በእነ በላይ ፍቃዱ አመራርነት አንድነት ፓርቲን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲመሩ የነበሩ አመራሮች ዛሬ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከቀድሞ ፓርቲያቸው አንድነት ጋር የፕሮግራምም ሆነ የስትራቴጂ ተመሳሳይነት ወዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግላቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
መግለጫውን የ‹ቀድሞው አንድነት ፓርቲ› አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ፣ ምክትል አፈ ጉባዔው አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ እንዲሁም የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ሌሎችን በመወከል ሰጥተዋል፡፡
‹‹የምናምነው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ ይህን ሰላማዊ ትግል ለመምራት ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ብቁ ነው ብለን በማመን ፓርቲውን ተቀላቅለናል›› ብለዋል በመግለጫው ላይ የተወከሉት አዲሶቹ የሰማያዊ አባላት፡፡
በዚህ መሰረትም በርከት ያሉ አመራሮችና አባላት በይፋ የሰማያዊ ፓርቲ የአባልነት ፎርም ሞልተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ወደ ሰማያዊ ቢሮ ባቀኑበት ወቅት ፖሊስ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ድረስ በመግባት ‹‹በሰማያዊ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት እንዳሉ ሰለሰማን ነው›› በሚል ለፓርቲው አመራሮች ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡