ከእውነት ጋር መቆም!
የዐምሐራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (ዐፋሕድ) እና ብአዴናዊው የነ ዘመነ አንጃ
ከይኄይስ እውነቱ
አካፋን አካፋ ብለው በትክክለኛ ስሙ ካልጠሩት አጉል ማስታመም ለዐምሐራ ሕዝብ የህልውና ትግል ብሎም ለኢትዮጵያ አንድነት በፍጹም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ከእውነት ጋር መቆም ክፍፍል መፍጠር አይደለም፡፡ ላንድነት መቆም እንጂ፡፡ መቼምእውነት ምንድን ነው ብሎ ጲላጦሳዊ ጥያቄ የሚያቀርብ ያለ አይመስለኝም፡፡ ካለም እንደ ባለ አእምሮ ተመራምሮ ይድረስበት፡፡ አንድነት በድቡሽት ላይ አይገነባም፡፡ እንገንባ ቢባልም አንድ ጀምበር አይቆይም፡፡ እውነታውን ፍርጥርጥ አድርጎ ሕዝቡ እንዲያውቀው ማድረግ ፋሺስታዊውን የጐሣ አገዛዝ መርዳት ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የአንጃው አመራሮች ነን የሚሉ ግለሰቦች (ተከታዮቻቸው ያላልኹት በስሕተትና በመንደር ቆጠራ ተገፍተው የተጃመሉ ይኖራሉና፡፡) ቀድሞውንም የአገዛዙ አሽከር የብአዴን ቅጥረኞች ናቸውና፡፡
በዚህ ረገድ ‹‹ቤተኞች ነን›› ምስጢር ዐዋቆች ነን የምትሉ አንዳንድ ‹‹የትግል ሚዲያዎች›› ላንድነት በመሳሳት ሰበብ ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ ባትከቱት መልካም ይመስለኛል፡፡ በሚዲያዎቻችሁ ላይ ርስ በርሱ የሚጣረስ አሳብ ይቀርባልና፡፡ ወንድማችን ሀብታሙ በቅርቡ በፋኖ ስም ብአዴናዊውን አንጃ ከሚመራው አንዱ ዘመነ ያወጣውን የማስመሰያ መግለጫ አንስቶ ያቀረበው ዝግጅት (በፖለቲካው ውስጥ እጅግ አወዛጋቢ የሆኑ ግለሰቦች የሚናገሩትን ንግግር ወይም በቡድን ስም ነገር ግን በግላቸው የሚያወጡአቸውን መግለጫዎች ሳይጠይቁ÷ በጥልቀት ሳይፈትሹ÷ ከጀርባ ያሉ ድብቅ ትርጕሞችን ሳይመለከቱ /ላንድነት ባለ ጉጉት ብቻ/ እንደወረደ (at face value) መቀበልና ማቅረብ) እና በማግስቱ ጋዜጠኛ ፋኖ ጌጥዬ ያለው‹‹ ያልተቀቡ ነገሥታትና የልሂቃን ጅምላ ጭፍጨፋ›› በሚል ርእስ ዘመነ በግሉ ካወጣው መግለጫ በተቃራኒው በኢትዮ ሪፈረንስ ድረገጽ (ፋኖ ጌጥዬ እንዳለው የሚመለከታቸውን በማነጋገርና በዓይን ምስክርነት ማስረጃነት) እ.አ.አ. ሴፕቴምበር 1/2025 ያስነበበንን ጽሑፍ ሐራ አምባና ቆቦነት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በርግጥ ወንድም ሀብታሙ እውነታው ጠፍቶት እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡
ሌላው ኢትዮ-360 ሚዲያ ላይ ‹‹በሚዲያው መደበኛ መርሐግብር አዘጋጆችም ሆነ በተባባሪ ጋዜጠኞች የሚቀርቡ መርሐ ግብሮች›› የግለሰቦቹን እንጂ የሚዲያ ተቋሙን አቋም አያንፀባርቅም የሚል ኃላፊነትን የሚያስቀር መግለጫ (disclaimer) ምስልና መረጃ ከሚያስተላልፈው ስክሪን ግርጌ በቋሚነት እናነባለን፡፡እንዲህ ከሆነ ከዜና ዕወጃው በስተቀር የትኛው መርሐ ግብር ነው የሚዲያው አቋም?
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና ከፍ ብዬ ላነሣሁት አሳብ በማመሳሰል አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ በዘመናዊው የጋዜጠኝነት (መደበኛውን መገናኛ ብዙኃን/Mainstream Media/ይመለከታል) ሞያ ባለሞያዎቹ በመርሕ ደረጃ የሚያተኩሩት የተለመደው‹‹ሚዛናዊነት /impartiality›› ላይ ሳይሆን ‹‹እውነትን›› መዘገብ ላይነው፡፡ እውነት፣ ሌሎች ‹‹መርሖችን›› ለማክበር ሲባል መጨፍለቅ የለባትምና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የዐምሐራን ሕዝብ የህልውና ትግልና የዐምሐራ ፋኖን አንድነት ጉዳይ ስናነሣ ሰንካለ ምክንያቶችን በመደርደር እውነትን ልንጨፈልቃት አይገባም፡፡ ኋላ ላይ በእጅጉ ያስከፍላልና፡፡ ሕዝባችን በግፍና በገፍ በተፈጸመ የዘር ጭፍጨፋ የከፈለውን መሥዋዕትነት እና የወንድሞቻችንና እኅቶቻችን እውነተና ፋኖዎች ውድ ሕይወት የተገበረለትን ትግል እስከ ማስጠለፍ ያደርሳልና፡፡
በሌላ አነጋገር ለዐምሐራ ሕዝብ የቆመ መስሎ በአፍ/መግለጫሽንገላ የሚያጭበረብረውን ከሃዲ ብአዴናዊ አንጃ እና ዐፋሕድን (ከነድክመቱ) በአንድነት ፍለጋ ስም በእኩል ሚዛናዊነት ማየት አለብን በሚል ምክንያት እውነትን ማፈን በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ትዕግሥትና የዋሐት ልክ አለው፡፡ አንዳንድ ነገር የማይገባው ሞኝ ወይም አቋሙን ከጠላቶች ወገን ያደረገ ‹ተጋደሉ› (ላልቶ ይነበብ) የሚል መልእክት አድርጎት ሊወስደው ይችላል፡፡ በጭራሽ!!!
መልእክቴ ጨለማ ከብርሃን ጋር ኅብረት ሊኖረው አይችልም ነው፡፡ ነቀርሳ ስለሆነው ብአዴን ከበቂ በላይ ተነግሯል፡፡ በአፍም በመጣፍም በተግባር ባደረሰውና እያደረሰ ባለው የማይቀለበስ ጥፋት አልገባኝም የሚል ካለ ለእሱ የሚዋጥ እንክብል ወይም የሚጠጣ ሽሮፕ የሚያዘጋጅለት የለም፡፡‹‹እንዲያሽረው ከፈለገ ኮሶ ይጠጣ ወይም መተሬ ይብላ፡፡›› ፋኖ ወታደራዊውንም ሆነ ፖለቲካዊ አደረጃጀቱን አንድ ወጥ አድርጎ ታገለም አልታገለም በርጉም ዐቢይ የሚነዳው የጐሣ ፋሺስታዊ አገዛዝ መውደቁ ጥርጥር የለውም፡፡ ምናልባት ሕዝብና አገር የሚደርስባቸውን መከራ በተወሰነ ደረጃ ከሚያራዝመው በቀር፡፡ በዚህ መልኩ የሚመጣው ለውጥ ግን የዐምሐራ ፋኖ ‹‹መነሻዬ የዐምሐራን ሕዝብ ህልውና ማስከበር፤ መዳረሻዬ የኢትዮጵያ አንድነት›› ብሎ በይፋ የሚያራምደውን ዓላማ ማስፈጸም ስለመቻሉ ዋስትና አይኖርም፡፡ ስለሆነም ዐፋሕድ መድከም ያለበት ብአዴናዊው አንጃ ጊዜ አግኝቶ ከእስካሁኑ የበለጠ ጥፋት እንዳያደርስ በአንጃው አመራሮች ውስጥ የወደቁትን ተከታዮች በራሱ እቅፍ ውስጥ ለማስገባት በትጋት መሥራት፤ በአመራርም ሆነ በተራ ፋኖነት ያሉ የብአዴን ርዝራዦችን ለቅሞ ማውጣት፤ በመቀጠልም ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካ አንድነቱን በቶሎ መሥርቶ ቀድሞ በነበረው የድል ግስጋሴ ለመቀጠል መሆን ይኖርበታል፡፡
አለበለዚያ ኢትዮጵያን አምርሮ የሚጠላውንና በሕዝብና ባገር ላይ በፈጸማቸው በርካታ ወንጀሎች ሊጠየቅ የሚገባውን የኦሮሞ ጽንፈኛ ጀዋርን እንቶ ፈንቶ በመስማት ላገር ጠበቃ አድርጎ እንደመውሰድ፤ በሌላ በኩል በደም ሥሩ ውስጥ ነቀርሳ የሆነው ብአዴናዊ ደም የሚመላለሰውን÷ ባገራችን የሚታየውን ምስቅልቅል ያመጣ የዘረኝነት ሥርዓት ላቆመው ወያኔ ሕወሓት ቋሚ ለጓሚ በመሆን የሚታወቀውን÷ ሁሌም ላገርና ለሕዝብ የሚበጅ የእውነተኛ ትግል እንቅፋት በመሆን የሚገለጠውን÷ በሥልጣን ጥማት የተቃጠለውን÷ አከርካሪ የሚባል ያልፈጠረበትን÷ በሚያወራው አርቲ ቡርቲ የፖለቲካ ዐዋቂ መስሎ ለመታየት የሚሞክረውን … አውደልዳዩ ልደቱን ለዐምሐራ ሕዝብ የህልውና ትግል ጠበቃ አድርጎ እንደማየት፤ እቆጥረዋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ይህን የኋላኛውን ግለሰብ በሚመለከት ከፍ ብዬ ያነሳኋቸው ‹‹የትግል ሚዲያዎች›› ያላቸው አመለካከት በእጅጉ የተዛባ ነው፡፡ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ለእነሱ እንዴት ተሰወረባቸው? መንፈሳዊ የሆነውን ምስጢራዊ ትርጕም አቆይተን ርእሰ መጻሕፍቱ ‹‹ወዮ ለዓለም… ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና÷ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት… የወፍጮ ደንጊያ ባንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቁ መስጠም ይሻለው ነበር፡፡›› እያለ የሚናገረው ለእንደዚህ ዓይነቱ ሙልጭልጭ ግለሰብ ነው፡፡ ጊዜ ቆሞ አይጠብቀንም፡፡ አስተውሎት የተሞላበት ውሳኔ አድርገን በቶሎ መንቀሳቀስ ያሻል፡፡
በሃይማኖትም በባህልም ያለ ወግና ልማድ እንዳይቀር በአገር ውስጥና በውጭ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ እንኳን ለርእሰ ዐውደ ዓመቱ ቅዱስ ዮሐንስ/ ለዘመን መለወጫ ዕንቊጣጣሽ በዓል በሕይወትና በጤና አደረሳችሁ፡፡ አደረሰን፡፡
የዘመናት ጌታ የጊዜያት ባለቤት ለአገራችንም ለዓለሙም እውነተኛውን ሰላም ይስጥልን፡፡ አፅራረ ኢትዮጵያን አጥፍቶ ቅድስት አገራችንን እና የመከራ ዶፍ የሚወርድበት ምስኪን ሕዝባችንንበምሕረቱና በቸርነቱ ብዛት ይታደግልን፡፡ አሜን፡፡