>
5:14 pm - Friday April 30, 6962

"እየመጡ ነው" "እየመጡ ነው"

“እየመጡ ነው” “እየመጡ ነው”

ብርሃኑ ድንቁ፤ ስሎ ኖርዌይ

አስከፊው አላዋቂነት የፖለቲካ አላዋቂነት ነው (The worst illitrate is the political illitrate) አስተዳደራዊ ሥራን ያልተካነ ፖለቲከኛ ሃገርን ያዋርዳል፣ በረሃብ ይጠብሳል፣ በሁከት ያምሳል። የሕዝቡን ሮሮ የማይሰማ ሰምቶም ፈጥኖ መወሰን የማይችል፣ እታች ወርዶ ሕዝቡን የማያነጋግር – ቢያነጋግርም ችግሩ የሚቀረፍበትን መፍትሄ የማያመጣ እንዲሁም በተመደበበት ቦታም ይሁን በሚውልበት አካባቢ የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ የማይችል ፖለቲከኛ የመከራ እርሻ ነው።

ሕንድ በቂ የትምህርት ዝግጁነት የሌላቸው በርካታ ፖለቲከኞች ሲኖሯት ካናዳ ደግሞ ፖለቲከኞቿ በትምህርት የበለጸጉ ናቸው። በሁለቱም አገሮች ፖለቲካ ሥራዋን ትሠራለች። የፖለቲካ አስተዋይነት (political prudence) በትምህርት ብቻ የሚመጣ አይደለም፣ በጸጋ እንጂ። እነ አጼ ሚኒልክ ሃገርን ከቅኝ ገዥዎች የጠበቁት፣ ያቀኑትና በዓለም አቀፉ ፖለቲካ ተጽዕኖ ማሳደር የቻሉት ማስትሬትና ዶክትሬት ይዘው አይደለም፣ አስተዳዳራዊ ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት ሕዝብን መጥቀሙን ወይንም አለመጥቀሙን ስለሚመረምሩ እንጂ። አላዋቂ ፖለቲከኛ የተሰጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ ለውጥ ማምጣት የማይችል – አስተውሎ፣ ብልሃትና፣ መልካም የግብረገብና የሥነምግባር እሴት ያልተፈጠረለት ግለሰብ ነው።

ሥልጣን እውር ታደርጋለች። ሥልጣን እፍረተቢስ ታደርጋለች። ይህማ ቢሆን ነው እንጂ ባለሥልጣናት ባስራቡት፣ ሥራ አጥ ባደረጉት፣ በኑሮ ውድነት በሚያፈጉት፣ መሬቱን ነጥቀው በሚቸበችቡበት፣ ቤቱን በተኛበት በሚያፈርሱበት፣ ታሪካዊ ባንዲራውን እንዳይዝ ባደረጉት፣ የትምህርት ሥርዓቱን ባዛቡበትና እንዲሰደድ በሚያደርጉት የአዲስ አበባ ወጣት ፊት አይቆሙም ነበር። የህዝብ ገንዘብ የሚመዘብር ባለሥልጣን እውር ነው። እውር ባይሆንማ ኖሮ በቁም በገደለው ባጎጎሳቆለው ኅልውናውን ባበላሸው ሕዝብ ፊት አይቆምም ነበር። ባለሥልጣን ተብዬዎች ታላቁ ሩጫ በሚካሄድበት ወቅት ሸጋ እንደሰራ ሰው እፀገነት ቆመው ልክ ልካቸውን በሚነግራቸው በመቶ ሺህ በሚቆጠር የአዲስ አበባ ወጣት ፊት መቆማቸው ኅፍረተቢስነት ካልሆነ ታድያ የጤንነት ነውስለ እንዲህ ዓይነቱ የሥነዓዕምሮ በሽታ ከእኔ ይልቅ ባለሙያዎች ቢናገሩ ይሻላል።

ሕወሃት አገሪቱን በክልል መከፋፈሉ ብቻ በበቃት – ነገር ነገር ግን ዛሬ ብልጽግና የተባለውን ኦህዲድ፣ ኢህድን፣ ደሕዲን፣ ወዘተ፣ የሚባሉ ድርጅቶችን አዋቅራ ከሕዝብ እውቅና ውጭ ወይንም ሕዝቡ ሳይፈልጋቸው የሃገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን አጎናጸፈቻቸው። አስቡት – ድርጅቶችን በማዋቀሯ ብቻ አይደለም ሕወሃት ኢትዮጵያን የገደለችውሆን ብላ የድርጅቶቹን ፖለቲካ ከሚዘውሩት ግለሰቦች መካከል በቂ የፖለቲካ ግንዛቤ የሌላቸውን መምረጧ ነው። ይባስኑ አንዳንዶቹ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ያልቀሰሙ አልያም ሞራላቸው የነጠፈ ምርኮኞች ናቸው። ሕወሃት ከነዚህ ሰዎች አንዳች የረባ ነገር እንደማይቀዳ ብታውቅም ነገር ግን እንዳሻዋ ልትነዳቸው በመቻሏ አብዛኛዎቹን የሥልጣን መንበሯ አጥር አድርጋ ጥቂቶቹን ደግሞ የእግሯ መቀመጫ አድርጋ ተዘባነነችባቸው። የሚያሳዝነው እነዚህ ግለሰቦች የተቀመጡበት የሥልጣን ወንበር – ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ጎበና ዳጬ፣ ባልቻ አባነፍሶ፣ አክሊሉ ኃብተወልድ፣ ከተማ ይፍሩ፣ ይልማ ደሬሳ፣ እንዳልካቸው መኮንን፣ ወዘተ የመሳሰሉት በአስተዳደርና በፖለቲካ ሥራ የገነኑ ሰዎች የተቀመጡበትን ወንበር ነው።

አብይ አህመድም በተካነው የቃላትና የዘር ፖለቲካ ካርታ ጨዋታ ፣ሙስናዊ እና ዘረፋዊ ሥርዓቱን በማስቀጠል የችግሩ ቁልፍ ጉዳይ እንዳይፈታ ይበልጥ አወሳስበው። ተጠፍጥፎ የተሰሩትን የቀድሞዎቹን አላዋቂዎችና ምርኮኞች እንደ አባቱ ህወሃት የሥልጣን አጥሩና እና የእግሩ መቀመጫ አድርጎ ሲያበቃ መልሶ ደግሞ እነዚህኑ የአላዋቂነት ስብስቦች (bunch of imprudents) “መሥራት የማትችሉ ሰነፎች ” እያለ ይወርፏቸዋል።

አብይ አህመድ በችግር ላይ ችግር እየደመረ፣ ጦርነትን በጦርነት እያባዛ፣ በሰው ልጆች ላይ ከግምት በላይ የሆነ ፍዳና በደል አኖረ። አብይ አህመድ በርካቶችን ካስገደለ፣ ካሳገተ፣ ካሰደደ እንዲሁም አካለ ጎዶሎ፣ ረሃብተኛ፣ ደሃ፣ ሥራ አጥ ካስደረገ በኋላ በእጁ መዳፍ የገባችውን የተከበረች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ሳይቀር አዋረደ። አብይ አህመድ በብልጽግና ስም እየማለ ኢትዮጵያን ሰው በልቶ የማያድርባት፣ በሰላም ወቶ የማይገባባትና ህግ ጨርሶ የማይከበርባት አደረጋት።

በታላቁ ሩጫ ወቅት የአዲስ አበባ ወጣት ልክ ልካቸውን የነገራቸው “ብልጽግናን” ወክለው ለመጡትና እፍረተቢስና እውር ባለሥልጣናት ነው። የአዲስ አበባ ወጣት – የአብይ አህመድን ዙፋን እንደ ሱራፌልና ክሩቤል ለተሸከሙት መዝባሪዎች ነገ ተጠያቂ መሆናቸውን አሳውቋቸዋል። አዲስ አበቤዎች – አንበሶቹ “እየመጡ ነው” “እየመጡ ነው” ሲሉ ለጅቦቹ እቅጩን ነግረዋቸዋል። ካብይ አህመድ ፊትና ኋላ የሚንጦዘጦዙት ጋሻ ጃግሬዎችም ሆነ ሕዝቡን የሚያደናግሩት አድርባዮች – እየዘረፉና እየተመጻደቁ ሳለ ነው ጃዊሳዎቹ ከተፍ የሚሉት።

እየመጡ ነው” “እየመጡ ነው” – ሕዝቡ ሽንገላን አሽቀንጥረው እውነት የሚናገሩ ልጆቹን እየጠበቀ ነው። ባለሥልጣናቱ እውርና እፍረተቢስ ሆነው እንጂ ገና ድሮ ነው – እነ መስከረም አበራ፣ ታድዮስ ታንቱ፣ እስክንድር ነጋ፣ ታዬ ቦጋለ፣ ክርስትያን ታደለ፣ ወዘተ፣ ምክር የለገሷቸው። አንዳንዱ ምክራቸውን ሰምቶ የዘረፈውን ገንዘብ ቋጥሮ ወደ ውጭ ፈርጥጧል። ሌላው ከዘረፈው መሬትና ወርቅ ጋር እቤቱ ተቀምጧል። ወደፊት ሕዝቡ እውጭ ያሉትንም እዚህ ያሉትንም – 33 ዓመት ሙሉ በደል የፈጸሙትን፣ የዘረፉትን፣ የገደሉትን፣ ኢትዮጵያን ያዋረዱትን – ሁሉንም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፣ ዋጋቸውንም ይሰጣቸዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Filed in: Amharic