>

ሰላማዊ ትግል፤ የኤርምያስና የልደቱ የወቅቱ ማጭበርበሪያ (መስፍን አረጋ)

ሰላማዊ ትግል፤

የኤርምያስና የልደቱ የወቅቱ ማጭበርበሪያ

መስፍን አረጋ

በኔ በመስፍን አረጋ ዕይታ በሰላማዊ ትግል አርበኝነቱ ወደር የሌለው አርበኛ እስክንድር ነጋ፣ ያማራን ሕልውና በማዳን ጦቢያን ለማዳን የወሰደው ትልቁ እርምጃ የሚከተለው ነው።  እሱም ሰላማዊ ትግል ሊሠራ የሚችለው ግባቸው ትግራይና ኦሮምያ ለሆነው ለትግሬና ለኦሮሞ ጎጠኞች እንጅ፣ ግቡ ጦቢያ ለሆነችው ለጦቢያ ብሔርተኛው ላማራ ሕዝብ እንደማይሠራ ተረድቶ የትጥቅ ትግል አርበኛ ለመሆን መወሰኑ ነው።  ሰላማዊ ትግል ግቡ ጦቢያ ለሆነችው ለጦቢያ ብሔርተኛው ላማራ ሕዝበ ለምን እንደማይሠራ ደግሞ በዚህ ጦማር ላይ እንመለከታለን። 

የኢትዮጵያዊነት ካባ የለበሱት የፀራማሮቹ ያቶ ኤርምያስ ለገሰና ያቶ ልደቱ አያሌው እንዲሁም የመሰሎቻቸው የወቅቱ ማጭበርበሪያ “ያማራ ሕዝብ ጥያቄ ፍትሐዊ ነው፣ ጥያቄውን ማስመለስ ያለበት ግን በትጥቅ ትግል ሳይሆን በሰላማዊ ትግል ነው” የምትል ቀልድ ናት።  ልጅ ለናቷ ምጥ አስተማረች እንዲሉ፣ አቶ ኤርምያስና መሰሎቹ፣ በሰላማዊ ትግል ደቁኖ የቀሰሰውን፣ በሰላማዊ ታጋይነቱ በወያኔና በኦነግ አረመኔወች ላያሌ ዓመታት መከራና ፍዳ የበላውን፣ ሳይወድ በግዱ ወደ ትጥቅ ትግል የዞረውን እስክንድር ነጋን ወደ ሰላማዊ ትግሉ እንዲመለስ ሊመክሩት ሲደፍሩ ይታያሉ።  ለምን? 

“አማራ፣ አማራ አትበሉኝ” ብሎ ኢትዮ360ን ጥሎ በመውጣት ከወያኔ ፀራማራ ሚዲያወች ጋር ተጣብቆ፣ እንደነ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔን  የመሰሉትን ያማራን ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ባልተገራ አፉ የሚዘልፈው አቶ ኤርምያስ ለገሰ፣ ላማራ ሕዝብ በጎ እንደማይመኝለት የታወቀ ነው።  ስለዚህም አቶ ኤርምያስ ለአማራ ሕዝብ ስለ ሰላማዊ ትግል ለመስበክ የተነሳው፣ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት እያመጣለት ያለውን የትጥቅ ትግል ርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ምንም ውጤት ወደማያመጣለት ሰላማዊ ትግል በመዞር፣ የኦነግን ጭፍጨፋ እንዳይክላከል ለማድረግ ባለው ምኞት መሠረት ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም።

ስለዚህም፣ ኤርምያስ ለገሰ፣ ልደቱ አያሌውና መሰሎቻቸው ያማራ ሕዝብ እንዲከተል የሚፈልጉት ሰላማዊ ትግል ላማራ ሕዝብ የማይሠራበት ምክኒያት ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ የግድ ነው።

ሰላማዊ ትግል ማለት መከራንና ፍዳን ላለም ሕዝብ በጩኸት ማሳወቅና፣ ባለም ሕዝብ አጋርነት መክራንና ፍዳን ማስወገድ፣ ቢቻል ደግሞ ወንጀለኞቹን በሕግ ማስጠየቅ ማለት ነው።  ባለመታደል ግን ባሁኑ የዓለም ሁኔታ፣ መከራንና ፍዳን ላለም ሕዝብ ማሳወቅ የሚቻለው በምዕራባውያን ሚዲያወች አማካኝነት ብቻ ነው።  

ምዕራባውያን በግዙፍ ሚዲያወቻቸው (BBC, CNN, New York Times, Economist, etc.) እና በሆሊወድ (Hollywood) አማካኝነት ባለማችን ላይ የፕሮፓጋንዳ የበላይነትን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ስለጨበጡ፣ ትርክቶችን (narration) ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመቆጣጠር፣ የሚፈልጉት ሰይጣን መልዓክ መስሎ፣ የማይፈልጉት መልዓክ ደግሞ ሰይጣን መስሎ ባበዛኛው ያለም ሕዝብ እንዲታይ ማድረግ ይችላሉ፣ አብዛኛው ያለም ሕዝብ የእውቀት ደረጃው እጅግም ነውና።  ስለዚህም ባሁኑ የዓለም ሁኔታ ማናቸውም ሰላማዊ ትግል የመሳካት ዕድል የሚኖረው፣ ትግሉ ለምዕራባውያን ጥቅም የሚበጅ መሆኑን ምዕራባውያን አምነውበት ግዙፍ ሚዲያወቻቸው ሙሉ ፕሮፓጋንዳዊ ድጋፍ ካደረጉለት ብቻ ነው።  

ለምሳሌ ያህል የትግሬ ወይም የኦሮሞ ጎጠኞች ሰላማዊ ትግል ቢያደርጉ፣ ሰላማዊ ትግላቸው የመሳካቱ ዕድል እጅግ ከፍተኛ ይሆናል።  ምክኒያቱ ደግሞ የነሱ የጎጠኝነት ትግል ጦቢያን በማዳከም ምዕራባውያንን የሚጠቅም በመሆኑ ሳቢያ፣ ምዕራባውያን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚደገፉትና ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳዊ ሽፋን ስለሚሰጡት ነው። በሺ የሚቆጠሮ አማሮች ባንድ ቀን ጀንበር ሲታረዱ፣ እንዲሁም አዲሳባ ላይ (አፍንጫቸው ሥር) አማሮች በማንነታቸው ብቻ በግፍና በገፍ ሲታሰሩ ድምጻቸውን ያላሰሙት BBC እና CNN፣ ለትግሬወች ሲሆን ግን ያልተፈጸሙ ወንጀሎችን እየፈበረኩ፣ አማሮችን ወንጀለኛ ለማድረግ በሚያስገርም ደረጃ የተጣጣሩት፣ ትግሬወችን በትግሬነታቸው ወደዋቸው ሳይሆን፣ የትግሬወች ጦቢያን የመበታተን ትግል ምዕራባውያንን እጅጉን የሚጠቅም ሁኖ ስላገኙት ብቻ ነው።

በሌላ በኩል ግን ያማራ ሕዝብ ትግል የነጭን የበላይነት ክፉኛ የሚገዳደር ለሁላፍሪቃነት (panafricanism) መሠረት የሆነ የጥቁር ሕዝብ ትግል ነው።  ያማራ ሕዝብ፣ ጦቢያዊነቱን ካማራነቱ የሚያስቀድም፣ ብሔርተኝነቱ ኢትዮጵያዊነት የሆነ፣ ድርና ማግ ሆኖ ጦቢያን ያስተሳሰረ የጦቢያ ትልቁ ሕዝብ ነው፡፡  የጦቢያ ብሔርተኝነት (Ethiopian nationalism) ያማራ ብሔርተኝነት (Amhara nationalism) ነው የሚባለውም በዚሁ ምክኒያት ነው፣ የጦቢያ ብሔርተኝነትን በብዛትና በጥልቀት በማቀነቀን ያማራን ሕዝብ የሚስተካክል ማንም የለምና፡፡  ሁሉንም የጦቢያን ብሔረሰቦች ባንድነት በማነሳሳት ታላቁን ያድዋን ድል እንዲጎናጸፉ ያስቻላቸው ይህ ያማራ ብሔርተኝነት ነው የሚባለው የጦቢያ ብሔርተኝነት ነው፡፡  መላዋ አፍሪቃ ነጻ እንድትወጣና የመላው ዓለም ጥቁሮች በማንነታቸው እንዲኮሩ (black pride) መሠረት የጣለውም ይኸው ያማራ ብሔርተኝነት ነው የሚባለው የጦቢያ ብሔርተኝነት ነው፡፡ 

የምዕራቡ ዓለም የሚሽከረከረው ደግሞ ጥቁርን በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ለመግዛት የተፈጥረን ነን ብለው በጽኑ በሚያምኑ በነጭ ላዕልተኞች (white supremacists) ዙርያ ነው።  ስለዚህም የምዕራቡ ዓለም ሙሉ ፍላጎት የጥቁር ብሔርተኝነት መሠረት የሆነው ያማራ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ቢጠፋላቸው ወይም ደግሞ ያማራ ሕዝብ በጦቢያ ፖለቲካ ላይ ይህ ነው የሚባል ሚና መጫወት እስከማይችልበት ደረጃ ድረስ በቁጥር ቢመናመንላቸው ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም፡፡   ወያኔና ኦነግ ባማራ ሕዝብ ላይ ለሚያካሂዱት መጠነ ሰፊ የዘር ጭፍጨፋ የተለያዩ ምክኒያቶችን ሰበብ በማድረግ ሙሉ ሞራላዊ፣ ቁሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፕሮፓጋንዳዊ ድጋፍ የሚያደርጉላቸውም ይህንኑ ፀራማራ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ነው፡፡  

ስለዚህም ሰላማዊ ትግል ላማራ ሕዝብ እስካሁን ድረስ አልሰራም፣ የምዕራባውያን የፕሮፓጋንዳ የበላይነት እስካለ ድረስ ደግሞ መቸም ቢሆን አይሰራም፡፡  በዚህ ምክኒያት ነው ያማራ ሕዝብ እስካሁን ደረስ ያደረገው ሰላማዊ ትግል ይበልጥ የጎዳው እንጅ ምንም ያልጠቀመው።  

ለምሳሌ ያህል በ1997ቱ የቅንጅት ዐብዮት ላይ፣ ለሰላማዊ ትግል የወጣው ባብዛኛው አማራ የሆነው ያዲሳባ ሕዝብ በመለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዛዝ በወያኔ አጋዚ ሠራዊት በግፍና በግፍ ሲጨፈጨፍ፣ አሜሪቃና እንግሊዝ ያደረጉት አጋዚን ለማሰልጥን በሚል ሰበብ ለመለስ ዜናዊ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር መስጠት ነው።  በሌላ አባባል እንግሊዝና አሜሪቃ ለመለስ ዜናዊ በተዛዋሪ የነገሩት፣ እልፍ አእላፍ ዶላር ፈሰስ እንድናደርግልህ ከፈለክ አማሮችን ጨፍጨፍ ነው።  ስለዚህም በ2000 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ላይ 2.5 ሚሊዮን (ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ) አማሮች ደብዛቸው ጠፍቷል በማለት መለስ ዜናዊ ትልቅ ጀብድ የፈፀመ ያህል በራሱ ፓርላማ ላይ በኩራት መንፈስ የተናገረው  ምዕራባውያን ጌቶቹን በማስደሰት ከፍተኛ  ገንዘብ ለማግኘት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።  

ስለዚህም ያማራ ሕዝብ ለሕልውናው የሚያደርገውን ትግል መቅረጽ ያለበት ትግሉ ከኦነግና ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ከምዕራባውያንም ጋር በመሆኑ ሰላማዊ ትግል የትም እንደማያደረሰውና ያለው አማራጭ የትጥቅ ትግል ብቻ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡  የአማራ ሕልውና ትግል አመራሮች ደግሞ፣ ፀራማሮቹ ኤርምያስ ለገሰ፣ ልደቱ አያሌውና መሰሎቻቸው፣ ላማራ ሕዝብ ሲሆን ብቻ ስለ ሰላማዊ ትግል የሚሰብኩት፣ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ያለውን ያማራን ሕዝብ የትጥቅ ትግል ለማኮላሸት ሲሉ ብቻ እንደሆነ ተረድተው፣ ጆሯቸውን ሊነፍጓቸው ይገባል።  

ባጭሩ ለመናገር አቶ ኤርምያስ ለገስ፣ አቶ ልደቱ አያሌውና መሰሎቻቸው ላማራ ሕዝብ አዛኝ መስለው የሚቀርቡ አዛኝ ቅቤ አንጓቾች ናቸውና፣ ያማራ ሕዝብ ጆሮ ዳባ ልበስ ሊላቸው ይገባል።  ባሁኑ ወቅት ከትጥቅ ትግል በስተቀር፣ ሰላማዊ ትግል፣ ሽምግል፣ ግልግል እንዲሁም ውይይት፣ ንግግር፣ ድርድር የሚሰኙት ሁሉ ያማራን ሕዝብ ይበልጥ የሚጎዱ እንጅ ምንም የማይጠቅሙ ያማራ ጣላቶች ወሬወች ናቸው።  

የወያኔና የኦነግ ውሾች፣ ውሾች ናቸውና በበሉበት ይጩሁ።  አህዮቹም አህዮች ናቸውና ምዕራባውያን በሚደፉላቸው ዐመድ ላይ ይንከባለሉ።  አንበሳው ያማራ ሕዝብ ደግሞ የውሾቹን ጩኸት ሰምቶ እንዳልሰማ፣ ያህዮቹን መንከባለል አይቶ እንዳላየ በመሆን፣ እንቅፋቶቹን ሁሉ በክንዱ እየሰባበረ፣ የጭራቅ አሕመድን መንግሥት ገርስሶ፣ ዘላለማዊ ጠላቶቹን ወያኔንና ኦነግን ለዘላለም እስከሚያስወግድ ድረስ ያንበሳ መንገዱን ይቀጥል።

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic