>
8:52 pm - Tuesday January 31, 2023

የአንድነት እና መኢአድ ነገር ቀላል አስቆዘመኝ እንዴ... (ቁጭት እንደወረደ!) [ኣቤ ቶክቻው]

በተለይ አንደነት ፓርቲ በበኩሌ ቀልቤን የሳበው ሲመሰረት ጀምሮ ነበር። ”የቅንጅት ህጋዊ እና ሞራላዊ ወራሾች ነን!” የምትለው ንግግር ዋዛ አልነበረችም።

በብዙነታችን ውስጥ አንድነት የሚለው ሃሳብ ለሀገሬ መልካሙ መንገድ ነው ብዬ ስለማስብ ይሁን፣ የብርቱካን ሚዴቅሳ እና ፕሮፌሰር መስፍን ፖለቲካዊ ስብዕና ደስ ስለሚለኝ ይሁን፣ እነ አርአያን የመሳሰሉ ወዳጆቼ በዙሪያው ስለነበሩ ይሁን ብቻ በቅጡ ባለየሁት ሁኔታ በልቤ አንድነት ፓርቲ ክፉ ባይነካው ብዬ ስጸልይለት ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ሊቀ መንበሯ ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ፤ ”በልቧ እና በውጪ ሀገር ለመፈታት ብለን በህግ አግባብ የጠየቅነው ይቅርታ የለም” ብላለች እና ሊዚህ አባባሏ ይቅርታ ትጠይቀን ብላ ኢህአዴግ ጠየቀች። ወቅቱም አንድነት የት ይደረስ ይሆን… የተባለለት ጊዜ ነበር… ሊቀመንበሯም ”ተበድዬስ ይቅርታ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ!” ብላ በቃሌ ጽሁፏ ቃሏን ደገመቸው! በዛ የተነሳም ታሰረች። የእርሷ መታሰር አንድነትን ያደበዝዛዋል እያልን ስንሰጋ ለነበረን ሰዎች አንደነቶች ጠንክረው ቀጥለው

ትንሽ ቆይቶ ደግሞ እነ ፕሮፍ እና ሌሎች የአንድነት ወጣቶች ”መርህ ይከበር” ብለው ሙግት ሲጀመሩ ኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ”ድብድቡ ተጀመረ” ብሎ ተሯሩጦ ካሜራውን ይዞ አንድነትን ለማኮሰስ በርካታ የቴሌቪዥን ዜናዎችን እና ዶክመንተሪዎችን ሰራ… እኔ እና ሌሎች አንድነትን ክፉ አይነካው ብለን የጸለይን ከአንደነቶች ሙግት ይለቅ የኢቲቺ ዘገባ አስደነቀን! እነ ህውሀት ቃ…ቃ….ቃ…..ቃ ብለው ሲሰነጠቁ ስባሪ ዜና እንኳ ያልነገረን ዜና አቅራቢ ድረጀት የአንድነቶችን መርህ ይከበር ሰበር ዜና በሰበር ዜና አድርጎ ማቅረቡ አስደመመን!

በአንድነት ፓርቲ ውስጥ መርህ ተጥሷል ያሉ አባሎች እና ደጋፊዎች የራሳቸውን መንገድ ሲይዙ አንድነት ደግሞ የራሱን መንገድ ይዞ ቀጠለ። አለቀለት ያልነው ፓርቲም እነ ስዬ እና ዶክተር ነጋሶን የመሰሉ በፖለቲካው ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች በውስጡ ሲያካትት ደግሞ ሌላ ተስፋ ሰነቅን… የምርጫ ሁለት ሺህ ሁለት ጊዜ አንደነት ከመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር ግንባር በመፍጠር ኢህአዴግን ገጠመ!

በወቅቱ የብርቱካን መታሰር የመርህ ይከበር አይከበር ሙግት እና ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በምርጫው እለት የሰሩት ”ፋዎል!” እና የኢአዴግ የተለመደ ማጭበርበር ተደማምረው የሁለት ሺህ ሁለት ምርጫ ላይ ቢያንስ ፓርላማውን ገብስማ ይሆናል ብለን ለገመትን ሰዎች ተስፋችን ወሃ በላው።

ከዛ በኋላ የሰላማዊ ትግል ተስፋችን በቀጣዩ ምርጫ ላይ ነበር…

አሁን የዛሬ አምስት አመት ይመጣል ብለን ተስፋ የሰነቅንለት ምርጫ ሁለት ሺህ ሰባት ልክ ሲመጣ ምርጫ ቦርድ እና ኢህአዴግ ተባብረው ተስፋ የሚጣልባቸውን ፓርቲዎች በታላቅ ቅናሽ ቸበቸቧቸው! መኢአድ እና አንድነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሏቸው አባላት ቀላል አልነበሩም…! ከእለት እለትም እያደረጉ የነበሩት እንቅስቃሴም እደግመዋለሁ በተለይ አንደነት ካይን ያውጣህ የሚያስብል አይነት ነበር። ታድያ እንዲህ አይነት ፓርቲ ሲኖር ድንኳን ሰባሪዋ ኢህአዴግ አብዳለች እንዴ! የዚህ አይነት ፓርቲማ ድንኳኑ ብቻ ሳይሆን ቅስሙም አከርካሪውም መሰበር አለበት ብላ ባለ በሌለ ሃይሏ እነሆ ቀሽ! አድርጋ ሰበረቸው! እነ አቶ አንዷለም አራጌን ብታሰር፣ እነ ሃብታሙም ብተጨምር… ፓርቲው ሌሎችንም በየጊዜው ብታግዝ አልከስም ሲላት ጠቅላላ ፓርቲውን ለአቶ ትግስቱ አሸከመቻቸው!

እንደኔ ሃሳብ አሁን በሰላማዊው ትግል መስመር አሁን የቀረን መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ ነው። መድረክ ከሆነ ጊዜ በኋላ አይናፋር ሆኖብኛል። ሰማያዊዎች ከተመሰረቱ አጭር ጊዜ ነው ያላቸው በሚል ልምድ ያንሳቸው ይሆን እያልኩ ፈራላቸዋለሁ… እርሱም ብቻ ሳይሆን ነገም ሆነ ዛሬ ኢህአዴግ መድረክንም ሆነ ሰማያዊን ከምርጫ ምህዳሩ ገፍትራ እንደማታስወታቸው ምንም ዋስትና የለም። ለርሷ እንደሆነ ሁላችንም በእርሳስ ነው የተጻፍነው እና ልታጠፋን ላጲሷን ማሾሏ አይቀርም!

ይሄን ሁሉ ቁጭ ብዬ ሳስብ እጅጉን ቆዘምኩ… እንግዲህ ተስፋዬ ማነው… ?

ጦሽ ዶሽ አይደለምን!!! እልና ደግሞ ሳስበው… ሌላ ሌላ ሌላ መላ…. ሌላ ሌላ ተስፋ… ከወዴት አለ… እያልኩ እታራለሁ… እስቲ ተስፋ አዋጡ እስቲ መላ አምጡ!!!

ምን ይበጀን! ወይስ ዝምምምም ብላ ትፈጀን!?

Filed in: Amharic