>

‹‹መንግሥት በሌለበት አገር›› አገራዊ ጥፋቱ ቀጥሏል

‹‹መንግሥት በሌለበት አገር›› አገራዊ ጥፋቱ ቀጥሏል

ከይኄይስ እውነቱ

ተሠርቶ ያደረ አገርን የሚያጠፋ፣ ነባር ቤተ እምነቶችን ከነ ቅርሳቸው የሚያወድም፣ ከነባር አገራዊ እሤቶች ጋር ሁሉ የተጣላ፣ የአገር መከላከያን ተቋም አፍርሶ ዳር ድንበርን ባለቤት አልባ አድርጎ ለወራሪዎች ያጋለጠ፣ ካንድ ሚሊዮን በላይ የሚገመት የሰሜን ሕዝባችንን የጨፈጨፈ÷ ብዙዎችን አካለ ስንኩል እና ሙልጭ ያለ ደሀ አድርጎ እጅግ ለከፋ ረሃብና ቀጠና ያጋለጠ፣ ከሁሉም በላይ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በቀዳሚነት አገርን በደምና ባጥንቱ ያቆመው የዐምሐራ ሕዝብ ላይ እንደ ውጭ ጠላት ቆጥሮ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እና ሙሉ ጦርነት አውጆ ንጹሐንን በሰው አልባ አውሮፕላን፣ በከባድ መሣሪያ የዘር ፍጅት እየፈጸመ ያለ፣ በሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ፣ ቤት ንብረታቸውን እያቀጠለና እየዘረፈ÷ እናቶችና እኅቶቻችንን ጨቅላ ልጃገረዶችን ሳይቀር ቅጥ ባጣ ነውረኛነት እየደፈረ፣ በማሳ ላይ ያለና የተሰበሰበ እህል እያቃጠለ፣ ግዙፍ የዝርፊያና የገዳይ ቡድን አደራጅቶ የለየለት ሥርዓተ አልበኝነትን እና ሽብርተኝነትን ያነገሠ፣ የምናከብራቸው ሰዎች እንዳይኖሩ ከቤተ እምነት መሪዎች እስከ ‹ምሁራን ነን› ወይም ፊደል የቆጠርን ነን እስከሚሉ÷ ከሃይማኖት መምህራን እስከ ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ሰዎች÷ ካንጋፋ የሚዲያ ሰዎች እስከ ታዋቂ ባለሀብቶች (በልፋታቸው ሀብት ያፈሩትን ብቻ ይመለከታል) ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙትን ያርመጠመጠና ያልከሰከሰ፣ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ታሪካዊና ጥንታዊት አገር በየትኛውም ዓለም አቀፍ መድረክ ያዋረደ፣ የዐረብና የምዕራባውያን ቅጥረኛና ተልእኮ አስፈጻሚ ሆኖ ነውሩን ሁሉ ክብር አድርጎ እያለማመደ ያለ፣ በፋሽስትና አረመኔነቱ ተወዳዳሪ የሌለውን የተራ ዱርዬዎችና ወንበዴዎች ቡድን ‹መንግሥት› ወይም ‹ሥርዓት› እያልሁ ብጠራ ወንጀለኛ የምሆነው እኔው ራሴ ነኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹን በቁማቸው ሥጋ የለበሱ አጋንንቶችን ነው ኢትዮጵያችን ላለፉት ስድስት የሰቆቃና ዋይታ ዓመታት ተሸክማ የዘለቀችው፤ አሁንም ገና ያልተገላገለችው፡፡

ተግባር ይናገር በሚል እምነት በሌላም የግል ጉዳይ ትንሽ ራቅ ብዬ ነበር፡፡ ለዛሬው የጽሑፌ ርእሰ ጉዳይ ላደርግ ያሰብሁት በየዕለቱ ፋሺስታዊው አገዛዝ በኢትዮጵያችን ላይ እየፈጸመ ያለውን ተጨማሪ በደል እየነቀሱ መዘርዘሩ ለሞት ሽረት ትግሉ እምብዛም ፋይዳ ባይኖረውም በታሪክ ተመዝግቦ እንዲያልፍና በቀጣይም እርምት እንዲደረግ ስለሚረዳ ሰሞኑን አገዛዙ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሚል ከሚጫወትበት ተቋም ሕዝብን መጨፍጨፊያ የሚሆን የጦር መሣሪያ ለመግዥያ የውጭ ምንዛሬ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ስላወጣው አገርን በእጅጉ የሚበድል ሕግ (መመሪያ) ጥቂት ነጥቦችን ለመሠንዘር ነበር፡፡ ባገሩ ሰላምና ጸጥታ፣ ሕግ ጠፍቶ፣ ሥርዓተ አልበኝነት ነግሦ እንኳን ለውጭ ባለሀብት ያገር ውስጡም አገዛዙ ባሰማራቸው ዘራፊዎች ምክንያት ረዥም ጊዜ አስቦ መዋዕለ ንዋይ ሊያፈስ ይቅርና ተራ ንግድም የማይሞከር ሆኖ ጥሪቱን እየተዘረፈ ባለበት ሁናቴ፣ ቤታችንን እስከ ችርቻሮ ንግድ ወርዶ ወለል አድርጎ ከፍቶ በስመ የውጭ ባለሀብት ስም ያለምንም ተጨማሪ እሤት ቡናውንም፣ ሙጫውንም፣ ቆዳውንም፣ ከብቱንም ባጠቃላይ ሸቀጣ ሸቀጡን ሁሉ ከገበያ ላይ እየገዙ እንዳሻቸው እንዲፈነጩበት ፈቅዷል፡፡ ወያኔ ለሀገር ውስጥ ባለሀብት ብቻ የተከለሉ የሥራ መስኮችን ይከፍት የነበረው ወይም አንዳንድ የኢንቨስትመንት መስኮችን ‹ለመንግሥት› ብሎ የሚያቆየው የአገርን ልማት አስቦ ሳይሆን አገዛዜን ያስጠብቁልኛል የሚላቸውና ካንድ አካባቢ የተሰባሰቡ ‹ዐዳዲስ ሀብታሞች› ሊሠማሩበት ይችላሉ ብሎ ሲያስብና ዐቅማቸውን እስኪያጎለብቱ ነበር፡፡ ዳፍንታሙና በወያኔ ሥር ሆነ ባሽከርነት ዘመኑ የጓዳ ምስጢር ያውቅ የነበረው ኦሕዴድ ከተንኮል በቀር የተማረው ስለሌለ አሳዳሪዎቹ ነጮች ለሚጥሉለት እርጥባን እና ፈቃዳቸውን ወይም የሚሰጡትን ተልእኮ በመፈጸም ለሚያደርጉለት ውለታ ሲል አገርን አሳልፎ ለመሸጥ ዝግጁ እንደሆነ በተለያየ አጋጣሚ ታይቷል፡፡ የአሁኑ ግን አሳዳሪዎቹ ሕዝብ ለመጨፍጨፊያ የሚፈልገውን ብድር (በራሳቸው ምክንያት) ስለነፈጉት ሌላ አማራጭ ሲያስብ ላገር ደንታ የሌላቸው ደናቊርት አማካሪዎቹ ያቀረቡለት (ዘላቂና የማይጠገን ጉዳት የሚያስከትል) መፍትሔ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በላይ በጉዳዩ ላይ በዝርዝር መጻፍ አልወደድሁም፡፡ ትኩረታችን ከ‹‹ጭፍጫፊ›› ጉዳዮች ‹ዐቢዩ› ላይ አተኩረን ርጉም ዐቢይንና አገዛዙን ማስወገድ ነውና፡፡

አለመታደል ወይም መረገም ሆኖ ወያኔ ሕወሓት፣ ኦነግ-ኦሕዴድ የሚባሉና ኹለቱን በቋሚ ለጓሚነት÷ በገረድ ደንገጥርነት ዘላለማዊ አሽከርነትን ገንዘቡ ያደረገውን የአገር ነቀርሳ ቡድን ብአዴን/አብን አባል በመሆን፣ በመደገፍ ወይም በአድርባይነት አብሮ በመቆም የኢትዮጵያን ፍዳ የሚያራዝሙ ቊጥራቸው አነስተኛ የማይባሉ  ታሕተ ሰብእ የሆኑ በዚሁ ምድራችን የበቀሉ አራሙቻ ፍጡራን ባገር ውስጥና በውጭም መኖራቸው የክፍለ ዘመናችን ታላቅ እንቆቅልሽ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡

አገራችንና ሕዝቧ በጣዕር ላይ በሚገኙበት በዚህ ፈታኝ ጊዜ ለመንግሥትነት ወግ ሳይበቃ ሊያልፍ አንድ ሐሙስ የቀረውን ፋሺስታዊ አገዛዝ የዐምሐራ ፋኖ በጀመረው ፍትሐዊ ጦርነት አማካይነት ሁሉም የድርሻውን አበርክቶ ፍጻሜውን ከማቅረብ በቀር ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አሁንም ለመጨረሻው ጠላታችን ብአዴን ማስጠንቀቂያ የምንሰጥ፣ ወገን አድርገን የምናስብ፣ ቃላቸውንም የምናደምጥ ከሆነ ትክክለኛው ቃል አልገባንም ሳይሆን፣ መከራችን ገና ነው ማለት ነው፡፡ በገዛ ምድራችን ሚሊሻ፣ አድማ በታኝ እያሠለጠኑ በሕዝባችን ላይ ሲያሰማሩ፣ አገዛዙ ህልው ነው ለማስባል ስብሰባ ሲጠሩ፣ ሕዝባችንን ሲዘርፉ ሲያዘርፉ፣ ከጠላትም ከፍተው ለጠላት ሲመርጁ ከማየት በስተቀር ምን ውርደት አለ! እነዚህን የኢትዮጵያ በተለይም የዐምሐራ ሕዝብ ‹ነቀርሶች› ያለ አንዳች ርኅራኄ ማስወገድ ካልቻልን የእስካሁኑን ትግላችንን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ በየትኛውም የዐምሐራ ክፍላተ ሀገር/ጠቅላይ ግዛት ባሉ ፋኖዎችም ሆነ ባጠቃላይ በሕዝቡ ዘንድ ወያኔ/ሕወሓትን የሚደግፉ ኃይሎች ካሉ እነሱ የዐምሐራ ልጆች አይደሉም፡፡ ጠላት ናቸው፡፡ 

ማኅበረሰብ ለማኅበረሰብ ድሮም ግንኙነት ነበር፣ አሁን በወያኔ÷ በኦነግና በብአዴን ታውኳል፡፡ ወደፊት ተስተካክሎ እንደሚቀጥል እምነት አለኝ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን የትግራይ ሕዝብ ከወያኔ ሙሉ በሙሉ ሲፋታ፤ የተወሰነም ቢሆን በአጋንንታዊ ስብከት ‹አውሬ› እንዲሆን የተደረገ የኦሮሞ ወጣትና ጎልማሳ ከኦነግ-ኦሕዴድ ሙሉ በሙሉ ሲፋታ እና የዐምሐራ ሕዝብ (ጥቂት ካለ) ከብአዴን ሙሉ በሙሉ ሲፋታ ብቻ ነው፡፡ ባጭሩ ‹ነፃ አውጭ› ነን ከሚሉ ወስላቶች ባርነት ሲላቀቅ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ተግባር ደግሞ አገር ወዳድ የሆኑና የየማኅበረሰቡ ፊደል የቆጠሩና ምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ 

የዐምሐራን ሕዝብና ኢትዮጵያን ከዚህ ፋሺስታዊ አገዛዝና ጀሌዎቹ ገላግሎ ዐዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት የሚታመነው የዐምሐራ ሕዝብ ተጋድሎ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ሰብአዊነት ወዳጅ የሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ትግል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ደጋግሜ እንደተናገርሁት በተጠቀሱት እሤቶች የሚያምን ሁሉ ተዘልሎ ሊቀመጥ አይገባም፡፡  አስተዋጽኦ፣ ኃላፊነትና ድርሻችን እንደ ዕድሜችን፣ የጤንነት አቋማችን፣ ዕውቀታችን እና ልምዳችን ሊለያይ ይችላል፡፡ ከነዚህ አስተዋጽኦዎች አንዱ ትግሉን ያግዛል ከትክክለኛው ሐዲድ እንዳይወጣ ይረዳል ብለን የምናምንበትን መልካም ሐሳቦች ማዋጣትንም ይጨምራል፡፡ 

1ኛ/ በዚህ ረገድ በመጀመሪያ ረድፍ የተሰለፉ ጀግኖቻችን ውስጥ ለጠላት ተልእኮ የተሰለፉም ሆነ ከጠላት ተመልሰናል ብለው ከጠላት ብአዴን እርሾ ወይም አስተሳሰብ ያልፀዱትን ደግሞ ደጋግሞ ራስን በመፈተሸ ያለ ርኅራኄ ማፅዳት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም በነዚህ ጥቂት ነውረኞች ድርጊት በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን እና ጀግኖቻችንን እናስጨርሳለንና፡፡

2ኛ/ የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ እንዲሉ የትግል መቋጪያው ወይም ማሰሪያው ‹ድርጅት› ነው፡፡ አለበለዚያ በተናጥል የተመዘገበው ድል ሁሉ ተበታትኖ ይቀራል፡፡ ድርጅት ስንል አንድ ዓይነት ዓላማና ግብ ይዞ ዐቅዶና ስልት ነድፎ የታሰበው ግብ ለመድረስ በወታደራዊውም ዕዝ ሆነ በፖለቲካው አመራር የሚኖረውን የተቀናጀ፣ ሥርዓት የያዘና በጠንካራ ዲስፕሊን የሚገዛ ማዕከላዊ አሠራርን ይመለከታል፡፡ በእስካሁኑ ጉዞ በአራቱም የዐምሐራ ክፍላተ ሀገር/ጠቅላይ ግዛት የተመዘገቡት ድሎች (ነፃ የወጡ አካባቢዎችን ማስተዳደር ጨምሮ) በእጅጉ የሚያኮሩ ናቸው፡፡ ለዚህ ክብር ላበቁን ጀግኖቻችንና በጠላት እጅ መከራ ለተቀበለው ሕዝባችን ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ጠላታችን ግን ሌት ተቀን የማያንቀላፋ፣ ህልውናውም የተንጠላጠለው በእኛው ምድር የበቀሉ ከሃዲ አራሙቻዎችን መሠረት አድርጎ መሆኑ ለአፍታ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ በዚህም ምክንያት ለፋሺስታዊው ቡድን አንድ ተጨማሪ ቀን በሰጠነው ቊጥር ፍዳችን ይረዝማል፡፡ የውስጥ÷ ነገር ግን ዋና የሆነውን ጠላት (ብአዴን) ያለአንዳች ርኅራኄ በማጥፋት ረገድ ያሳየነው ቊርጠኝነት በቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ወጥ የሆነ ዐምሐራዊ የወታደራዊና ፖለቲካው ድርጅት ለመመሥረትም (ፋታ የማይሰጠው ውጊያ እና ፈተናው እንደተጠበቀ ሆኖ) የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑ ጀግኖቻችንና መሪዎቹም በሚገባ ያውቁታል፡፡ ፍጥነቱ ያስፈለገው ትግሉን ከጀመርንበት ጊዜ ርዝመት አኳያ ሳይሆን ጠላታችን እስካሁን ካደረሰውና በየዕለቱ እያደረሰ ካለው በቀጣይም ሊያደርስ ከሚያስበው አገራዊ ጥፋት አንፃር ነው፡፡

3ኛ/ ወታደራዊ መረጃዎች አዘጋገብ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ቢያንስ በክፍለ ሀገር ደረጃ ወጥነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ተዋጊ ወይም አመራር ሁሉ ቃል አቀባይ መሆን የለበትም፡፡ ከሁሉም በላይ መነገር ያለባቸውንና የሌለባቸውን ወታደራዊ መረጃዎችን መለየትና ማጥራት ይገባል፡፡ የትግሉ አካል የሆኑ ሚዲያዎችም በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን እስከ ታላላቅ ዓምዶቿ እያጠፋ ያለውን ርጉም ዐቢይን ‹ዶ/ር› እያለ የሚጠራው ግርማ ካሣ የተባለ ግለሰብ ለወታደራዊ ጉዳይ ‹ጨዋ› ሆኖ ሳለ ራሱን እንደ ወታደራዊ ጠበብት በመቊጠር ከሚዘባርቀው የወታደራዊ ጉዳዮች ‹ትንተና› ቢቆጠብ ትግሉን በእጅጉ የሚያግዝ ይመስለኛል (ዓላማው ፋሺስታዊውን አገዛዝ ለማስወገድ ከተነሡት ጋር ከሆነ)፡፡

4ኛ/ ወያኔ ሕወሓት የፋሺስታዊው አገዛዝ የጡት አባትና የአጋንንታዊው የጐሣ ሥርዓት ተካሊ እንደመሆኑ ከምድረ ገጽ መጥፋት ያለበት ባጠቃላይ የኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ የዐምሐራው ቋሚ ጠላት ነው፡፡ ይህ ቆሻሻ ቡድን በኢትዮጵያ ዳግም የማንሰራራት ዕድል ባይኖረውም አሁንም በትግራይ ሕዝብና በምዕራባውያኑ ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ ይገኛል፡፡ መጥፎ ዝና ካለውና ‹‹የፕሪቶሪያ ስምምነት›› እየተባለ ከሚጠራው የኦሕዴድ/ኦነገ እና የወያኔ ሸፍጥ ጀምሮ እያደባና ስሌት እየሠራ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፈውን የጦር መሣሪያ እንደተሸከመ ይገኛል፡፡ ይህ ነውረኛ ቡድን ጥሩ አጋጣሚ ያገኘ መስሎ ሲታየው አሁን ባሽከርነት ካደረለት ርጉም ዐቢይ ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ ለመፈጠም ወደ ኋላ እንደማይል ቀደም ብሎ የሚታወቅና ሲነገር ሲተነተን የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የመጣ ክስተት አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የገረመኝ ጉዳይ ቢኖር የዐምሐራ ፋኖ በተለይም የቤተ ዐምሐራው በሁሉም የወሎ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ (ራያ አለማጣ ኦፍላን ጨምሮ) የብዙዎች ግምት ነበር፡፡  በመሆኑም ቅድመ ዝግጅት እንደሚኖር ግምት ነበር፡፡ በጎንደርም በኩል ወልቃይትና አካባቢው በጎንደር ፋኖ ቊጥጥር ሥር እንደነበር ነው የብዙዎች እምነት፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎችና የራያ ዐምሐራ አስመላሽ ኮሚቴ ከሚባለው አካል የሰማነው ግን ብዙዎችን ያስደነገጠ ያስገረመ ብሎም ያሳዘነ እውነታ ነው፡፡ ርጉም ወያኔ ሕቅታው እስካለ ድረስ የጎንደሩ ወልቃይት እና የወሎው (የቤተ ዐምሐራው) ራያ መወዛገቢያና ደም መፋሰሻ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ወያኔ ሕወሓት፣ ኦሕዴድ/ኦነግ እና የጋራ አሽከራቸው ብአዴን በተለይ፣ የጐሣ አገዛዝ ከነ ‹ደደቢት ሰነዱ› ባጠቃላይ ከኢትዮጵያ ምድር ቢወገዱ እነዚህ የዐምሐራ ግዛቶች እንኳን የትግራይ ወገናችን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ግዛቶች ሀብቶች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ወያኔ የዐምሐራ ፋኖን ዐቅም ለመፈተሽም ይሁን ግዛቶቹን በኃይል ለመንጠቅ ሰሞኑን ከፋሺስታዊው አገዛዝ ጋር ተመሳጥሮ ትንኰሳ ጀምሯል፡፡ 

ግርምቴና ሐዘኔ

የራያ አለማጣ ሕዝብ የወሎ (ቤተ ዐምሐራ) ዐምሐራ እንደሆነ ያምናል፡፡ ይህን የማንነቱን ጥያቄ የሚፈታለት የዐምሐራ ሕዝብ ጠላት የሆነው ፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ እንደሆነ የራያ ዐምሐራ አስመላሽ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆነው ግለሰብ ሲናገር መደመጡ ብቻ ሳይሆን ያምንበታል፡፡ ለወሰኑም ጥበቃ ከዐምሐራ ፋኖ ይልቅ የአገዛዙን ሠራዊት አምኖ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም ደጋግሞ በድፍረትም ይናገራል፡፡ እንደውም የዐምሐራ ፋኖ ራያ አለማጣ ወሰን እንዳይደርስ ‹ቀይ መስመር› ስለተሠመረ በአካባቢው ድርሽ እንደማይል ይናገራል፡፡ 

ፋሺስታዊው አገዛዝ በመላው የዐምሐራ ሕዝብ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አውጆና በይፋ ጦርነት ከፍቶ ሕዝባችንን በጅምላ በአየርና በከባድ መሣሪያዎች ሲጨፈጭፍ እነሆ አንድ ዓመት ሊሞላው እየተቃረበ ይገኛል፡፡ ይህንንም የዘር ፍጅት የሚፈጽመው ብአዴን በተባለ ‹ውርዴ› አማካይነት ነው፡፡ ይህ የኮሚቴው ሊቀመንበር የተባለው ግለሰብ የዐምሐራ ሕዝብ በአገዛዙና ባሽከሩ ብአዴን ለሚደርስበት ሁለንተናዊ መከራ እንግዳ ካልሆነ በቀር ለወንድማችን አበበ በለው የሰጠውን ቃለ ምልልስ አሁን ላይ በድፍረት ባልተናገረ ነበር፡፡ ባንድ ወገንም መናገሩ ጥሩ ማንቂያ ደወል ነው፡፡ ወንድማችን አበበም የአካባቢው ሕዝቡ በወያኔ እየደረሰበት ያለውን ግፍና መከራ በማየትና ነገሮችን ለማለዘብ በመፈለግ እየተገረመም ቃላት እያጠረውም ፊቱም እየተለዋወጠም ቢሆን ሰውየውን በጥያቄ ለመወጠር አልፈለገም፡፡ ይህ ግለሰብ ፋሺስታዊው አገዛዝ የዐምሐራም ሆነ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን ገና አልተቀበለም፡፡ ባካባቢው ያለው አስተዳደር የቀንደኛ ጠላታችን የብአዴን ካድሬዎች ናቸው፡፡ ሰውየው እንደሚነግረን ሕዝቡ ከዐምሐራ ፋኖ ይልቅ እነዚህን ካድሬዎች፣ የፋሺስቱን በጣት የሚቈጠር ሠራዊት እና አገዛዙን ተማምኖ እንዳለ ነው፡፡ እናንተዬ የዐምሐራ ትግል ‹ሀ ሁ› ያልገባው ሰው ወይም ከአጠቃላይ አቋሙ ‹የአገዛዙ ታማኝ› የሚመስል ሰው የራያ ዐምሐራን ነፃ አወጣለሁ ሲል አለማፈሩ የሚደንቅ ነው፡፡ ‹‹አንተኑ ነገድ ለኢትዮጵያ››/ለኢትዮጵያ እንግዳ ነህ ወይ ብዬ ልጠይቀው?/ ከንግግሩ ሁሉ የምረዳው የዐምሐራ አይደለም የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ የሆነውን ፋኖ እንደሚጸየፍ ነው፡፡ እንደ ድፍረት አትውስዱብኛና ካገዛዙ ተልእኮ ተሰጥቶትም ይሁን አምኖበት ግለሰቡ ከተናገረው በመነሳት ዐምሐራነቱን ለመቀበል ተቸግሬአለሁ፡፡ የሚቀርበው ለብአዴንነት ነው፡፡ ብአዴን ደግሞ በእኔ እምነት ‹‹ዐምሐራ አይደለም፡፡›› ወንድሜ ‹ፌዴራል›፣ ‹ሕገ መንግሥት›፣ ‹ሕዝበ ውሳኔ› የምትለው አርቲ ቡርቲ ቀርቶ ‹መንግሥት› የሚባል በኢትዮጵያ ምድር የለም፡፡ ውጣና ተናገር ተብለህ ተልእኮ ተሰጥቶህም ከሆነ የራስህ ጉዳይ ነው፡፡ በተጀመረው ሕዝባዊ ትግል ላይ የምታመጣው አንዳች ለውጥ የለም፡፡

አሁን ወያኔ የጀመረውና መጨረሻው ያልለየለት ትንኮሳ እንደሰማነው የራያ አለማጣ ዐምሐራ ሕዝብን በእጅጉ መጉዳቱና ነውር መፈጸሙ ቢያሳዝነንም የተጀመረውን ትግልና ትኩረቱን የሚቀይር አይደለም፡፡ ሽልም ከሆነ ይገፋል ቂጣም ከሆነ ይጠፋል እንዲሉ የትንኮሳው ዓላማ ሲውል ሲያድር ጥርት ብሎ ይለይለታል፡፡

ወያኔ ከርጉም ዐቢይ ሠራዊት ጋር ተባብሮ በመሣሪያ ብዛት እነዚህን ግዛቶች በኃይል ለመንጠቅ የጀመረውን ትንኮሳ የሚገፋበት ከሆነ የዐምሐራ ፋኖ (የወሎ ጠ/ግዛት ዕዝ ብቻ ሳይሆን) በተጠና ወታደራዊ ርምጃ፣ መሥዋዕትነትና ውድመት በሚቀንስ የውጊያ ዓይነትና ስልት የጥፋት ርምጃውን ቀልብሶ ትኩረቱን ወደ ዓፄ ምንይልክ ቤተ መንግሥት ወደ አራት ኪሎ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ጉዳዩ በአላማጣ ኦፍላ የሚገኘው የራያ ዐምሐራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ዐምሐራ ፋኖ እና ሕዝብ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ‹የኮሚቴው ሊቀመንበር› ነኝ የሚለው ሰውዬ እውነት ለራያ ዐምሐራ ሕዝብ ተቆርቋሪ ከሆነ ወያኔ እና ኦነግ/ኦሕዴድ ሕዝቡን እስኪጨርሱና ከቤት ንብረቱ ሙሉ በሙሉ እስኪያፈናቅሉ ከሚጠብቅ ውገናው ከዐምሐራ ፋኖ ጋር ሊሆን ይገባል፡፡ እውነታው መጋለጡ ስለማይቀር ‹ቀይ መስመር› የሚለውን በፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝና በሽብርተኛው ወያኔ ላይ ያስምር እንጂ በፋኖ ላይ ማድረጉ የነውር ነውር ነው፡፡ ፋኖ እኮ የዐምሐራ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የሰብአዊነት፣ የፍትሕ እና ነፃነት ብራንድ ስም መሆኑን እንኳን ዐምሐራ ነኝ የሚል ወገን ቀርቶ ሁሉም የተገነዘበው ነው፡፡ ዐምሐራ ጠላቱ የሆነውን ፋሺስታዊ የርጉም ዐቢይ አገዛዝ ካደኝ ሊል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ክህደት የሚፈጸመው እኮ አስቀድሞ በሚተማመኑ ወይም ባንፃራዊነት መልካም ግንኙነት በነበራቸው ወገኖች መካከል መሆን አለበት፡፡ ፋሺስታዊው የርጉም ዐቢይ አገዛዝ በዐምሐራ ሕዝብ ላይ በይፋ ጦርነት ከማወጁም በፊት ሆነ በኋላ የዐምሐራ ሕዝብ ዋና ጠላት ነው፡፡ በመሆኑም አምርረን የምንዋጋው ደመኛ ጠላት እንጂ የ‹ካደን ወገን› አይደለም፡፡ የ‹ኮሚቴው ሊቀመንበር› የተባልከው ‹ወንድም› በሁለት ልብ ማነከስህን አቁም፡፡ ኹለት እግር አለኝ ተብሎ ኹለት ዛፍ ላይ አይወጣም፡፡

ለዚህ ነው ለርጉም ዐቢይ በየጊዜው ሊያጭበረብርበትና የትግሉን አቅጣጫ ሊያስት፣ ጊዜ ሊያራዝም የሚችል ዕድል አንስጠው የምንለው፡፡

ወገን ዕርፍ ተይዞ ወደ ኋላ አይታረስምና ዐምሐራ ያለው ብቸኛ አማራጭ ወደ ፊት ወደ ምንይልክ ቤተ መንግሥት መጓዝ ብቻ ነው፡፡ 

ድል ለተገፋው ዐምሐራ! ድል ላገራችን ኢትዮጵያ!

Filed in: Amharic