>

ጥፋትን በጥፋት ለማረም መሞከር እጅግ አደገኛ ነው

ጥፋትን በጥፋት ለማረም መሞከር እጅግ አደገኛ ነው

ከይኄይስ እውነቱ

በሥልጡን ዓለምና ኅብረተሰብ ውስጥ ሰው ሐሳቡን ለመግለጽ የማንንም ፈቃድ አያሻውም፡፡ ተፈጥሮአዊ ነፃነትና መብት ነውና፡፡ ይሁን እንጂ ስለ ነፃነትና መብት ስንነጋገር ሁሌም ገደብ እንዳለው ልናስተውል ይገባል፡፡ ልቅ ነፃነት ልቅ መብት የሚባል ነገር የለም፡፡ ለነፃነትም አቻና ተነፃፃሪ ኃላፊነት÷ ለመብትም አቻና ተነፃፃሪ ግዴታ አለው፡፡ ሰው ማኅበራዊ ፍጡር በመሆኑና ለብቻው ደሴት ሠርቶ መኖር ስለማይችል ነፃነትና መብቱን ለመጠቀም ሲፈልግ እሱን የሚመስሉ የሌሎችንም የሰው ልጆች ነፃነትና መብት መጋፋት እንደሌለበት ይገነዘባል፡፡ ከዚህ የወጣ አካሔድ ሥርዓተ አልበኝነትና ሕግ አልባነት ይሆናል፡፡ ውጤቱም አብሮነትና መተሳሰብ ቀርቶ መጠፋፋትን ያስከትላል፡፡ 

በተለይም መደበኛም ሆኑ መደበኛ ባልሆኑ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት በአደባባይ የሚሠነዘሩ ሐሳቦች ወይም አመለካከቶች ብዙ ሰዎች ጋር ስለሚደርሱና ተጽእኖም ስለሚያሳድሩ ታስቦባቸው በኃላፊነት መንፈስና በጥንቃቄ ሊነገሩ ይገባል፡፡ መርምረውና አስተውለው የሚያዳምጡ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በግልብነትና በጅምላ ሰምተው ለድርጊት የሚፋጠኑ ወይም የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉም እጅግ በርካቶች መኖራቸው የማይካድ ነው፡፡ ተደማጭነትና ብዙ ተከታታይ ባላቸው ‹የሕዝብ› ሚዲያዎች በአዘጋጁ ወይም በተጋባዥ እንግዶች የሚተላለፉ ተግባርን የሚጠይቁ ሐሳቦች ለበለጠ ምክንያት ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡ ያልታሰበና የማይቀለበስ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉና፡፡

ከፍ ብሎ የተመለከተውን በመግቢያነት ካልሁ፣ ዓለማዊ (ሥጋዊ) ሕይወት የሚመራባቸው ሕግጋትና አስተሳሰቦች መንፈሳዊ ሕይወት ከሚመራባቸው ሕግጋትና አስተሳሰቦች የተለዩ ናቸው፡፡ የጋራ ጉዳይ ሊኖራቸው ቢችልም በአንዱ ለታየው ሕማም ለመፍትሔነት የታዘዘውን መድኃኒት እንዳለ ወስዶ ለሌላው ለመጠቀም መሞከር እጅግ አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡ 

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የካቲት 18/2016 ዓ.ም. በዐዲስ ድምፅ ‹‹ዝምታችን እየጨረሰን ነው፤ ተነሥ ልንል ግድ ይሆናል…›› በሚል ርእስ ነዋሪነታቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ከሆኑ ኹለት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተደረገ የውይይት መርሐ ግብር ነው፡፡ 

የዐምሐራ ሕዝብ በማንነቱ ምክንያት የመኖርና አለመኖር ህልውናው ፈተና ውስጥ በመውደቁ፣ ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅርና ስሱነት በመጠቀም ሞኝ ሊያስብለው በሚያስችል ደረጃ ጠርዝ ድረስ ተገፍቶ ጅምላ እልቂት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ እስር፣ አፈና፣ ስቃይ፣ ውርደት፣  የዕለት ሕይወቱ እስኪሆን ቢታገሥም ለሁሉም ነገር ልክ አለውና ካንድ ዓመት ገዳማ በፊት  በዐምሐራነቱ ተደራጅቶ ግልጽ ጦርነት ካወጁበት የውጭ ቅጥረኞች በሆኑ ሀገር-በቀል ጠላቶች ጋር የህልውና ፍልሚያ ውስጥ ይገኛል፡፡ ትግሉም በከፍተኛ ድል ታጅቦ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ውጣ ውረዶች ቢኖሩትም፣ ፈሪና የለየለት አረመኔ የሆነው የጠላት ኃይል በጀግንነቱ ቦታ ባይሳካለትም ንጹሐንን በመጨፍጨፍ፣ የገበሬውን ሰብል በማቃጠል ዐምሐራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በጀመረው ጥፋት ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ የዐምሐራ ሕዝብ በዐምሐራ ፋኖ አማካይነት የሚያደርገው ትግል እንደ ጐሠኛ ፋሺስቶቹ ኢትዮጵያን ለማዋረድና ለማጥፋት ሳይሆን ህልውናውን አስከብሮ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ መሆኑን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ የዐምሐራ ሕዝብ ህልውናን የማስጠበቅና አገርን ከጥፋት የመታደግ መራራ ትግል ውስጥ የገባው የጐሣውን ሥርዓት ተከትሎ ሳይሆን አማራጭ በማጣትና ብቸኛው መንገድ ይኸው በዐምሐራነት መደራጀቱ በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚያነሡት ኢትዮጵያዊነት ስለተሸነፈ አይደለም፡፡ እንዲህ ብሎ ማሰብም ሆነ መናገር ነውር ነው፡፡ የተሸነፉት በኢትዮጵያዊነት ስም በእውነትም ሆነ በሐሰት እንታገላለን ብለው የተነሡ ደካሞች ሰዎች ናቸው፡፡ የተሸነፉት አሁንም በዚህ ታላቅ ስም የሚነግዱ በተግባር ግን ለጐሣ ፋሺስታዊው አገዛዝ ያደሩ ተራ አስመሳዮችና አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡ የተሸነፉት በኢትዮጵያዊነት ስም የፖለቲካ ማኅበራት አቋቁመው ፖለቲካን የገቢ ምንጫቸውና መተዳደሪያቸው ያደረጉ፣ በግፍ ሲጨፈጨፍና ሲፈናቀል ለኖረው ኢትዮጵያዊ በተለይም የዐምሐራ ማኅበረሰብ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አንዴ እንኳን ማደራጀት ያልቻሉ፣ ለፋሺስታዊው አገዛዝ አጃቢ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ድኩማን ድርጅቶችና አመራሩ ናቸው፡፡ የተሸነፉት በኢትዮጵያዊነት ስም ተከልለው፣ ይልቁንም ዐምሐራ ነን ብለው የዐምሐራ ፋኖ ለህልውናና አገርን ከአረመኔዎች ለመታደግ የሚያደርገውን እልህ አስጨራሽ ትግል ያሰናከሉ መስሎአቸው በአፍቅሮተ ንዋይና ሥልጣን ለአገዛዙ መሸጦ ሆነው የሚሯሯጡ ጭንጋፎች ናቸው፡፡ የተሸነፉትማ የዚህች የተቀደሰች ምድር ባለቤት ባለርስት እንዲሆኑ ከተደረጉ በኋላ ወደ ትፋታቸው ተመልሰው የጋራ ጥንታዊ ታሪኳን፣ ሃይማኖቷን፣ ሰንደቅ ዓላማዋን፣ ባህሏን፣ እሤቶቿን፣ ብሔራዊ ተቋማቷን፣ ቅርሶቿን፣ አውድመው የቅዠት አገር ለመመሥረት የሚጣደፉት ራሳቸው ባሮች ሆነው ሕዝብን ለባርነት የዳረጉ በ‹ነፃ አውጭ› ስም የሚንቀሳቀሱ÷የታሪካዊ ጠላቶች ቅጥረኞች ታሕተ ሰብ ድውያኖች  (ሕወሐት፣ ብአዴን፣ኦሕዴድ/ኦነግ እና ተከታዮቻቸው) ናቸው፡፡  

ኢትዮጵያዊነትማ የኃያሉ እግዚአብሔር ገንዘብ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች ‹ቆሻሻዎችን› ከላዩ ላይ አራግፎ እንደ ቅዱስ መስቀሉ ለዓለም ሁሉ የሚያበራበት ጊዜ ቅርብ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ‹እምነት›፣ ፍልስምና፣ ርእዮተ ዓለም ብሎም ረቂቅ ምሥጢር መሆኑን ከተገነዘብን በጊዜው እንደሚገለጥ ፍሕም ተዳፍኖ ይሆናል እንጂ አልተሸነፈም፤ ሊሸነፍም አይችልም፡፡ አይሁድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን፣ ዓለም የዳነበትን፣ በርካታ ገቢረ ተአምራትን የሠራውንና የሚሠራውን ቅዱስ መስቀል የሚያጠፉ መስሎአቸው ቆሻሻ ተራራ እስኪያህል ድረስ ከምረውበት ቀብረውት ነበር፡፡ ቅዱስ መስቀሉ ተሸነፈ እንበል? ክብርና ምስጋና ይግባውና ይህ ለቅዱስ መስቀሉ አይነገርም፡፡ ኢትዮጵያዊነትም እንዲሁ ነው፡፡ ከርእዮተ ዓለምነት እና ከብሔራዊ ማንነት በእጅጉ የላቀ ልዕለ ሐሳብ በመሆኑ አይሸነፍም፡፡ በልጆቹ የዐምሐራ ፋኖዎች የሚመራው የዐምሐራ ሕዝብ የህልውናና አገርን የመታደግ የተቀደሰ ትግል ሰይጣናዊውንና ፋሺስታዊውን የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ያለ ጥርጥር ያሸነፋል በሚል በድፍረት የምንናገረው ኢትዮጵያዊነት የምንለው ታላቅ ምሥጢር ዐምሐራው በደሙና በሥጋው የተዋሐደው ስለሆነ ጭምር ነው፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚታየው የፋሺስታዊው አገዛዝ ጥፋት የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ተልእኮ ቢኖረውም፣ ኢትዮጵያ ከቆመችባቸው ዋነኛ ዓምዶች ቀዳሚዋ የሆነችውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጨርሶ በማጥፋት የአገር ማፍረስ ተልእኮ ዋነኛ ተግባር መሆኑ ቢታወቅም፣ ቤተ ክህነቱም ሆነ ሲኖዶሱ ማኅበረ ምእመናኑን፣ ማኅበረ ሊቃውንቱን እና ማኅበረ ካህናቱን በተግባር የከዱትና በአመዛኙ ለፋሺስታዊው አገዛዝ በማደር ቤተ ክርስቲያኒቷን የወንበዶችና የሌቦች መሰባሰቢያ ዋሻ ማድረጋቸው የአደባባይ ምሥጢር መሆኑ ባይካድም፣ መለካውያን በመሆን ሲኖዶሱ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የእውነተኛ እረኞች ጉባኤ መሆኑ ቀርቶ የአገዛዙ ፈቃድ ፈጻሚዎች ተራ ሸንጎ ከማድረግም አልፈው ሐዋርያት ‹‹እኛና መንፈስ ቅዱስ›› በማለት የሚወስኑበትን ቅዱስ ጉባኤ የጐሠኞች መጫወቻ በማድረግ ኹለት የሐሰት ‹‹የጐሣ ሲኖዶሶች›› ተመሥርቶ ባገሪቱ ባሉ ነገዶች/ጐሣዎች ልክ ከፋፍሎ ለመበተን የጥፋቱን መንገድ መጀመራቸው እውነት ቢሆንም፤ 

ይህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የገጠማት ፈተና ከፋሺስታዊው አገዛዝ ዓላማና ተልእኮ ጋር የተቈራኘ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሃይማኖታዊ ገጽታ ስላለው መፍትሔውም ኹለት ወገን ነው፡፡ 

ሀ/ የዐምሐራው ሕዝብ የጀመረውን የህልውናና አገር የመታደግ ትግል አጠናክሮ በመቀጠል እና ከውስጡ የበቀሉ ከሀዲዎችን ያለምንም ርኅራኄ አጥፍቶ ፋሺስታዊውን አገዛዝ ማስወገድ ቀዳሚው ሲሆን፤ በዚህ ትግል ውስጥ ዘረኝነትን የሚጸየፍና ኢትዮጵያ አገሩን ከጐሠኛ ፋሺስቶች ለመታደግ የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድርሻ አለው፡፡ ተዘልሎ ተቀምጦ የዐምሐራ ፋኖ ነፃ ያወጣኛል ብሎ በስንፍና የሚጠባበቅ ካለ እሱ ሸክም/ዕዳ ነው፡፡

ለ/ የዐምሐራው ሕዝብ ህልውናውን ለማስጠበቅ ሲል በዐምሐራነቱ የመደራጀቱ ጉዳይ በሃይማኖት ጉዳይ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ሰማያዊ የሆነ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት ስላላት ነው፡፡ ይህንን የማይታለፍ የነፍስ ጉዳይ ትተን ማኅበረ ካህናቱ፣ ማኅበረ መነኰሳቱ እና ማኅበረ ምእመኑ በጐሣ ተደራጅተው ይታገሉ ካልን ስለ ቤተ ክርስቲያን ወይም ስለ ሃይማኖት መነጋገር እናቆማለን፡፡ በመሆኑም ኹለተኛው መፍትሔ ተደጋግሞ ከሊቃውንትና ከቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ምእመናን እንደተነገረው ራሱ ባለ ሁለት አንጓ ነው፡፡ 1/ ማኅበረ ሊቃውንት፣ ማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ያገባናል ብለው በተደራጀና በተጠና መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመታደግ ባንድነት መንቀሳቀስ፤ ለዚህ አንድነትና ኅብረት መሠረቱ አንዲት ተዋሕዶ ሃይማኖት፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እና አንድ ሐዋርያዊት ሲኖዶስ ነው፡፡ እና 2/ የአኀት አብያተ ክርስቲያናት አባቶችና ሊቃውንት ተጠርተው፣ ከሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ታዛቢዎች ባሉበት፣ ጉባኤ በማካሔድ የተሻረ ቀኖና እንዲመለስ፣ በንስሓ የሚስተካከለው ጥፋት እንዲታረም፣ መለየት የሚገባቸው እንዲለዩ፣ ባጠቃላይ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ተፈትሸው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና አኳያ እንዲስተካከሉ ማድረግ ነው፡፡ 

በመርሐ ግብሩ እንደተላለፈው የተማሪዎቹ ፖለቲከኞች፤ 1ኛ/ ከዐምሐራው ሕዝብ ብቻ የተገኙ አይደሉም፤ 2ኛ/ የጐሣ ፖለቲካ መሥራቾቹ ከትግሬዎቹና ከኦሮሞዎቹ ብቻ ሳይሆን ከዐምሐራውም መካከል የወጡ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ነገድ ቆጠራ ውስጥ ከገባን በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ እጅግ መጥፎ በሆነ ዝና የሚታወቀው ዋለልኝ መኮንን የዐምሐራ ተወላጅ አይደለም እንዴ?

የሞቃድሾ ሱማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ኢሕአፓ የተባለውና በተማሪዎቹ ንቅናቄ የተመሠረተው የፖለቲካ ድርጅት አባላት መካከል የተወሰኑት ከሱማሊያ ጎን ቆመው ኢትዮጵያን እስከ መዋጋት እንደደረሱ ታሪክ አልመዘገበውም? የተማሪዎቹን ንቅናቄ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ብቻ ለማዛመድ መሞከሩ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ይሁን ትክክል ነው ብለን  ብንቀበል እንኳን በዘመናችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በጐሣ ፋሺስታዊው አገዛዝ ለገጠማት ፈተና በየትኛውም መመዘኛ በማመሳሰል (analogy) ምሳሌ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል እንዲሉ፡፡

የመርሐ ግብሩ አዘጋጅ በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩትን  ካህናት አንድ መሪ የሆነ ጥያቄ (leading question) አቅርቦላቸዋል፡፡ 

‹‹… በብሔርተኝነት ዐምሐራ ገና ዳዴ እያለ ነው…እነዛ በዚያን ጊዜ [በተማሪዎቹ ንቅናቄ ጊዜ] የነቁት ብሔርተኞች ተረክበው ሥልጣን ይዘው እየገዙን ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኗም ላይ ያን እያየን ነው፡፡ እናንተ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ቁጭ ብላችሁ አጠገባችሁ ያሉ ጳጳሳት ከብሔርተኛ ካድሬ ጋር እየሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን እያፈረሱ የራሳቸውንም እያቋቋሙ ነው፤ እና እንደ ቀድሞ የተማሪ ፖለቲከኞች እናንተ አሁን ያላችሁ ኢትዮጵያዊ ስሜት ያላችሁ የዐምሐራ ቀሳውስት ካህናት መነኰሳት በሙሉ ካልነቃችሁ የዚያ ዓይነት ዕጣ ፈንታ ያጋጥማችኋል፣ ትጠፋላችሁ፤ መንጋችሁንም ትበትናላችሁ የሚል ነገር ነበር ያነሳነውና… ይሄ ስሜት አይሰጥም ወይ?… እያያችሁት አይደለም?›› 

ከፍ ብሎ ከአዘጋጁ የቀረበው ጥያቄ በተማሪዎቹ እንቅስቃሴ (ዐምሐራዎቹ) ኢትዮጵያን ሲሉ ባለመንቃት ጐሠኞቹ የበላይነት አግኝተው ከሥልጣን መገለል ብቻ ሳይሆን እንዲጠፉ ተደርጓልና አሁንም ቤተ ክህነቱና ሲኖዶሱ ሙሉ በሙሉ በጐሠኞች የሐሰት ‹ጳጳሳት› ቊጥጥር ሥር ከመዋሉና ከመጥፋቱ በፊት የዐምሐራ ማኅበረ ካህናት የራሳቸውን የነገድ ቤተ ክህነትና ሲኖዶስ እንዲያቋቁሙ አንድምታ ያለው ንግግር ይመስላል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ የመርሐ ግብሩ አዘጋጅ እጅግ ግዙፍ የሆነ ታሪካዊ ስሕተት እየፈጸመ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ በብስጭትም እንኳ ቢሆን የነገድ ሲኖዶስ እናቋቁም የሚል ከሃይማኖት የወጣ ሐሳብ እንኳን ከቤተ ክርስቲያን አባት ከተራ ምእመንም መነገር የለበትም፡፡ ከተሳታፊዎቹ ካህናት መካከል ቆሞሱ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሐሳብ አንጸባርቀው ነበር፡፡ በወቅቱ ከተዋሕዶ አባት የማይጠበቅ መሆኑን ተናግሬአለሁ፡፡ በአሁኑ መርሐግብር ላይ ዐምሐራው የራሱን የነገድ ሲኖዶስ ያቋቁም የሚል ከተሳታፊዎቹ አባቶች በቀጥታ የተነገረ መልእክት አልሰማሁም፡፡ ሆኖም ይህንን በሚዲያው መሪ የተደገፈውን እና በጥያቄ መልክ የቀረበውን ሐሳብ እነዚህ አባቶች ደግፈውት (endorse አድርገውት) ከሆነ በውይይቱ ያነሡአቸውን መልካም ሐሳቦች ሁሉ ከንቱ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

ዐምሐራው ሕዝባችን ለዓመታት እየደረሰበት ያለውን ግፍና በደል መቃወም፣ ማውገዝና እንዲቆምም የድርሻን መወጣት እንኳን ከእግዚአብሔር አደራ የተቀበሉ ካህናት የማንኛውም ኢትዮጵያዊና ሰብአዊ ፍጡር ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ረገድ እውነተኛና ጥብዐት ያለው ጳጳስ ካለ ማኅበረ ካህናቱና ማኅበሩ ምእመናኑ እንዲሁም የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፋሺስታዊው አገዛዝ እንዳይገዙ መገዘት/ማውገዝ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ታላቅ ሥልጣን አገርና ቤተ ክርስቲያን እየጠፉ ላለበት ለዚህ ክፉ ጊዜ ካልሆነ ለመቼ እያሳደሩት እንደሆነ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ቋሚ የሃይማኖት አስተምሕሮ ወይም መመሪያዎች አሏት፡፡ ‹ቱምቢዋ› ዶግማ (መሠረተ እምነት) እና ቀኖና (ሥርዓት/ሕግ) ናቸው፡፡ ‹ከምትጠፋ› ዶግማና ቀኖናዋ ይፍረስ እያልን ከሆነ ጥፋቷ የሚሆነው ዶግማና ቀኖናዋን የሻረች ጊዜ ነው፡፡ አሁንስ ቀኖናዋ አልተሻረም ወይ የሚል ጥያቄ ከተነሣ እኔ ሳልሆን የጠ/ቤ/ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጳጳስ ቀኖና መሻራቸውን በአደባባይ ወጥተው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሻሩት የሲኖዶስ አባላት በሙሉ ቀኖናውን ቦታው እስካልመለሱ ድረስ የምእመናን አባትነታቸውን አጥተዋል፣ ነፍሳችንን በአደራ የምንሰጣቸው እረኞች አለመሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ ይህ ግን የዚህ ወይም የዛ ነገድ አባል ከመሆናቸው ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ 

ባንፃሩም የነገድ ወይም ጐሣ ማንነት ከሃይማኖት ይበልጥብናል ያሉት የሐሰት ‹ጳጳሳት›፣ በአገዛዙ አይዞአችሁ ባይነት በጉልበት በተለያየ ኃላፊነት በቤተ ክህነቱ የሚገኙ ሰዎች (እንደነ በላይ ዓይነቱ)፣ እንዲሁም ተገንጥለው የጐሣ ሲኖዶስ እና ቤተ ክህነት አቋቁመናል ያሉ ቡድኖች ከክርስቲያን ማኅበር አንድነት የተለዩ ወንበዶች ናቸው፡፡ የተወገዙት በሙሉ ከክርስቲያን አንድነት በመሆኑ ክርስቲያኖችም አይደሉም፡፡ 

የጥምቀት ልጅ የሆነ ክርስቲያን በሙሉ የተወለደው ከማይጠፋ ዘር ከእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹ቤተ ክርስቲያን እንዳትጠፋ› የዐምሐራ ካህናት (ከአናጉንስጢስ እስከ በትርያርክ) በነገድ ተደራጅተው ዐዲስ ቤተ ክህነትና ሲኖዶስ ያቋቁም እያልን ከሆነ ከክርስቶስ አንድነት መለየት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ የተለያት ሰውነትና ተቋም ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ልትሆን አትችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጠፋች የሚባለው ይህ ሲሆን ነው፡፡ 

በመሆኑም የፖለቲካውን/የቤተ መንግሥቱን አካሔድ በማመሳሰል መንገድ ለሃይማኖቱ/ለቤተ ክህነቱ አምጥቶ ለመጠቀም መሞከር አስቀድሞ የተፈጸመን ጥፋት በሌላ ጥፋት ለማረም መሞከር እጅግ አደገኛ አካሔድ በመሆኑ፣ በዚህ ጽሑፍ በፊደል ተራ ‹ሀ› እና ‹ለ› የተመለከቱት መፍትሔዎች ላይ በትኩረት መሥራት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በመርሐ ግብሩ ተሳታፊ የነበሩት ካህናት አባቶች የውይይት መንፈስ ከዚህ የወጣ እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም የአዘጋጁ መሪ ጥያቄ ከርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዶግማና ቀኖና ጋር በግልጽ የሚፋለስ ነውና፡፡

በመጨረሻም ለኢትዮጵዮጵያውያን እና በዓለም ለምትገኙ የጥቁር ዘር በሙሉ፤

የሰው ልጆች እኩልነት ለተበሰረበት ለታሪካዊው የዓድዋ ድል ብሔራዊ በዓላችን እንኳን አደረሰን፡፡ አደረሳችሁ፡፡

Filed in: Amharic