ታሪኳንና ሥርዓቷን በማይመጥን፣ ከሕግ መንፈሳዊ፣ ከሕግ ጠባይአዊ እና ከሕገ አእምሮ በወጣ መልኩ የደረሰባት የዶግማ፣ የቀኖናና የአስተዳደር ጥሰት ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ አሳዝኖታል፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገር አንድነት፣ ለፍትሕ፣ ለጥበብ፣ ለሕዝብ ትስስር፣ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ለጤና፣ ለሥነ-ምግባር መሠረትና ዐምድ፤ ሆና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈራች፣ የተከበረችና የተወደደች፤ ዕሴቷ እና ዕምቅ የዕውቀት ሀብቷ በምሁራን የታወቀ፣ በትምህርተ ዓለም ሳይቀር የተቀረጸ፤ በእውነተኛ ሊቃውንት የተመሠከረ፣ ቅርሶቿ የተመዘገቡላት ስትሆን፤ ከፍተኛውን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲወጡ አደራ በተሰጣቸው ሊቃነ ጳጳሳት በማኅበረሰብ ዕድገትና አስተዳደር ውስጥ ከሕዝብ ጋር በቆመች፣ ከፖለቲካ በጸዳች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ መንፈሳዊና ሕዝባዊት ተቋምነቷን በመካድ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥ ድርጊትና ተቋምን የመናድ እንደሁም መዋቅሯን የማፍረስ ተግባር ተከናውኗል፡-
በዚሁ መሠረት፡-
ሐምሌ 16 እና 23 ቀን 2015 ዓ/ም በክልል ትግራይ በማእከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ገዳም ውስጥ የተፈጸመውን ሕገወጥ የሆነ አስነዋሪ፤ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አስመልከቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐምሌ 26ቀን 2015 ዓ/ም አስቸኳይ ምልዐተ ጉባዔ አድርጓል፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈተና የኖረችበት ጊዜ እንደሌለ ቅዱሳት መጻሕፍትና የታሪክ መዛግብት ሲመሰክሩ በዘመነ ሐዋርያት ቢጽ ሐሳውያን፣ በዘመነ ሊቃውንት የተለያዩ መናፍቃን፣… በየጊዜው እየተነሡ ሲፈታተኗት ኑረዋል፡፡ አሁንም በግልጽ እንደሚታየው ከውጭም ከውስጥም በተደራጁ ምንደኞች በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንኑ በመረዳትም ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባዔ፣ የሊቃውንት ጉባኤ፤ የሕግ አገልግሎት መምሪያና የህግ ባለሙያዎች አቢይ ኮሚቴ፤ የውጪ ግንኙነት መምሪያ፣ ካቀረቡት ዶግማዊ፣ቀኖናዊ፣ታሪካዊና ትውፊታዊ ሰነዶች በመነሣት የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለማስከበር ያስችል ዘንድ ጥልቅ ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህም መሠረት ሐምሌ 16 እና 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በክልል ትግራይ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ገዳም ውስጥ በትግራይ ክልል በሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፡-
1. አባ ኢሳይያስ
2 አባ መቃርዮስ
3. አባ መርሐ ክርስቶስ
4 አባ ጴጥሮስ መሪነት እጅግ አሳዛኝ ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፣ ሕገ-ወጥ፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በመፈጸም 10 መነኮሳትን በእጩነት በመምረጥና ለዘጠኙ ህገወጥ ሲመት በመፈጸም፣ ሥርወ ትውፊት ዘሐዋርያት የሆነውን የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መንበር በመካድ “መንበረ ሰላማ” የሚባል ህገወጥ መንበር በመሠየምና በህገወጥ መንገድ የሾሟቸውን ግለሰቦች ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው በሀገር ውስጥና በውጪ በሚገኙ አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ በመመደብ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አልፎ አንዲት ኩላዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የሚከፋፍል፤ የሀገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት ወጣትን ከወጣት የሚያጋጭ ሰላም የሚያናጋ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተገንዝቧል። በመሆኑም፤
– የቤተ ክርስቲያን መንበር ሐዋርያዊ ነው፡፡ ሐዋርያዊ መንበር ጌታችን አስተምሮ ከሾማቸው ከዐሥራ ሁለቱ ከሐዋርያት የወጣ አይደለም፤ ሥልጣነ ክህነት የሚተላለፍበት፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትምህርተ ሃይማኖት እና ቀኖና ምንጩ ወይም ሥሩ የሚነገርበት፣ የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን አማናዊና ሐዋርያዊ ታሪክ፣ ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት የሚጀመርበት መነሻ ነው፡፡
– ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በሐዋርያት ሥልጣነ ክህነት ነው፤ ይኽንን ሥልጣን ማንም እንደፈለገው ሊከፋፍለው አይችልም፤ በየትም ቦታ ያሉ ጳጳሳት ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከቅዱስ ፓትርያርክ ዕውቅና ውጭ እንደፈለጉ በቡድኑ እየሆኑ መንበር አቋቁመናል ሊሉ አይችሉም፤ ይህ ከቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ታሪካዊ ቅብብል ውጭ የሆነ መናፍቅነት ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ እና ሥርዓት ውጭ መውጣት ሕገ ወጥነት፣ ቀኖናን መሻር፣ ኃይማኖትን ማፍረስ ነው፡፡ የገቡትን ቃል መጣስ ነው፤ ከጥንት ጀምሮ መንበር ያለ ፓትርያርክና ከሀገሪቱ ርእሰ ከተማ ውጭ የማይሰየም መሆኑ እየታወቀ መንበር አቋቁመናል ማለት የፓትርያርክን እና የሲኖዶስን ሥልጣን መቃወም፤ ከሃይማኖትም፣ ከቀኖናዊ ትውፊትም፣ ከአስተዳደራዊ መዋቅርም መውጣትና ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያን መንበር የለዩ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ድርጊቱን አውግዟል፡፡
ይህን ህገወጥ ተግባር ለመፈጸም በሀገራችን ተከስቶ የነበረው ጦርነት እንደ ምክንያት የተጠቀሰ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከጦርነቱ በፊት ጦርነት እንዳይከሰት ያደረገችውን ጥረት በጦርነቱ ወቅት ለተደረጉ ድጋፎችና ከጦርነቱ በኋላ ለተደረጉ የእንወያይ ጥረቶች እንዲሁም በቤተክርስቲያን በኩል የተዘረጋውን የሰላምና የእርቅ በር ይልቁንም ለሰላም ሲባል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የተጠየቀውን ይፋዊ ይቅርታ በመግፋት የተደረገ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ነው።
በመሆኑም
• በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 30 የአጲስ ቀጶሳት መሾም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንዲመረጡና እንዲሾሙ የመወሰን ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆን የሚደነግገውን ክፍል በግልጽ የጣሰ በመሆኑ • በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 31 ንዑስ ቁ 1 እና 3 የቅዱስ ፓትርያርኩን የመዓርግ ስምና መንበር በተመለከተ የተደነገገውን ድንጋጌ የሚያፋልስ ህገወጥ ተግባር የተፈጸመ በመሆኑ
• በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 ንዑስ ቁ.1 የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሚፈጸመው ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስፈላጊ መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲታመንበትና ሲወሰን ብቻ እንደሚፈጸምና መደንገጉ፤
• በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 18 ንዑስ ቁጥር 5 የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ሕግጋትንና ቀኖናን የሚያፋልስ ሊቀ ጳጳስ /ኤጲስ ቆጶስ/ ከአባልነት እንደሚሰረዝ በመደንገጉ፤
• በአጠቃላይ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ተግባር በሕገ ሰብእም ሆነ በሕገ እግዚአብሔር ሚዛን የተወገዘ ከመሠረተ እምነት የተለየ፣ በአበው ቀኖና፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ተቀባይት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ
1ኛ. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 138 መሠረት ሐምሌ 16 እና ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በክልል ትግራይ በማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ውስጥ
1. ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ የመቀሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንቅስቃሴው ሰብሳቢ
2. ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በክልል ትግራይ የማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
3. ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
4. ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ስልጣን 9 ኤጴስ ቆጰሳትን ሾመናል፤ ሲኖዶስ አቋቁመናል በማለት በተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫና በክልሉ መንግሥት ሚዲያ በተላለፈው የቀጥታ ስርጭት የተረጋገጠ በመሆኑ በዚሁ ድርጊታቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ሕዝበ ክርስቲያንን በማታለል የክህደት እና የኑፋቄ ተግባር በመፈጸማቸው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ፤ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ ለይቷቸዋል፡፡
በመሆኑም፡-
ሀ. ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የተነሣ ስለሆነ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ፤
ለ. በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡
• ይሁን እንጅ ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳውቃል፤
2ኛ. የቅዱስ ሲኖዶሱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና በመዳፈር እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በተነሳሱ ግለሰቦች አማካኝነት የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት አግኝተናል፤ ተሹመናል እያሉ የሚገኙ 9 መነኮሳት
፩. አባ ዘሥላሴ ማርቆስ
፪. አባ ኃይለ ሚካኤል አረጋይ
፫. አባ እስጢፋኖስ ገብረ ጊዮርጊስ
፬. አባ መሓሪ ሀብቶ
፭. አባ ኤልያስ ታደሰ ገብረ ኪዳን
፮. አባ ጽጌ ገነት ኪዳነ ወልድ
፯. አባ ዘርአ ዳዊት ብርሃነ
፰. አባ ዮሐንስ ከበደ
፱. አባ የማነ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያ በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡
3ኛ. ይህ ህገወጥ ሢመት እንዲፈጸም ከመጀመሪያው ጽንሰ ሀሳብ ጀምሮ መሪ ተዋናይና ቀስቃሽ በመሆን ኢትዮጵያን ኤልዛቤል በማለትና ስሟን የሚጠራ የተረገመ ይሁን በማለት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር የዶግማ ልዩነት አለን በማለት የኑፋቄ ትምህርት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩትና በህገወጥ ሢመቱ ላይም በእጩነት ተመርጠው በሂደት ላይ ያሉት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልና ሂደቱን በዋና አስፈጻሚነት በመምራትና መግለጫ በመስጠት ላይ ያሉት መ/ር ተስፋዬ ሐደራ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተክርስቲያን ተለይተዋል።
ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳውቃል።
4ኛ. “መንበረ ሰላማ” የሚለው ሕገወጥ ሥያሜን በተመለከተ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትውፊትም ሆነ በቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት የማይታወቅ፣ ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለው፣ ከቀኖና የወጣ፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን የሚያዛባ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፤ በተጨማሪም ከአንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊትየሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መንበር መሠረተ እምነት፣ ታሪክና ቀኖና፣ ከአስተዳደር እና ሕግ ባፈነገጠ ሁኔታ ትውፊትን በመዳፈር ጎሣን መሠረት አድርጎ የተፈጠረ ሕገ ወጥ አደረጃጀት በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዞታል፡፡ ይሕንንም የክርስትናን ትውፊት እና ሐዋርያዊ መሠረት የሚዛባና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማይወክል መሆኑ ታውቆ በመላው ዓለም ለሚመለከተው ሁሉ በደብዳቤ እንዲገለጽ እንዲደረግ፤
6. በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት፤ አገልጋይ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማህበራት እና ምእመናን እና ምእመናት ይህን ሕገ ወጥ አድራጎት ከመከላከል እና የቤተ ክርስቲያናችሁን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ለዚህ ሕገ ወጥ አድራጎት ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያደረግ ተቋማት እና ግለሰቦችን አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የመከላከል ሥራችሁን እንድትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
8. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስምን ከፊትም ሆነ ከኃላ በመጨመር እና በመቀነስ በከፊልም ሆነ በሙሉ መጠቀም፤ ዓርማዋን፤ አድራሻዋን፤የአምልኮ እና የሥርዓት መፈጸሚያ የሆኑ ንዋያ ቅዱሳትንና አልባሳት እንዲሁም መጻሕፍት መገልገል የማይችሉ መሆኑ ታውቆ ይህንን ጉዳይ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በተጨማሪም ይህን ውሳኔ ተላልፈው በሚገኙ ማናቸውም ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ተገቢውን ሕግ አግባብ ተከትሎ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለማት የሚያስፈጽም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች በመመደብ ተገቢውን ሁሉ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
9. በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ መንግስታዊም ሆነ መነግስታዊ ያልሆነ ተቋማት፤ አኃት አቢያተ ክርስቲያናት፤ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፤ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት፤ የዓለም አቢያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያት ክርስቲያናት ጉባዔ እና ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ጉባኤዎች በሙሉ እነዚህ የተወገዙት ግለሰቦች የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ እና ምንም አይነት የሥራ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ታውቆ ማናቸውም ግንኙነት በቤተ ክርስቲያኑቱ ስም እንዳያደርጉ በጽሑፍ አንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
11. እነዚህ ግለሰቦች የፈጸሙት ተግባር ሃይማኖቱን የሚወድ፣ አባቶቹን የሚያከብር እና አስተዋይ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ የማይወክል፣ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ያደረጉት ሕገወጥ የቀኖና ጥሰት መሆኑ እንዲታወቅ፤ በተጨማሪም ለሚያሠራጩት የሐሰት አሉባልታ ወደፊት ተገቢው መልስ እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።
12. ይኽ ሕገወጥ አደረጃጀት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የታሰበበት፤ በየጊዜው የነበሩ የፖለቲካ እና የመንግሥት ኃላፊዎች በመታገዝ ሥር የሰደደ ድብቅ አጀንዳ በሚያስፈጽሙ ግለሰቦች የተቀናበረ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተገንዝቦ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞታል፡፡ በመሆኑም ሕገ ወጥ አደረጃጀትን ማምከን እና ቤተ ክርሰቲያንን ነፃ ማድረግ የሚቻለው ጠንካራ ውስጣዊ አደረጃጀት እና ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ሲደረግ በመሆኑ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ ሊቃውንት፣ መላው ውሉደ ክህነት፣ ወጣቶች ሰንበት ትምሀርት ቤት አባላት፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያን ወዳጆች በሙሉ በመጾም፣ በመጸለይ፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮና መዋቅር በጠበቀ መልኩ በመደራጀት አፍራሽ እና የጥፋት መረጃዎችን፣ በመሰብሰብ፣ በመተንተን፣ ለውሳኔ በማቅረብ የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ደኅንነት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ተጋድሎ መበርታትና የመጣብንን ፈተና በጽናት መታገል እንደሚገባ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
13. በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በተለያዩ ክፍሎች እየተከሠተ ያለውን የሰላም መደፍረስ እና የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመት የተፈጠረ አለመግባባት ካለፈው ስህተታችን በመማር ችግሩን ተቀራርቦ በውይይትና በእርቅ እንዲፈታ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም አካላት የሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
14. እንደ ሀገር የገጠመንን የሰላም መደፍረስ በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ እንደ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰላም ጉዳይ የሚሠሩ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን ያካተተ ዐቢይ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ በኩል ተቋቁሞ ሥራው እንዲሠራ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም እስከ አሁን ድረስ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን በመሆን አጋርነታችሁን ያሳያችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ሉዐላዊነት መከበር የበኩላችሁን በመወጣት መግለጫ የሰጣችሁ ሁሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም እያመሰገንን ለወደፊቱም በጸሎታችሁ እና በመልካም አጋርነታችሁ ከጎናችን እንድትሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ