ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም ብለን ትተን ነበር
ከይኄይስ እውነቱ
ማንም ሰው ተገቢ ነው ብሎ የሚያምንበትን ሐሳብ ለመግለጽ ተፈጥሮአዊ ነጻነት አለው፡፡ መንግሥትም ሆነ ግለሰብ የሚሰጠውና የሚነሣው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ አጠቃላይ አገላለጽ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መብትም ሆነ ነጻነት ልቅ ሳይሆን ገደብ አለው፡፡ ስለሆነም የመብትም ሆነ ነጻነት ባለቤት የሆነ ሰው ይህን መብቱንና ነጻነቱን መጠቀም የሚችለው የሌላውን መብትና ነጻነት አለመጋፋቱን ሲያረጋግጥና ኃላፊነት ሲሰማው ብቻ ነው፡፡ የተፈቀደ ሁሉ ይጠቅማል ማለት አይደለም፡፡ አንድ ሰው ጤነኛ አእምሮ እስካለውና ዕድሜውም ለአካለ መጠን ያደረሰ ከሆነ ካንደበቱ ለሚወጣው ቃልና ከአእምሮው አፍልቆ ለሚጽፈው ጽሑፍ ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ በተለይም የጠቅላላውን ጥቅም (ያገርና ሕዝብ) የሚነካ ጉዳይ ሲሆን ሁለት ሦስቴ ሊያስብበት ይገባዋል፡፡ ይህ ኃላፊነት ደግሞ ፊደል ቈጥረናል በሚሉ ሰዎች ለበለጠ ምክንያት ከበድ እንደሚል ይታመናል፡፡
ባለፉት ሠላሳ ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ አገራችን ላይ ሰፍኖ በቆየው ጐሣዊ የፋሺስት አገዛዝ በርካታ ፊደል ቈጥረናል የሚሉ ባገር ውስጥም ይሁን ነዋሪነታቸው በውጩ ዓለም የሆኑ ዜጎችም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች በቅሌትና ውርደት ማጥ ውስጥ ሲጨመላለቁ አስተውለናል፡፡ እንደ እርያ ደጋግመው ሲቡካኩ÷ እንደ ከልብ ወደ ትፋታቸው ሲመለሱና ከሰውነት ተለይተው ከሕሊናቸው ሲፋቱ ታዝበናል፡፡ የአድርባይነትንም ጥግ በተግባር አሳይተውናል፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ የሰብእና ቀውስ ያጠቃቸው ሕሊና ቢሶች በየወቅቱ ከመገለባበጥ የሚያግዳቸው የእምነትም ሆነ የሞራል ልጓም የላቸውም፡፡ ከአገር አፍራሾች ጋር ኅብረት ፈጥረው ጭራቸውን በመቁላት አገርንና ሕዝብን በመበደላቸው ጸጸት ጎብኝቶአቸው አያውቁም፡፡ ለሆዳቸውና ለሥልጣን ፍርፋሪ ሲሉ መሸጦ ለመሆን ሁሌም ዝግጁ ናቸው፡፡ ያሰቡት ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ ያለአንዳች ኀፍረት ለፈጸሙት ግዙፍ ጥፋት ይቅርታ ሳይጠይቁ ያለኛ ለሕዝብና ላገር ማን ተቆርቋሪ አለ ሲሉ የሚገኙ ይሉኝታ ቢሶች ናቸው፡፡
እነዚህ ጉዶች ዓላማቸውና ማንነታቸው በይፋ ከሚታወቁት ወያኔና ውላጁ ኦነግ/ኦሕዴድ የከፉ ናቸው፡፡ ከምዕራቡ ዓለም የቃረሙትን ወይም የተጫነባቸውን – ሀገር-በቀል ታሪክ፣ እምነት፣ ባህልና የእሤት ሥርዓቶችን ያልዋጀ – መረጃ እንደ ዕውቀት ጥግ አድርገው በመያዝ ለፋሺስታዊ አገዛዞች ገረድ ደንገጥር ሆነው በማገልገል በተግባር የሌለ መንግሥታዊ የሕግና ሥርዓት ቅብ በመቀባት የተካኑ÷ እውነተኛውን አስቀያሚ ገጽታ በመሸፈን ቊጥሩ ቀላል የማይባለውን ወገን የሚያሳስቱ ‹ሜክ-አፕ አርቲስቶች› ናቸው፡፡ በፈረንጅ አንደበት በመናገራቸውና በመጻፋቸው ከሁሉ የላቁና በሚያቀርቧቸውም መጣጥፎች ከነሱ በቀር ‹ምሁር› ለኀሣር የሚሉና የማይተካ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሚመስላቸው በትእቢት የታጀሩ ግብዞች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ በውጭ ቋንቋ መጻፍና ምድር ላይ ያለውን የአገርና የሕዝብ ተጨባጭ እውነታ ለውጩ ዓለም ማሳወቅ አይገባም እያልሁ እንዳልሆነ አንባቢ ይረዳኛል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ግብዝ ግለሰቦች ሕዝቡ የሚረዳውን ብሔራዊ ቋንቋ የሚያውቁ ከሆነ በቅድሚያ ጽሑፋቸው ለሕዝባቸው/ለወገናቸው በሆነ ነበር፡፡ የዐደባባይ ምሁር ከሚለካበት በርካታ መስፈርቶች አንዱ መልእክቱን ሕዝቡ በሚረዳበት ቋንቋ ማስተላለፍ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ርእሰ ጉዳይ ያደረግኋቸው ግለሰቦች ምሁር ናቸው እያልሁ አይደለም፡፡ ነፍሳቸውን በመካነ ዕረፍት ያኑርልንና እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕሮፌሰር መሥፍን፣ ፕሮፌሰር ዐሥራት በዚህ ረገድ በአብነት የምንጠቅሳቸው ኢትዮጵያውያን የዐደባባይ ምሁሮች ናቸው፡፡
በተቃራኒው በዚህ ጽሑፍ ያነሣኋቸው ፊደል ቈጣሪዎች ሕዝብ ፋሺስታዊ አገዛዞች ያፀኑበትን ቀንበር ሰባብሮ ከባርነት ለመገላገል ትግል በሚያደርግበት ወሳኝ ወቅት ብቅ በማለት አንድም ትግሉ ግለቱን ጠብቆ እንዳይሔድ እንቅፋት ለመሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ እነርሱ ያልመሩት ትግል እንደማይሠምር ባገኙት ሚዲያ ሁሉ በመቀባጠር ሕዝብን በማስተባበር መሥዋዕትነት እየከፈሉ ያሉና በፈታኝ ጊዜ ‹ሰው› ሆነው የተገኙ ኢትዮጵያውያንን ሰብእና በማጉደፍና በማናናቅ የተጠመዱ መሆናቸው ዓይነተኛ መገለጫቸው ነው፡፡
በዚህ መልኩ ከምናነሣቸው ግለሰቦች አንዱ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የተባለ ነዋሪነቱን ከኢትዮጵያ ውጪ ያደረገ÷ ዕድሜና የጸጕር ለውጥ ጠቢብና አስተዋይ ያላደረገው ሰው ነው፡፡ አንድ ፊደል ቈጥሬአለሁ የሚል ሰው ንጹሐን ኢትዮጵያውያን እንደ ቅጠል በሚረግፉበት በዚህ ወቅት በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ ቢሳነው ቢያንስ መሰናክል ከመሆን መቆጠብ በተገባው ነበር፡፡ የሕዝቡን ህልውና በማስከበርና ኢትዮጵያን በመታደግ የሚጠናቀቀው የዐምሐራው ሕዝብ ትግል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ቢገኝም ተጀመረ እንጂ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ይህ ግለሰብ ከፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ጋር ‹ዝሙት› ሲፈጽም የቆየ እንደነበር ዘንግተነው አይደለም፡፡ እውነታውን ዐውቆና ተረድቶ ከተመለሰ ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም (let bygones be bygones) ÷ በዚህን ወቅት ጠላት ማብዛት አያስፈልግም ብለን እስከነ ነውሩ የተውነው ሰው ነው፡፡ የዚህም ጽሑፍ ዓላማ ያለፈው አድርባይነቱ አገርሽቶበት እንቅፋት እንዳይሆን ለማሳሰብ እንጂ የኋላውን ጎትቶ እሰጥ አገባ ውስጥ ለመግባት አይደለም፡፡ እንኳን በዚህ ወቅት በሰላሙም ጊዜ ስለ ግለሰብ ለማውራት ጊዜውም ፍላጎቱም የለንም፡፡ በትችትና በዘለፋ መካከል ያለው ዳር ድንበር በትክክል ዐውቀን ብንናገር መልካም ይመስለኛል፡፡
የጐሣ ፋሺስታዊው አገዛዝ ደጋፊዎች የነበሩ ብዙ ምልሶች አንድም በዝምታ አሊያም ዐቅማቸው በፈቀደላቸው ኢትዮጵያን ከአውሬዎቹ መዳፍ ለማስመለስ በሚደረገው ትንቅንቅ የበኩላቸውን ለማበርከት ደፋ ቀና በማለት የሚገኙ አሉ፡፡ ባንጻሩም እንደ ዶ/ሩ ደርሶ ‹ፈታውራሪ› ካልሆንሁ ÷ ትግሉን እኔ ካልዘወርሁት ባፍጢሙ ይደፋ የሚል አንደምታ ያለው ንግግር የነውረኛነት ጥግ ብቻ ሳይሆን ከቀደመውም እጅግ የከፋ ጥፋት ይሆናል፡፡ ዶ/ር ዮናስ ለመሆኑ ፊደል ላስቈጠረችኝ አገሬና ለወገኔ ምን አድርጌአለሁ ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? የምታገኘውስ መልስ ከሕሊናህ የማይጣላ ነው? እንደ ብዙዎቹ የአገራችን የወሬ ፖለቲከኞች የሥልጣን ፍትወት አስክሮህ በሌላው መሥዋዕትነት በመንጠላጠል ለምዕራባውያኑ ተረኛ ቅጥረኛ ለመሆን ዳር ዳር እያልህ ይሆን? ጉንጭህን ወይም ጭንህን የሚቆነጥጥልህ ፈልግና ከቅዠትህ ወደ ውኑ ዓለም ተመለስ፡፡ ኹላችን በተሰጠን ጸጋ የምናደርገው ጥረት ‹ጋኑን› ከሚደግፈው ‹ጠጠር› የሚቈጠርልን እውነትንና ቅንነትን ስንይዝ እና ከሁሉም በፊት አገርንና ሕዝብን ስናስቀድም ብቻ ነው፡፡ በአእምሮህ ከሆንህ የወንድማችንን የዶ/ር አጥናፉን ምክር ገንዘብ ብታደርግ መልካም ነው፡፡