እኔና ተመስገን
ተመስገን በሚፅፋቸው ፅሁፎች ጥንካሬ ብዙ አንባቢዎች እንዳሉት የሚታወቅ ቢሆንም የሚናደዱ እንዳሉም የሚረዳ ሰው ነው፡፡ የሁልጊዜ መልሱም ሁሉን ማስደሰት አይቻልም የሚል ሲሆን፣ በተለይ ለተገፉት ከተናገርኩ በቂ ነው ይል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አይቀሬው እስር በታቀደለት ጊዜ ከመጣ በኋላም ተመስገን ቃሊቲ መታሰር ምርጫው አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለአዲስ አበባ ቅርብ ስለሚሆን ሰዎች እሱን ለመጠየቅ እንዲቸገሩ ፍላጎት ስለሌለው ብቻ ሳይሆን ጊዜውንም እንደወትሮ በጥንቃቄ እና በአግባቡ ለመጠቀም ስለሚፈልግ ነበር፡፡ አሁን ያሉት ማረሚያ ቤቶች በትክክለኛ ስማቸው ማጎሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ሲጀመር የሚታረመው ያጠፋ ነው፡፡ የተመስገን ዓይነቱን ተፈጥሮአዊ መብቱን አውቆ ለመጠቀም የሚፈልግ ሰውን ማሰር ከማጎር ውጭ ምንም ሊሆን ስለማይችል ነው፡፡ ይህንን ግፍ ወደ እድል መቀየር አቅም ያላቸው የተመስገን ደሳለኝ ዓይነት ድንቅ ሰዎች ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ግፍ ይፈፀምባቸዋል፡፡ በቤተሰብ በወዳጅ በዘመድ እንዳይጠየቁ እግድ ይጣልባቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በብርቱካን ሚደቅሳ አሁን ደግሞ በአንዱዓለም፣ እስክንድር፣ ናትናኤል፣ ርዕዮት፣ ሀብታሙ፣ ዳንኤል፣ ወዘተ ላይ የሚደረገው ግፍ በተመስገን ላይም በርትቶ ቀጥሎዋል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ የሚፈፀም የቶርቸር ዓይነት ይመስለኛል፡፡ የተመስገን ደሳለኝን ልዩ የሚያደርገው ከጠያቂዎች እንዳይገናኝ ብቻ ሳይሆን ምግብ እንዳይገባ መከልከሉም ጭምር ነው፡፡ በእነ ብርቱካን ጊዜ እንደተደረገው አሮጊት እናቱ እንኳን እንዲያዩት አለመፍቀድ ተመስገንን ሳይሆን አሮጊቷ እናቱ ላይ የተፈፀመ ግፍ ነው፡፡ ተመስገን እናቱን የሚጦር ድንቅ ልጅ ነው፡፡ ከተሜ ጋር የሚኖረን የምሳ ቀጠሮ ለውጥ ከሚደረግባቸው ምክንያቶች አንዱ እናቱን ለመጠየቅ የሚሄድበት ፕሮግራም ሲኖረው ነው፡፡
በነገራችን ላይ ተመስገን ሁለት የሚያሳድጋቸው ህፃናት ነበሩት፡፡ እነዚህን ህፃናት ከልክ በላይ ሲያዝናናቸው ብዙ ጊዜ ገጥሞኛል፡፡ የእነዚህን ህፃናት ፍቅር ቀምቶ በእሰር ቤት ማጎር አልበቃ ብሎ እነዚህ ልጆችም ሆኑ፣ እናቱ እንዲሁም ወዳጆቹ እንዳያዩት ከህግ ውጭ መከልከል ተመስገን ለተገፉት ብሎ የያዘው አቋም ገዢዎችን ምን ያህል እንዳበሳጫቸው ማሳያ ነው፡፡ ለክልከላው ትክክለኛነት በግሌ ዝዋይ ድረስ ሄጄ አትችልም ተብዬ መመለሴ ማረጋገጫ ሲሆን፣ የሚያሳዝነው ደግሞ ስም ምዝገባ ተከናውኖ ከተጠናቀቀ በኋላ አይቻልም የሚባልበት ሚስጥር ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን አንድ ይህን ማጣራት የሚፈልግ አካል ቢገኝ ኧረ በፍፁም ብለው ሊክዱ እንደሚችሉ እና የጠያቂዎች ዝርዝር ውስጥ የእኛን ስም ሊያሳዩ መቻላቸው ነው፡፡ ይህ በእውነት በተቋም ደረጃ ማድረግ ሳይሆን ማሰቡ በራሱ የደረስንበትን የውርደት ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡
ለማንኛውም ተመስገን በግፍ መታሰር ሳያንሰው፣ ከህግ አግባብ ውጭ በወዳጅ ዘመዶቹ እንዳይጎበኝ የተደረገበት ሁኔታ ኢ-ህገመንግስታዊ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል፡፡ ይህ አስተያየት ከእኛ እንዳይቀር ብለን ነው እንጂ ገዢው ፓርቲም ሆነ ይህን የሚተገብሩ አካላት ያዳምጣሉ ከሚል አይደለም፡፡ ለማንኛውም ተሜን በአካል ባናየውም በመንፈስ አብሮን ነው፡፡ ምርጫ! ምርጫ! … ስንል ለነበርን ለእኛ “የምን ምርጫ!!” ይለን የነበረው ተመስገን፤ በወህኒ ቤት ሆኖ ልክ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ የምን ምርጫ!!!!!
አቶ ግርማ ሠይፉ ስለ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የፃፉት ማስታወሻ
Filed in: Amharic