>

የመጨረሻው ደወል ሲደወል፤! 

ኳ ! ኳ ! ኳ ! ሲል፤ 

የመጨረሻው ደወል ሲደወል፤!

ያንዱ ፍፃሜ፤ የሌላው ጅማሬ ይሆናል !!

አሥራደው ከካናዳ

ኳ ! ኳ ! ኳ ! ሲል ሲደወል: የመጨረሻው ደወል፤ ከወዲያ ከሩቅ፤ ከሚካኤል ደጅ፤ ከማርያም ደብር፤ ከጊዮርጊስ ደጃፍ፤ ከተክልዬ ገዳም፤ ከእየሱስ ደጅ፤ ሲያስተጋባ የደወሉ ጥሪ፤ በዱር በገደሉ፤ በየመንደሩ በከተማ በገጠሩ፤በክፍላተ ሃገሩ፤ የግፍ አገዛዝ ፍጻሜ፤ የፍትሃዊ አስተዳደር ጅማሬ ይሆናል !!

በተራሮች አናት ተሻግሮ እንደገና፤ ግው! ግው! ግው! ብሎ ሲጣራ፤ ያልሰማው እንዲሰማ፤ የተኛው እንዲነቃ፤ ያልታጠቀው እንዲታጠቅ፤ የመጨረሻው ደወል ሲደወል፤ የመጀመሪያው ክብሪት ተጭሮ፤ የድል ችቦ ተለኩሶ፤ ደመራው ሲነድ: ሲንቦገቦግ፤ ምድር ተቀዳ ቀውጢ ስትሆን: አቧራው እንደ ጭስ ሲቦን፤ ሰማዩ ቀልቶ፤ ጨለማው ሲሸሽ፤ የማለዳው ጮራው ሊፈነጥቅ: የነፃነት ጠሃይ ፍንትው ብላ ልትወጣ ቀኑ ቀርቧል:: 

ያንዣበበው የፍርሃት ደመና ተገፎ: ጎህ ሲቀድ፤ ከአድማስ ባሻገር: በሚፈነጥቀው የጠሃይ ጮራ፤ በሃዘን የተሰበሩ ልቦች፤ በብርሃኗ ሙቀት እንደ ጽጊረዳ ተፈልቅቀው ይፈካሉ:: በቁጭት የከሰለ አንጀት: በሃሴት ያቆጠቁጣል፤ በግፍ የወደቁ ወንድሞቻችን ደም: የሚያስተጋባው የድል ጩኸት፤ ከአጥናፍ አጥናፍ ሲያስተጋባ ይደመጣል:: የእናት አገራችን ኢትዮጵያ ትንሳኤ: የመጨረሻው ደወል የሚሰማበት ቀኑ ቀርቧል ::

ክርፋት ክርፋት በሚሸት: የዘረኝነት፤ የጥላቻና የጎሣ ሽታ: የታፈኑ አፍንጮች፤ በጽጌረዳ ጣዕም የታወደ የነፃነት አየር በመተንፈስ፤ በጥላቻ የጠቆሩ ሳንባዎቻቸውን ይፈውሳሉ :: በዘረኞችና አምባ ገነኖች በትር: በዝምታ የተሸበቡ አፎች ተከፍተው፤ የእናት አገራቸው ኢትዮጵያን፤ ሕዝባዊ መዝሙር በአብሮነት ጮክ ብለው በመዘመር፤ የደስታ ዕንባ እየተናነቃቸው ተቃቅፈው፤ ዳግም በዘር፤ በሃይማኖትና በጎሣ ተከፋፈለው፤ አገራቸው በደም ላትርስ፤ በታንክ ላትታረስ፤ አረንጓዴ፤ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማቸውን፤ በኢትዮጵያ ተራሮች ላይ፤ ከፍ አድርገው በማውለብለብ፤ በአያት በቅድም አያቶቻቸው መቃብር ላይ ቆመው ቃል የሚገቡበት የመጨረሻው ቀን ቀርቧል::

ጉንጮቻቸው በሃዘን ዕንባ የተሸረሸሩ እናቶች፤ እድላቸውን የሚያማርሩበት፤ ጧሪ ልጁን በጠራራ ፀሐይ የተነጠቀ አባት፤የሚተክዝባት፤ በረሃብ ቆዳቸው ከአጥንታቸው የተጣበቀ ሕፃናት የሚያለቅሱበት፤ በገዛ አገሩ ተስፋ ቆርጦ የሚሰደድ ወጣት፤ ዳግም የማይኖሩባት ኢትዮጵያን የምንገነባበት ቀን ቀርብውል:: ክብሩን ማንነቱንና አገሩን ተሰርቆ፤ የድቀላ ስንዴና ቦቆሎ እየተመጸወተ፤ ዳግም ዲቃላ ሆና የሚፈጠር ትውልድ የሚያበቃበት ቀኑ ቀርቧል:: 

የስደት በሩ ተዘግቶ፤ የመመለሻው በር ወለል ብሎ ሲከፈት፤ ሁሉም ዜጋ የስደት ኑሮውን ትቶ፤ ወደ ጥቁሯ እየሩሳሌም፤ እናት አገሩ ኢትዮጵያ በመመለስ: በፍቅር፤ በወንዳማማችነት፤ በአንድነትና  በእኩልነት የምንኖርባት አገራችንን የምንገነባበት ቀኑ ቅርብ ነው::

የደወል ጥሪውን እናዳምጥ፤ የነፃነት ቀን ቀርቧል! ዳግም ሌቦች ድላችንን እንዳይነጥቁን፤ ሁላችንም ለመብታችን ዘብ እንቁም :: ትግል በውክልና፤ ድል በልመና መቋመጡ ያብቃ ! ሁሉም የበኩሉን የዜግነት ድርሻና ግዳጁን ይወጣ፤ ተጎልቶ በሌሎች ደም የተዋጀ ድልና ነፃነት መጠበቁ ያብቃ ! ::  

የኢትዮጵያን ህዝብ ድል፤ በመጀመሪያ ወታደሩ ሲነጥቅ፤ ቀጥሎ ህወሃት ሁለት ጊዜ መንትፏል፤የኦህዴ/ ኦነግ እና የጃንደረባው ብአዴን ጥምር፤ ብልጽግና በሚል የዳቦ ስም ለአራተኛ ጊዜ ሰርቆናል ::

የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ከአሁን በኋላ የሚሰረቅ ድል ሊኖረው አይገባ፤ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ለአገራችንና ለመብታችን ዘብ እንቁም፤ ይህ ካልሆነ ታሪክ በድጋሚ ይቅር አይለንም፤ እግዚአብሔርም በስንፍናችን ይጠየፈናል ::   

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !! 

አላህ ከእኛ ጋር ይሁን !

 

 

Filed in: Amharic