>
12:21 pm - Wednesday December 1, 2021

“ኮሚሽነር ጄነራል”ትዕግሰቱ አወሉ…[ግርማ ሰይፉ ማሩ]

ብዙ ሰዎች ስለ እነ ትዕግሰቱ አወሉና ግብረ አበሮቹ መፃፍ ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውም ደረጃቸውን ከፍ ያደርገዋል የሚለው አንዱ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከፍ ቢሉም ቢወርዱም እውነቱን ሰው አውቆት ፀሐይ ሞቆት መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሰለዚህ እፅፋለሁ፡፡ በቅርቡ የወጣ “የእኛ ፕሬስ ጋዜጣ ላይ አቶ ትዕግሰቱ በእርሱ ብሶ ቱግ ቱግ እያለ የሰጠውን ቅጥፈት የተሞላበት ቃለ መጠይቅ አይቼ ማለፍ አልቻልኩም፡፡ በዚህ ደረጃ ለሆዱ ያደረን ሰው ለምን ዋሸ ተብሎ አይጠየቅም ያሉ ሰዎች ቢኖሩም ውሸታም መባል አለበት ብዬ ስላመንኩ ይህችን አጭር ነገር ለማለት ወደድኩ፡፡ በነገራችን ላይ የኢህአዴግ ካድሬዎ ስለ ትዕግሰቱ ሲፃፍ ከሱ ይልቅ ይነዳቸዋል፡፡ በማህበራዊ ኑሮ እንዲገለል ለማድረግ ነው ይላሉ፡፡ በእኔ እምነት ትዕግሰቱን ከማህበራዊ ኑሮ ለማግለል ማህበረሰቡ የሚፈልገው የእኔን ምክር ሳይሆን የእርሱ ተግባር ነው፡፡ የሰራሁት ስራ ጥሩ ነው ካለ ማፈርም መገለልም የለበትም፡፡ ነውር ይዞ ግን ማህበረሰብ ውስጥ ለመቅረብ ስትሞክር ግን ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ወደ ተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስሄድ፤ በእኔ ግምት ጋዜጠኛው ብዙ ነገር ሊጠይቀው ተዘጋጅቶ ቢሆንም እንኳን ከትዕግሰቱ ጋር ከዚህ በላይ መነታረክ አያስፈልግም ብሎ ያቆመው ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ትዕግሰቱ ሰራው ትዕግሰት ነስቶት ጥያሰቄ ለመመለስ ዝግጁ አይደለም፡፡  አንድነትን ለማፍረስ እና አቶ ትዕግሰቱን ለማንገስ በተጠራው ስብሰባ ላይ የተሰበሰቡት ሰዎች የአንድነት አባላት ናቸው? ለሚል ጥያቄ ሲቀርብለት እኔ አባል አይደለሁም? የማነ አባል አይደለም? ብርሃኑ አመራር አይደለም? ብሎ ጋዜጠኛ ጋር መነታረክ መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ነበሩ የተባሉት 193 ሰዎች ሰም ዝርዝር ማቅረብና አባላት መሆናቸውን ማስረዳት ነው፡፡ አቶ ትዕግሰቱ ሰማቸውን እየተጠራ አባል አይደሉም ወይ ያላቸው ሰዎች በቅጥረኝነት ከትዕግሰቱ ቀድመው የተሰለፉ ናቸው፡፡ ትዕግሰቱ ከኋላ ሆኖ ሲጫወት ከፊት ያጠቁ የነበሩ ናቸው፡፡ ከትዕግሰቱ ጋር ባደረኩት የስልክ ንግግር ለምን ወደፊት አትመጣም? ከኋላ ሆነህ ለምን ትረብሻለህ? ብዬ ስጠይቀው “ሞሪኖ ሜዳ አይገባም፡፡” ብሎ ነው የመለሰልኝ፡፡ አሁን ሲቀጥፍ እኔ ቅሬታ ያላቸውን ሰዎች የተቀላቀልኩት ጥር 3 ነው ይለናል፡፡ ከፈለክ ድምፅህን ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ልለጥፈው እችላለሁ፡፡

ትዕግስቱ አወሉ “የፖለቲካ ውሳኔ” ምን ማለት እንደሆነ አያውቅም፡፡ ምርጫ ቦርድ በህግም ሆነ በአሰራር ባልተሰጠው ስልጣን አንድን ፓርቲ ለእገሌ ሰጥቻለው ማለት እና በድፍረት መወሰን የፖለቲካ ውሳኔ ማለት ነው፡፡ ይህ ድፍረት የሚመጣው ደግሞ ህግን በጡንቻቸው ስር ባደረጉ ፖለቲከኞች ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ውሳኔዎች ፖለቲካዊ ውሳኔ ይባላሉ፡፡ ውሳኔው ፖለተካዊ አይደለም የሚባለው ህግና በመረጃ መሰረት ተደርጎ በፍርድ ቤት ሲወሰን ነው፡፡ ለአንባቢዎች ግልፅ እንዲሆን አንድ ምሳሌ ማንሳት ጥሩ ነው፡፡ ሁለት በጋራ ንግድ ያላቸው ሰዎች አለመገባባት ውስጥ ሲገቡ ንግድ ሚኒሰቴር ንግዱን ለእገሌ ሰትቸዋለሁ ብሎ እንደ መወሰን ነው፡፡ ይህ ደግሞ አልበቃ ብሎ ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ንግድ ሚኒሰቴር ፖሊሲ ማዘዘ ከቻለ ነው፡፡

የፖሊስ ነገር ከተነሳ ደግሞ በአቶ ትዕግሰቱ አወሉ ቃለ መጠይቅ ውስጥ አስገራሚ ነገር አንብቢያለሁ፡፡“ፖሊሱንም ያቆሙኩት ከውሳኔው ከሁለት ቀን በኋላ ነው፡፡ ሁሌም ፖሊስ አለ፡፡ የዚያን ሰዓት ንብረት እንዳይጠፋ እንዲቆጣጠር ተደርጓል፡፡” የሚል ነው፡፡ አቶ ትዕግሰቱ ፖሊስ የማዘዝ ያህል ስልጣን እንዳለው አላውቅም ነበር፡፡ “ኮሚሽነር ጄኔራል” ትዕግሰቱ አወሉ ከፓርቲ ፅ/ቤት የወጡ ሁሉ እንዳይገቡ አድርጓል፡፡ በጥር መጨረሻ በምክር ቤት በነበረ ሰብሰባ ለአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ምርጫ ቦርድ ፖሊስ የማዘዝ ስልጣን ከየት አመጣ? በሚል ላነሳሁት ጥያቄ መልስ አልሰጡኝም ነበር፡፡ ለካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳያውቁት ሌላ የፖሊስ አዛዥ የሆኑት አቶ ትዕግስቱ አወሉ ነበሩ፡፡

ሌላው አስገራሚ ነገር ንብረት እንዳይጠፋ የምትለዋ አስተያየት ነች፡፡ ሌባ እናት ልጇን አታምንም እንደሚባለው ነው፡፡ በፓርቲ ፅ/ቤት የነበርን የአንድነት ስራ አስፈፃሚ አባላት ሐሙስ በአስራ አንድ ሰዓት አካባቢ የምርጫ ቦርድን ነውረኛ ውሳኔ ከሰማን በኋላ  በማግሰቱ ጠዋት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ከሰዓት በኋላ ደግሞ የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲጠራ ወሰነን ወደ ቤታችን ገባን፡፡ ጠዋት ስራ አስፈፃሚ ተሰብሰቦ ከወሰናቸው ውሳኔዎች አንዱ በምርጫ ቦርድ ውሰኔ ፓርቲውን ለትዕግሰቱ አወሉ እንደማንሰጥ፣ ፍርድ ቤት ከወሰነ ግን ርክክብ እንዲፈፀም ርክክቡንም የፓርቲው ዋና ፀሃፊ ከኦዲትና ኢንሰፔክሽን ጋር ሆኖ በዝርዝር እንዲፈፀም ነበር፡፡ ይህ ውሳኔ የተላለፈበት ቃለ ጉባዔ ጠረጴዛ ላይ እንዳለ ለምሳ ወጥተን ስንመለስ “ኮሚሽነር ጄነራል” ትዕግስቱ አወሉ ያዘዟቸው ፖሊች የፓርቲውን ፅ/ቤት ወረውት አገኘን፣ ወደ ጊቢ መግባት ተከልክለን፤ በመጨረሻም መኪናችን በፖሊስ ተበርብሮ መኪናችንን ከጊቢ እንድናወጣ ተደረገ፡፡ በዕለቱ መኪናችን ጊቢ ውስጥ የነበረው እኔ፣ በላይ እና አቶ ተመስገን ዘውዴ ነበርን፡፡ እኛ ደግሞ ንብረታችንን አንዘርፍም፡፡

ሌላ አቶ ትዕግሰቱ ያነሳው ሰለ 2004 እና 2006 ደንብ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ደንቡን ከአረቀቁት ሰዎች አንዱ ነበርኩ የሚለው ነው፡፡ ትዕግሱ ብሎ ደንብ አርቃቂ፡፡ የአንድነት ደንብ በ2006 መጠነኛ መሻሻሎች ብቻ ነው የተደረገበት፡፡ ይህም በብሔራዊ ምክር ቤት ተወሰኖ ያለቀ ጉዳይ ነበር፡፡ አቶ ትዕግሰቱ ግን የተሻሻሉትን አንቀጾች እንዲያስገባ ኃላፊነት ተሰጥቶት ሁለት ዓይነት ደንብ አባዝቶ እንዲሰራጭ ያደረገው እና በወቅቱ ለምራጫ ቦርድ እንዳይገባ ያደረገው እራሱ ነው፡፡ ይህም የሆነው በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አመራር ወቅት ነው፡፡ ተጠያቂውም ግዛቸው ነው የሚሆነው፡፡ ይህን ሳቦታጅ ሲሰራ የነበረው ደግሞ ከአዲስ አበባ ሰብሳቢነት ተነስቶ ከስራ አስፈፃሚም እንዲወጣ በመደረጉ ነው፡፡ እውነቱን የተናገረው አልህ ምላጭ ያስውጣል የሚለው ነው፡፡ እርሱ ሰራ አስፈፃሚ ውስጥ ካልገባ አንድነት በምርጫ ቦርድ ቅርቃር ውስጥ ቢሆን ትዕግሰቱ ግድ የለውም፡፡ ይህን አስነዋሪ ሰራውን ሰው የማያውቅ መስሎት “የፖለቲካ ሳቦታጅ” ብሎ ሰው ለመክስስ አፉን ሲከፍት ግን ትንሽም ከጭንቅላቱ ጋር ሰላም እንደማይፈልግ ያስታውቃል፡፡ ለሆዱ የሚያድርን ሰው እንዴት አድርጎ ለእውነት ቁም ተብሎ ይጠየቃል? ለምንስ ዋሽ  ይባላል? በግለጭ ውሸታም ከማለት በዘለለ፡፡

ሌላው ነጭ ውሸት ደግሞ ምርጫ ቦርድ የአንድነት አመራርን አላውቅም አለ የሚለው ነው፡፡ ምርጫ ቦርደ የአንድነትን አመራር አላውቅም ብሎ በግልፅ ደብዳቤ ፅፎ አያውቅም፡፡ ከምርጫ ቦርድ ጋር ያደረግናቸውን ደብዳቤ ልውውጦች መመልከት ይቻላል፡፡ www.girmaseifu.blogspot.com :: ልክ ነው ምርጫ ቦርድ በህዝብ ግንኙነት ሰራተኛው በኩል ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባላቸው ግንኙነት የአንድነት አመራር እውቅና የለውም ብለው አውጥተዋል፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ላይ ሆነን ስናየው ፍንትው ብሎ የሚታየን ሀቅ አንድነት ላይ ዘመቻ በይፋ የተከፈተው የዛን እለት እንደሆነ ነው፡፡ የዚያን ዕለት ጀምሮ ጫማቸው ስር ብንወድቅ አንድነትን ድንክ አድርገን በእጃችን ለማቆየት ይቻል ነበር፡፡ በእኛ እጅ አንድነት ድንክ ከሚሆን ደግሞ ለእርሱ የሚመጥን ሌላ ድንክ ትዕግሰቱ አወሉ ስለ አለ በዚህ ደረጃ መወዳደር አያስፈልገንም፡፡ በጭንቅላታችን ያለው የአንድነት አስተሳሰብ ግን ሁሌም አብሮን እንዳለ እርገጠኛ መሆን ያሰፈልጋል፡፡

አቶ ትዕግስቱ ሌላ አስቂኝ አስተያየት ሰጥቷ፡፡ “ተለጣፊ የሚሉን ሰዎች ምንጫቸውንም ስናስስ አሁን ካለው ስርዓት አሰተሳሰብ የወጡ ናቸው፡፡ እኛ በዚህ ሂደት ያለፍን አይደለንም፡፡” ይለናል፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚከሰን የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች በሚል ሲሆን ትዕግሰቱ ደግሞ የዚሁ ስርዓት ውላጆች ይለናል፡፡ ለማነኛውም ትዕግሰቱ ከየት ወዴት የሚል አጭር መድበል የሚያውቁህ ሰዎች እንዲፅፉ ከማስታወስ ውጭ ከሀሰብ- እሰከ አዲስ አበባ ያደረካትን የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ጉዞህ የሚፈተሸ ሰው ይጠፋል ብዬ አልገምትም፡፡ በድህነትህ መቀለድ ስለማይገባ የኢኮኖሚ ጉዳይ ባይነሳ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ዳቦ መግዢያ ሲያጥርህ የደረሱልህን የፓርቲ አመራሮች የምትረሳቸው አይሆንም፡፡ በሰብዓዊነት እንጂ አንተን ለመግዛት እንዳልነበር ግን ልቦናህ ያውቀዋል፡፡

በመጨረሻም “ኮሚሽነር ጄኔራል” ትዕግስቱ አወሉ ስልጣንህን መከታ አድርገህ በፖሊስ መግቢያ መውጫ እንደማታሳጣን ተሰፋ በማድረግ አንድ ነገር ላንሳ፡፡ የኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከስልጣን መውረድን በተመለከተ ከአንተ እና ከአስራት አብርሃ ማን ነበር በትጋት የሰራው? በተለይ በሴራ መንገድ፡፡ አሰራት አብርሃም ሆነ እኔ በግሌ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው እንዲመራን እንደማንፈልግ በግልፅ ኣቋም እንደያዝን ይታወቅ ነበር፡፡ ለዚህ ነበር በስራ አስፈፃሚ በማንኛም አማላጅ አንገባም ስንል አንተ ሰራ አስፈፃሚ ለመሆን እድል ያገኘኸው፡፡ ምክንያታችንንም በግልፅ አስቀመጠናል፡፡ ነገር ግን አንተ ግዛቸው በሚመራው ካቢኔ ውስጥ ሆነህ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋርም ሆነ በሀገር ውስጥ ካለን ሰዎች ጋር ምን ስትሰራ እንደነበር ኢ/ር ግዛቸውም ሆነ ሌሎች ሁሉ የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡ ብትክድ ግን ብዙ ማሰረጃዎች ይቀርብብሃል፡፡ በዚህም መነሻ ግዛቸው አንተን ማየት እንዴት እንደሚጠላ ታውቃለህ፡፡ የግዛቸው ፍቅር እንዲህ ካቃጠለህ፡፡ ምነው ዛሬ አትደውልለትም እና ሰራ አስፈፃሚ ሁነኝ አትለውም?

ለማነኛውም፤

  • ተሰብሰበው የተሰጡህን ለፖለቲካ ያልደረሱ ህፃናት ይዘህ የምታመጣውን ለማየት እንጓጓለን፡፡ መልካም እድል አይባልም እንደ አንተ ያለን ክፉ ሰው እግዜር ይገላግለን ከማለት ውጭ!!
  • የምርጫ ቦርድ መቅረብ የነበረበት ሪፖርት የዘገየበትን ምክንያት ካንተ ውጭ ሌላ ሰው ካለ በአሁኑ ስዓት ሊመሰክር የሚችለው ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ስለሆነ ጋዜጠኞች ይህን ጥያቄ እንዲያነሱ አሳሰባለሁ፤ ግዛቸው መልስ አልሰጥም የለሁበትም ሊል አይችልም፡፡ ከትዕግሰቱ ባለነስ ለአንድነት መፍረስ ተጠያቂ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ እኛም ማስታወስ ይኖርብናል፡፡
  • አቶ ትዕግሰቱ ተመረጥኩ ያልክበትን ጉባዔ ተሳታፊዎች ዝርዝር መያዝና የአንድነት አባላት መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለብህ መዘንጋት የለብህም፡፡ የአንድነት አባል አይደለም፤ ዝም ብለህ የምትፅፈው 193 የስም ዝርዝር እንደሌለህ እናውቃልን፡፡
  • 2004 እና 2006 ደንብ እያልክ ማምታታት ማቆም አለብህ፡፡ የ2004 ደንብ ነው የሚገዛኝ ካልክ ደግሞ ኢ/ር ግዛቸውም ህጋዊ መሪ እንዳልሆነ መርሳት የለብህም፡፡ በተጨማሪ የአንድነት ፕሬዝዳንት የሚል ነገር የመጣው በ2006 ደንብ ሰለሆነ ሁሌም እራሰህን ከዚህ ማዕረግ አርቅ፡፡ አይመጥንህም፡፡
  • ፕሮፓጋንዳ ለመስራት ሰለማንፈልግ ነው እንጂ አዲስ አባለት ገብተዋል ያልከውን እናውቃለን፡፡ እነማን እንደሆኑ ዝርዝር ብታወጣ ጥሩ ነው፡፡ ከየትኛው ሰፈር ከተደራጀ ፎረም እንደመጡ ህዝቡ ያውቃልና፡፡
  • ሌላ ፓርቲ ለመግባት ሰለሞከሩት የአንድነት አባላት “ከሞራል አንፃር አይመከርም” ብለህ መምከር ሞክረሃል፡፡ ስለ ሞራል ለመምከር ለጊዜው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሞራል ብቃት እንደማይኖርህ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ እልህ ምላጭ ያሱጣል ማለትህ ልክ ቢሆንም የዋጥካት ምላጭ ግን ጩቤ ሆና እንደምትዘለዝልህ መርሳት የለብህም፡፡ ከአሁን በኋላ ምንም ብትውጥ ሞራል የሚባል ነገር ሊኖርህ አይችልም፡፡
  • በመጨረሻም የካቢኔህን ዝርዝር እና የትምህርት ደረጃ ይፋ ብታደርግልን በእውነት አንድነትን ምን ያህል ድንክ እንዳደረከው ህዝቡ ይረዳል ብዬ ስለማምን ፈቃደኛ ከሆንክ ብታደርግልን፡፡ ዝርዝሩ ለማነኛውም ምርጫ ቦርድ ገቢ አድርግ ያለበለዛ ሌላ አንጃ አስነስተው ከስልጣን እንዳያወርዱህ

አበቃሁ፡፡ መልስህን በዝርዝር እጠብቃለሁ!!!

Filed in: Amharic