እናንት ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያን›* የእሰካሁኑ ነውራችሁ ይበቃል
ከይኄይስ እውነቱ
ከአይሁድ የእምነትና ፖለቲካ ማኅበራት መካከል ጸሐፍት ፈሪሳውያን ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ስብስቦች አመዛኙ በግብዝነት የታወቁ፣ ቀሚሳቸውን እያስረዘሙና ካባቸውን እያንዠረገጉ እምነትን ለርእይ (ታይታ) ብቻ የሚፈልጉ፣ በወግ አጥባቂነት ተከልለው ለግል ጥቅማቸው ያደሩ፣ ከእውነት የተጣሉ ነገር ግን የአምልኮ መልክ ያላቸው፣ የሕይወት ባለቤት መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና ተቃዋሚዎች ነበሩ፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ ስለ ጻፎችና ፈሪሳውያን ጠባያት ሲናገር፤
‹‹ … እናንተ ዐላዋቆች የውጭውን የምታጠሩ ውስጣችሁ ግን በቅሚያ የተመላ ነው፡፡ …ከዐሥር አንድ የምትቀበሉ÷ ሃይማኖትንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ቸል የምትሉ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! በሸንጎ ፊት ለፊት መቀመጥን÷ በገበያ እጅ መነሣትን ትወዳለችሁና፡፡ …ሰው በላዩ እንደሚመላለስበትና እንደማይታወቅ መቃብር ናችሁና፡፡ … ሰውን ከባድ ሸክም ታሸክሙታላችሁና፤ እናንተ ግን ያንን ሸክም ባንዲት ጣታችሁ እንኳን አትነኩትም፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ትሠራላችሁ፡፡ የሀገር ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! የጽድቅንና የአእምሮ መክፈቻ ይዛችሁ ተደብቃችሁአልና፤ እናንተም አትገቡምና፤ የሚገቡትንም መግባትን ትከለክሉአችዋላችሁና፡፡ …ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፤ ይኸውም ግብዝነት ነው፡፡ የማይገለጥ ሥውር የማይታይ ሽሽግ የለምና፡፡›› ይላል፡፡
ይህ የወንጌሉ ቃል ትርጓሜ ሳያሻው ስለ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ማንነት ብዙ ይናገራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በጥቂቱ ልናነሣ የፈለግነው ስለ ዘመናችን ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያን› ነው፡፡
ባለፉት አራት ዐሥርታት በኢኦተቤክ ተቋማት ባጠቃላይ በቤተክህነቱ፣ በተለይም በሲኖዶሱ ተከልለው፣ የቀሩትም በየአድባራቱና ገዳማቱ ሳይገባቸውና ሳይገባቸው (‹ገ› ላልቶና ጠብቆ የሚነበብ) በኃላፊነትና በተለያየ የአገልግሎት ደረጃ ተሰይመው የሚገኙ፣ መሠረተ እምነት÷ ቀኖና እና ሥርዓት ተጥሶ በዘረኝነትና በንዋይ የተሾሙ፣ ተልእኮአቸውን ያልተረዱ፣ ከእምነትም ሆነ ከምግባር የተራቆቱ፣ ከትምህርቱም ሆነ ከመንፈሳዊነቱ ጦመኞች የሆኑ፣ ጥብዐት የሌላቸው፣ ታላቁን የክህነት ሥልጣን ያቀለሉ፣ አርዓያ ክህነት የሌላቸው፣ ገሚሱም ክህነታቸውን በነውር ያፈረሱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዐላውያን አገዛዞች ያስደፈሩ፣ መንጋውን ያለ እረኛ የበተኑና ተቅበዝባዥ ያደረጉ፣ ምእመኑን እንደ ጥገት ላም ለገንዘቡ ብቻ የሚፈልጉ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ቅርስ የመዘበሩና ያስመዘበሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን የወንበዶች (የመናፍቃንና የአገዛዞች ካድሬዎች) ዋሻ ያደረጉ፣ ምእመኑን አንገት ያስደፉ÷ቤተ ክርስቲያንን ያዋረዱ፣ አልፎ ተርፎም የዐላውያን አገዛዞች መሣሪያ በመሆን በመንፈስ ቅዱስ ይመራ የነበረውን ሲኖዶስ የጐሣ ሸንጎ ያደረጉ፣ ከአገር ዐበይት አዕማዶች መካከል ቀዳሚው የሆነውን የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲናጋ በማድረግ የአገርና የሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ በመጣል የበኩላቸውን አፍራሽ ሚና የተጫወቱ ከርእሰ ሊቀ ጳጳስነት እስከ አናጕስጢስነት ያሉ ‹ካህናትን› ይመለከታል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከዚህ በላይ በተመለከተው አገላለጽ ውስጥ የሚወድቁ ‹ካህናት›ን ብቻ ነው ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያን› የሚል ስያሜ የሰጠኋቸው፡፡
ሰሞኑን በኹሉም የውጊያ ዐውደ ግምባር ከፍተኛ ሽንፈት የገጠመው የርጉም ዐቢይ ሠራዊት መጨረሻው መቃረቡን ዐውቆ የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፍቶት የሐሰት ሽምግልና ካርድ እንደገና መዝዟል፡፡ የዐምሐራው ሕዝብ ስስ ብልት ሃይማኖቱ ነው በሚል በዚህ ተውኔት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ሊያደርግ ያሰበው ‹ጳጳሳትን› እንደሆነ መረጃው ይፋ ወጥቷል፡፡ ለዚህ ተልእኮ የተመረጡት ‹ጳጳሳትም› በጎንደር ከተማ ውስጥ ከአገዛዙ አሽከሮች ጋር እየዶለቱ መሆኑን እና ምእመኑንም የዚህ አጥፊ ተልእኮ ተባባሪ ለማድረግ እንዳቀዱ ታውቋል፡፡
የዐምሐራው ሕዝብ ለሠላሳ ኹለት ዓመታት በምድራችን ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ሰቈቃ ሲደርስበት ላንድ ጊዜ እንኳን ዐደባባይ ወጥተው በይፋ ያልተቃወሙና ያላወገዙ፣ ምእመኑን ያላጽናኑና ያልደገፉ፣ ክቡሩ የሰው ልጅ እንደ ቆሻሻ በግሬደር እየተዛቀ በጅምላ ሲቀበር ሥርዓት ያለው ቀብር እንዲያገኝ ያላደረጉ፣ ጸሎተ ፍትሐት ያላደረጉ፣ በአካል በመሔድም ይሁን በሲኖዶስ ተሰባስበው ለሟች ቤተሰቦች አንዳች ድጋፍና ዕርዳታ ያላደረጉ (ይልቁንም ምእመኑ ለምኖ ጭምር የሚሰጠውን ገንዘብ ለፋሽስታዊው አገዛዝ አሳልፈው የሚሰጡ)፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቃዮችን አይዞአችሁ አለንላችሁ በማለት ርኅራኄ÷ልግስናና ቸርነት ያላሳዩ፤ ይልቁንም ፋሺስታዊው አገዛዝ በመላው የዐምሐራ ሕዝብ ላይ ከወራት በፊት ያወጀበትንና ሲያከሒደው የቆየው ጦርነት ባሰበው መልኩ ሳይሳካለት ሲቀር ሰላማዊውን ሕዝብ በአየርና በከባድ መሣሪያ በመደብደብ እልቂት ለመፈጸም ይፋ ዓዋጁን ተግባራዊ ባደረግ ማግስት የፋሽስቱን ዓዋጅ በተግባር በመደገፍ ሕዝባችን ከህልውናው ትግል እንዲናጠብ የሚያደርግና በርጉም ዐቢይ በተቀነባበረ የውሸት ሽምግልና ውስጥ ለመሳተፍ መወሰናቸው በራሱ እነዚህን ‹ጳጳሳት› የዐምሐራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኢኦተቤክ ብሎም የኢትዮጵያ ጠላት ጋር ባንድነት የሚያሰልፋቸው ነው፡፡
እነዚህ ራሳቸው ሽባ ሆነው ምእመኑንም አላላውስ ያሉ የስም ጳጳሳት ደግመው ደጋግመው የሚያሳዩት ግብዝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ጥብዐት ማጣት፣ ሆዳምነት ባጠቃላይ ነውረኛነት፣ ውገናቸው ከእውነት ጋር ሳይሆን የጥፋት ኃይሎች ከሆኑት የአጋንንት ሠራዊት ጋር በመሆኑ በምድርም ሆነ በሰማይ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ የርጉም ዐቢይ ፋሺስታዊ አገዛዝ አገር የማፍረሱ አንዱ ተልእኮ አገራችን በእምነት እና በባህል በኩል ለዘመናት ያፈራቻቸውን ድልብ እሤቶች (ሽምግልናን ማቅለል፣ የሃይማኖት አባቶችን ማዋረድ) ማጥፋት መሆኑ ቢታወቅም በዚህ አጋንንታዊ ተልእኮ ውስጥ የተሰማሩት ‹ጳጳሳት› ራሳቸውን ያዋረዱ በመሆናቸው የአባትነት ክብራቸውን ያጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ምእመኑ በዚህ ተልእኮ ውስጥ የሚሳተፉትን ‹ጳጳሳት› በሚገኙበት አድባራትና ገዳማት እንዲሁም የስብሰባ አዳራሾች ኹሉ ጥሎ በመውጣት ተቃውሞውን በግልጽ ሊያሳይ ይገባል፡፡ እነዚህ ራሳቸውን ያዋረዱ ‹ጳጳሳት› ናቸው በቅርቡ የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነው ወያኔ ሕወሓት ጋር አጋንንታዊ ኅብረት ፈጥሮ ከኢኦተቤክ ተገንጥያለሁ ላለው የትግራይ አህጉረ ስብከት ማቋቋሚያ ከብር 20 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የምእመኑን ገንዘብ የሰጡትና (የጽሑፍ ውገዘቱ እንዳለ ሆኖ) በተግባር ግንጠላውን የደገፉት፡፡ ይህ ገንዘብ ባብዛኛው አሁን እልቂት እየተፈጸመበት ከሚገኘው የዐምሐራ ሕዝብ/ምእመን እንደተሰበሰበ ስንቶቻችን እናውቃለን? አሁን በሽምግልና ስም ሕዝባችንን ለፋሽቱ አሳልፈው ሊሰጡ የተዘጋጁት ‹ጳጳሳት› የሚንደላቀቁት ይህ ደሀ ሕዝብ አንጀቱን ቋጥሮ እምነቴ (ሰማያዊው መንግሥት) ይበልጥብኛል ብሎ ከሚሰጠው ገንዘብ እንደሆነ መረዳት ያቅተናል? ለቤተ እግዚአብሔር የምንሰጠውን ማናቸውንም መባዕ ያለ ኃላፊነት በትነን ዞር የምንል እኛ በውኑ ክርስትናው ገብቶናል? ቤተ ክርስቲያን እኮ የማኅበረ ምእመናኑ እና የማኅበረ ካህናቱ አንድነት እንጂ የ‹ጳጳሳቱ› ብቸኛ ገንዘብ አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ምእመናን ማሰብ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ቤክ ምእመን እስከ መቼ ነው እግዚአብሔር ላቡን ባርኮለት ያገኘውንና ከትርፉ ያልሆነውን ገንዘብ ለወንበዶችና ዘራፊዎች አሳልፎ ሲሰጥ የሚኖረው? ቢያንስ ዐምሐራው ፋሺስታዊውን የርጉም ዐቢይ አገዛዝ አስወግዶ፣ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት አስከብሮና አገር አረጋግቶ ሰላማዊ ሽግግር እስኪደረግ በየክፍላተ ሀገሩ ያሉ አድባራትና ገዳማት የሚገኙ ምእመናን የራሳቸውን አድባራትና ገዳማት በመቆጣጠር ገንዘቡ ወደ ቤተ ክህነቱ ቋት እንዳይተላለፍ በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ቤቱን ማፅዳቱ አይቀርም፡፡ እናንተ ምእመኑን የምትንቁና ‹የአባትና ልጅነት› ግንኙነታችሁ የተቋረጠ ‹ጳጳሳት› ተብዬዎች ከሕሊናችሁ ጋር ከሆናችሁ ቢያንስ ተጨማሪ ነውሮችን ከመፈጸም እንድትቆጠቡ የቤተ ክርስቲያን ራስ በሆነው በእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንማፀናችኋለን፡፡ በመንፈሳዊነት ወይም በመልካም አርዓያነት ‹ሀብት› መሆን ቢያቅታችሁ እባካችሁ ዕዳ አትሁኑብን፡፡ እባካችሁ የእሳካሁነ ነውር ይበቃችኋል፡፡ ለምእመኑ የመሰናከያ ደንጊያ አትሁኑ፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቶስ ዓለሙን ለማዳን መሞት እንዳለበት ሲናገር ባንተ አይሁንብህ ባለው ጊዜ በጴጥሮስ ያደረ ሰይጣንን አምላካችን እንደገሠፀው፤ አሁን በፋሽስቱ አገዛዝ የጥፋት ተልእኮ የተቀበሉትን በግብር ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያን› የሆኑትን ‹ጳጳሳት› (የቅዱስ ጴጥሮስ ዓይነት ሕይወት ባይኖራቸውም፣ በሥርዓቱ ተሰይመውና ጠብቀውት ከሆነ የሐዋርያት ሥልጣነ ክህነትን ተቀብለዋልና) በነሱ አድሮ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ሕዝባችንን እና አገራችንን ሊያጠፋ የተነሣውን ሰይጣን ወግድ ልንለው ይገባል፡፡
እነዚህ ‹ጳጳሳት› አሁን ባገራችን የሚታየው ግዙፍ ችግር ከፋሺስታዊው አገዛዝ ጋር የተያያዘ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ የፖለቲካ ችግር መሆኑ ስላልገባቸው ወይስ ለቤተ መንግሥቱ ያስለመዱት ሎሌነት ነው በዚህ ባለቀ ሰዓት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በድጋሚ ለማዋረድ የተዘጋጁት? በመከራው በችግሩ ጊዜ አለንልህ ያለለው ቤተ ክህነት አሁን ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የመጨረሻ ተፈጥሮአዊ መብቱን ተጠቅሞ ለመኖር ወይም ህልውናውን ለማስከበር የሞት ሽረት ትግል ሲያደርግ ‹ልሸምግል› ማለት እልቂቱን ተቀበል ወይም በባርነት ልግዛህ ከሚለው የርጉም ዐቢይ ዓዋጅ ተነጥሎ የማይታይ ነው?