ዕድል ፣ ድል እና ገድል እንደ ወንጀል
- ሶስተኛ ክፍል እያለሁ አንድ ቀን የእንግሊዘኛ መምህራችን ከመማሪያ መፅሃፋችን ላይ አንድ ጥያቄ ጠየቀን ። “The donkey has big ears” (ጥያቄው ምስልና ፅሁፍ / Picture and text አለው) ማለት ትርጉሙ ምንድነው? የሚል ነበር።
በምስሉ ላይ አንድ አህያ ጎንበስ ብላ ሳር ስትግጥ ይታያል።
ጥያቄውን ለመመለስ እጅ በማውጣት የክፍል አለቃችንን የቀደመው የለም። የክፍል አለቃችን ዘግይቶ ትምህርት ቤት ስለገባ ከሁላችንም በጣም ትልቅ ነበር። መምህሩም ለአለቃችን እድሉን ሰጠው።
አለቃችንም “አህያዋ ሳር ትበላለች” ብሎ ጮክ ብሎ በኩራት መለሰ። በወቅቱ ሳቃችንን መቆጣጠር ያቃተን ልጆች መገረፋችን ትዝ ይለኛል። በእርግጥ መሳቅ አልነበረብንም ግን ያው ልጆች ስለነበርን ይህን ማድረግ አልቻልንም።
ይህን ጉዳይ ያስታወሰኝ የዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ጋር ለመወያየት አራት ታላላቅ አለም ዓቀፍ ድርጅቶች ( ኢጋድ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ ተወካዮች) ፋኖ የሚገኝበት ድረስ ሄዱ የሚለውን ዜና የማህበራዊ ሚዲያ ግሪሳ የተረዳበት መንገድ ነው።
በርካታ ውግዘቶች በእስክንድር ነጋ እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ላይ ሲሰነዘሩ አይቸ ተገረምኩ። ጉዳዩን ሶስተኛ ክፍል እንደነበረው አለቃችን ሲተረጉሙት ስላየሁ እንዲሳቅባቸው ሳይሆን እውነታውን እንዲገነዘቡ ስለፈለኩ ይህን ፅሁፍ ለማጋራት ወደድኩ።
እርግጥ ነው “እስክንድር ተደራደረ” በሚል ጉዳዩን ለተራ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማዋል የተንቀሳቀሱና ” የዐማራ ህዝብ ተከዳ” የሚል narrative ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆችና ተከፋይ የስርዓቱ ቀለብተኞች ከፍተኛ የማደናገር ስራ ሰርተዋል።
በመጀመሪያ የዐማራ ህዝብ የህልውና ትግል ከምንም ተነስቶ ዛሬ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ ትግሉ አሁን ላይ የደረሰበትን ከፍታ ያሳያል። ትናንት ያልተሰሙ በርካታ ጩኽቶች፣ ሰላማዊ ሰልፎች በሀገርቤትና በውጭ በአሜሪካ በነጩ ቤተመንግስት፣ በአውሮፓ የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማትና በተለያዩ ሀገራት ኤምበሲዎች ፊትለፊት ተደርገዋል። ነገር ግን እዚህ ግባ የሚባል ተፅዕኖ መፍጠር ፣ የዐማራን ህዝብ ከረሃብ፣ ከመፈናቀል፣ ከስደት እና ግድያ ማዳን ግን አልተቻለም።
የዐማራ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ነፍጥ አንግበው፣ ነፃነት በነፃ አይገኝም በለው ለዐማራ ህዝብ አንድ ህይወታቸውን ለመስጠት ጫካ ሲገቡ ግን ታሪክ ተቀየረ። በተለይ ትግሉን ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ፓለቲከኞች፣ የስርዓቱ አገልጋይ የነበሩ ካድሬዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የዐማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ አባላት እና የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ቆርጠው መቀላቀላቸው የትግሉን ገፅታ እና ከፍታ አንድ ደረጃ እንዲያድግ አድርጎታል።
ከዚህም ባሻገር ተበትኖ የነበረው የዐማራ ፋኖ ትግል ከባህላዊ አደረጃጀት ወጥቶ በአጭር ጊዜ በሻለቃ፣ በብርጌድ፣ በክፍለጦር፣ በእዝ ፣ በኮር እና በድርጅት ከፍ ብሎ መምጣቱ የዐማራ ህዝብ የህልውና ትግል እየተጠናከረ እና መልክ እየያዘ ፣ እየሰፋ እና እየተስፋፋ መምጣቱ አለማቀፉ ማህበረሰብ ሳይወድ በግድ እውቅና እንዲሰጥ አስገድዶታል።
ይህ ደረጃ ለዐማራ ህዝብ እና መስዋእትነት እየከፈሉ ላሉ የዐማራ ፋኖ ታጋዮች እና አመራሮች የምስራች እና በዐማራ ህዝብ ልጆች የከበረ መስዋዕትነት የተገኘ ሊዘከር የሚገባው ታላቅ ድል ነው!
የዐማራ ህዝብ ጠላቶች፣ ወዶገብ እና ስርዓቱ ከፍሎ ያሰማራቸው ተከፋይ የማህበራዊ ሚዲያ ግሪሳዎች፣ እንዲሁም ምንደኛ የስርዓቱ ሚዲያዎች ይህንን ገድል ለማንኳሰስ ፣ ይህንን ድል ለማሳነስ የሄዱበት ርቀት እና ያሳዩት ከፍተኛ ርብርብ በጣም በጣም ይገርማል።
እነዚህ ሃይሎች ለዐማራ ህዝብ ካላቸው ጥላቻ ባሻገር የዐማራን ህዝብ ንቃተ ህሊና የሚገነዘቡበት መንገድ ሁል ጊዜ ይገርመኛል።
ለመሆኑ በዐለማችን ላይ አሉ የሚባሉ እነዚህ አራት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የዐማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ጋር ለመወያየት እዛው የዐማራ ፋኖ ያለበት ቦታ ድረስ በ እግር በፈረስ አፈላልገው፣ አድራሻ ጠይቀው ሄዱ ማለት ትርጉሙ ምንድነው?
በትንሹ አራት ዓበይት ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል።
1ኛ. ለዐማራ ህዝብ የህልውና ትግል እውቅና ሰጥተዋል! Congratulations!
2ኛ. በስርዓቱ በዐማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስ እንዲሁም ስርዓቱ ባሰማራቸው የስርዓቱ ወንበር ጠባቂ ሰራዊት በንፁሃን ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ( አስገድዶ መድፈር ፣ ንብረት ማውደም ፣ግድያ እና ሌሎች ወንጀሎች) እንዲሁም በማህበራዊ ተቋማት ( ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ወዘተ) ላይ እየደረሱ ያሉ ውድመቶች እንዲጋለጡ ታላቅ መደላድል ይፈጥራል።
3ኛ. የዐማራ ፋኖ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች ቀጥተኛ አለማቀፍ የምግብና፣ የመድሃኒት እና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲያገኙ እድል ይፈጥራል።
4ኛ. ለዓለም አቀፍ ዲፕሎመሲ እና ከተለያዩ ሀገራት ጋር የዐማራ ፋኖ ለሚያደርጋቸው አለማቀፍ ግንኙነቶች ትልቅ በር ይከፍታል።
ይህ ድል በነፃ የተገኘ አይደለም። የብዙ ወድ እና እንቁ የዐማራ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ህይወታቸውን ገብረው የተገኘ ድል ነው። ወደ እነሱ ተቋም በተደጋጋሚ ተመላልሰን፣ በፀሃይ፣ በዝናብ፣ በብርድና በቁር ጮኽን ፣ ጮኸን ያልሰሙን አካላት እዚያው አለንበት ድረስ መጥተው እንዲሰሙን ያደረግንበት ታላቅ ድል ነው!
ይህ ድል ለትግሉ አምስት ሳንቲም ያላዋጣ የማንም አልፎ ሃጅ የሚተረጉምልን ሳይሆን ግልፅ፣ የትግሉ ባለቤት የዐማራ ህዝብ በሚገባ የሚረዳው፣ በደንብ ጊዜ ወስዶ የሚያጣጥመው፣ ቀጣይነቱን የሚያስጠብቀው እንዲሁም በአግባቡ ሊጠቀምበት የሚገባ የማይገኝ እድል ነው!
ግሪሳ ሆይ እባክህ የተሰጠህን ሁሉ ሳታላምጥ አትዋጥ።
ዕድል ፣ ገድል፣ ድልና ወንጀል ለየቅል!
@Dagimawit Getaneh