>
7:09 pm - Thursday February 2, 2023

“ዜና አትስሙ” ለሚለው ፓስተር ምላሽ [ ክንፉ አሰፋ]

በከፊል የተቀዳውን የፓስተሩን ንግግር የሰማሁት “ሰልማ” የተሰኘውን ፊልም አይቼ እንደተመለስኩ ነበር። በዚህ አመት ለአራት የኦስካር ሽልማት የበቃው “ሰልማ” ፊልም ኦፕራ ዊንፍሬን ጨምሮ ምርጥ አክተሮች ይተውኑታል። ፊልሙ እ.ኤ.አ. በ1965 በዩናይትድ ስቴትስ የጥቁሮች የመምረጥ መብት ገፈፋን ተከትሎ፣ ዶክተር ማርቲን ሉተር ይህ መብት እንዲከበር የሚያደርገውን ትንቅንቅ ያሳየናል። ፓስተር ሉተር ለዜጎች የመምረጥ መብት እንዲከበር ያለማቋረት በመስበኩ ሲደበደብ፣ ሲንገላታና ሲታሰር እናያለን። በአላባማ ግዛት የሚኖሩ ጥቁሮች መብታቸውን ስለጠየቁ ብቻ የመርዝ ጭስ ቢረጭባቸው፣ ቢደበደቡ፣ ቢታሰሩ እና ቢገደሉም ሉተር ተስፋ አልቆረጠም። ሰቆቃውን በብሄራዊ ቴሌቭዥን የሚያዩ ሁሉ በቁጭት ትግሉን ተቀላቀሉ። ከግዜ በኋላም የ”ሰልማ” እና የ”ሞንትጎመሪ” ጥቁሮች የመምረጥ መብታቸው ተጠበቀ። በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተውን ይህንን ፊልም የሚያዩት ሁሉ በእንባ ይታጠቡ ነበር።

እዚህ ላይ ተስፋ ያለመቁረጥን ብቻ ሳይሆን የሜድያን ሚና፣ በተለይ ደግሞ የቴሌቪዥንን ሃይል እናይለን። ዘረኞች እና አንባገነኖች ሜዲያን የሚጠሉት ያለምክንያት አይደለም። በዩናይትድ ስቴትስ ዘረኝነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የመገናኛ ብዙሃኑ ነጻ በመሆኑ ህዝቡን ነጻ ሊያወጣው ችሏል።

የኛ ፓስተር ደግሞ ጭራሽ “ዜና አትስሙ” ሲል ይደመጣል። በዚያ በተነሳሽነት እና በቁጭት ስሜት ሆኖ የፓስተሩን ንግግር ለሚሰማው ደግሞ በጣም ያበሳጫል። “አትስሙ” ሲል የመስማት መብትን መጋፋቱን አላስተዋለው ይሆናል። ፓስተሩ በዚህ አላበቃም የኢሳት ሰዎች ቅዥታሞች ናቸው ሲልም ይዘልፋል። ቀን ከለሊት ይቃዣሉ ሲል ፍርድ ሰጥቷል። ፍርድ ለመስጠት እርሱ ማን ሆኖ? መጽሃፍ የሚለን “አትፍረድ ይፈረድብሃል” ነው።

ክፉውን ነገር አትቃወሙ የሚል ነገር በመጽሃፍ ቅዱስ የለም። እንዲያውም በብሉይ ዘመን ነብያት የገዥዎችን ክፉ ስራ ያወግዙ ነበር። ይህ ሰው መንፈሳዊ ነኝ የሚለን ከሆነ ኢትዮጵያ በሚሰራውን ክፉ ነገር አንዲት ቀን ተቃውሞ ያውቃል?

ቄስ ወይንም ፓስተር ሲሆኑ ስራቸው ወንጌልን መስበክ ነበረበት። “ዜና አትስሙ” ማለት ወንጌል አይደለም። ፖለቲካ ነው። ለዚያውም ያንድ ወገን ፖለቲካ። እንዲህ አይነት መልእክት በቤተ-ክህነት ውስጥ ማስተላለፍ መንፈሳዊነት አይደለም። ንግግሩ የጉባኤውን የግንዛቤ አቅም ዝቅ ከማድረግ የሚመጣ ንቀትም ይመስላል።
በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ይህ ነው። ዜጎች በሽብር ስም ይታሰራሉ፣ ሰዎች ያለአግባብ ይሰቃያሉ፣ ወገኖቻችን ያለአግባብ ይገደላሉ፣… መሬታቸው ለባእዳን እየተሰጠ ይፈናቀላሉ፣ ባለስልጣናቱ ያለ አግባብ ሃብት እያካበቱ ነው፣ ምርጫ ይጭበረበራል…. ዜናዎቹ እነኝህ ናቸው። ይህንን ሰምቶ የራሱን ግንዛቤ የመስጠት መብቱ የሰሚው ነው። ይህንን አትስሙ ማለት ምን ማለት ነው?

ዶክተር ማርቲን ሉተርም ፓስተር ነበር። ህልም ያለመ ፓስተር። ዜና ከመስማት ባሻገር ህዝብን ለመብቱ እንዲነሳ የሰበከ ፓስተር። በአመጽ-አልባ ትግል የጥቁሮችን መብት ያስጠበቀ ፓስተር። ፐሉተር ህልም የጥቁሮች የመምረጥ መብት ብቻ ላይ አላበቃም። አንድ ቀን ጥቁር ሰው ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካን ይመራታል ብሎ ነበር። ይህ ህልሙ ከሞላ ጎደል በባራክ አኦባማ እውን ሆኗል።

እንዲህ አይነት አመለካከት ላላቸው የሃይማኖት መሪዎች፤ ዲታቆን፣ ቄስም ሆነ ፓስተሮች በሙሉ አንዲት መል እክት አለችኝ። ህልም ባይኖራችሁም፣ የዜጎች ህመም ባይሰማችሁም፣ ግፍን መቃወም ባትፈልጉም፤ ዝም ብላችሁ ወንጌልን ብቻ ስበኩ። መንፈሳዊ ባልሆነ ንግግር የሌላው መብት አትጋፉት።

Filed in: Amharic