>

ኪዳነ ምሕረት - የካቲት ፲፮

ኪዳነ ምሕረት – የካቲት ፲፮ 

መ/ር ጌታቸው በቀለ 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም ዓመታዊ መታሰቢያ ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀት ይከበራል ። በዓሉም ኪዳነ ምሕረት ይባላል። 

‹‹ኪዳን›› የሚለው ቃል <<ተካየደ – ተዋዋለ፤ ቃል ኪዳን ተጋባ፤ ተማማለ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ኪዳን፣ ውል፣ መሐላ፣ ቃል ኪዳን፣ የውል ቃል ማለት ነው /ዘዳ.፳፱፥፩፤ ኤር ፴፩ ፥ ፴፩-፴፫፤ መዝ. ፹፰፥፫/፡፡ በሌላ በኩል ኪዳን የጸሎት ስም ሲኾን፣ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ፣ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት ኪዳን ይባላል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ዕለት ደግሞ ኪዳነ ምሕረት ይባላል፡፡ 

በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የምናከብረው ይህ በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ኾና ‹‹ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ፣ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው ስለመኾንህ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስለቻለችህ ማኅፀኔ፤ ከአንተ ጋር ከአገር ወደ አገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ›› እያለች ስትጸልይ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ ወደእርሷ መጥቶ << እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይኹን! እንዳደርግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?›› አላት። እመቤታችንም በስሟ የሚማጸኑትንና መታሰቢያዋን የሚያደርጉትን፣ ለችግረኛ የሚራሩትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትን፤ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን፤ ለእመቤታችንና ለሃይማኖታቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ልጆቻቸውን በስሟ የሰየሙትን ዅሉ እንዲምርላትና ከሞተ ነፍስ እንዲያድንላት ጠየቀችው፡፡ 

ጌታችንም ‹‹ይህን ዅሉ እንዳደርግልሽ በራሴ፣ በአባቴ እና በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ›› ብሎቃል ኪዳን ገብቶላት ወደ ሰማይ ዐርጓል። ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው <<ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት፡፡ አንተ (መታሰቢያሽን ያደረገ፣ ስምሸንም የጠራ፣ የዘለዓለም ድኅነትን ይድናል› ብለሃታልና›› በማለት የሚማጸነው፡፡ 

በተአምረ ማርያም መጽሐፍ እንደተመዘገበው በዚህ ዕለት የሚታሰቡ ሁለት ተአምራት አንደኛው የስምዖን ታሪክ ነው፡፡ ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት ከቤቱ ገብቶ <<ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ ሌላ ምግብ አልበላም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ሲያወጣና ሲያወርድ ቆየና <<አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው የእግዚአብሔር ሰው የተባለው›› በማለት፣ <<የእግዚአብሔርን እንግዳ›› ላለማሳዘን ሲል ልጁን አርዶ አቀረበለት፡፡ እንግዳ መሰሉ ሰይጣንም ሥጋውን ቅመስልኝ ብሎ ግድ አለው፡፡ ስምዖንም (በላዔ ሰብእ) አርዶ ያዘጋጀውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ሰይጣን ስላደረበት (ስለተዋሐደው) ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ቤተሰቦቹን፣ ጎረቤቶቹንና መንገደኛውን ዅሉ ይበላ ጀመር። በአጠቃላይ ፸፰ ሰዎችን ከበላ በኋላ አንድ በቍስል የተመታ ሰው አገኘና ሊበላው ሲል <<ወኃ አጠጣኝ›› ብሎ በሥላሴ፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ለመነው፤ እርሱም ዝም አለው፡፡ 

በመጨረሻም <<በድንግል ማርያም ስም›› አለው፡፡ ስምዖን የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜም ወደ ልቡናው ተመልሶ <<እስኪ ቃሉን ድገመው›› አለው፤ በሽተኛውም መልሶ ‹‹ስለ ድንግል ማርያም ውኃ አጠጣኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ <<ይህችስ እንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ›› ብሎ ጥቂት ወኃ ሰጠው፤ ወኃው ጕሮሮውን እንኳን ሳያርስለት <<ጨረስህብኝ›› ብሎ ነጥቆት ሔደ፡፡ በሌላ ቦታም አንድ ገበሬ አግኝቶ ሊበላ ሲል ገበሬው <<በላዔ ሰብ የምትባል አንተ ነህ?›› ባለው ጊዜ <<ለካስ

አመሌን ሰው ዅሉ አውቆብኛል›› ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን <<ልጄ በማይታበል ቃልህ ይህችን ነፍስ ማርልኝ?›› አለችው፡፡ ጌታችንም <<ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋ፣ ፈጣሪውን የካደ ሰው ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹በስሜ የተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?›› ብላ ስምዖንን (በላዔ ሰብእን) አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል። 

እግዚአብሔር አምላካችን <<ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ›› ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ዅሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን <<ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን›› እያሉ ለሚለምኗት ዅሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ እናምናለን፡፡ 

የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትም እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር፦ ‹‹ለሕዝብሽ፣ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪ ዘንድ፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ዅሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ትኾኚ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ሥልጣን አግኝተሻል›› በማለት አመስግኗታል /አንቀጸ ብርሃን/፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታቸው፡- ‹‹የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት፣ መርገም (ኀጢአት) ባጠፋን ነበር›› ብለዋል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው – <<ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ። መዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ፡፡ ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ። ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሳስቢ፤›› ሲሉ ይማጸኗታል /ቅዳሴ ማርያም ቍ ፻፷፭-፻፸፩/፡፡ :: 

በአጠቃላይ <<ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፤›› በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት፣ ጻድቃን፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባ፣ እንደሚገባ ተናግሯል /መዝ. ፹፰፥፫/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም <<እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው?›› በማለት እግዚአብሔር ሰዎችን እንደሚጠራ፣ እንደሚያከብር፣ እንደሚቀድስና ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል /ሮሜ.፰፥፴፫/፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ዅሉ ልዩ ነው። ስለዚህ ከንቱ አሳቦችን ትተን፣ እንደበላዔ ሰብእ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን፣ የስሙ ቀዳሽ፣ የመንግሥቱ ወራሽ ለመኾን ያብቃን፡፡ 

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ 

የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቴሌግራም ገጽ የተወሰደ
Filed in: Amharic