>

የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን! [ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ]

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አብሮ ስለመስራትና ሌሎቹም ትብብሩን እንዲቀላቀሉ በየጊዜው የሚወተውተው አገራችን በዚህ ዘመን በማይመጥን አምባገነንና የጭካኔ ስርዓት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመረዳቱ ነው፡፡ ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነንና ጨካኝ ስርዓት ህዳሩ 27/28 2007 ዓ.ም የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በወጡት አመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና በየጎዳናው የተገኙት ንፁሃን ላይ ከፍተኛ ድብደባና የጅምላ እስር በመፈፀም ስርዓቱን ለመታገል የተነሳነበትን አላማ ትክክለኝነት አረጋግጦልናል፡፡

በዛሬው ዕለትም ገዥው ፓርቲ በፓርቲያቸው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የሚፈፅመውን ደባ፣ ምርጫ ቦርድንና የህዝብ ሚዲያን ተጠቅሞ ፓርቲውን ለመከፋፈልና አሳንሶ ለማሳየት የሚያደርገውን እኩይ ተግባር በመቃወም ሰልፍ የወጡ የአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና የፓርቲው ጽ/ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ቤተ ክርስትያን አካባቢ የነበሩ አዛውንት ምዕመናንን ሳይቀር በመደብደብ ጭካኔውን ዳግመኛ አሳይቶናል፡፡ ፖሊስ በትዕዛዝ በአንድነት አባላት ላይ ከፍተኛ የጭካኔ እርምጃ ወስዷል፡፡ አብዛኛዎቹንም በጅምላ አስሯል፡፡Andinet Demo. 25.01.2015

ስርዓቱ በእነዚህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሁንም የጭካኔ እርምጃውን መድገሙ ስልጣኑን የማጣት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳለ እና ከይስሙላ ያለፈ ለሰላማዊ ትግሉ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ትብብራችን የስርዓቱን ጨካኝነት እያወቁም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በስርዓቱ የማይከበረውን ህገ መንግስታዊ መርህ ተከትለው ሰልፍ ለወጡ ቆራጥ የአንድነት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል፡፡ መስዋዕትነታችሁ ለነገ ድላችን ስንቅ በመሆኑ ይበልጡን ተጠናክራችሁ በጋራ ትግላችን እንደምናጠናክርም እምነታችን ነው፡፡

በተቃራኒው ገዥው ፓርቲ ህግ የማክበርና የማስከበር ሚናውን ረስቶ ፖሊስ፣ ደህንነትንና ሌሎች ተቋማትን ለራሱ ስልጣን ማስጠበቂያ በማዋል በአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች ላይ የፈፀመውን ለዘመኑ የማይመጥንና በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለጠየቁት ኢትዮጵያውያንም የማይገባ የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡

ኢትዮጵያውያንን የማስተዳደር አቅምና ሞራል ያጣው ገዥው ፓርቲ የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ማዳፈን የማይቻል መሆኑንና አገራችን ወደባሰ ችግር እንደሚከታት ተረድቶ ከዚህ የጭካኔ እርምጃው እንዲቆጠብ፣ እርምጃውን የወሰዱትን አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የታሰሩትን በአስቸኳይ እንዲፈታ እናሳስባለን፡፡ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያና ሌሎች ተቋማት ገዥው ፓርቲ አላፊ መሆኑን በመገንዘብና ከገዥው ፓርቲ ታዛዥነት በመውጣት ወገኖቻቸሁ ላይ እንዲህ አይነት የጭካኔና አሳፋሪ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥባችሁ ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!

ጥር 17/2007 ዓ.ም

አዲስ አበባ

Filed in: Amharic