>

ይድረስ ለዶ/ር ዮናስ ብሩ (በቃሉ አጥናፉ ታዬ (ዶ/ር))

ይድረስ ለዶ/ር ዮናስ ብሩ

በቃሉ አጥናፉ ታዬ (ዶ/ር)

የጎሳን ፖለቲካ በሚያራግበው ሕገ መንግስት እና ፀረ አማራ በሆነ የህወኃት እና የኦነጋውያን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መነሻነት በአማራ ህዝብ ላይ በርካታ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ግድያዎች ተፈፅመዋል፡፡ ለምሳሌ ጃዋር ተከበብሁ ባለበት ዕለት 86 አማራዎች ተገደሉ፤  ሀጫሉ የተገደለ ቀን 350 አማራዎች መስዋዕት ሆነዋል፤ በአማራነታቸው 17 ሴት ተማሪዎች ከደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ሲመለሱ ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡ በምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲ፤ የጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ፤በምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ አርቁምቢ መንደር፣ኪረሙ  ወረዳ ሀሮ ከተማ፣በጊዳ አያና ወረዳ፣በሆሮ ጉድሩ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ፣በሆሮ ጉድሩ ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ እና አቤ ደንጎሮ ወረዳ፣ በምዕራብ ወለጋ ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ሰዴቃ እና ሎንቺሳ ቀበሌዎች፣ ቆንዳላ ወረዳ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ጅባት ወረዳ፣ ዳርጌ ቀበሌ፣ አምቦ ወረዳ መንቃት ቀበሌ፣ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳማ ወረዳ እና በቄለም ወለጋ ሃዋ ገላን ወረዳ፣ በዶዶላ፣ በአርባ ጉጉና በበደኖ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ አርሲ፣በመተከል፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሌሎችም ክልሎች  በተለያዩ ጊዜዓት በተደጋጋሚ ከ2011 እስከ 2015ዓ.ም ባሉት ጊዜ ውስጥ የአማራ ተወላጆች በጥይት ተጨፍጭፈዋል፤ አሰቃቂ በሆነ አገዳደል ህይወታቸው አልፏል፤ በቀስት እየተወጉ ተገድለዋል፣ በኦነግ ሸኔ በጥይት ተጨፋጭፈዋል፡፡ አጣዬን ከአስር ጊዜ በላይ ስትወድም ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ አማራዎች ተገድለዋል፡፡ 

ይህ አሠቃቂ ግድያና የዘር ፍጅት ከብዙ በጥቂቱ እንደ ማሳያ የቀረበ ሲሆን የግድያ ዘገባዎች በተለያዩ የአለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቶች ተከትበው ይገኛል፡፡ ይህ ጥቃት መንግሥታዊ በሆነ መዋቅር የታገዝ ሲሆን በድብቅ የተፈጸሙት በቁጥር በገሀድ ከወጡት ሊበልጡ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአጠቃላይ በህወኃት ጊዜ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት እና ማፅዳት ጨምሮ ኢትዮጵያ በአማራ ደም የጨቀየች ሀገር ሁናለች፡፡ የአማራን ደም ከማፍሰስ በተጨማሪ በአገዛዙ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ የዴሞግራፊ ቅየራው፣ የአዲስ አበባን ኮንዶሚኒየምና የመሬት ወረራው፣የቤት ፈረሳው፣ መፈናቀሉ እና ተረኝነቱ የሰው ልጅ አዕምሮ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ይከብዳል፡፡ 

በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ይህን ሁሉ ዘግኛኝ እልቂት ለመታገል ቤት፣ ትዳር፣ ልጅ፣ ስራ፣ ህይወት ሳይሉ በየትኛውም ሁኔታ ዜጎች የሚያደርጉትን ትግል ለመተቸት ማናችንም የሞራል አቅም የለንም ዶ/ር ዮናስም እንዲሁ፡፡ ዶ/ር ዮናስ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸውን ትንታኔ አውንታዊ ቢሆኑም ከርዮት አለሙ ጋር ከቀናት በፊት የሰጡት ትንታኔ ግን ከእርሳቸው የማይጠበቅ ሁኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ዶ/ር ዮናስ በውይይቱ ካነሷቸው ጉዳዮች በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዬርጊስ እና እስክንድር ነጋ የትግሉ ችግሮች ናቸው እንጅ መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም፤ እነዚህ ግለሰቦች የመምራት ብቃት እንደሌላቸው፣ ስልታዊ አሳቢ እንዳልሆኑ፣ እና ተቀባይነት እንደሌላቸውገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ዮናስ የተማሩ በርካታ ልምድ ያላቸው ሰው ቢሆኑም ይህ ንግግራቸው ግን የብልፅግናን ካድሬ ትችት ይመስላል እንጅ የምሁር ትችት አይመስልም፡፡ እነዚህ የተጠቀሱ ሁለት ግለሰቦች (ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዬርጊስ እና እስክንድር ነጋ) የመምራት ብቃትም ስልትም ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ ስራቸው ይናገራል፡፡ በሞቀ ቤታችን ተቀምጠን ዋጋ እየከፈሉ ባሉ ዜጎች ላይ አላስፈላጊ አስተያየት ከመስጠት ብንቆጠብ መልካም ነው፡፡ 

Filed in: Amharic