>

የመላው አምሓራ ጠቅላይ ግዛቶች የድሮን ጭፍጨፋ – ማነው ተጠያቂው?

የመላው አምሓራ ጠቅላይ ግዛቶች የድሮን ጭፍጨፋ

 ማነው ተጠያቂው?

በ17 ዓመታቱ የደርግ ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው በተለይም መጨረሻ አካባቢ የትግራይ ክልል የበላይ አስተዳዳሪ ተደርጎ የተሾመው ለገሰ አስፋው 1983 ዓም በቴሌቪዝን ቀርበው በአንድ ጋዜጠኛ ጥያቄ ቀረበላቸው። ከጥያቄዎቹ መካከል ሓውዜንን የሚመለከተው “…ህጻን፣ ሽማግሌ አሮጊት በሃውዜን ከተማ መኖራቸው እየታወቀ ለ6 ሠዓታት አንድ ከተማ በመደብደብ ህዝብን መጨፍጨፍ ለምን አስፈለገ?” የሚለው ይገኝበታል።

አንድ ሹመኛ በእርሱ የሥልጣን ዘመን ለተፈጸመው ወንጀል ኃላፊነት ይወስዳል። በሠለጠኑት አገሮች ላይ ተጠያቂነት አንዱ የሥነ-ምግባር መስፈርት ነው። ምንም እንኳን ለገሠ አስፋው እንደ ደርግ አባልነታቸው ለፈጸሙት የንጉሡና የባለሥልጣኖቻቸው ግድያና ሌሎች ወንጀሎች ተጠያቂ ቢሆኑም ሓውዜን ግን የፖለቲካ አጀንዳ ተደርጎ – ደርግ በምዕራብያውያኑ አገሮች እንዲወገዝ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ድርጊት ለመሆኑ ከብዙ ወገኖች ሲሰማ ቆይቷል።

በገዛ ራሷ ሕዝብ ላይ ሳይቀር ወንጀል ሠርታ ለመንግስትነት የበቃችው ህወሃት ደርግ ከተወገደ በኋላ ስትወነጅለው ከቆየችው ደርግ የባሰ መጠነ ሠፊ ወንጀል ከመፈጸሟ ባሻገር ለ27 ዓመታት ስርቆትና ምዝበራን ህግ አድርጋ ኢትዮጵያን ቆዳዋን ገፈፈቻት። “የባሰ አታምጣ” የሚለው ሕዝብ ጸሎት እግዚአብሄር ዘንድ አልደረሰ እንደሆን እንጃ እንጂ – ኦሮሙማው ብልጽግና በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማውራትም ሆነ ለመናገርም ዘግናኝ የሆኑ ግድያዎችና እገታዎች ከማካሄዱ ባሻገር ከቅርስ ማፍረስና ማፈናቀል ጀምሮ የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እስኪሟጠጥና የውጭ ኢንቨስተሮች አገሩን ለቀው እስኪወጡ ድረስ ምጣኔ ኃብቱን አወደመ። ብልጽግና በሰሜን በኩል በትግራይና አምሓራ ላይ በከፈተው ተከታታይ ጦርነት ሳብያም ከጎብኚዎች የሚገኘው ገቢ እጅግ አሽቆልቁሏል። በብልጽግና ዘመን መብላት አይደለም በሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስ ትልቅ ነገር ነው።

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ –

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ባጠቃላይ በአምሓራ ሕዝብ ላይ ደግሞ በተናጠል ለተሰሩት መጠነ ሠፊ አሰቃቂ ወንጀሎች ምን ምን ዓይነት ጥያቄዎች ይነሳሉ? ኃላፊነቱ የሚወስዱት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦችስ እነማን ናቸው? የሚለውን ለመዳሰስና መነሻ ሃሳብ ለመፈንጠቅ ነው።

ለዚህ ሁሉ የተቀነባበረ ግፍና መከራ የትኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠያቂ ይሆናሉ –

ትህነግ/ሕወሃት – ይህች የጎጥ ድርጅት ከሻዕቢያ ጋር በመሆን ደርግን ስትዋጋ ቆይታ ግንቦት 1983 ዓም አራት ኪሎ ደረስች

ኦነግ – እጅግ ረዥም እድሜ ያስቆጥረ የኋላ ኋላ ሕወሃት በአንቀልባ አዝላ አዲስ አበባ ያመጣችው ድርጅት

ኦህዴድ/ኦዴፓ – ሕወሃት አዲስ አበባ ስትገባ እንዲያገለግላት የዋሆችንና ምርከኞችን ቀያይጣና ጠፍጥፋ ያበጀችው ድርጅት

ኢህድን/ብአዴን/አዴፓ – አምሓራን እንዲወክል በሕወሃት የተበጀ የእናት ጡት ነካሾች፣ የሆዳሞችና የጨካኞች ስብስብ

ብልጽግናና ሸኔ –  አምሓራውን ኦሮሚያ ከሚሉት ክልል አስወጥተው ወይንም ገለው ጨርሰው ታላቅዋን ኦሮሚያ ለመገንባት እኔነኝ እኔነኝ እያሉ የሚጣሉ።

ሌሎች የኦሮሙማ ፓርቲዎች – ብቅ ጥልቅ የሚሉ – ሥልጣን ለመጨበጥ የጓጉ አምሓራ ጠል ብልጣብልጦች የመሸጉባቸው

ሊጠየቁ ከሚገባቸው ግፍና ወንጀሎች መካከል ጎልተው የሚነሱት –

ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ተዋርዳለች። መከራውን ሸሽተው የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ሳይቀር በንቀት እየታዩ እንደ ቆሻሻ ተወርውረዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝና ተጎናጽፋ የነበረች ኢትዮጵያን አዋርዶ መቀመቅ የከተታት ማነው? ኢትዮጵያ ደካማ እንድትሆን የጠላቶችዋ ወኪል ሆኖ ያገለገለው ባለቀንዳሙ ጭራቅ የት ነው ያለው? በምድር ወይንስ በገሃነም?

አምሓራ ነገድ ጨርሶ እንዲጠፋ አልያም አንገቱን ደፍቶ ተሸማቆ እንዲኖር ልዩ ግፎች ተፈጽመዋል። ማነው የዕቅዱ ባለቤት? በበደኖና በአርባጉጉና በመተከል የአምሓራ ህጻናትን አዛውንትን እርጉዞችን ጨምሮ ጉድጓድ ተጥለዋል። በመተከልም ግፉ ተመሳሳይ ነው። የሞቱትን እንኳን በስርአቱ እንዳይቀበሩ አርገው በዶዘር ቆፍረው ነው የቀበሯቸው።ለዚህ ወንጀል ኦነግ ብቻውን ተጠያቂ ነው ወይንስ ሕወሃትን እና ኢህድንን ይጨምራል?

በህወሃት ዘመን የአምሓራው ወጣቶች በቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ብር ሸለቆና በምስጢራዊ እስር ቤቶች ታስረው ፍዳ አይቷል። ማነው ይህን የሚያዘው? የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ወይንስ የደህንነት ጉዳይ ኃላፊው?

የአምሓራው ቁጥር በሃያ ዓመታት ውስጥ በሁለት ተኩል ሚሊዮን ማሽቆልቆሉ በፓርላማ ውስጥ አንድ ወቅት ተነስቶ ነበር። ማነው ግልጽ ለሆነው የዘር ማጽዳት ወንጀል ኃላፊው? የኢሕአዴግ መንግሥት ወይንስ የፓርላማው አፈ ጉባኤ?

አምሓራ ከደቡብ ክልል፣ ከጉራፈርዳ፣ ቤንች ማጂ ዞን፣ ወዘተ፣ እንዲፈናቀል በማድረግ ጥቃት ተፈጽሟል። ማነው ያፈናቀለው? የክልሉ ፕሬዚዴንት?

ድህነትን ባክቴርያ፣ ነቀርሳንና ኤድስን – ሆን ብሎ በአምሓራ ክልል ማስፋፋት፣ የወሊድ መቆጣጠርያ እንክብል በመስጠትና ማምከኛ መርፌ በመውጋት ተፈጥሯዊ መራባትን ማጨናገፍ እንዲሁም ልዩ ልዩ ክፋቶች ተደርገዋል። ማነው የዚህ አስከፊ በደል አርኪቴክቸር? የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ፟ ወይንስ መንግሥት?

በመርዛማ ማዳበርያ ምርታማነትን መቀነስና ለጤንነት ተስማሚ ያልሆነ ገዳይ ሰብል እንዲበቅል ማድረግ በአምሓራ ላይ የተፈጸሙ የግፍ ሥራዎች ናቸው። በዚህ ዓይነቱ ፋሺስታዊና ዘረኛ ግፍ የተካነው ክፉ ሰው ማነው?

ዘርን ማጥፋት ማለት ግድያ፣ በሰውነት ወይም ዓዕምሮ ላይ የህመም ስሜት በመፍጠር ስነልቦናን መስለብ፣ ዘሩ በከፊልም ሆነ በሙሉ እንዲጠፋ ልዩ ልዩ ሰቆቃዎችን መፈጸም፣ መራባትን መግታትና ልጆችን እየሰረቁ በሌላ ቦታ ማዛወር ወይንም በበሽታ አስጠቅቶ እንዲሞቱ ማድረግ ነው። ማነው ይህን ግፍ ያደራጀው? ማነው የአምሓራ ሕዝብ ደመኛ ጠላት?

ከላይ የተመለከትናቸው ግፎች አምሓራው ላይ ለመፈጸማቸው በራሱ በወያኔው ፓርላማ ለውይይት የተነሳ ሲሆን የበርካታ ከአምስት ዓመት በታች የአማራ ሕጻናት መሞታቸው ወይንም መጥፋታቸው ራሱ ማስረጃ ሆኖ ቀርቧል። በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራርያ የሚሰጠው የህወሃት አባል ሞቷል ወይንስ በህይወት አለ?

ወያኔ መርዛማ ማዳበርያዎችንና የወሊድ መከለከያ መድሃኒቶችን እንደምን አስገብቶ በአምሓራው ክልል ላይ ብቻ አርከፈከፈው። የዚህ እኩይ ተግባር ባለቤት ማነው?

ከዚህ ሁሉ ፀረ-አምሓራ ስውር ሴራ ጀርባ የትኞቹ የውጭ አገሮች ወይንም ድርጅቶች አሉ። ማነው ለዕለት ጉርሱ ሲል ከነሱ ጋር አብሮ የሚሰራው ከሃዲና ነውረኛ?

ባላስፈላጊው ጦርነት ብዙዎች ተጎድተው ሳለ ለትግራይ ክልል ብቻ እርዳታ ሲታደል አምሓራና አፋሮች በረሃብ ይለቁ ብሎ ያዘዘው ሰው ማነው? ዘግናኝ የጦር ወንጀል ከተሰራ በኋላስ ህወሃትና ብልጽግናን ምን አስማማቸው?

ዛሬም የአምሓራ ማህበራዊ አንቂዎችና ምሁራን በአዋሽ አርባና በልዩ ልዩ እስር ቤቶች ይማቅቃሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው ወይንስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህ በደል የበላይ አዛዥ? በወለጋ፣ በአርሲና በአንዳንድ የኦሮም ክልል አካባቢዎች ለሚደርሰው እገታ፣ መፈናቀልና መገደል ማነው ተጠያቂው? የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሃገራዊ ባንዲራ አትያዙ ያለውስ ማነው? በሥልጣን ለመቆየት ግጭቶችን በዕቅድ የሚጠነስሰው ማነው? ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወይንስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ?

አምሓራዎች አዲስ አበባ አትገቡም ተብለው በመከልከላቸው በርካታ ህመምተኞች ሲሞቱ የብዙ ባላሙያዎችና ተማሪዎች እድል ተበላሽቷል። ማነው ያዘዘው? ከአምሓራ ጋር አትጋቡ፣ አትገበያዩ ያሉት የኃጢዓቶች ምንጮችስ እነማን ናቸው?

አምሓራን ትጥቅ የማስፈታቱ ሙከራ አልሆን ቢላቸው ሰላማዊውን ሕዝብ ለመጨረስ በብሬን፣ ዲሽቃ፣ ዙ23፣ መድፍ፣ ታንክ፣ ድሮን – የበቀል ጭፍጨፋ እንዲደረግ የሚያዘው የጦር ወንጀለኛ ማነው? ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወይንስ ጠቅላይ ኤታ-ሞዦር ሹሙ?

የበርካታ የአምሓራ ባለሃብቶች የባንክ አኳውንት እንዲዘጋ ያዘዘው ማነው? የባንኩ ገዥ ወይንስ የየከተማዎቹ ከንቲቦች?

በርካታ የአምሓራ ፖለቲከኞችና ማህበራዊ አንቂዎች በአዋሽ አርባ እስር ቤት ሲማቅቁ አንዳንዶቹም ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ገብቷል። የአምሓራ ብሄር ተወላጆች ሠብዓዊ መብታቸው ተገፏል። ማነው ተጠያቂው? ኦዴፓ ወይንስ ኦነግ-ሸኔ?

መደምደምያ –

ትላንትና ሓውዜን፣ ያውም ለፖለቲካ ፍጆታና ለሥልጣን ግብ የዋለን የአውሮፕላን ድብደባን አስመልክቶ፣ ለገሰ አስፋው በቴሌቪዥን ቀርቦ ተጠየቀ። ዛሬስ ከዚህ በላይ ለዘረዘርኳቸው ለ32 ዓመታት በኢትዮጵያ እንዲሁም በመላው የአምሓራ ነገድና የአምሓራ ጠቅላይ ግዛት ሕዝብ ላይ ተግባራዊ ለሆነው የዘር ማጽዳት፣ የዘር መድልዎ፣ ልዩ ልዩ ግፎችና ስውር ጥቃቶች፣ አፈና፣ እገታ እንዲሁም ሠብዓዊ መብት ጥሰቶች – ስንት ሺህ የሕወሃት፣ የብልጽግና እና የኦነግ ሰዎች ተጠያቂ ይሆናሉ?

ትላንትና ሓውዜን – ሓውዜን ተባለ – ዛሬ ላይ የድሮን ጭፍጨፋ የሚደረግባቸው የአምሓራ ከተሞች ስንት ናቸው? ሓውዜን – በስንት ሺህ ሓውዜን ተባዝቶ ነው መከረኛው አምሓራ ላይ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ የሚዘንበው። ብልጽግና ፋኖን ፊት ለፊት መግጠም አቅቶት ለምን ደሃውን አምሓራ ይፈጃል? ለምን ሠብሉን ያቃጥልበታል? ለምንስ ታሪካዊ ቅርሶቹ አጠገብ ይመሽጋል? ለምን ቤተ ክርስትያኑን ያፈርሱበታል? ለምንስ መነኮሳቱን ይገድሉበታል? ለምንስ ወጣቱን አፍነው ወስደው ይረሽናሉ?

ትላንትና – ህጻን፣ ሽማግሌ አሮጊት በሃውዜን ከተማ መኖራቸው እየታወቀ ለ6 ሠዓታት አንድ ከተማ በመደብደብ ህዝብን መጨፍጨፍ ለምን አስፈለገ? ተብሎ ለገሰ አስፋው እንደተጠየቁት ዛሬ ደግሞ “መላውን የአምሓራ ሕዝብ – ጨቅላ ሕጻናትን፣ አዛውንትንና እርጉዞችን ጨምሮ ለመጨርስ ታስቦ ነው በየቀኑ የከባድ መሳርያና ድሮን ድብደባ የሚደረገው ወይንስ የእውነት ዓላማ አንጋቢውን ፋኖ ለማሸነፍ?” ተብለው – አቢይ አህመድ፣ ሺመልስ አብዲሳ፣ ብርሃኑ ጁላ፣ አበባው ታደሰ፣ አዳነች አቤቤ፣ ዳንኤል ክብረት፣ ወዘተ፣ ቢጠየቁ ምን መልስ ይሰጣሉ? ወይንስ እነዚህን ጥያቄዎች ላለመመለስና ከወንጀል ተጠያቂነት ለመዳን ከህወሃት ጋር እንዳደረጉት ከፋኖም ጋር የይስሙላ ዕርቅ ለማድረግ የውጭውን ዓለም የሙጥኝ ይላሉ?

እውን የሕወሃትና የብልጽግና ባለሥልጣናት ከለይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች እንደ ለገሰ አስፋው – በራስ መተማመን – ተሞልተው ይመልሱ ይሆን አልያስ ያንኑ የተካኑበትን ውሸት እንደ መዝሙረ ዳዊት ይደጋግሙ ይሆን? ለመሆኑ – ዘረኛ፣ አስመሳይ፣ ዘራፊ፣ ወስላታ፣ በደሆች ገንዘብ የሚቀማጠል፣ ጉቦኛ፣ የሃገር ኃብት ሻጭ፣ ሰንካላ አስተዳዳሪ – በራስ የመተማመኑ ኃይል ሊኖረው ይችላል?

ሁሉም እግዚአብሄር በፈቀደው ቀን ይፈጸማል። “ወላሂ! ሁለተኛ አምሓራ አልሆንም” ያለችውን ያችን ሕጻን ፍትህ አድራጊውና የእውነት ዳኛው የኢትዮጵያ አምላክ አይረሳትም። እግዚአብሄር የመላው የአምሓራ ነገድና የአምሓራ ጠቅላይ ግዛቶች ዋይታን ይሰማል።

አሁን ዳመናው ከብዷል ችግር ችግርን አዝሎታል ኃላ ግን ፀሃይ ትወጣለች ድልም ወደ ሰፊው ህዝብ ትሆናለች!

ብርሃኑ ድንቁ – ከኦስሎ ኖርዌይ።

Filed in: Amharic