>

አባት ሀገር አማራ፤ እንደገና? (ጋዜጠኛና ፋኖ ጌጥዬ ያለው - ከትግል ሜዳ)

አባት ሀገር አማራ፤ እንደገና?

ጋዜጠኛና ፋኖ ጌጥዬ ያለው

ከትግል ሜዳ

ኦነጋውያን እንደሚዘውሩት የኦሮሞ ብሔርተኝነት፣ ወያኔ እንደሚያሾረው የትግሬ ብሔርተኝነት ሁሉ የአማራን ብሔርተኝነትም የተገንጣይነት ቦርሳን ለማስነገት በፀሀይም፤ በጨረቃም እየተሠራ ይገኛል። ይህ የአማራ ታሪካዊ ጠላቶች ላለፉት 83 አመታት ከትውልድ ትውልድ የድርጅት ስም እየቀያየሩ የሚቀባበሉት ውጥን ነው። የክፋቱ ባለቤቶች ዋነኛ አላማ አማራን ትንሽ፣ ደካማ፣ ተንበርካኪ እና ቅኝ ተገዥ ማድረግ የነበረ ሲሆን የፋሽስት ጉልት ወራሽ ኦነጋውያን ደግሞ ትልሙን የዘር ፍጅት መስፈንጠሪያ አድርገውታል። ቃሉ ‘በመጨረሻም በስሜ ይመጣሉ’ እንዳለው በስማችን የሚጠሩ የደም ነጋዴዎችም ውጥኑን ለመቋጨት ሲውተረተሩ ይስተዋላል። “‘መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ’ ስለምን ተባለ! ኢትዮጵያ የራሷ ጉዳይ! መነሻችንም ሆነ መድረሻችን አማራ ነው” በማለት ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶች ጉዳዩን ሲያነሱት የእይታ አድማሳቸው ከታክሲ ፌርማታ ያለፈ አይመስልም።
ከመራይ ባሕር ዳር፣ ከቆቦ ወልድያ፣ ከማጀቴ ማጀቴ በሚለው የከተማ ትራንስፖርት ቀመር ያሰቡት ይመስላል። የአስተሳሰብ አድማሳቸው ከዚህ የሰፋ ነው ቢባል እንኳን ‘መነሻ ባሕር ዳር….መድረሻ አዲስ አበባ’ ከሚለው ሀገር አቋራጭ የአባይ ባስ የጉዞ አድማስ የራቀ አይደለም። ነገሩ ሀሰት ስለሆነ የወረሱትን ውጥን የሚያስፈፅምላቸው የመሰላቸውን አጀንዳ ማስረዳት አልቻሉም። ጉዳዩን ከስሩ እናፍታታው፦

#ታሪካዊ ዳራዎች

1888 ዓ.ም. ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር ባሕር ተሻግሮ ሲመጣ ሽንፈትን ከቶ አላሰበም። በጦር እቅዱ ውስጥ የነበረው ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ካሰፈሰፉ የአውሮፓ አቻዎቹ ላይ እንዴት ወታደራዊ የበላይነትን እንደሚጨብጥ ነበር። የፖለቲካ መኮንኖቹ ጭንቀት የሆነውም በተሻሚ አውሮፓውያን ላይ እንዴት የዲፕሎማሲ ድልን መቀዳጀት እንዳለባቸው ነው። ኢትዮጵያን እንዴት እናሸንፋት የሚለው እምብዛም ያሳሰባት አይመስልም። ምክንያቱም በወታደራዊ ስልጠናቸው እና በጦር መሳሪያ ሀብታቸው ተመክተዋል። ምኒልክ ሲመሰርቱ ዮሀንስን በማታለል፤ ዮሀንስ እንጃ ሲሉ መንገሻን በመደለል ባለቺን ገጀራ እንኳን በሕብረት እንደማንዋጋቸው ገምተዋል። ሆኖም ጦርነት ተለዋዋጭ ነውና የገመቱት ቀርቶ ፈፅሞ ያልጠረጠሩት ሆነ። እምዬ ምኒልክ መላው ሕዝባቸውን እንደ አንድ ሰው አድርገው በማስነሳት ከእነርሱ አልፎ ለነጭ ዘር ሁሉ የተረፈ ሽንፈትን አከናንበው መለሷቸው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የዓለም የፖለቲካ ሚዛን ተወዛወዘ። የነጭና የጥቁር ፖለቲካ ተናወጠ። (የአለም ጦርነት መባል የነበረበት የአድዋ ጦርነት ነበር) የጌታና ሎሌ ግንኙነት ሻከረ። የደራው የባርያ ንግድ እንደ ጉልት ገበያ ቀዘቀዘ። ጥቁሮች ብቻ ሳይሆኑ ማህበራዊ ዝቅታ ላይ የነበሩ ነጮችም ጭምር ቀን ወጣላቸው። ከቅኝ ተገዥ ነጮች መካከል አውስትራሊያ እና ቬኒዞላ በመሪዎቻቸው በኩል ለምኒልክ የላኩት ደብዳቤ ልዩ ነው። ስለ ድሉ የተሰማቸውን ደስታ እና አድናቆት ከገለፁ በኋላ የእምዬ ወታደር መሆን እንደሚፈልጉ ያስረዳሉ።
ከአመታት በኋላ ከፍ ብሎ የመጣው የእነ ማርከስ ጋርቬይ እና ዊልያም ቦኢዝ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻው አድዋ ነው። የእነማርቲን ሉተርኪንግ እንቅስቃሴ መሰረቱ ይህ ነው። 1888 ዓ.ም. ለሰው ልጆች ሁሉ የእኩልነት ችቦ የተለኮሰበት የነፃነት ብስራት ነው። ይህም ሰውን እንደ በግ በእጃቸው መዝነው ይሸጡና ይገዙ ለነበሩ የባርያ ከበርቴዎች አስቆጭ ሆነ።
ጣልያን ያለፈ ደሟን ለመመለስ ብቻ ሳይሆን ‘የአዋረድሽንን’ ወቀሴታ ለመመለስ ድፍን 40 ዓመታት ተዘጋጀች። ሰራዊቷን እስከ ጦረታ ዘመኑ አሰለጠነች። በ1928 ዓ.ም. ለዳግም ወረራ ወደ ኢትዮጵያ መጣች። በዚሕኛው ጦርነት በጠላትነት የፈረጀቺው መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ አይደለም። እንደውም አንዳዶችን እንደ አጋር ማሰብ ጀምራለች። በጠላትነት የፈረጀቻቸው እነኝህን ነበር፦

✓ 1. የአማራ ሕዝብ

✓ 2. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

✓ 3. የዘውድ ስርዓት

ሦስቱን ለማንበርከክ ከአርባ አመት በፊት እንዳደረገቺው በንቀት ሳይሆን በፍርሀት፤ እግሯ እንደመራት እያንፈራጠጠች ሳይሆን ተረከዟን አስቀድማ በቀስታ ለዱካዋም ተጠንቅቃ መጣች። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ያለፈው ውርደት እንዳይደገም ጠመንጃ ባርካ፣ ለወታደሮች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ምስል አስይዛ ላከች። በምድር የሚያንባርቀው ታንክ፣ ከሰማይ የእሳት ጉማጅ የሚያዘንበው የጦር አውሮፕላን አልበቃ ብሏት የመርዝ ጭስ ጭምር ታጠቀች። የታጠቀቺውን ሁሉ ተዋጊና ንፁሃን ሳትለይ በአማራ ሕዝብ ላይ አርከፈከፈቺው። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአንድ ጀንበር ብቻ 30 ሺህ ሰዎችን በመሀል አዲስ አበባ ጨፈጨፈች። እነ አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ፣ እነ አሞራው ውብነህ፣ እነ ራስ አበበ አረጋይ ፋሽስት ጣልያንን ለአምስት ዓመታት ለብልበው ወደ መጣበት መለሱት።
ከዚህ በኋላ ጣልያን ኢትዮጵያን በጦርነት ማሸነፍ እንደማትችል ተረድታለች። መፍትሔው በኢትዮጵያውያን መካከል ጠንክሮ የመለያየት ፖለቲካን መዝራት እንደሆነ ደመደመች። በዚህም አማራው በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጠላትነት እንዲታይና አንዱ በብዙዎች ተለይቶ እንዲጠቃ የሚያስችሉ መሰረቶችን ጣለች። የጥላቻ ፅሁፎች የሰፈረባቸው በራሪ ወረቀቶችን በአውሮፕላን ጭምር አስቀድማ በትናለች። የዓመታት ልፋቷ በ1950ዎቹ ገደማ ፍሬ ማፍራት ጀመረ። ያ ርካሽ ትውልድ መጣ። በወቅቱ ሞገደኛው ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ ጥቁር ጣልያኖች ይላቸው የነበሩት ውርጋጥ ተማሪዎች ፓስታ ብቻ ሳይሆን እንደ ቋራ ፍየል ቅጠል ጭምር እየበሉ መጡ። ሞሶሎኒ ዋለልኝ መኮንን እንደ ሮቦት ገጣጥሞ ሰራ። ፀረ አማራ ትርክቶች ከፍ ብለው መቀንቀናቸውን ቀጠሉ። ንፅህትና ቅድስት ቤተክርስቲያን የአላዋቂነት፣ የኋላቀርነት መገለጫ ብሎም የመናጢ ድህነት ምንጭ ተደርጋ በሀሰት ተወነጀለች። ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በይፋ በወታደር ከስክስ ጫማ መረገጥ ጀመረች። በተመሳሳይ እንግሊዛውያን ዛሬም ድረስ ጠብቀው በፖለቲካቸው ውስጥ ያዘለቁት የዘውድ ስርዓት ለኢትዮጵያ ሲሆን የኋላ ቀርነት መገለጫ ተደርጎ ተራከሰ። ዘውድ ቀርቶ አፍንጫው ሰልከክ ያለ መልከ መልካም ሰው ሁሉ የንጉሳውያኑን ቤተሰብ፤ የዘውዱን ወራሾች ይመስላል ተብሎ በኢሰፓ ፖለቲካ ውስጥ ዝር እንዳይል ተደረገ። መንግሥቱ ኃይለማርያም በሃሳብ ብቻ ሳይሆን አይን፣ አፍንጫ፣ ከንፈር እየቆጠረ በመልክም ጭምር የሚመሳሰሉትን ብቻ በዙሪያው ሰበሰበ። ሰበብ ተፈልጎላቸው በመልካቸው ብቻ የተረሸኑትንም ታሪክ ይቁጠራቸው።
ጥቁር ጣልያናውያን በፖለቲካ ፓርቲነት በተለያየ አንጃ መደራጀት በጀመሩ ጊዜም ሦስቱን፥ በተለይም አማራን ነጥሎ ማጥቃት የፖለቲካቸው ሀ፣ ሁ አደረጉት። ለአንድ ኦሮሞ የኦነግ አባል ለመሆን ዋነኛው መስፈርት ‘አማራን ምን ያህል ይጠላል?’ የሚለው ነው። ኦነግ እና ወያኔ ተቀናጅተው እምዬ ምኒልክ ቤተመንግሥት በገቡ ሰሞን የአባት ሀገር አማራ ውጥን ዳዴ ማለት ጀመረ። በርግጥ ሁለቱ አንጃዎች ለጎሪጥ የሚተያዩ በመሆናቸው ኦነግ እንደ አሮጌ ቁና ተወርውሮ በምትኩ ኦሕዴድ ተሰፋ። ኦሮሞን ይዞ የመገንጠል ተልዕኮም ተሰጠው። ወያኔ ትግራይን ይዞ ለመሸግለል ድብሉን ሸክፏል። መገነጣጠሉን እና ኢትዮጵያን ማፍረሱን ሕጋዊ ለማድረግ አንቀፅ 39 ተሰናድቷል። ሆኖም ወያኔ መቀሌን ሚስቱ፤ አዲስ አበባን እቁባቱ አድርጎ የአራት ኪሎን ክሽን ሲያጣጥም ለወራት ያቀደው 27 ዓመታት አለፈበት።
ከአንቀፅ 39 እኩል የተዘጋጀው ኦሮሞና ትግሬ ሲገነጣጠሉ ከቀሪ ኢትዮጵያውያን ጋር አማራ ገናና ሆኖ እንዳይቀጥል እርሱንም የሚገነጥል ድርጅት መፍጠር ነበር። ለዚህም ሻቢያ ከማረካቸው የደርግ ወታደሮች አሰባስቦ ኦሕዴድ-ን የፈጠረው ወያኔ፥ አማራ ባይሆኑም ኢሕአፓ በወቅቱ በአማራው በኩል የነበረውን ስሁት ቅቡልነት ከግምት በማስገባት ይመስላል፤ ከኢሕአፓ አፈንግጠው የወጡ ግለሰቦችን አሰባስቦ ኢሕዴን-ብአዴን-ን መሰረተ። ብአዴን አባት ሀገር አማራን ሲያቆም የእስራኤል አባት ዳዊት ቬንጎሪዮን በጽዮን ከተማ እንዳውለበለቡት የሕይዎት ዋስትና፣ የነፃነት፣ የሀገር ባለቤትነት ሰንደቅ አላማ በባሕር ዳር የዘር ፍጅት፣ የባርነት፣ የሀገር አልባነት አርማን ለማውለብለብ ተሰናድቷል። የዳዊት ኮከብን እንዳነገበው እና የጽዮናውያንን የሁለት ሺህ አመታት እንባ እንዳበሰው የዚያች ሀገር ሰንደቅ አላማ ሁሉ የአንድ ቢጫ ጨርቅ ያህል እንኳን ከአማራ ሕዝብ ጋር ትውውቅ የሌለው አርማ ሰንደቅ ተብሎ ተዘጋጀለት። ብሔራዊ መዝሙር፣ ሀገራዊ ካርታ ሁሉ ተሰናዳለት። ሆኖም ይህን ሁሉ የአማራ ሕዝብ ወረወረበት። ወያኔ በ27 ዓመታት የቤተ መንግሥት ቆይታው በወረቀት ላይ ያስቀመጠውን አባት ሀገር አማራ፤ በአማራ ሕዝብ ልብ ውስጥ ማስቀመጥ አልቻለም። ሀገር ያለሕዝብ ማይቆም ሆኖበት ተቸገረ።
በግዳጅ ለመሞከርም ሁኔታው አልፈቀደም እንጂ፤ የክፋት ርዕዩ አሁንም ከተወራራሽ ጠላቶቻችን ጠረንጴዛ አልወረደም። ወያኔ ከአራት ኪሎ ክሽን ጋር ተጣብቆ የመቀሌ ጉዞውን በማዘግየቱ የአባት ሀገር አማራ ፕሮጀክትም አብሮ ዘገየ እንጂ ፈፅሞ አልተረሳም። ተረኞች በውርስ ይዘውታል። ከብአዴን ፍርሰት በኋላም በስማችን ለሚጠሩ የደም ነጋዴዎች አቀብለዋቸዋል። ዘንድሮም አማራን ወደ ተገንጣይ ብሄርተኝነት ለማስገባት ተከታታይ ክፉ ሥራዎች እንደቀጠሉ ናቸው።
ኦሕዴድ እና ብአዴን ወያኔ ያወጣላቸውን ስም ቀይረው፤ ወያኔንም ወደ መቀሌ አባረው በፍቅር መተሻሸት በጀመሩበት ሰሞን በማህበራዊ ሚዲያ ባሰማሯቸው ባለሁለት ማንነት ሰዎቻቸው በኩል የአባት ሀገር አማራን አጀንዳ እንደ አዲስ መዘውት ነበር። እንዳውም ለእውነተኛ የአማራ ብሔርተኞች ሊያቀብሉን ሞክረዋል።
ዛሬም የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ወደ ትጥቅ እንቅስቃሴ ተለውጦ የአራት ኪሎ ርምጃውን በዲሽቃና በመትረጊስ እየከነዳ ባለበት ጊዜ አጀንዳው እንደገና ተመዟል። አማራን ወያኔ በአጠረለት በረት ውስጥ ለማስገባት እየተሞከረ ይገኛል። በስማችን የሚጠሩ የደም ነጋዴዎች ከብአዴን ፍርስራሽ ያነሱትን የተገንጣይነት ፖለቲካ በስውር ለማስረፅ ‘ኢትዮጵያ ሚባል ቃል እንዳንሰማ’ ብለዋል። እነኝሁ ሰዎች ከመቀመጫቸው ሳይነሱ ‘አማራ ሀገር መስራች ነው’ ይሉናል። የትኛዋን ሀገር ቢባሉ መቼም ‘ኢትዮጵያን’ ማለታቸው አይቀርም። ‘ታዲያ የመሰረታት ሀገሩን ለማን ይሰጣል?’ ሲባሉ ምን እንደሚመልሱ እንጃ። የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ከማለት በቀር ምን ይባላል! ‘አዲስ አበባ የማን ናት?’ የሚለው ጥያቄ በአንድ ወቅት የፖለቲካ መተርጉማን አርዕስት እንደነበር አስታውሳለሁ። ዛሬም ፖለቲካ የሚያጣጥለው፤ ታሪክ የሚያከብረው ተመሳሳይ ጥያቄ ላንሳ፦

#ኢትዮጵያ የማን ናት?

የአማራ አፅመ ርስቶች ወልቃይት፣ ራያ፣ ደራ እና መተከል ብቻ አይደሉም። አዲስ አበባ፣ አሰበ ተፈሪ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት፣ ሽንብራኩሬ፣ አሰላ እና ጎሬ ብቻም አይደሉም። መላ ኢትዮጵያ የአማራ አፅመ ርስት ነች። በሕይዎት የመኖር መብታችንን ከማረጋገጥ በዘለለ የምንታገለው ይህቺን ኢትዮጵያ ለመረከብና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር ለመኖር ነው። አፅመ ርስታችን በሆነቺው ኢትዮጵያ ከቁጥራችን ተመጣጣኝ የሆነ ከሌሎች እኩል የፖለቲካ ውክልና እንዲኖረን፣ ተስተካካይ የምጣኔ ኃብት ተጠቃሚ እንድንሆን ብሎም ከሌሎች ነባር ኢትዮጵያውያን ጋር በፈጠርናት ሀገራችን ማህበራዊ መገለል እንዳይፈፀምብን ለማድረግ ነው። ‘መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ’ ስንልም በዚህ አድማስ ልክ ነው። ጥንታዊ አባቶቻችን እነ ንጉሥ ኢትዮጲስም ሆኑ እነ ዮቶር መነሻቸው አማራ ነበር። አድማሳቸውም ኢትዮጵያ ነበረች፤ ያውም እንደ ዛሬው እግሮቿን ኮርኩማ፣ እጆቿን በደረቷ ላይ አመሳቅላ፣ አንገቷን አቀርቅራ የተቀመጠች ኢትዮጵያ ሳትሆን አንገቷ ገንቦ የመሰለ፣ እጆቿ እንደ ዋንዛ አውራጅ የተንጠራሩ ዘለግ ያለች ነበረች።
ዘመናዊ ታሪክ አበጥሮ የሚያውቃቸው አባታችን እምዬ ምኒልክ መነሻቸው አማራ መድረሻቸው ኢትዮጵያ ነበረች። አማሮቹ ንጉስ ምኒልክ እና ንጉስ ተክለሀይማኖት ግባቸው ኢትዮጵያ ላይ ለመድረስ ብዙ ተባብረዋል።
ከ70 ዓመታት በላይ በዘለቀው የመሳፍንት ዘመን መይሳው ከሣን ከወንድማቸው ደጃዝማች ክንፉ ኃይሉ፣ ከጌታቸው ደጃች ጎሹ፣ ከአብሮ አደግ ባልንጀራቸው ደጃች ብሩ ጎሹ፣ ከአማታቸው ራስ አሊ፣ ከእቴጌ መነንም ሆነ ከደጃች ውቤ የሚለያቸው ‘መነሻየ ሰሜን መድረሻየ ኢትዮጵያ’ ማለታቸው ነው። መሳፍንቱ በጠቅላላ መነሻቸውም መድረሻቸውም ሰሜን ኢትዮጵያ ነበረች። በዚህም መይሳው ባይደርሱ ኖሮ ሀገራችንን ለውጭ ወራሪ አሳልፈው ከመስጠት አይድኑም ነበር። ዛሬም እንደትናንቱ ቴዎድሮሳውያንን የመውጋት አዙሪት ቀጥሏል። ገድሎ ብቻ ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ሞቶም ማሸነፍን ከቴዲ መማር ይገባል!
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ የአማራ አፅመ ርስት ነች የምንልባቸው ከሀገር ብሎም ሀገረ መንግሥት ምስረታ ጋር የተያያዙ በርካታ ማሳያዎች አሉ። እናት ኢትዮጵያ በአማራ ቤት ተወልዳ ያደገች በመሆኗ የምትለብሰው የአማራን ሸማ ነው። የምትበላው የአማራን እንጀራ በወጥ ነው። የምትጠጣው የአማራን ጠላ ነው። የምትናገረው የአማራን ቋንቋ ነው። የምትዘፍነው የአማራን እስክስታ ነው። የምታለቅሰው የአማራን ለቅሶ ነው። የምታመልከው የአማራን ሃይማኖት ነው። እናት ኢትዮጵያ ራሷ መነሻዋ አማራ ነው፤ ብሄሯም ያው አማራ ነው። መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ የምንለው ለዚህ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና አጠቃላይ ማንነት የማዳበር መብታቸው ጥቡቅ ነው።
አማራና ኢትዮጵያ አንድም፤ ሁለትም ናቸው ስንል ሌላውን ብሄር በዓድ የሚያደርጉ አይደሉም። አማራው አማራነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያዊ እንደሆነው ሁሉ፤ አፋሩም፣ ጉራጌውም፣ ጋምቤላውም ከእነ መነሻ ማንነቱ ኢትዮጵያዊነቱን አልተነጠቀም። አይነጠቅምም!
ጉዳዩን የበለጠ ለማንፀር ዘመነኛውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ህልዮት መዳሰስ ተገቢ ነው። ከትግል አድማስ አንፃር ፖለቲካችን ሦስት ፈርጆች አሉት። እነርሱም ብሄርተኝነቶች ናቸው።

#ሦስቱ ብሄርተኝነቶች

ሦስቱ የብሄርተኝነት አድማሶች እነኝህ ናቸው፦
1. የኢትዮጵያ ሀገራዊ ብሄርተኝነት
2. ተገንጣይ የጎሳ ብሄርተኝነት
3. የአማራ ብሄርተኝነት
‘መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ’ ስንል ጉዳዩን ከዜግነት ፖለቲካ ጋር የሚያዛምዱት በርካቶች ናቸው። ስህተት ነው። ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ብሄርተኝነት ነጥለው ለመረዳት ሲቸገሩም ይስተዋላል። ሆኖም ሁለቱን የሚለያቸው ግልፅ ወሰን አለ።
በአሁኑ አውድ የዜግነት ፖለቲካ ከሕዝብ ፍላጎትና ችግሮች በታች ነው እየሠራ ያለው። ይህ ደግሞ ከአቅም ማነስ ሳይሆን ከርዕዮት የመነጨ ነው። ትለብሰው የሌላት ትከናነበው አማራት እንዲሉ ዜጎች በሕይዎት ለመኖር ተከልክለው እርሱን የሚያስጨንቀው የከተሞች የመንገድ መጣበብ ነው። በመሆኑም ነገሩ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው። የአማራው ባድማ ተቆርሶ ለትግሬ ቢሰጥ ለዜግነት ፖለቲካ ጉዳዩ አይደለም። ምክንያቱም መሬቱ ከኢትዮጵያ አልወጣም። ይህ ፖለቲካ መነሻውም መድረሻውም ኢትዮጵያ ነች። በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው መንግሥት መር የዘር ፍጅት እንኳን ከአማራ እንዲነሳ አላስገደደውም። የዘር ፍጅቱንም ቢሆን የዜጎች የእርስ በእርስ ግጭት አድርጎ ነው የሚመለከተው። አማራ ከሌሎች ተነጥሎ በጅምላ መጨፍጨፉን አይቶ፤ አልተመለከተም። ስለዚህ ‘ኢትዮጵያኒስት’ ሃይሉ በአማራ ጉዳይ ጭፍን ነው። አናውጤንም ሆነ ዘሪቱን በኢትዮጵያዊነታቸው እንጂ በአማራነታቸው አያውቃቸውም። ከአማራ ብሄርነኝነት ጋር ከሚለዩት ወሰኖች መካከል አንዱ ይህ ነው። ከዚህ በዘለለ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች እንደ ተገንጣይ ብሄርተኞች በይፋ በማኒፌስቶ ባይሆንም በስውር አማራን በጠላትነት መፈረጃቸው የሚታበል አይደለም። ለአብነትም የቀድሞው ግንቦት 7፣ ኢዜማ እና የሕይዎት ዘመን የፖለቲካ ኪሳራ ተምሳሌቱ ኢሕአፓ ይጠቀሳሉ።
በአንፃሩ የአማራ ብሄርተኝነት መነሻው በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው የዘር ፍጅት ነው። መዳረሻ ግቡ ደግሞ የኢትዮጵያ የግዛት ኢ ተነጣጣይነትና አንድነት ነው። አማራ በፈጠራት ሀገሩ በሕይዎት የመኖር መብቱ እንዲጠበቅ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳው ነው። ይህ ከፖለቲካም በዘለለ የነፍስ አድን ተግባር ነው። ፋኖ እያደረገ ያለውም ይህንኑ ነው። በሕይዎት የመኖር መብታችንን ካረጋገጥን በኋላ መኖር ብቻውን በቂ አይደለም። መኖርማ ጠባቂ ሕግ ተደንግጎላቸው፣ መንግሥታት የሚጠብቁት ነፃ አውጭ ድርጅት ተቋቁሞላቸው እንስሳትም በጫካ እየኖሩ ነው።
ከመኖር በዘለለ መኖሪያ ሀገርም ያስፈልገናል። ስለዚህ ጀግኖች አባቶቻችን በአፅሞቻቸው ያጠሯትን፣ በደማቸው ካፊያ ያለሟትን፣ በመስዋዕትነት ያፀኗትን ሀገራችን ኢትዮጵያን ሳትሸራረፍ መጠበቅ አለብን። የአድዋ ተራራ ድንጋዮች ቢፈነቀሉ ከስራቸው ከብዙ አጎቶቼ ቢያንስ የአንዱ አፅም አለ። ካራማራ ቢታሰሰ ከታላላቅ ወንድሞቼ የአንዱ ደም የፈሰሰበት ቀይ ቀለሙ አልጠፋም። ከአፄ አንበሳ ውድም እስከ መይሳው ካሣ፣ ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ ፊታውራሪ ገብርዬ ቤተዘመድ ቢቆጠር ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ በመላ ኢትዮጵያ አማራ ወድቆበታል። ኢትዮጵያ ከገበያ የተገዛችልን የገና ስጦታ አይደለቺም። ጀግኖች ሙተው የሰጡን ነች። አማራ ይህቺን ሀገር ሙቶ የመጠበቅ ግዴታ አለበት የትውልድ አደራ ነውና። መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ የምንለው ለዚህ ነው።
ሌላው ተገንጣይ የጎሳ ብሄርተኝነት ነው።
ይህ መነሻውም መድረሻውም የራሱ ጎሳ ነው። ግቡም ሽራፊ መንደር ፈጥሮ ሀገር ማፍረስ ነው። ኢትዮጵያን አፍርሶ ትግራይን መገንባት፣ ኢትዮጵያን አፍርሶ ኦሮሚያን መገንባት ነው የትግል ዘመን ዕቅዱ። ከላይ ከጠቀስናቸው ሁለቱ ብሄርተኝነቶች ፍፁም የተለየ ነው። የአማራ ብሄርተኝነት ወደዚህ ጎራ እንዲገባ ጠላት ከፊት ይስባል፣ ከኋላም ይገፋል። በስማችን የሚጠሩ የደም ነጋዴዎችም ጋሪ ሆነውታል።
በአጠቃላይ የአማራ ብሄርተኝነት በአማራ መዳን ውስጥ ኢትዮጵያን የመሰብሰብ አላማን ያነገበ ሲሆን የተገንጣዮች ብሄርተኝነት ደግሞ ኢትዮጵያን መበተንን አላማው አድርጓል። የዜግነት ብሄርተኝነቱ በበኩሉ ኢትዮጵያን መሰብሰብ ላይ ባይታማም አማራ በሀገር እና ሀገረ መንግሥት ምስረታ ላይ የተጫወተውን ታሪካዊ ሚና ይክዳል። እንደ ፖለቲካ ሁሉ ታሪክንም አመቻምቾ ራሱ ለመወሰን ይዳዳዋል። የታሪክ ፍርድ ይግባኝ እንደሌለው አልተረዳም። ከሁሉም የከፋው የአማራን ጅምላ መጨፍጨፍ ሸምጥጦ መካዱ ነው። አማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ ራሱን እንዲከላከል አለመፍቀዱ ነው።

#መቋጫ

በአጠቃላይ ፀረ አማራ ትርክቶች ከአድዋ ድል ማግስት ጀምሮ የተፀነሱ ቢሆንም ጉልበት ያገኙት ከ1950ዎቹ ወዲህ ነው። ባለፉት 50 ዓመታት ደግሞ ቀጥተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ተያይዘውታል። ይህንን ጉዳት ለመቀልበስ በተለያዩ ጊዜያት ትግሎች ተደርገዋል። የአማራ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ እያደገ ያለው ትግል ግን ከ1966 ዓ.ም. ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት የተመዘገበበት ነው። በአማራ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የሽምቅ ውጊያ ታሪክ እንዲህ ያለ ስኬት ታይቶ ለመታወቁ እንጃ። ይህንን ስኬት ለመቀልበስ ሲባል በፋኖ ውስጥ የጠላት ወኪሎች ተሰግስገዋል።
አየለ ጫሚሶ በቅንጅት ውስጥ የተጫወተውን ሚና በፋኖ ውስጥ የሚጫወቱ አሉ። የፋኖን ወታደራዊ ንቅናቄ እንደ አብን ለማድረግ እየተሠራ ነው። ይህን እየሠሩ ያሉት ደግሞ እንደ በለጠ ሞላ የትግሉ መሪነት ላይ ፊጥ ለማለት ቋምጠዋል። ይህን የሚያደናቅፍ የመሰላቸውን ሁሉ ሰበብ እየፈለጉ፤ ሐሰት እየፈበረኩ ያጠቃሉ። የአባት ሀገር አማራ ውጥንም ተደብቆ የመጣው ለዚህ ነው።
ሆኖም ይህ ሁሉ መውተርተር ትግሉን አንድ ደረጃ ወደ ኋላ ይጎትተው ካልሆነ በቀር ፈፅሞ አያስቆመውም።

አማራ ያሸንፋል!

Filed in: Amharic