ስለወደቀው የጋዜጠኝነት ክብር!
ሢሣይነሽ መንግሥቴ
“ጋዜጠኛው. . .ጋዜጠኛው፣
ጋዜጠኛው
ኑሮው ልቤን ነካው”
– ድምጻዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳ
ከሰሞኑ በአቶ ጸጋዬ ደበበ ባለቤትነትየሚተዳደረው ሱፐር ደብል ቲ ጄኔራልትሬዲንግ ስም በመገናኛ ብዙሃን አየር ላይናኝቶ ነበር። ኩባንያው ከፈጸማቸው የተለያዩየመብት ጥሰቶች እና አስጸያፊ ድርጊቶች ባለፈ፣ ብዙዎች ትኩረት የሰጡት እነዚህን ተግባራት“በጽኑ” ለማስተባበል የገንዘብ እና የሃሳብስምሪት ተላልፎላቸው በተንቀሳቀሱጋዜጠኞች ላይ ነበር። ጉዳዩን በተመለከተከመነሻው አንስቶ በትኩረት እየተከታተለሲዘግብ የቆየው ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት፣ ጋዜጠኞቹን በ”አልጀዚራ” እና በ”ኩኪስ” ምድብ ከፍሎ ሰይሟቸው እንደነበርየምታስታውሱ ይመስለኛል። በራሱ ይፋዊየፌስቡክ ገጽ ላይ የሁለቱ የጋዜጠኞች ምድቦችምንነት ከዚህ እንደሚከተለው አብራርቶትነበር፣
“አልጀዚራ:–
በዚህ ምድብ ያሉት ልክ እንደ አልጀዚራጋዜጠኞች ትልልቅ የቪድዮ እና የፎቶካሜራዎችን ተሸክመው በጋዜጣዊመግለጫዎች፣ ድግስ፣ ኮንሰርት፣ ኮንፈረንስ፣የዝነኞች ቤቢ ሻወር፣ ሰርግ… ወዘተ በመሄድምስል የሚቀርፁ በመምሰል ይገኛሉ። ብዙዎቹግን ቪድዮ መቅረፅ የማይችሉ፣ ካሜራቸውንየውጭ በር ማለፊያ አርገው የሚጠቀሙናቸው፣ ከዛም የተገኘውን ምግብም ሆነ የኪስአበል በመጠቀም ኑራቸውን ይገፋሉ።
ኩኪስ:–
እነዚህኛዎቹ ቁጥራቸው በዛ ያለ ሲሆን አዲስአበባ ውስጥም ሆነ ክፍለ ሀገር ዝግጅት አለሲባል በፍጥነት በመገኘት ይታወቃሉ። ኩኪሶችየሚሰሩበት የሚድያ ተቋም የላቸውም፣ስራቸው የሚሰጣቸውን መረጃ በግል የፌስቡክገፃቸው ማጋራት ነው። የጋዜጠኛ መለያየሆኑትን እንዴት? መቼ? ለምን? የሚሉጥያቄዎችን አይጠይቁም። ተፅፎየሚሰጣቸውን ጋዜጣዊ መግለጫ (press release) በቀጥታ ያጋራሉ፣ የኪስ አበል እናኩኪስ/ድግስ ይቋደሳሉ።”
በርግጥም፣ የዛሬ ሳምንት ዓለምገና የዘመቱትጋዜጠኞች በሁለቱም ምድብ ውስጥየሚቀመጡ መሆናቸው አያጠራጥርም። እኔምከጋዜጠኞቹ መካከል አንዷ ነኝና ያለምንምርህራሄ ራሴን በሁለቱም ምድብ ውስጥ ነውየማስቀምጠው። ምክንያቱም መጀመሪያ ዘገባለመስራት እንደቅድመ ሁኔታ የምመለከተውጉዳይ ውሎ አበል እና ምግብ ነው። ዝግጅቱ“ጠቀም ያለ” ውሎ አበል ካለው፣ ኪሴም ሆነጥርሴ ፈገግ እያሉ ዜናውን አሽሞንሙኜእሰራዋለሁ። ነገር ግን የረባ ምሳ ወይም ኮክቴልየሌለው ዝግጅት ላይ ለዘገባ ከተመደብኩ፣ ዜናውን አኮስምኜ ለአንባቢ አቀርበዋለሁ። አንባቢዎቼ ይህ አካሄዴ በዋናነት ከራሴውየድህነት ሁኔታ (የገንዘብ ድህነት) ጋርእንደሚያያዝ ልታውቁልኝ ይገባል።
የዛሬው ጽሑፌን ዋና ትኩረት “ጋዜጠኝነት እናድሕነት” በሚል ርዕስ ስር ለመቀንበብ ነበር ዋናዓላማዬ። ይህ ርዕስ ከሚፈልገው ሰፊ የንባብአቅም እና ጊዜ የተነሳ ሃሳቤን ወደ ግላዊልምዶች እንድቀይር ተገደድኩ። ጽሑፌ የሁለቱምድብተኛ ጋዜጠኞች ነባራዊ ሁኔታ ምንእንደሚመስል ይዳስሳል።
ከሁሉም በላይ “የዓለምገና ትዝብቴ” የተሰኘውየጉዞ ማስታወሻዬ የራሳቸውን ጎራ ቀልሰውበሚንቀሳቀሱ “ጋዜጠኞች” ዘንድ አቧራማስነሳቱን እዚህ ላይ ለመጥቀስ እወድዳለሁ። የአቧራው መቡነን አንዳንድ ጉዳዩ በቀጥታየማይመለከታቸውን ዜጎች እያሰቃየ እንደሚገኝየተለያዩ መረጃዎች ደርሰውኛል። እንግዲህመራር ሃቅ ሲወጣ፣ ተጓዳኝ እና አላስፈላጊጉዳት ለሚገጥማቸው ሰዎች ከወዲሁ ሃዘኔንእየገለጥኩ፤ ወደ ዋና ነጥቤ ልመለስ።
እኔ ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ ከገባሁ ወደ አስርትዓመታት ገደማ እየተጠጋሁ ነው። በዚህየጋዜጠኝነት ሕይወቴ ክፉንም ደጉንምተመልክቼአለሁ። የሞያተኞቹን ደግ እና ዕኩይተግባራት ወይም ባሕርያት ታዝቤያለሁ። ከሁሉም የሚደንቀኝ ነገር አንዳችም ሞያዊአቅም ሳይኖራቸው የጋዜጠኝነት መድረኩንያጣበቡ ሰዎች መብዛታቸው ነው። በተቃራኒው ደግሞ፣ የሞያው ፍሬ ነገርገብቷቸው ለመስራት እየሞከሩ፣ ግና በገንዘብዕጥረት የሚሰቃዩ በርካታ ጋዜጠኞች አሉ።
በኢትዮጵያ ከመንግስት ቀጥተኛ ቁጥጥርውጪ ባሉ የግል መገናኛ ብዙሃን ተቀጥረውየሚሰሩ ጋዜጠኞች በጋራ የሚያሰቃያቸውአንዳች ሕመም አለ፤ እርሱም “ድህነት” ይባላል። በተቋማቸው የሚከፈላቸው ገንዘብ ከቤትኪራይ እና ከዕለት ጉርስ ባለፈ፣ ሌላ የተሻለ ነገርየሚያሰራ አይደለም። ይህም የደመወዝዝቅተኝነት ወደ “አልጀዚራ”ነት ይገፋፋቸዋል። ተቋማቸው አሰማርቷቸው ከሚሄዱበትዝግጅት ሌላ፣ ራሳቸውን ደብቀውባልተጠሩበት ድግስ ላይ ድንኳን ሰባሪ ሆነውይመጣሉ፤ ችግር የወለደው ዕርምጃ!
ሌሎቹ — ከላይ በጥቂቱ የጠቃቀስኳቸው — በድሮ ዓመታት በመጽሔቶች፣ በጋዜጦች እናበሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች ላይተቀጥረው ሲሰሩ ወይም ተቋማቱንበባለቤትነት ሲያስተዳድሩ የነበሩ “ጋዜጠኞች”፣ አንድ የፌስቡክ ገጽ ወይም የዩቲዩብ ቻናልከግለሰብ በመግዛት፣ አዲስ የ”ሚዲያ” ስምበመሰየም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች በየጋዜጣዊ መግለጫው፣ በየሁነቱ የሚገኙ በመሆናቸው በጣምይታወቃሉ (በዓለምገናው ጉዞ ላይ በተነሷቸውፎቶግራፎች ላይ በሰፊው የታዩት ናቸው)። ለእነርሱ ድንኳን መስበር የዕለት ተለት ገቢእንጂ ተጨማሪ ገንዘብ አይደለም። የትኛውምዓይነት ሁነት ቢጠፋ፣ ሕልውናቸው ያከትማል፤ ዕድሜም አይኖራቸውም።
የሰዎቹን ስም አልጠራም፤ ነገር ግን በየሁነቱወይም በየጋዜጣዊ መግለጫው፣ ጠጋ ብለውቢሞክሩት የማይሰራ ማይክራፎን ከሎጎ (አርማ) ጋር አሰርተው ሲደቅኑ የሚያዩዋቸው ሰዎችያውቋቸዋል — ይህንን ጽሑፍ ሲያነብቡ። “የማይሰራ ማይክራፎን?” በማለት የምትደነቁአንባቢዎቼ እንደምትኖሩ ርግጠኛ ነኝ።
አትደነቁ፤ ሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችአርማዎቻቸውን ያነገቡ ማይክራፎኖችንስለሚይዙ “ተዓማኒ ናቸው” ብለው ለሚያስቡ፣ ለእነዚህ ሰዎች፤ ይህ የማጭበርበር ስራቸው“የመጠቀ እና የተመሰጠረ” መስሎ ነውየሚታያቸው። ግና ማይክ ደቅነው የቀረጹትንዝግጅትም ሆነ ቃለ መጠይቅ በፌስቡክገጻቸው ወይም የዩቲዩብ ቻናላቸው ላይለተከታዮቻቸው ሲያጋሩ አንመለከትም፤ ለምን? “አልጀዚራ” ስለሆኑ!
የሚያሳዝነው ነገር እነዚህን ሰዎች በአክብሮትጠርተው፣ “ሞቅ ያለ” ውሎ አበል ከፍለውየሚጋብዟቸው መንግስታዊ እና የግል ተቋማትመኖራቸው ነው። የየተቋማቱ የሕዝብግንኙነት ክፍሎች ስለእነዚህ “ጋዜጠኞች” ምንነት እና ስራ ለማጣራት ጊዜ የላቸውም። ስራ በዝቶባቸው ሳይሆን፣ ከሰዎቹ ጋር የጥቅምሽርክና ስላላቸው ነው። የሚኒስቴር መስሪያቤቶች የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችን ልብይሏል!
ይግረማችሁና እነዚህ ሰዎች የዕዝ ማዕከልአላቸው። ማዕከሉ በትልቅ ሕንጻ ውስጥየሚገኝ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። በአንድየአዲስ አበባ ኮስማና ሰፈር ውስጥ በሚገኝአረቄ ቤት ግለሰቦቹ ተሰባስበው ከየመረጃምንጮቻቸው የመጡትን የ“ይዘገብልኝ” ደብዳቤ ይከፋፈላሉ፤ የዓይኑ ቀለምያላማራቸው “የሚመታ” (በሃሜት ስሙየሚጠፋ) ግለሰብ ካለ፣ ወሬ ይቀመማል፤ ይሰራጫል። በቀረው ጊዜ ደግሞ፣ ሌሎችአጓጉል ተግባራትን ያከናወናሉ። (ለአንባቢክብር ስል፣ ድርጊቶቹን ከመጥቀስ እቆጠባለሁ!)
ጋዜጠኞቹን በአበል የሚያሰባስብ አንድ ግለሰብደግሞ አለላችሁ፤ ስሙን አልጠቅስም። ይህሰው ብዙ ዓይነት ማዕረግ አለው። ጋዜጠኛ፣ ፕሮሞተር፣ የማስታወቂያ ባለሞያ…ብዙ ቅጽልስሞች አሉት። በየጋዜጣዊ መግለጫውለሚመጡ ሪፖርተሮች የውሎ አበል መክፈልያለማመደው “እርሱ ነው” ይባላል። ይህምከዘጠኝ ዓመታት በፊት ማለት ነው። ቀስ በቀስየክፍያ መጠኑን በማሳደግ ጋዜጠኞችንበቁጥጥሩ ስር ማዋል ችሏል። ይሁንናሰውዬው መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ዕውቀትየሌለው “ምስኪን” ሰው ነው። ሆኖም ግንድፍረት ብቻ ነው እዚህ ደረጃ ያደረሰው። ኢትዮጵያ ውስጥ ድፍረት ወለድ ስራዎችበየጊዜያቱ የወለዱት ጥሩ ልጅ የላቸውም፤ ከብልሹነት በስተቀር!
እነዚህ የሙሉ ጊዜ “አልጀዚራ” እና “ኩኪስ” ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት መድረክበአቅመ ቢስነታቸው ጥልቀት እየበከሉት ነው። ይህም ቢቀር እንኳ፣ ጥያቄ የሚያነሱ እናከእነርሱ የቡድን ጠገግ የራቁ ጋዜጠኞችንጠልፈው ለመጣል ብሎም ለመስበርእየተንቀሳቀሱ ነው። ከኢትዮጵያ የመገናኛብዙሃን ባለስልጣን ሕጋዊ የዲጂታል ሚዲያፈቃድ ሳይኖራቸው፤ የንግድ ፈቃድ እና የግብርመክፈያ ቁጥር (ቲን ነምበር / TIN Number) ሳያወጡ በሃሰተኛ ማሕተም እናየመገጣጠሚያ ደብዳቤ ብዙ ሺሕ ብሮችንወደ ሒሳብ ቁጥራቸው ገቢ የሚያደርጉናቸው። እናም፣ እስከ መቼ ነው ዝምየሚባሉት?
እነጳውሎስ ኞኞ፣ እነሙሉጌታ ሉሌ፣ እነበአሉግርማ ያቀኑት የጋዜጠኝነት ክብር ወደቀድሞው ስፍራ ለመመለስ ጊዜው መቼ ነው?
