>
8:37 am - Saturday February 4, 2023

የዶርዜ ማርያም [አስፋ ጫቦ]

Page 1 of 6
የዶርዜ ማርያም
አስፋ ጫቦ
Denton Texas USA
1.
ዶርዜ ዴሬ (አገር) የዶርዜ ማርያም የለችም። ያሉ ሁለቱ አድባራት የጥንቱ ፣የጥዋቱ የዶርዜ ጊዮርጊስና የዶርዜ ሚካኤል ናቸው።ሚካኤል ከጨንቻ በልጅ እግር ከ30-45 ደቂቃ ቢወስድ ነው። በምን ሊከድ ኖሯል!? ልጅ ሆኜ አንድ ሁለቴ ሚካኤልን ለማንገስ መሔዴ ትዝ ይለኞል።ማንገሱ ሳይሆን የዶርዜ ዘፈኑ መስለኝ የሚጠራኝ።ታላቅ የሙዚቃ ትዕይንትና ቲያትር አደራሽ እንደመግባት ይሰማኛል። አዳራሹ ሜዳው መሆኑ ነው።
ዶርዜ ማርያም ብትኖርም እንኳ ዶርዜ ማራሞ ነው የምንለው። ታሪካዊዋንን የዜናሁ ለጋለ ፤የአባ ባሕርይ መጽሐፍ መፍለቂያ የብርብር ማርያም ደብረ ነች። ያችን እኛ ቢርቢራ ማራሞ እንላለን። ዚኒ ከማሁ፤ኤሌ ጋብሬሌ፤ዶርዜ ሚካሌ ነው የምንለው።
አጠራሩን የእናት ቋንቋው፣ አፉን የፈታበት ይወስናል እንደማለት ይመስለኛል። ይመስለኛል ማለቴ ኣጥንቸ ሳይሆን የማውቀውን ነው ለማለት ነው። አፉን የፈታበት ስንል አንድ መጠንቀቅ ያለብን ነጥብ አለ።የጋሞ ብሔረስብ ሳይሆን ጋሞ የተወለደ ሁሉ ማለት ነው።ያ ደጎሞ ነፍጠኛውን(አማራውንና ኦሮሞውን)በሌላ የተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸው መጥተው እዚያ የተወለደውንና ያደገውን ያጠቃልላል። በወቅቱ እንደሚናገረው ቋንቋ እንደማለት ነው። በአማርኛ ይናገር /ትንጋር እንደሁ ማርያም ፣ገብርኤል ይላሉ። በጋሞኛ ከሆነ ደግሞ ማራሞ፤ ጋብረሌ ይላሉ። ለምሳሌ፤ሲሚሉ “ማርይምን!” ያሉ እንደሆነ “ማራማ በይን!” (ማርያም ባየች)) ይላሉ። ። ማስብ የሚያስፈልገው ሳይሆን ኣውቶማቲክ ማርሽ መለወጥ ነው። የጋሞ ሰው፤አሁን የጋሞ ሰው ስል ትርጉሙ ግልጽ የሆነ የመስለኛል፤ ባማርኛ ሲናገር አዲስ አበባን አዲስ አበባ ይላል። ወደጋሞኛ ማርሹን ያዞር እንደሁ ቱንጋ ይላል።
Page 2 of 6
አንዴ ሽገር፤ደሞ አዲስ አበባ፤ደግሞም ፊንፊኔ ፤እየተባለ በምትጠራው በዚህ ፈላጊዋም ስሟም በበዛ ከተማ ገብቼ አዲስ ተፋላሚና ባላንጣ ከምሆን ብየ እንጅ ለመሆኑ ጋሞ ከየት አምጥቶና ለምን ቱንጋ አለ ? ብለህ ጠይቅ የሚለኝ ነገር አለ። የሚነገረኝ ባገኝም ደስ ይለኛል። ከባዶ ሜዳ ተነስቶ ቱንጋ ያለ አይመስለኝም። በዚህ ላይ አዲስባን አዲስባን ያደርገው ጉርጌና ዶርዜ ነበር። ጉርጌው እንኳን እየተገፋም ቦታ ቦታውን ይዟል። ዶርዜው “ያዉ በገሌ!” ላይ ነው።
2.
ወደተነሳሁበት ልመለስና የዶርዜ ማርያም የሚለው ስም የተለጠፈው አዲስ አበባ፤ሽሮ ሜዳ፤ኮልፌ፤ጉለሌ ነው። ያ፤ ጋሞ፤ ሸማኔ ተስባስቦ ከሚኖርበትና ከሚሽምንበት መንደር ነው። የዶርዜ መባሉ ፈር ቀዳጁ ዶርዜ ሆኖ እንጅ ዛሬ መላው ጋሞ በሽመና ስራ ተስማርቷል። የኔ ስጋ ዘመዶቼም፤የክርስትና ልጄ ጭምር ሸማኔ ናቸው።
ሙሉ ስሙ” ሰኞ የዶርዜ ማርያም!” ነው።ይህ ስም ይወጣል ከቤት የከተላል ከጎሮቤት አይደለም። ይኸኛው ስም የወጣዉ ሙሉ-ለሙሉ ከጎረቤት ነው። ታዝቦ! ታዝቦ! ሰኞ ሰኞ የዶርዜ ማርያም ነች ያለው አገር፣ ጎሮቤት ነው።
ታሪኩ፤ወይ የታሪኩ አመጣጥ ምንጩ እንዲህ ነው። ሰኞ ሰኞ፤ዶርዜ /ጋሞ ስራ አይሰራም።አይሸምንም። እርቅ ላይ ነው የሚውለው። የምን እርቅ ነው? ትላንትና እሁድ ጠጥቶ ፤ሞቅ ብሎት፣ስክሮ የስራረውን ጎሜ ሳይጸዳ፤ሳያስተሰርይ ማለት ይሻላል፣ ወደ ስራም ወደማቅሰኞም ሊሻገር አይችልምና ነው።
3.
ጋሞ ዓለማዊውም የመንፈሳዊ ሕይወቱ ከጎሜና ከዱቡሻ ጋር ተዋህዶ የከበረ ነው። ስለዱቡሻ በሌላ አጋጣሚ እንመለስ ይሆናል። ዱቡሻ የጋሞ ፓርላማ ማለት ነው ማለት ለጊዜው ይበቃል። የይስሙላ ሳይሆን ተግባራዊ ፓርላማ ነው።
ጎሜ መደርግ የሚገባቸውንና የማይገባቸውን አለማዊና መነፋስዊ ድነጋጌዎች ዳር ድንበር የሚያሳይ መሠረታዊና ባሕላዊ ሕግ ነው ብንል ጥሩይመስለኛ። አትስረቅ፤አታመንዝር፤በውሸት አትናገር፤ለአባቶችህ አምላክ መስዋዕት አቅርብና የመሳሰሉትን ባብዛኛው እመነትና የሰው ልጅ ባህል ውስጥ ያሉትን አይነቶች የሚደነግግ ነው።
የነዚህ ድንጋጌዎች መጣስ የሚያስከትለውን ጣጣ -ፈንጣጣ ተለይቶ የተወሰንነና የታወቀ አይደለም። ድንጋጌውን በጣሰው ሰው በራሱ፤ወይም በቤተስቡ፤ወይም፤በንብረቱ፤በጎረቤቱ፤ በጎሳው (ቆሞ) ከዚያም አልፎ በዴሬው (አገሩ) ላይ መቅሰፈት ሊያመጣ ይችላል። ይችላል ብሎ ያምናል State of Mind or Psychological makeup of the people
Page 3 of 6
4.
ጋሞ በአንድ አምላክ በሳሎ ጾሳ(የሰማዩ አምላክ) ያምናል። ከቀረቱ ክርስትናና እስልምናን ከመሳሰሉት ሀይማኖቶች ጋር በዚህ ሲመሳሰል የሚለይበትም ዋና ነጥብ አለው። በጋሞ ዕመነት አንድ ሰው የሰራውን ጥሩ ስራ ወይም መጥፎ ስራ ዉጤት የሚያጭደው ከሞተ በኋላ በገነት ወይም በገሐነም አይደለም። እዚሁ ጥሩውንም ሆነ መጥፎን ድርጊት በፈጸመበት ምድሪቱ ላይ ነው። የጎሜ ጽንሰ ሀሳብ ከዚህ የሚወጣበት ሳይሆን ከዚህ የሚነጻበት፤ጎሜው የሚፋቅበት አብሮ የታነጸ መፍትሔ አለው። ጥፋቱን፤ስህተቱን ማመን፤መቀበልና ባደባባይ ይቅርታ መጠይቅ። ይህ በቃላት ሲገለጥ የተዋሳሰበ የሚመስለው ለጋሞ ያልለተወሳሰበና እሱነቱቱን፣ጋሞነቱን ገለጭ አብሮ የተወለደ የውስጥ ባህርዩ ነው።
ይህንን የጋሞ፤የሳሎ ጾሶ፤የዱቡሻ፤የጎሜና የባህል ድንጋጌዎች ከእስልምናው የሻሪያ ህግና ድንጋጌ ጋር አዛምጄ ለማየት ፈለግኩ። ህግ ትምህርት ቤት፤ የ፫ኛ አመት ተማሪ እያለሁ፤ከጃፋር ኤል ኑሜሪ ሸሽተው የተሰደዱት፤የሱዳን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የነበሩት ፕሮፌሰር ዛኪ ሙስታፋ ስለሻሪያ ህግ አንድ ኮርስ አስተምረውን ነበር። ከዚያ ውስጥ ጠልቆ ከገባኝ ነገሮች አንዱ እስልምና ዕምነት ብቻ ሳይሆን ያንድን ሰው ሁለንተናዊ ኑሮ ሕይወት የሚመራ የ አኗኗ ዘይቤ (Way of Life/Living)ጭመር መሆኑ ነው። የሻሪያ ህግ የተውጣጣው ከቅዱስ ቁራንና ከሐዲስ(ባህል ስብሰብ)ነው። የእለት- ተእለት ኑሮ፤ባልና ሚስት እንዴት እንደሚገናኙ ጀምሮ፤ውርስን ፤የውስጥ ውስጣችንን ጭምር በውሐ መቸና እንዴት መጸዳዳት እንዳለብን ይደነገጋል። በዚህ ከጋሞ ጋር ይቀራረባል። የሚለየው የሥራ ዋጋ ክፍያው እዚህ ነው ወይስ በኋላ ታዛቢና ተመልካች በሌለበት ነው የሚለው ላይ ይመስለኛል።
ከዚህ የተነሳ አንድ ጋሞ አንድ ጎሜ ከሰራ፤ከሰው ጋር መጣላት ፤መደባብደብም ጎሜ ነውና በዳዩን ይቅርታ ጠይቀኝ፤ወይም ይቅርታ አድርግለኝ ማለት ግዴታ አለበት። ሁለቱንም አለመድርግ ጎሜ ነው።
ሌላ መታውቅ ያለበት አንድ መሠረታዊ ድንጋጌ አለ። ጋሞ ቢከሰስ እንጅ( ያ ከሱ ቁጥጥር ውጭ ነዉና) ሊከስ አይችልም። ወይም መክሰስ ጭራሱንም አይተያውም። ምክንያቱ ቀላል ነው። ለጋሞ ቀላል ነው ማለት የሚሻል ይመስለኛል። ከሳሽነት እሱነቱ ውስጥ የለም። መደበኛ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ፍርድ ነው። ፍርዱ እገሌ በዳይ፤እገሌ ደግሞ ተባዳይ ነው የሚል ነው። አጥፍና ንጽሁ ለመለየት። የጋሞ ፍርድ ማስታረቅና ስረ ነገሩን ከስሩ መፋቅና፣መሰረዝ፣ ማስወገድ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው በዳዩና ተበዳዩ ጀማ ፊት ቀርበው ፤ድርጊታቸውን ተናዘው በዳይ ነህ የተባለው ፫ ጊዜ ዝቅ ብሎ፤አንዳንዴም መሬት ድረስ አጎንብሶ ማረኝ ሲል፤ተባዳይም ፫ ጊዜ ምሬሐለሁ ሲል ነው። ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ያ ነገር ድርጊት ተፍቋል። ላንዴም፤ለዘለአለምም!
5.
Page 4 of 6
ዶርዜ /ጋሞ፤ የሌላውን ባላውቅም አዲስ አበባ ያለው ሰኞ ሰኞ አይሽምንም። ለዚህ ሕዝባዊ ጸብ የመፋቅ ሸንጎ ላይ ያዉላል፤ይውላል!! ያ ስም ከጎሬቤት ይወጣል ያልኩትን ሆነ።፤ ሰኞን የዶርዜ ማርያም በለው ሰየሙት። አድሮ ዉሎ፤ስንብቶ ምንጩ የማይታውቅ ወደ እውነትነት የሚጠጋ ስም ሆነ። አንዳንዱ ታሪክ ነው ብለው የሚያስተምሩን የዚህች ታክል መነሻ እውነት ያለው አይመስለኝም።
እሁድ፤ጠቡ፤ድበድቡ፤የ አፍ- እላፊ በተደረገበት በጠጅ ቤቱ ፤በሌላውም መጠጫ ቤቶች አካባቢ ፖሊስ መገኘቱ፤ወይ ጩኸት ስምቶ መድረሱ አይቀርምና እንደተለመደው አጋብሶ ወስዶ ፖሊስ ጣቢያ ያሳድራል። ሰኞ ጥዋት ያለ- የሌለ ዶርዜ/ጋሞ በተለይም ፬ተኛና ፫ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ደጅ ይኮለኮላል።እዚያ ላይ ነዉ ችግሩ!ጋሞ ፤የፖሊስ ጣቢያ ፤የፍርድ ቤት ነገር ምኑንም ምኑንም አያውቀውም።ስለአለተቀበለውና አመለካከቱ outlook ላይ አስገብቶ ስለአለመዘገበው ይህ የመንግስት ተቋማት ነገር በመጣ ቁጥር አዲስ፤ ግራ የሚያጋባው ነገር ይሆንበታል።
ከምኒልክ ወረራ፤መስፋፋት(እንደተርጓሚው)በኋላ ጋሞ ግበር ገበረ እንጅ ሥርዐቱን አልገበረም። ዛሬም፤በሐይማኖት ሳቢያ የሚቦረቡሩት ቢኖሩም እንደጸና ነው። ይህን ያሰኘን በ፩፱፰፫ ነሐሴ የሽግግር መንግስት ምክር ቤትአባል እያለሁ ጨንቻ ሔጄ ነበርና እግረ መንግዴን ዶኮ ማሾ ሔድኩኝ። ከጨንቻ በስተምእራብ የሚገኝ አገር ነው። ገበያው ላይ ዱቡሻ ተቀምጠዋል። ገረማኝ። ደርግ መጥቶ፤መሠረታዊ ለውጥ አድርጎ ፤የነበሩ ስርአቶች ሁሉ ባይቀበሩ እንኳን ገሸሽ ተደርገዋል በዬ አስብ ነበር። እዚህ እንዳለ ነው። ጥዋት ወደ ፫ ሰአት ገዳማ የመጣሁትን ሰውዬ፤ያውም ያዲሱ መንግስት ባለስልጣን፤ ወደ ፯ ሰ አት ላይ አነጋገሩኝ። የጀመሩትን ጉዳይ ከጨርሱ በኋላ። እዚያ ልብ ላለው ሁለት መንግስት፣ ግብር አስከፋይ፤ትዕዛዝ ሰጭ፤ይህንን አድርግ፤ይህንን ደግሞ አታድርግ የሚል መንግስትና ችግር የሚፈታ ፤የማያዝ ግን የሚፈጽም መንግስት ፊት ለፊት ተያዩ ብለንም ልንወስድ እንችላለን ብዬ አስባለሁ።
6.
ወደፖሊስ ጣቢያዎቹ ስንመለስ፤አንድ ሻምበል ከተማ የሚባል፤ለስላስ የፖሊስ መኮንን ፤ማእከላዊ፤ላይ ግቢ፤ ፩ ቁጥር ውስጥ የነበረ የነገረኝን አስታወስኩት። “ዶርዜ ታስሮ ያደረለት ሰኞ ጥዋት ግቢው ስለሚጠብ ቶሎ መልቀቅ እንፈልጋለን። በዚህ ላይ አማረኛ በደንብ ስለማይናገሩ፤የሚናገርትም ስለማይገባን ዋስ አስጠሮቶ የታሰርውን መፍታቱ የተለመደ ነው።ወንጀለኛ አለአግባብ ተፈታትባን ብሎ የሚመጣ ችግር እንደሌለ ከልምድ እንውቃለን። በዚህ ላይ የሚገርማው ትላንትና የተፈንከተው ሰውዬ ጭመር ፈንካቹን ሊያስፈታ ይመጣል “አለኝ እኔን ባየ ቁጠር ሻምበል ከተማ ይስቃል”እውነት ዶርዜ ነህ ?!” ይለኛል።
Page 5 of 6
እና ትልቁ ችግር ሰኞ ጥዋት ማስፈታቱ ላይ ነው። ታሳሪው ዋስ መጥራት አለበት። የሚያስከትለው ችግር ኖረ አልኖር ይህ የፖሊስ አሰራር ነው። ዋስ የሚሆን ሰው ደግሞ መታወቂያ ያስፈልገዋል። የዚያን ጊዜ እንኳን የጋሞ ሸማኔ አብዛኛው ሰው መታወቂያ የለውም።
7.
አንድ ቋሚ ስራው ዋስ የሚመስል ሰው የማውቀው ጋሽ ሽዋ ሻሌን ነው። አሁን ሳስበ ውጋሽ ሽዋ ሻሌ ሁሌም የገረመኝ ይመስለኛል። ዶርዜ ነው። የማውቀው የዲታ ወረዳ የግምጃ ቤት ሠራተኛ ሆኖ ነው። ጋሞ የዚያን ጊዜ የመንግስት ስራ የሚሰራ የማወቀው ከጋሽ ሸዋ ጋር ሁለት ሶስት ቢሆኑ ነው። ከዚያ ለፓርላማ ተመረጠ። በዚያው ምጥቶ አዲስ አበባ ገዳም ሰፈር ኗር ሆነ። ለጋሞ ጉዳይ፤ዋስትናም ሆነ ሌላ ለሚያስፈልገው የመንግስት አገናኝ ጋሽ ሸዋ ነበር። አንድ ሰው ስንቱ ፖሊስ ጣቢያ ይደሳል?
ከዚያ እኔም ጋ መምጣት ጀመሩ።እኔን እንዴት አንዳገኙኝን እርግጠኛ አይደለሁም። አዲሳባ ሆነ ጨንቻ ከጋሞ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘን ኑሮ ኖሬ አላውቅም። አንድ ሁለት አመት፤ ዘመዴና የፓርላማ አባል ከነበረው ከቀኛዝማች ኢልታሞ ኢቻ ጋር ጉለሌ ከሸማኔዎቹ ጋር እቁብ እንጥል ነበር። ያም ቢሆን የቀኛዝማች እንጅ የኔ አይመስለኝም። ያም ሆነ ይህ ዋስ ሲያስፈልግ እኔም ቤት መምጣት ጀመሩ።
የጋሞ ነገር ይገርመኛል።ቤት አንኳኳተው ይገቡና “ ዋስ ያፍለገናልና ተነስ እንሂሁድ!” ይላሉ። አላውቃቸውም።አያውቁኝም እንዳልል ይኸው ቤቴ ድረስ መጥተዋል።እሔድና ፈርሜ አስፈታለሁ።አንዳንዱ ፖሊስ ማታውቂያየን ማየት ብቻ ሳይሆን ወስዶ ከፋይሉ ጋር ያያዘዋል።በዚህ አይነት አንድ ሁለት ሁለት መታውቂያዬ ወይ ፫ኛ ወይም ፬ኛ ፖሊስ ጣቢያ የቀር ይመስለኛል።
በኋላ እንደምሰማው እኒያ መጥተው የጠሩኝና ዋስ የሆንኩለትም በሚመጣው እሁድ ጠጅ ቤት ይሁን በተገኘው አጋጣሚ ስለኔ ያወራሉ። ስለኔ ብቻ ሳይሆን ስለዘር ማንዘሬ ካዳም ጀምሮ ያወራሉ።ጋሞ ሲጥራህም፤ሲያወራህም ዘርህን ካዳም ጀምሮ መቁጠሩ ያለ ነው።እኔ የማለውቀውንም ያለስማሁትንም ጨምሮ።
8.
ለነግሩ እኔ ወጥ የከተማ ልጅ ነኝ:: ባይ ነኝ! ብቻ ነኝ ወይ? የሚያሰኘኝ ነገር ብዙ ጊዜ ይመጣብኛል።ነኝ እንዴ ? ከማዕከላዊ እንደተፈታሁ ፤ተክለ ሐይማኖት፤ድሮ የ ስኮ ጫማ ሱቅ የነበረበት ፎቅ ላይ የጥብቅናና የንግድ አማካሪ ቢሮ ከፍቼ ነበር። አንድ አመት እንደስራሁ ነው ያሁን መንግስት የመጣብኝ። ታዲያ የጥብቅና ውክልና አንዱ ደንበኛዬ ሲሰጠኝ የሚከሰሰውን ሰው እፈልግና” ከመክስሴ በፊት ባስታርቃህ ምን ይመስለሃል? ከተከሰስክ ይህንን ያክል
Page 6 of 6
ተጨማሪ ወጭ ይኖርብሃልና!” እላለሁ። አንድ ሁለቱ ከዚህ ጥፋ ብለውኛል። በማግስቱ መልሰው የደወሉልኝም አሉ። በዚህ አይነት ፍርድ ቤት ሳይደርስ አንድ አራት አምስት ጉዳይ ጨረስኩ። የሚገርመው ሁለቱ፤ተከሳሽ ሊሆኑ የነበሩ ሰዎች ጭመር ገንዘብ ሰጡኝ። ታዲያ አሁን እዚህ አሜሪካ ሳየው ከፍርድ ቤት ውጭ ነገር መጨርስ Out of Court Settlment የፍርድ ቤቶቹ የአስራር አካል ነው። የኔው እንኳን ከዚያው ከቤት፤በቅጡ አላውቀውም ከምለው ቤት ሳይሆን አይቀርም!
በዚህ ፤አንድ አመት ይሁን እንዲህ በቆየው ጥብቅናዬ ሁለት የገረሙኝም፤ያሳቁኝም ገጠሞች አሉ።አንደኛው፤ላንድ የቅቤ ነጋዴ ጉራጌ፤ የአገር ውስጥ ታክስ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ቆምኩለት። በጣም የሚያስፈራ ታክስ ጭነውበት ነበረና፣ ታፋቀለትና ሂሳቤንም ከፈለኝ። አንድ ቀን ጥዋቃ በር ተንኳኳቶት ስከፈት የሆነ ነገር ተሸክሞ ቆሟል። ገርሞኝ !”ምነው በደህና ገባ!” ስለው እንደማፈር ብሎ “እችን ለአመት በአል ብየ ነው!” ብሎ የተሸከመውን ወለሉ ላይ አስቀመጠና ሔደ። ለአመት የሚበቅ ቅቤ ነበር ያመጣው።
ሌላው ደግሞ አንድ ቀን ሁለት የጋሞ ሰዎች እንዲሁ በጥዋት አንኳኳትው አስከፈቱኝ። አላውቃቸውም። ብቻ በመልካቸውም በሰላምታቸውም ጋሞ መሆናቸውን አውኩት።የመጡት የአገር ውስጥ ገቢ ከሷቸው ስለነበር ለዚያ ነው።” ቢሮየ አይቀርባችሁም ነበር? እዚህ ድረስ ከምትለፉ ይሻላችሁነበር “አልኳቸው። ያለሁት አራት ኪሎ፣ ያውም መጨርሻው ፎቅ ፣ያውም በኤለቬተር ነዉ የሚደረስው። ብቻ “እዚህ ይየሻላል !”ይሁን “ይመቻል ብለን ነው!” አሉ። ቢሮውን ሳይሆን ሰውየውን የምንፈለገው እንደማለት።ያገሬ ሰው ዳር እስከዳር ይገርመኛል። መርዳትን ግን የሚጠይቅ ይመስለኛል።
9.
“ዶርዜ ማራማ፤የሰኞ የዶርዜ ማርያም “ይህንን ትመስላለች። ከኔ የተሻለ የሚያውቁ ሞልተዋልና ቢያዳቡሩት ወይ ቢያሻሽሉት፤ወይ ቢያርሙኝ ደስ ይለኛል።ይኸ “ የያዘውንየወረወረ ፈሪ አይበልም!” ከሚባለው ይደመርልኝ።
በተረፈ፣ በጋሞ፤ ሸማኔነት የተከበረ ሙያ ነው። ላይ፤ወደሰሜን ኢትዮጵያ ቁጢ ት በጣሽ የሚለው አይነት ነገር የለበትም።
ዶርዜ፣ ጋሞ፣ ለእትዮጵያ በመላው ዓለም ያስደነቀውን ይህንን የጥበብ ሸማ ምስል ያለበሰው “ዛሬም በገሌ!” ነው። በስራው ውጤት አገርም ዓለምም ተደነቀ እንጅ ባለጥበቡ ተጠቃሚ አልሆነም።
አይገርማችሁም!! አይገርመንም! ሊገርመንስ አይገባም!

Filed in: Amharic