>

አገር እያፈረሰ ላለ ድርጅት የግዳጅ መዋጮ፤የነውር ጣራ

አገር እያፈረሰ ላለ ድርጅት የግዳጅ መዋጮ፤የነውር ጣራ

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

‹‹ብልግና›› የሚባለው የጐሠኞች ማኅበር ነውር ጣራ ነክቷል፡፡ ‹‹ምርጫ›› ላካሒድ ነውና በድርጅቱ የተጣለባችሁን መዋጮ በዚህ የባንክ ሒሳብ እንድታስገቡ የሚል በብጫቂ ወረቀት ላይ የተጻፈ ቀጭን ትእዛዝ ሕዝብ ጋር መድረስ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የስብሰባ ጥሪ ይደረግና ጉዳዩን አስቀድሞ የማያውቀው ተሰብሳቢ በመዋጮ ስም የዝርፊያው መርዶ በይፋ ይነገረዋል፡፡ በተለመደው ሰይጣናዊ የድርጅት አሠራር በስብሰባው የሚካፈሉት ካድሬዎች በተገኘውም ሆነ ባልተገኘው ተሰብሳቢ ላይ ወስነው ይወጣሉ፡፡ ጉዳዩ ከሕውሓት ወያኔ የተላለፈ ‹ውርዴ› ቢሆንም በኦሮሞ ጐሠኞች ግን አለ አንዳች ኀፍረት ባደባባይ እየተፈጸመ ነው፡፡ 

በዐዲስ አበባ ከትንሹ ነጋዴ እስከ ትልቁ ነጋዴ፣ ከወረዳ አንሥቶ ዘረኞች እስከ ተቆጣጠሩት የላይኛው የከተማው መዋቅር ድረስ ካድሬዎቻቸውን አሰማርተው የገንዘብ መጠን ወስነው በሱቆቻቸው ላይ በመለጠፍ (ማባሪያ ለሌለው ምክንያት/በከፊልም የአገዛዙ ሰዎች ኪስ ለሚገባ ገንዘብ) ዝርፊያውን ከጀመሩት ቆይቷል፡፡ እምቢኝ አሻፈረኝ ያለውን ሱቁን በማሸግ፣ ንግድ ፈቃዱን በመቀማትና እስከ እስር በማስፈራረት ቁም ስቅሉን ያሳዩታል፡፡ ከመሀል ለዘረኞቹ ያደረ ‹ነጋዴ› ወይም የተጠየቀውን ከፍሎ የሚገላገል የመሰለው አንዱ ቦቅቧቃ ዝምታውን ይሰብርና ክፍያውን ሲፈጽም የታሰበው ኅብረት ይናዳል፡፡ ከዚያ በኋላ በተቀደደው ቦይ መፍሰስ ይሆናል፡፡ ከዐቅም በላይ በሆነና ማንም እንዳሻው በሚተምነው ግብር መሰቃየትህ ሳያንስ ለምንድን ነው ለቀማኞች የላብህን ውጤት አሳልፈህ የምትሰጠው? ምን ነካን ጎበዝ? እነዚህ ምናምንቴዎች ሀብት ንብረትህ ሲያልቅ አንተንም አይተዉኽም፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረው በባንክ ያለህ ጥሪት የነሱ እንደሆነ ዘንግተኽዋል? እናንተም የምትወቀሱበት ጉዳይ አለ፡፡ ግን የአሁኑ ርእሰ ጉዳይ ቦታው አይደለም፡፡

ይህ ለፓርቲ የግዳጅ መዋጮ ትእዛዝ እየደረሰ ያለው ለድርጅቱ አባላት አይደለም፡፡ እነሱማ አገር በማፍረሱ ተግባር አባሪ ተባባሪ ሆነው የሚፈጽሙት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በምኞት ብቻ የሚሆን ነገር የለም እንጂ የመዋጮው መጠን ተወስኖባቸው ክፈሉ እየተባሉ አብዛኛዎቹ ይህ አገር አጥፊ ድርጅት ከኢትዮጵያ ምድር ድራሹ እንዲጠፋ ሌት ተቀን የሚመኙት ሕዝብና ‹ነጋዴዎች› ናቸው፡፡ ምን ዓይነት እንቆቅልሽ ነው!? ገንዘቤን ሰጥቼህ እኔንም አገሬንም ግደል የሚል ሕዝብ በኢትዮጵያችን ምድር እንጂ በሌላው ዓለም ይገኛል ለማለት ይቸግረኛል፡፡ በተናጥል የሚደረግ ተቃውሞ የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት ሳላውቀው ቀርቼ በሰው ቊስል እንጨት ለመስደድ አይደለም፡፡ ኹለትና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች (ቢቻል አብዛኛው ነዋሪ) ኅብረት ፈጥረው እስከ መጨረሻው እምቢኝ አሻፈረኝ የማይሉ ከሆነ ባርነቱን በዝምታ ለመቀበል እንደተስማሙ ምልክት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ‹‹ሬሳነት›› በዐዲስ አበባ ከራርሟል፡፡ በሌላው የአገሪቱም ክፍል ተመሳሳይ ነው፡፡ ይባስ ብሎም ፋኖ ባልተቆጣጠረው የጦርነቱ ቀጣናዎች (በተለይም በክፍለ ሀገራት ዋና ከተሞች) አሸከሮቹ ብአዴኖች ይህንኑ ዝርፊያ ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ገንዘብን በጉልበት፣ በዛቻ/ማስፈራራት ወይም በማስገደድ ማግኘት (extortion of money) እኛን ጨምሮ በብዙ አገሮች ወንጀል ነው፡፡ ተጠያቂነት በሌለበት፣ ሕግና ሥርዓት በሌለበት፣ ‹መንግሥትና ፓርቲ› በማይለይበት የወንጀለኞች አገዛዝ ውስጥ ይህ ድርጊት  ‹መንግሥታዊ/የፓርቲ መዋቅርን› ተገን አድርጎ ዕለት ተዕለት የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡  

ነውሩ ለጊዜው ተግባራዊ መሆን የጀመረው ፋሺስታዊው አገዛዝ ዐዲስ አበባን ባነቀበት ‹‹ሸገር›› ብሎ በሚጠራው ቦታ እና ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በሰየመው የአገራችን ክፍል ነው፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ ዐዲስ አበባ እና ሌላውንም ክፍለ ሀገራት መመልከቱ የማይቀር ይመስላል፡፡ ተካክለን ‹ሬሳ› የመሆናችን ምልክት ነው፡፡ ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቈስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ ይላሉ ቀደምት ሊቃውንት፡፡ ይህም ሲባል ነገሮች ከቊጥጥር ውጭ ከመሆናቸው በፊት በአእምሮም ሆነ በቁስ ተዘጋጅቶ መመከት ሲቻል (ሽባ ሆኖ ከመቀመጥ በፊት ብዙዎች ሲያሳስቡ ቢቆዩም)፣ አገዛዙ በግድያም፣ በሕገ ወጥ እስሩም፣ በማሰደዱም፣ ከቤት ንብረትና ከሥራ በማፈናቀሉም፣ በመከፋፈሉም፣ የሕዝቡን ኃይል ከማደከሙ በፊት በኅብረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ወሮ በላውን አገዛዝ ለማስቆም ዋስትና መሆኑን ለመናገር እንጂ አሁን ምንም ማድረግ ስለማይቻል በድን ሬሳ ሆነህ የማንም ጨካኝ ደናቊርት መጫወቻ ሁን ለማለት አይደለም፡፡ በአእምሮም በቁስም ባዶ ከሆንኽ በኋላ የምታደርገው ልቅሶም ሆነ ጩኸት ስለማይጠቅም እንደ ባለአእምሮ ሰው እንኹን ለማለት ነው፡፡ በጎ ቀን ለማየት ከፈለግኽ በምኞት እንዲሁም በመልካም ሥራ ባልተደገፈ ጸሎት ብቻ አይመጣም፡፡ ለቸርነቱ ምክንያት የሚሆን መልካም ሥራ የግድ ያስፈልጋል፡፡ የድርሻህን ሳትወጣ ከሰማይ የሚወርድ ‹መና› የለም፡፡ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም አገዛዙ በሚያስቀምጥልህ ወጥመድ ገብተህ በጥቃቅን ጉዳይ የወሬው ሰላባ ሳትሆን የጋራ አገራችንን ለማዳን ከመቼውም ጊዜ በላቀ በኅብረት የምንነሣበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ፋሺስታዊውን አገዛዝ በጥብዐት ተጋፈጠው፡፡ ያለ ይመስልሃል እንጂ ቀፎ ነው፡፡ የርጕም ዐቢይ ጥንካሬ የሱ ብርታት ሳይሆን ያንተ አለመተባበር፣ ጫንቃህን አመቻችተህ ግፍና ጭቆናን ለመቀበል ዝግጁ መሆንህ ብቻ ነው፡፡ ሕፃናት ልጆችህ፣ እናቶችህ፣ እኅቶችህና ሚሽቶችህ በግፍና በገፍ በጦርነትና በረሃብ በሚያልቁበትና በነውረኞች በሚደፈሩበት አገር፣  የትኛው ኑሮ አሳስቶህ ነው ወደ ኋላ የምትል፡፡ ለነሱና ለልጆችህ ስትል ለፈሪ ዘረኞች ከምትንበረከክና ከሰው በታች ሆነህ ‹‹አለሞትኹም ብዬ አልዋሽም›› የተባለ ሕይወት ከምትኖር መልካም ታሪክ ሠርተህ ማለፍ አይሻልም?

ሕይወትህን፣ ሕልምህን፣ መልካም ምኞትህን፣ ትናትህን፣ ዛሬህን፣ ባጠቃላይ ጊዜህን ለሠረቀብህና ነገህንም ለማሳጣት የሚታገልህን፤ እምነትህን፣ እሤቶችህን፣ ታሪክህን፣ ማንነትህን፣ ባህልህን፣ ቅርስና ውርስህን ካጠፋና እያጠፋ ያለን ደመኛና ከሀዲ ጠላት ለምንድን ነው የምትፈራው? 

እግዚአብሔር አምላክ እንድትኖርባት በሰጠህ ምድር ያጎደለብህ አንዳች ነገር የለም፡፡ አፈሩ ነው? ውኃው ነው? አየሩ ነው? የተፈጥሮ ሀብቱ ነው? ምንድን ነው ያጎደለብህ? ታዲያ በገዛ አገርህ እንዴት ነው ለማኝና መጻተኛ ሆነህ የምትኖር? መቼ ነው ግፍን በቃኝ የምትል? በዚህች በነፃነት ምድር ባሪያ ሆነን እስከ መቼ? ወገኖቻችን በዱር በጫካ እየከፈሉ ያሉትን መሥዋዕት እያሰብን፣ እኛ የቀረነው ቢያንስ ከክፉዎች ጋር አልተባበርም ማለት እንዴት ተሳነን? ይሄ አንድ ሐሙስ ከቀረው ቆሻሻ አገዛዝ ጋር በየመንደሩ የሚርመጠመጡትን፣ ለከርሣቸው ተገዝተው መውጫ መግቢያ ያሳጡህ ወገኖችን አደብ እንዲገዙ ብትመክሯቸውና ብታስጠነቅቃቸው መልካም ነው፡፡ ከግድያ፣ ከእስር፣ ከስደት የተረፋችሁ ወጣቶች ከጥልቅ ድባቴአችሁ ንቁ፡፡ ወላጆቻችሁንና ወገናችሁን አበርቱ፡፡ ነገን የራሳችሁ ለማድረግ ዛሬን ዕወቁበት፡፡

Filed in: Amharic