ነገረ አማራ ዘኢትዮጵያ
እነ ፕሮፌሰር ሃብታሙና አቻሜለህ በቀጥታ በብአዴን መንገድ ሊታሙ የሚችሉ ባይሆኑም በዘወርዋራ እየተነካኩ መሆኑን የተገነዘቡት አይመስልም ወይ በቀናነት አለያም ኋላ በሚጋለጥ መሰሪነት፡፡ በዚህ ከኢህአዴግ-ብልጽግና-ብአዴን ጋር የሞት የሽረት ትንቅንቅ በሚደረግበት ቀውጢ ወቅት በግንባር ለአማራውና ለኢትዮጵያ በሚታገሉት እስክንድር ነጋና ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ስለከፈቱ እኛም እነርሱ ላይ መደገን ግድ ሆኖብናል፡፡
ሲጀመር ፕሮፌሰር ሃብታሙና አቻምየለህ ተመርጠው በዚህ ወሳኝ ሰዓት በቂ ዝግጅት አድርገው በተጨባጭ የፋኖን እንቅስቀሴ ከሚመሩት መሀከል ሻለቃ ዳዊትንና እስክንድር ነጋን አነጣጥረው ለማጥቃት ለምን ተነሱ? ደግሞስ ቃለ ምልልሱን እዚህ ግባ በማይባል የኢትዮጵያ ህዝብ በማያውቀው ኢንተርናሽናል የፋኖ አስተባባሪ ተብዬ በኩል ይዘው ለምን ብቅ አሉ? ወግ አይቀር ”ኢንተርናሽናል” ተባለልና! መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ ነውና መንደርተኛ ሁላ ”ኢንተርናሽናል” ሲባል ሰማን፡፡ እነዚህኑ መንደርተኞች መሰለኝ መዓዛ አሜሪካኖቹ ጋ ይዛ የገባችው፡፡ ነጥቦቹን ስናያይዛቸው ከአገር ውስጥም ከውጪም አሜሪካ የተሰባበሰቡና የሚያቶሶትሱ ብዙ እንዳሉ ግን ደግሞ እንዳልተሳካላቸው እንገነዘባልን፡፡ ሌላው ሌላው አልሳካ ሲል አማራ ምሁራን ናቸውና ተሰሚነት ይኖራቸዋል ብለው ነው ፕሮፌሰር ሃብታሙንና አቻሜለህን ይዘው የቀረቡት፡፡
ዘንድሮ መቼም የማይሰማ የለም፣ ብለን ብለን አማራና ኢትጵያዊነትን ነጣጥለው ኢትዮጵያኒስት ምናምን እያሉ የሚቀበጣጥሩ ሌጣ አማሮች ነን ባይ የብአዴን ግርፎች ፈልተውብናል፡፡በተለይ ሃብታሙ ”ጸረ አማራ ኢትዮጵያዊነት” የሚል እርስ በርሱ የሚቃረን ወለፈንዴ ይዞ ቀርቧል፡፡ ፀረ አማራ ቀርቶ ፀረ ትግሬ፣ ፀረ ኦሮሞ ሆነህ እንዴት ስለ ኢትዮጵያዊነት ማውራት ይቻላል? አማራነትና ኢትዮጵዊነት አይነጣጠሉም፡፡ ይልቁኑም ከፕሮፌሰር ሃብታሙ ሃተታ መረዳት የሚቻለው ሰውየው በተገላቢጦሽ አዲስ ፀረ ኢትዮጵያዊ አማራነትን ሊያስተዋውቀን የፈለገ ይመስላል፡፡ ይቺ ከፀረ ኢትዮጵያዊ ትግሬነትና ኦሮሞነት የምትቀዳ ትግሬና ኦሮሞ ወዘተ ላይ የሠራች ስንኩል አስተሳሰብ እንደ ብአዴንና አብን አማራነትህን የተሰለብክ ካልሆንክ በስተቀር በሌላው አማራ ላይ አትሠራም፡፡ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት የተዋሃዱ ናቸው፣ አማራ ያለኢትዮጵዊነት ምኑን አማራ ሆነ? አማራ አገሩ ኢትዮጵያ ናት፡፡
የአማራው ከፍተኛ የስብዕና ማማ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ኢትዮጵዊነት ደግሞ ረቂቅም መንፈሳዊም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ ደግሞ ዋናው አገር ገንቢ ነፍጠኛው ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ያለ ነፍጥ አገር አልተሠራም፡፡ ነፍጠኛው ደግሞ በዋናነት አማራው ነበር፡፡ ነፍጠኛው በመላው ኢትዮጵያ ጠመንጃ ተሸክሞ መንገድ መብራት ስልክና ሥልጣኔ በሌለበት ዘመን ደሞዝ ሳይከፈለው እሾህ መንጥሮ አገር አልምቶ፣ ከባለጌ፣ከወሮበላ፣ ከጠላት ጋር ተዋግቶ ደሙን በማፍሰስ አጥንቱን በመከስከስ በምግባሩ ረቂቁን ኢትዮጵያዊነት የተጎናጸፈ ጀግና ነበር፡፡ ኢትጵያዊነት እንዲህ በደም በአጥንት የተገነባ እንጂ እንደ ዛሬ ዘመን በየዩቲዩቡ በመለፍለፍ የሚመዘን አልነበረም፡፡ ጠላቾቻችን ከኛ የበለጠ የኛን ታሪክ ስለሚያውቁ ነው ለባንዳዎቹና ጠባቦቹ ነፍጠኛ ላይ እያነጣጠሩ በፕሮፓጋንዳም በጭፍጨፋም እንዲያጠፉት ያገዟቸው፡፡
ነፍጠኛው ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር የሚያውቅ፣ በሄደበት ተጋብቶና ተዋልዶ፣ ተምሮና አስተምሮ መስተጋብር ፈጥሮ በኢትጵየዊነት ድስት ውስጥ ተቀቅሎ የበሰለ የኢትዮጵያ ባለውለታ ነበር፡፡ የመለሳለስ ዘመን አብቅቷል ፡፡ ለሁሉም ዕውነታውን በደረቁ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ነፍጠኛው ዘመድ አዝማዱን፣ የትውልድ ቀየውን ትቶ ሰፊ ራዕይ በመሰነቅ ለሚመጣበት አደጋ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ራሱን አጋልጦ ዋጋ የከፈለ ነበር፡፡ ያ መስዋዕትነት ነው ኢትዮጵያን ያስተሳሰራት፡፡ እሳት አመድ ይወልዳል ሆነና ነገሩ ”ነፍጠኛው” በ” ያ ትውልድ” ተተካና በገዛ ልጆቹ ተወግዶ የገነባው ሁሉ ተንዶ፣ ይኸው አገር ንፍጣሙን ሁሉ የሚያናፍጥ አጥታ ግማሽ ምዕተ ዓመት ማቀቀች፡፡ ዛሬ አገር ነጻ ለማውጣት ፋኖ ነፍጥ አንግቦ አጋንንታዊውን የብልጽግና የአሳማ ሥርዓት በሚገባው መንገድ ሲያርበደብደው እንደ ፕሮፌሰር ሃብታሙና አቻሜለህ ዓይነቶቹ የጭቃ ውስጥ እሾህ ሆነው ብቅ ማለት በኢትዮጵያ ታሪክ በተደጋጋሚ ያየነው ክህደት ስለሆነ አንገረምም፡፡
ባንዳው መለስ ዜናዊ ከጣሊያኖች የቀዳውንና እርሱ በምርቃና ያሰመረውን በህግ እንኳ ያልተደገፈውን ክልል/በረት ቁም ነገር አድርጎ ክልሌ ክልሌ እያለ የሚለፈልፍ የብአዴን ጀሌ የአማራውን የጠራ አመለካከት ለመበከል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በጣሊያን ጊዜ ባንዳው ሁሉ ቱቲ ፊታውራሪ እንደተባለው ሁሉ መለስ እንደ አሸን ካፈላቸው ቱቲ ዩኒቨርስቲዎች የተፈለፈሉ ቱቲ ፕሮፌሰሮችና ቱቲ ዶክተሮችን ወሬ እየሰሙ ክልል/በረት እያሉ የሚያላዝን ብዙ በረታም ብላሽ አማሮችን እየታዘብን ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አማሮች ተበላሽተዋል፤ ብላሽ ከሆኑ ደግሞ እጣ ፈንጣቸው መጣል ነው፡፡ የብአዴን ባንዳዎች ክህደት ያቆሰለን አንሶ በብላሽ አማሮች ዓይን ያወጣ ዘመቻ ተከፍቶብናል፡፡
ፕሮፌሰር ሃብታሙና አቻምየለህ የሚታወቁት በታሪክ ጉዳዮች ሲሆን ከላይ በተጠቀሰው ቃለ ምልልሰ ግን ጭራሽ ከነርሱ አቅም በላይ ወደ ሆነው የስድሳ ስድሰቱ አብዮት ወደ ኋላ ሄደው ብዙ አወነባጅ ሃሳቦችን ወንጭፈዋል፡፡ የስድሳ ስድስቱ አብዮተኞች አቋማቸው ምንም ይሁን ምን፣ የፕሮፌሰር ሃብታሙና አቻምየለህን ጨቅላና ጭቃ አስተያየት ስለሚረዱት መልስ አይሰጡበት ይሆናል እንጂ በታሪክም፣ በፖለቲካም ባጠቃላይ በአስተሳሰብ ከባድ ሚዛን ኢንተለክችዋል ስለሆኑ ቀሊሎቹ ሓብታሙና አቻምየለህን በመጀመሪያ ምት እንደሚዘርሯቸው የታወቀ ነው፡፡ የስድሳዎቹ ወይም ” ያ ትውልድ” ማለት ባጭሩ ኢሕአፓና መኢሶን ማለት ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ በስድሳ ስድስቱ አብዮት ወቅት ዋናዎቹ የነበሩትን ኢሕአፓና መኢሶንን ከወያኔና ኦነግ ወዘተ ከሚባሉ ዝቅተኛ አስተሳሰብ የነበራቸውና በአብዮቱም ወቅት ምንም ሚና ያልነበራቸው የትውልድ ጥራጊዎች ለይቶ የማየት ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ አዲሱ ትውልድ በዚያ ፋታ በማይሰጥ አብዮት ወቅት በየስርቻው ተወትፎ ሆዱን ሲሞላ የነበረ የማንንም ጠንባራ ሽማግሌ ባየ ቁጥር ስድሳዎቹ እያለ የመዘባረቅ አባዜውን መተው ይኖርበታል፡፡ የስድሳዎቹ የኢትዮጵያ ምርጦቹ ምሁራን በመንግሥቱ ኃይለማሪም ቁርጥምጥም ተደርገው ተበልተዋል ዛሬ በየሜዲያው የሚያናፉት ሽማግሌዎች በእድሜ ካልሆነ ትውልዱ በተፈተነበት እሳት ያልተፈተኑ የዚያ ትውልዱ ዝቃጮች ናቸው፡፡
እጅግ የሚገርመው ፕሮፌሰር ሃብታሙ ሁሉንም በአብዮቱ ዘመን የነበሩ ድርጅቶች ሁሉ፤ ደርግንም፣ ኢህአፓንም መኢሶንንም ጠራርጎ ጸረ አማራ ነበሩ ብሎ በመፈረጅ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ የሚያሳየው ሰውየው ከዛቹ ከሚሠራባት ዩኒቨርስቲ ወጣ ብሎ ከኢትዮጵውያን ጋር በተለይም ደግሞ ከስድሳዎቹ ምሁራን ጋር ጨርሶ ተነጋግሮ እንደማያውቅ ነው፡፡ ይልቁኑም ከርሱ መሰል መንደርተኞች ጋር በመዋል የቡድን አስተሳሰብ ሰለባ ሆኗል እንጂ ከተወሰኑት ያንን ዘመን በሚገባ ዋኝተው ካለፉበትና ከሚያውቁት ምሁራን ጋር ደፈር ብሎ በግል ቢወያይ ኖር እንዲህ በአደባይ አይቀባጥርም፣ አይቀልም ነበር፡፡ ከነርሱ ጋር በግል ጊዜውን ወስዶ ቢከራከር የሰላ አዕምሮ ስላለው አስተሳሰቡን ሞርዶ በገንቢ ሃሳብ ሊመጣ ይችል ነበር፡፡
ሰውየው ”ፀረ አማራ ኢትጵያዊነት” በማለት በድፍረት ተንተባትቧል፡፡ ድሮ የምናውቀው ድንቁርና ነበር እንዲህ ያለ ደፋር የሚያደርገው ዘንድሮ ቱቲ ፕሮፌሰርነትም ደፋር ሳያደርግ አይቀርም፡፡ ሰውየው በቱቲ ፕሮፌሰርነት ባይታማም ዙሪያው ባሉ መንደርተኞች ሆሆታና ዝና የታወረ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያዊነትንና አማራን በሚያህሉ ግዙፍ ጉዳዮች እንዲህ ዘሎ ገብቶ ማንቦጫረቅ አልነበረበትም፡፡ ካንቦጫረቀው ደግሞ እንግዲህ ቆዳውን አደንድኖ ምሱን መቀበል ነው፡፡
ስለስድሳ ስድሰቱ ፖለቲካ ያነሳውን ብቻ ስንመለከትና በተለይም ደግሞ የኢህአፓን ዴሞክራሲያ እየጠቃቀሰ ካወራው እንኳ ብንነሳ ሰውየው ያነሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ከዚያም የባሱ በተለይ ኤርትራን በተመለከተ ቅልጥ ያለ የባንዳ ጽሁፍም ተጽፏል፡፡ ስህተትማ ተሰርቷል ያውም እጅግ እጅግ ከባድ ስህተት! ለዚህ ነው ኢትዮጵያ እንዲህ የተዋረደቸው፡፡ ማን ስህተት ያልሠራ አለ? ቁምነገሩ ከስህተቱ መማሩ ላይ ነው፡፡ ሃብታሙ ትልቅ ሚስጥር ያወጣ መስሎት ብዙ ቢዳክርም ምሁራዊ ኢንተግሪቲውን እንኳ ሳይጠብቅ እነርሱ በሰባዎቹ አጋማሽ ያለርህራሄ በራሳቸው ላይ ሂስ አካሂደው ስሕተታቸውን በማመን የደመደሙትን ሳይጠቅስ ለሱ በሚመቸው መንገድ ወደ ኋላ ሄዶ ኢህአፓን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በጸረ ኣማራነት ፈርጆ የታሪክ ክለሳ አምጥቷል፡፡
ተቃዋሚ ነን የሚሉትም በመንግሥትነት የተሴሙትም አንድ ዓይነት ነበሩ እያሉ ከመቀለድ በተጨማሪ እነ ፕሮፌሰር ሃብታሙ እኮ ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ እንደሚባለው በመኢሶንም በኢህአፓም ውስጥ ይገኙ ከነበሩት አማሮች በላይ አማራ ሆኑብን እኮ! የኢሕአፓ አመራር ትግሬዎቹ የበዙበት እነደነበር የሚሸት ነገር ቢኖርም አብዛኛው አባላቱ አማሮች ነበሩ፡፡ መኢሶንም አብዛኞቹ አመራሮቹ አማሮች ነበሩ፡፡ ዛሬ በወያኔና በብልጽግና ይልቁኑም በብአዴናዊ የባንዳ አስተሳሰብ የተበከሉ እንደሚያወሩት ያ ደሙን ለቆመለት ዓላማ ያፈሰሰ ትውልድ በቀጥታ በጸረ አማራነት የሚከሰስበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ የሚከሰስበት ሌላ ብዙ ጉዳይ አለ፡፡ የዛሬው ትውልድ ዛሬ ላጋጠመው ችግር ዕውነታውን አበጥሮ በመመርመር መጋፈጥ እንጂ በወያኔና በብልጽግና ይልቁኑም የአማራው ወጣት በብአዴን የተረጨበትን መርዝ እንደማርከስ ችግሩን ወደኋላ በመውሰድ የ60ዎቹ እያለ የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ዝባዝንኬ አያዋጣም፡፡ በአንጻሩ ከዚያ ትውልድ ውድቀት ትምሕርት መውሰድ ነው የሚገባው፡፡
ለመሆኑ ሃብታሙ በዚያን ዘመን ፖለቲካ በማይታወቅበት አገር የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት ዕድር እንደመመሥረት ቀላል መስሎታል? አሁን እነ ሃብታሙም ሆኑ እነ አቻምየለህ ባጠቃላይም ዳያስፖራ ተብየው በአሁኑ ሁሉም ጉዳይ በተመቻቸበት ዘመን ለምን ፓርቲ አታቋቁሙም? መሬት ላይ ያለው ሀቅ የሚያሳየን እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢሕአፓ ባመጣው የፓርቲ ፖለቲካ እንኳ መጫወት አቅቶት ስንቱ ተወላገደበት? ተወላግዶም እኮ ለሆነ ነገር መብቃት አንድ ነገር ነው፡፡ ምንም፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ስህተቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕዝብ ድጋፍ የነበረው፣ አገሪቱ ባፈራቻቸው ምርጥ ወጣቶች ተገንብቶ እንደነበረው እንደ ኢሕአፓ ያለ የትኛው ፓርቲ ነው? ገለባ ሁሉ!
ኢሠፓ የሚባል የተግበሰበሰ ፓርቲ ያን የመሰለ እንኳን ለምሥራቅ አፍሪካ በመላው አፍሪካ አለ የሚባል ሠራዊት ይዞ በጭካኔ የአገሪቱን ክሬም ትውልድ የፈጀውን መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ተከትሎ ሲያዘጠዝጥ በመጨረሻ ሠራዊቱንም አገሪቱንም አዋርዶ ለወያኔ አስረክቦ አመድ ሆኖ ቀረ፡፡ ሌሎቹም በደርግ ዙሪያ ሲልከሰከሱ የነበሩት በሙሉ በደርግ ተበልተው ቀሩ፡፡ ኢሕአፓ ግን በደርግም በወያኔም ተቀጥቅጦ በመጨረሻ ዓለም አቀፉ የቀዝቃዛ ጦርነት ማብቃትም ተጨምሮበት በወያኔ ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር መሬት ላይ በነበረው የጠመንጃ ትግል ቢሸነፍም በፖለቲካው ረድፍ ግን ዛሬም አለ፡፡ በወያኔ ዘመን የተፈለፈሉትም ሆነ በደርግ ዘመን የነበሩት ሁሉ ትቢያ ሆነው ሲቀሩ አሁንም በፖለቲካው ዘርፍ ኢህአፓ ግን አለ፡፡ ጠንቃቃ ፖለቲከኛ ለምን ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ሥልጣንም ሀብትም በ17 ዓመት እና በ27ዓመታት በእጃቸው ስር የነበረው ደርግ/ኢሠፓና ወያኔ ይኸው የውሃ ሽታ ሆነው በታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ሲጣሉ ኢሕአፓ ግን አለ፡፡
ህዝብን ማክበር የስፈልጋል ግን ደግሞ ህዝብ ታሪክ ይሠራል ምናምን ይቺ የጅሎች አስተሳሰብ ናት፡፡ ህዝብ ተገቢውን መሪ ሲያገኝ ነው ታሪክ የሚሠራው፡፡ ፋኖ ፋኖ የሆነው የአካባቢ መሪዎች አግኝቶ ነው፡፡ እነእስክንድርን አግኝቶ ነው፡፡ ህዝብ ተገቢውን መሪ አግኝቶም ሊከተል ካልቻለ ደግሞ ከ66 ጀምሮ እንደምናየው እንደ መንግሥቱ መለስና አብይ ያሉ የአጋንንት ቁራጭ መናጢ ኮምፕሌክሳሞችን ተከትሎ መዓት ይወርድበታል፡፡
ለመሆኑ የአማራ ህዝብ የአማራ ህዝብ የሚባለው የዛሬን አያርገውና የአብይን መንግሥት ከኦሮሞው በላይ ሲደግፍ የነበረው ማን ነበር? የአማራ ህዝብ ከተወሰኑት በስተቀር ፕሮፌሰር አስራትን የመሰለ አርቆ አስተዋይ መሪ ሲያገኝ የት ነበረ? እርሳቸውን አስበልተን ሆዳችንን ስንሞላ አልነበረም እንዴ የከረምነው፡፡ በርግጥ ሁሉንም ህዝብ በአንድ ኮሮጆ ጨምሮ መውቀስ አይገባም፡፡ ደብረብርሃን ላይ እርሳቸው በጠሩት ስብስብ ላይ የወጣውን ህዝብና በምርጫ 97 ኢሕአዴግን ያርበደብደውን የጎጃምን ሕዝብ ስናስታውስ ከህዝብም ህዝብ አለ፡፡ ከ97 በኋላ በወያኔ በተጠና ብቀላ ቢያስጠቃውም በሃይሉ ሻውል መኢአድ ተመርቶ ነው ጎጃም ወያኔን በምርጫ ካርድ የቀጣት፡፡ ያኔ ጎጃም መኢአድ ኢትዮጵያኒስት ነው እኛ አማሮች ነን ብሎ አላለም! ከመአህድ ወደ መኢአድ ድርጅቱ ሲሸጋገርም የአማራና ኢትዮጵያዊነትን ተዋህዶ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጎጃሜ እንደናንተ ኢትዮጵያኒስት እያለ አልወሻከተም፡፡ ወይስ ሃብታሙና አቻምየለህ አዲስ ጎጃሜነት ልታመጡ ነው? የናንተ ችግር ኢትዮጵያዊነትን በምግባር አታውቁትም ወረቀት ላይ ነው የምታውቁት፡፡ እንደ ደንበኛው ልጅ ወጥታችሁ ወርዳችሁ የኢትዮጵያን ጣዕምና ዥንጉርጉርነት ቀርቶ አዲስ አበባን እንኳን በቅጡ አታውቁም፡፡ አዲስ አበቤ እንኳ አንዱ የሚወቀስበት ኢትዮጵያን አያቃትም እየተባለ ቢሆንም ራሷ አዲስ አበባም የኢትዮጵያዊነት እምብርትና ትንሷ ኢትዮጵያ በመሆኗ ከየትኛውም አካባቢ በተሻለ በትንሷ ኢትዮጵያዊነት ድስት ውስጥ በየቀኑ የሚንገረገብ ህዝብ ነው፡፡
ሁለታችሁም ከዚህ የኢትዮጵያዊነት ሂደት ብዙ በቅጡ ያልተቋደሳችሁ ስለሆናችሁና ይልቁኑም በምዕራቡ ዓለም የምትኖሩ ስለሆነ አይፈረድባችሁም፡፡ በአንጻሩ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ኢትዮጵያን ከማንም በተሻለ የሚያውቅ፣ በውትድርናው፣ በቢሮክራሲው፣ በዲፕሎማሲው ሆነ በኢንተለክችዋልነቱና ይልቁኑም በጂኦፖለቲክሱ የበሰለ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ስለዚህም ታሪክ እየከለስን እንጻፍ የምትሏትን ደካማ ዘመቻችሁን ትታችሁ ከነዚህ አንጋፋ ምሁራን ከስህተታቸው በመማር ከዕውቀታቸውና ልምዳቸው በመቅሰም ጠጋ ብላችሁ ብታወያዩዋቸው በሙያችሁም በአመለካከታችሁም ብዙ ታተርፋላችሁ፡፡
እስክንድር ነጋም በመታሰሩ፣ በትግሉ ብዙ መስወዕትነት በመክፈሉ ብቻ አይደለም የመሪነት ሥፍራ ያገኘው፡፡ ለአገሩ ኢትዮጵያ የጠራ ራዕይ ያለው፣ በዕምነቱ ብዙዎቻችን የሌለን ጠንካራ ዕምነት ያለው፣ የተፈተነና እየተፈተነም ያለ እጅግ ቆራጥ ያውም ሩህሩህ ጀግና ምሁር በመሆኑ ነው፡፡ ወሬና ፈስ እንደማይታፈሰው ሁሉ የፕሮፌሰር ሃብታሙና አቻምለህ ቀደዳ ፈስ ሆኖ ሲቀር እስክንድር ግን ፋኖ ሆኖ በመላው አማራ ግዛት ከሚገኙ ጀግኖች ፋኖዎች ጋር በመሆን ይህን አጋናንታም የአሳማ ሥርዓት እያራወጠው ይገኛል፡፡ ለመሆኑ ከዚያው ከነዋሪው አማራ በስተቀር ከአዲስ አበባም ሆነ ከውጪ የሞቀ ቤቱን ትዳሩን ትቶ ፋኖን የተቀላቀለ ስንቱ ነው? ውጪ ያለውም ያችኑ በውጭው ዓለም መለኪያ ዝቅተኛ የሚባለውን ኑሮ እየገፋ አዲስ አበባ ያለውም በችጋር እየተጠበሰ እየተዋረደና ሆዱን ብቻ እየሞላ ፋኖን ይጠብቃል፡፡ ፈሳም ሁላ! ጀግናማ ፋኖን ይቀላቀላል፡፡ እንዲያው ሌላው ቢቀር ፈሳችንን ቋጥረን በምንችለው መጠን በፕሮፓጋንዳው፣ በገንዘብ፣ በምንችለው ሁሉ ግንባሩን ለሰጠው ተዋጊው ፋኖ መርዳት ሲገባ ጭራሽ እስክንድርና ሻለቃ ዳዊት ላይ መነሳት? ለመሆኑ በዚህ ግቢ ውጪ ነፍስ ታሪካዊ ወቅት ሻለቃ ዳዊትና እስክንድር ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ፕሮፌሰር ሃብታሙና አቻምየለህ ተመርጣችሁ እንድታካሄዱባቸው የተደረጋችሁት ከዕውነታ በመራቅ ወይስ እዚህ ግባ የማይባል መንደርተኛ ስብስብ ሸውዷችሁ ነው እንዲህ ተዋርዳችሁ አማራንም የምታዋርዱት?
ታሪክ ያውም የኢትዮጵያን ታሪክ እናውቃለን የሚሉትን ሃብታሙና አቻሜለህ ለዚህ ውርደት ያበቃቸው ሌላው ዋናው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ታሪክና ፖለቲካን እንደሚመቻቸው አቀላቅለው በማውራታቸው ነው፡፡ ሁለቱም ስለታሪክ ቢያወሩ ተገቢ ሆኖ ሳለ ዘለው እጅግ ውስብስብ የሆነውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዳቦ በሰባራ የታሪክ ሹካ ቆራርሰው ሊመግቡን በመሞከራቻው እጅግ ተሳስተዋል፡፡ ፖለቲካና ታሪክ ባይነጣጠሉም ሁለቱን እያምታቱ ለራስ በሚመች መንገድ መቀባጠር ግን በተለይም በዚህ ታሪካው ቀውጢ ወቅት ያውም በግንባር ለኢትዮጵያ እየታገሉ ባሉት በእስክንድር ነጋና ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ላይ መዝመት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ተልዕኮ ተቀብሎ ከማስፈጸም ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህም በጊዜ አቋማችሁን አስተካክሉ፡፡
ሃይሉ አስራት