>

የወደብ አገልግሎት የመግባቢያ ሰነድ  አስመልክቶ በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ የተቃውሞ መግለጫ

የብልጽግና መንግስት ከሶማሊ ላንድ ጋር ያደረገውን የወደብ አገልግሎት የመግባቢያ ሰነድ  አስመልክቶ በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የባህር ወደብ ለአንድ አገር እድገት ያልው ጥቅም የላቀ ነው። የባህር ወደብ ለንግድ እንቅስቃሴ፣ የሀገር ደህንነትንና ሰላምን ለማስከበር እንዲሁም የኢኮኖሚ ጥቅሞችን ለማስገኘት ያስችላል።  በመካከለኛዉ ዘመን ቱርኮች፣ በ19 ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ደግሞ በጣሊያን ቕኝ ገዥዎች ከመያዙ በቀር በቀይ ባህር ምስራቃዊ ጠርዝ ላይ የተዘረጋዉ የባህረ ነጋሽ ግዛት ከነባህር በሮቹ ለሺ ዘመናት የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወደቦቿ ነበሩ።  ኤርትራ ከኢትዮጵያ እስከተገነጠልችበት ግንቦት 16/1985 ዓ.ም ድረስ  ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር አዋሳኝ ሃገራት መካከል አንድዋ ነበረች። የባህር አዋሳኝ ግዛቷን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል የባህር ኃይል የነበራትም ሀገር ነበረች።

ይሁንና በነገድ ፖለቲካና በኢትዮጵያ ጥላቻ የታወሩት የሕወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች ኢትዮጵያን ወደብ አልባ እንድትሆን አድርገው ሃገራችን  በዓለም ላይ የነበራትን እስትራቲጅያዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም አሳጥተዋታል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምሥራቅ አፍሪካ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ የሚተላለፍበት ቁልፍ ቦታ ነው። አውሮፓ ከኤስያ፣ ኤስያ ከአውሮፓ ጋር የሚደረጉ ንግዶች የሚተላለፉበት እንዲሁም የአረብ አገራት ለአውሮፓ ነዳጅ  ውጤቶቻቸውን የሚያስተላልፉበት በትሪሊዮን ዶላር የሚሰላ የዓለም ንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚከናወነብት፣ ከ40% በላይ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በኮንቴነሮች የጫኑ የንግድ መርከቦች በየቀኑ የሚተላለፉበት ስትራተጂካዊ የ‘ባብ ኤል መንደብ’ የባህር ሰርጥ (Bab-el-Mandeb Strait/the Gate of Tears)  የሚገኝበት ቦታ ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ቀይ ባህር ላይ የባህር በር ያላቸው ሀገራት ጋር የምትዋሰን  ሀገር ናት። ከነዚህም ውስጥ የጅቡቲ፣ የኤርትሪያ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን የህዝብ ብዛት ሲደመር 126 ሚሊዮን ገደማ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከዚሁ ቁጥር ጋር የሚመጣጥን ነው።  ይህም ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ይዘው የባህር በር ከሌላቸው አገራት አንደኛ ያደርጋታል። ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ በማንኛውም መልኩ የባህር በር ተዘግቶባት መኖር እንደሌለባትና ፍትሃዊም እንደማይሆን የሚታወቅ ሲሆን፣ የዓለም ማህበረሰብ ይህንኑ ሀቅ እንደ ሚገነዘበው ይገመታል።

የ‘ባብ ኤል መንደብ’ ሰርጥ ለየመን ለጅቡቲና ለሶማሊያ እንዲሁም ለኤርትራ ወደቦች በቅርብ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል።  በአሁነ ሰዓት በዚህ የባህር  ሰርጥ ዙሪያ  የየመን ሁቲ  ኃይሎች እስራኤል በጋዛ የፍልስጤም ኃይሎች ላይ እያካሄደች ያልችውን ጦርነት በመቃወም ባደረሱት የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት፣ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካንና እንግሊዝ የጦር መርከቦች በሁቲ ሃይሎች ላይ በሰነዘሩት የአፀፋ ጥቃት ምክንያት የባህር ላይ የንግድ እንቅስቃሴው ከ35% እስከ 40% እንዲቀንስ ተገዷል። በዚህም ምክንያት በነዳጅ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እየተከሰተ ይገኛል። የአውሮፓን የእስያንና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን ኢኮኖሚንም እየጎዳ ከመሆኑም በላይ፣  ግጭቱ ከቀጠለ ወደ አለምአቀፍ የፋይናንሰ ቀዉስ ሊያመራ እንደሚችል ታዋቂ የኢኮኖሚ ጠቢባን በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ።

ለዚህም ነው ከ1 ሚሊዮን ህዝብ በታች ባላት ጅቡቲ ብቻ ወደ አስራ አንድ የሚጠጉ ማለትም ፈረንሳይ፣ቻይና፣አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጣሊያንና ጀርመን እና ሌሎች የወታደራዊ የባህር ሃይል ቤዝ በሊዝ ተከራይተው የያዙት። ጅቡቲ የጂኦ ስትራተጂካዊ ጠቀሜታዋ ላይ የተመሠረቱ ስምምነቶችን በማድረግ የኢኮኖሚክ ጥቅም እያገኘች ትገኛለች።  ሳውዲ አረቢያና ሌሎች የአረብ ሀገራት በጅቡቲ ያደረጓቸው የተለያዩ የወደብ አግልግሎት ስምምነቶች ሁሉ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአለም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምንያህል ወሳኝ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። ከሳውዲ ጋር በመካከለኛው ምሥራቅ  ፉክክር በማድረግ የምትታወቀው የተባበሩት አረብ ኢመሬትስ እንዲሁም በወታደራዊ ኃይሏ ገና የወጣችው ሩሲያ እንደሌሎቹ ምእራባውያን ሀገራት  በቀይ ባህር እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የባህር ሃይል ጣቢያ ለማግኘትና ለመገንባት መሯሯጥ ከጀመሩ ቆይተዋል። ሩሲያ ከኤሪትራ በተለይም ከሱዳን ጋር በተለያየ ጊዜ የባህር ሃይል ቤዝ ለመገንባት ያደረገቻቸው ስምምነቶች ቢኖሩም ተግባራዊ እንዳይሆኑ ሱዳን ውስጥ የተፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶች ስምምነቱ ዳር እንዳይደርስ አድርገውባታል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ሩሲያ እገዛ ካደረገችላትና  ከተቀላቀለች በሗላ ከሩሲያና ከተባበሩት አረብ ኢመሬትስ ጋር  ከፍተኛ ቅርርብ ማሳየቷ፣ በተለይም የተባበሩት አረብ ኢመሬትስ መሪ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መመላለስና ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ለተደረጉና እየተደረጉ ላሉ የርስ በርስ ጦርነቶች በተለይም የኦሮሙማ ብልፅግና መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ ላወጀው ጦርነት የንፁሃን ዜጎችን መጨፍጨፊያ ጭምር ለሚውል  የዘመናዊ የጦር መሳሪያ  እንዲሁም የተራቀቁ የጦር ድሮኖችን ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ይታወቃል። የኦሮሙማው/ብልፅግና መንግሥት ከሶማሊ ላንድ ጋር ያደረገዉ የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ማድረግን በዋናነት ያለመ ነዉ ብሎ ለመቀበል ያዳገታል።  ይልቁንም ለነዚህ ሀገራት  ስትራተጂካዊ እና ጅኦ ፖለቲካዊ ጥቅም የሚውል የባህር ሃይል ጣቢያ በተዘዋዋሪ መንገድ ለማስገኘት ተብሎ የተደረገ የዉክልና አገልግሎት(proxy service)  መስጠተን ያለመ ሊሆን  እንደሚችል እንዲገመት አድርጎታል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ኢትዮጵያ  አስተማማኝ የባህር ወደብ ልታገኝ የምትችለው የጦርነት አደጋ ዉስጥ በማይከታት ሁኔታ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ባስተማማኝ ደረጃ ስታገኝና ፍትሃዊ ጥያቄዋን  በአለም አቀፍ ህግና መርህ ላይ በተመሠረቱ ስምምነቶች ስትቋጭ   ብቻ ነው ብሎ ያምናል። ኢትዮጵያን ለቀውስ በሚዳርግ መልኩ የኦሀዴድ/ብልጽግና የኦሮሙማ መንግሥት ከሶማሊ ላንድ ጋር የባህር ወደብ ለማግኘት በቅርቡ የደረሰበት የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ  በራእይነት ያነገበዉን የኦሮምያ ሪፓብሊክን የባህር በር ለማስገኘት አልያም በእጅ አዙር የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማሟላት ካልሆነ በስተቀር፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ያማከለ ነዉ ለማለት አይቻልም።

በመሆኑም ፓርቲያችን ባልደራስ ለሃገራቸን ለኢትዮጵያ የባህር ወደብ የማስገኘቱን አካሄድ በተመለከተ የሚያምንባችዉን ነጥቦች እንደሚከተለዉ ያቀርባል።

የግዛት አንድነታቸውና ድንበራቸው በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና የባህር በር ካላቸው ጎረቤት ሀገሮች ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ኬንያ ጋር የሀገርን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ በሰለጠነና ውጤታማ በሆነ የሰጥቶ መቀበል የዲፕሎማሲ መርህ አካሄድ ለአገራችን ወደብ ማስገኘት ዋና እና የመጀመሪያ አማራጭ ሁኖ ሳለ ፣መንግሥት ይህንን ከማድረግ ይልቅ ሰምምነቱ ዳር ድንበሯ አለም አቀፍ እዉቅና ከሌላት፣ የሱማሊያ ሪፐብሊክ  አንድ አካል ከሆነች ግዛት ጋር መሆኑ ሃገራችንን በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በመደገፍ ላይ ካለችዉ ከሱማልያ ጋር ወደማያባራ የጦርነት አዙሪት የሚከተን መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም።

በመሆኑም፣
1. ይህን የከሸፈ የዲፕሎማሲ አካሄድ ለማካካስ በሚመስል መልኩ በአለም አቀፍ ደረጃ ግዛቷና ድንበሯ እውቅና ከሌላት ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ  ፊርማ ኢትዮጵያ ቀዳሚ መስራች ከሆነችባቸዉ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ከአፍሪካ አንድነት ድርጀት ቋሚ የሃገሮችን የግዛት አንድነት የማክበር መርሆን የሚጥስ በመሆኑ፤

2. ይህ የመግባቢያ ሰነድ  ችግር ላይ ያለውን የአገሪቱን የዲፕሎማሲ አካሄድ የባሰ ችግር ውስጥ ስለሚያስገባው፣ ከዚህም የተነሳ በአውሮፓ ሕብረት፣ በአፍሪካ ሕብረት፣ በአሜሪካ፣ በቻይና እና በአረብ ሊግ አባል አገሮችና በሌሎችም አገሮች ተቃውሞ በማስከተሉ፤

3. በአገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካና የደህንነት ቀውስ፣ በአማራ እና በኦሮምያ  እንዲሁም  በሌሎች ክልሎች ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባትና መሥራት የአለመቻላቸውን ጥያቄ መንግሥት መመለስ ሲያቅተው፣ ይህንን ቀውስ ወደ ሌላ ትኩረት ሊስብ ይችላል ተብሎ ወደ ታሰበ ጉዳይ እንደመውሰድ ስለሚቆጠር፤

4. የመግባቢያ ሰነዱ ፊርማ በአገሪቱ ውስጥ ካለው የብልጽግና መንግሥት የጫረዉ የእርስ በርስ ጦርነት በህዝቡ ላይ ካስከተለዉ የመከራ ቀንበር በተጨማሪ ሌላ ችግር የሚያመጣና ቀንበሩን የሚያባብስ በመሆኑ፣

5. ላለፉት አርባ አመታት ተኝቶ የነበረዉን የሱማልያ ተስፋፊ ብሄረተኝነት (Somali Irredentism) በመቀስቀስ ሃገራችንን ኢትዮጵያን በተለይ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አገሮችን ባአጠቃላይ እጅግ አደገኛ ለሆነ እና በቀላሉ ለማያባራ የጦርነት አዙሪት እና ቀውስ የሚዳረግ በመሆኑ፣

6. ይህ የማይቀር የጦረነት ሁኔታ ሲከሰት ደግሞ ከሱማሊ ላንድ ተገኘ በተባለዉ ወደብ መጠቀም የማይቻል በመሆኑ፣

7. የመግባቢያ ሰነዱ ኢትዮጵያን በአለም አቀፍ እና በአህጉር አቀፍ ድርጅቶች ህገ-ደንብ መሠረት በጠብ አጫሪነት የሚያስፈርጃት በመሆኑ፤

8. እንዲሁም በሱማሌና በኢትዮጵያ መካካል ያለውን የአልሽባብን ሽብርኝነት በጋራ የመዋጋት ትብብር የሚያሻክር ፣አካባቢያችን ለሽብርተኝነት ይበልጥ መስፋፋት አመች ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ፣

9. ስምምነቱ ከመደረጉ በፊት በብቁ የሕግ  ባለሙያዎችና የዲፕሎማሲ አዋቂዎች በቂ ጥናት ሳይደረግበትና ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው በሚገባ ሳይገመገም ለመንግሥት የገጽታ ግንባታ ሲባል በችኮላ የተፈጸመ ስምምነት በመሆኑ፤

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይህንን የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ይቃወመዋል።

ከላይ ከቁጥር 1 እሰከ 9 የተመለከቱትን ነጥቦችን በሚያርም መልኩ ወደብ የማግኘት ጥረቱ የተሻለና የላቀ የዲፕሎማሲ አካሄድ መከተል ይገባዋል ብሎ ፓርቲያችን ባልደራስ በጽናት ያምናል።

በመሆኑም የመግባብያ ሰነዱ ወደ አሳሪ ውል ከመሸጋገሩ በፊት የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት እርመጃዉን እንዲያስትካክል አበከሮ ያሳስባል።

ከላይ በተጠቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መንግስት ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገዉን የወደብ አጠቃቀም የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ በጥር 1 ቀን 2016 ዓ. ም. በኢሊሊ ሆቴል በተደረገው ስብሰባ የወሰደው ጭፍን የአድርባይነት የድጋፍ አቋም መግለጫ የፓርቲያችን የባልደራስ አቋም አለመሆኑን ለደጋፊዎቻችንና ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለጽ ይፈለጋል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ
ጥር 09/2016 ዓ. ም.

Filed in: Amharic