>

ታሪክ መዛባቱ አያከራክርንም! ለመሆኑ ማን ነው ያዛባው? [ዩሱፍ ያሲን - ኦስሎ]

ESAT Interview with Isaias Afwerki: Part 1-2በቅርቡ ኤርትርያን የጎበኙት የኢሳት ጋዜጠኞች ከፕረዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ብዞዎቻችን እያነጋገረ ነው። እንደገና የሁለቱ ሃገራትና ሕዝቦች ዝምድናና የወደፊቱ እጣ ተጣማርነት በተለያዩ ሚዲያዎች መነጋገሪያ አጄንዳ እየሆነ እየመጣ ነው። ልክ እንደ በፊቱ እያወዛገበ ነው ማለቱ ሳይሻል አይቀረም። የኢሳት ጋዘጤኞቹ በኤርትራ ጉዞቸው ሌሎቹ ተጨማሪ ተልእኮዎች ነበሯቸው። እነሱንም አሳክተው ነው የተመለሱት።ዋናው ተልእኳቸው አድርገው የሄዱትን በኤርትራ በኩል የትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩትን ሃይሎችን ሁኔታ፣ ይዞታና እንቃስቃሴ በሰፊው ዳስሰው ለኢሳት ተመልካችና አድማጭ በተለየ፣ ለኢትዮጵያዊ በጥቅል በማሳወቅ ላይ ናቸው። የኤርትራ ሕዝብ አኗኗር ሁኔታም ተመልክተው በዲያስፖራ ለሚገኘው ሕዝባችን እያካፈሉ ናቸው። ከፕረዝዳንቱ በተጨማሪ ሌሎች የሃገሪቷ ባለሥልጣናትም ማነጋገራቸው ታውቆዋል።እነዚህን ርእሰ ጉዳዮች ሁሉ ይህ ጽሑፍ አይመለከታቸውም። ለጊዜው ትኩረቴ በፕረዝዳንቱ ቃለ ምልልስ ላይ ነው ። ከእሱም ውስጥ በተለይ ያነጣጠረው በታሪክ “መዛባቱ” ጉዳይ ላይ ነው። እንዲያውም ጠበብ አድርጎ ፕረዘዳንቱ የኤርትራና ኢትዮጵያ ሕዝቦች ትስስር አስመልክቶ የሰጡትን ረዥም ማብራሪያን ነው ቢባል ያስኬዳል። “ምዝንባዕ” የሚትለዋን የትግርኛ ቃል ብዙ ጊዜ ተደጋግማለች በፕረዘዳንቱ ኢንተርቪዩ ውስጥ።እንድያውም በእንግሊዘኛው የቃለ ምልልሱ ክፍልም “Distortion”አዝማችና ተዘውታሪ አባባላቸው ነበር።ትርጉሙ “መዛባት” ነው ወደ አማርኛ ሲመለስ።

ማኛውም ተገንጥሎ አዲስና ነፃ ሃገር የመመሥረቱ ውጥን “የተለየ ማንነት ባለቤቶች ነን” ነው ሥርዎ መሠረቱና ውልደቱ። አዲስ ማንነት ለይታው ደግሞ አንዱን የማንነት መግለጫ መካድና ሌላውን ማንነት መገለጫ ወይም ዝምድና ማረጋገጥ ሂደት ነው ተብሏል።ተገንጠለው አዲስ ሃገር ለመመሥረት ከሚገነጠሉባት ሃገር የግድ ዝምድናም ሆነ ታሪካዊ ትስስር ፈፅሞ የለንም ማለት የተለመደ አካሄድ ነው። የኤርትራ ነፃነት ትግልም ከዚህ ያፈነገጠ ሂደት ከቶ ሊሆን አይችልም። በቅድሚያ የግድ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ራሳቸውን “ነፃ ማውጣት” ነበረባቸው ማለት ይቀላል።ስለዚህ ለመዛባቱ ነበራዊ ምክንያቶች ነበሩ ለማለት ነው።

“ብሔረተኛነት” በመሠረቱ የተለየ ማንነትን መገለጫዎችን ተንተርሶ የራስን መንግሥት የመቀለስ ኢድዮሎጂና እንቅስቃሴ ነው ቢባል እምብዛም ማጋነን የለበትም። የመገንጠል ጥያቄ አንግበው ለሚነሱ ወገኞች ይህ ሂደት ተፍጥሯዊ ነው።የተለመደ የነፃነት ፍለጋ ትግል አንዱ አካል ነው። ስለዚህ ታላቁ መዛባት ኤርትራ “በረዥም ታሪኳ ራሷን በቻለ ሕልውናዋ” ከጎሮቤት ኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት ትስስር ሳይኖራት የዘለቀች ሃገር ነበረበች ትረካ መሠረቱ ይህው ነው። ስለዚህ ትስስሩና ዝምድናው መካድ ነበረበትና ተካደ፣ ባጭሩ።ኢትዮጵያ የመጨረሻዪቱ የኤርትራ ቅኝ ገዢ ሃገር ነበረች ትረካ ቦታውን ተካ። በዚሁ ኤርትራ የቅኝ ገዢዎች ፍርርቆሽ ታሪክ መሠረ በቱርክ፣ በግብፅ፣በጣልያንና በእንግሊዝ ተራ በተራ ከተገዛች በኋላ የመጨረሻዪቱ የኤርትራ ቅኝ ገዢ ሃገር ኢትዮጵያ ነበረች ነው፡። የዛሬ አያድረገውና “ሓበሻነት” ሲያልፍ አይነካካንም ዓይነቱ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ትረካውም ግልብ የዓረብ አሚሮችን ማሞኛ ማታልያ በዚህ ማዛባት ሥር ልጠቀስ የሚችል ታሳቢ ነው። ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊም ለሙዓመር አል-ጋዳፊ በትውልዱ የየመን ዓረብነት ዝምድናው ያረጋገጠው ይህንን ዱካ ተከትሎ ነው። የዛሬ አያደረገውና “ኮሌጅ ከመግባት ይልቅ ስምነት ሳዓት ከኢሳያስ ጋር ማሳለፉ ይበልጣል” ያለውም በዚያ ይፍ ይፍ በምያስብለው ፍቅራቸው ነበር።

የኤርትራ ብሔረተኛው እንቅስቃሴ ኤርትራውያኑን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ራሳቸው እንዲያገሉ ማድረግ ቀዳሚ ተግባሩ ነበር። “እኛ ኤርትራውያን እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደለንም ነው” የክርከሩ መነሻ።የራቢጣ እስላሚያው መሪው ሼክ ኢብራሂም ሡልጣን በ 1949 (እ.ኤ.አ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ላይ ከሰጡት ማብራሪያ አንስቶ የብሔረተኛው እንቅስቃሴ እንደርዳሪ ሃይሉ ” እኛ ኤርትራዊያን፣ በረዥሙ ታሪካችን የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ሆነን አናውቅም” ነው በየዓለም አቀፍ መድረክ ክርክሩና እሰጣ-አገባው ። በ30 ዓመቱ የነፃነት ተጋድሎ ዘመን የተደረገው የርዮተዓለሙ ማጠንጠኛ ይህው ነበ። የብሔረተኛ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ ከዚያ በፊት ወደ እናት ሃገራችን ኢትዮጵያ ጉያ እንመለሰ ብለው ለተ.መ.ድ.ጠያቂ ቡድን ከኢትዮጵያ መቀላቀል ፍላጎታቸውን ያረጋገጡትም ወገኖች ጭምር ለዚህ ዓላማ ከጎኑ ማሰለፍ ቻለ ማለት ነው።በመሠረቱ በዚህ ሂደት ብሔረተኛው እንስቃሴ ታሪክን ሁለት ጊዜ ነው ያዛባው።አንዴ በነፃነት ትግል ወቅት ሌላ ጊዜ ደግሞ ነፃነት እወጃ ማግሥት። በመጀመሪያው ጊዜ የነፃነት ትግሉን ሕጋዊነት ለማለባስ ተብሎ፣ ሌላው ጊዜ ደግሞ የአዲስቷ ሃገር ነፃ ሃገራዊ ሕልውናን ለማረጋገጥና የግድ አዲስ ሃገራዊ ማንነት ለማስረፅ ስሉ።ይህ በሃገሮች ግንጠላ ታሪክ ያልተለመደ አካሄድ አይደለምም፣ አልነበረምም።

የታሪክ መዛባቶች መኖራቸው ከተቀበለን ዘንዳ ቀጣዩ ጥያቄ ለመሆኑ ማን ነው? ታሪክን ያዛባው ነው የሚሆ ነው። እንዴት? የትኛው ዓላማ ለማሳካት? እንደ ወትሮው በርካታ ጥያቄዎች መግተልተላቸው አይቀሬ ነው።እውነት እነዚህ የታሪክ ማዛባቶች ናቸው በሁለቱ መንግሥታት ብሎም ሕዝቦች መሓል መልካም ጉርብትና ግንኙነት እንዳይኖር ዳንቃራ ሆነው አሁንም የሚያስቸግሩን? ላለመግባባቶቻቸን መሠረት የሆኑት? እነሱን ከመንገዳችን አስወግደን ማለፊያ በይነ-መንግሥታት ትስስር እንዴትስ ነው የምንፈጥረው?የኤርትራ ፕረዝዳንት ለምን በአማርኛ አልተናገሩም፣ ለምን ስለ አስተዳደጋቸው፣ ስለ ቤተ ሰብ ሁኔታቸው በሚገባ አልገለፁም ዓይነቱ ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ መዘፈቅ አይዳዳኝም።ግን ስለ ድርጅቶቹ ምስጢራዊነትና ስለ መሪዎቻችን ማንነት አደባባይ የማይወጡ መገለጫዎች እንደ አንድ የግርጌ ሕዳግ ጣል ማድረጉ አይከፋም።ወደ ጽሑፉ ማሳረጊያ ላይ እመለስበታለሁ።

ባጭሩ ሲጠቃለል፣

  • ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ትስስር ኖሯት አያውቅም
  • ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ-ግዛት ነበረች
  • ከትግራዊ ኢትዮጵያውን ጋርም ዝምድና የለንም
  • ሓበሻም አይደለንም ፣ዓረብ እንጂ

ብለው የሚያስተጋቡ መመሪያዎች በዚያን ጊዜ እንደ አንድ የትግል መሣሪያ የተወሰዱ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር የነበራቸው ትስስር የመካዱ ሥር የሚካተቱ ዋናዎቹ የብሔረተኛው ወገን ድርጊቶች ናቸው ለእኛ የታሪክ መዛቦች ሆነው የሚታዩት። ስለዚህ ክቡር ፕረዝዳንት! “ታሪክ መዛባቱ አያከራክረንም! ነገር ግን አንድ ጥያቄ መልሱልን ለማለት ይሚንገደደው።ለመሆኑ ታሪክን ያዛባው ማን ነው? እነዚህ በመሰሉ የሕዝቡን ማንነት “የሚያዛቡ መዛባቶችን” ሲገፋ የነበረው ማን ነው?እነዚህ “ማንነት ያዛቡ ” ታሪኮች ናቸው የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነትን “ያዛቡትም” አልፎ ተርፎ የመረዙት ከሚለው ግንዛቤ ነው አነሳሴ።

እነዚህን አባባሎች ገባ ብለን እንመለከታቸው፣ እስቲ፦

ለዓረቦች ኢትዮጵያ እንደ ሃገር መጠሪያ ስሟ ሓበሻ ወይም አል-ሓበሻ ነው። ሌላ ትርጉም የለውም።ከታሪክ መዛግብት እንደምንረዳው፣ ከቅድመ እስልምና ጊዜ የነበራት ስያሜ ነው።አሁን በቅርቡ በወጣው ISIS የወደፊቱ ሙስሊማዊ ካሊፌት ካርታቸው ላይ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ኤርትራ ጋር ባንድ ላይ መድረ ሓብሻ (አርዳል-አልሓበሻ) በተሰኘው እንደ አንድ ትልቅ አድያም (ወላያ) ወይም ክፍፍል ነው የተከለለችው።በነፃነቱ ትግሉ ዘመን ዓረብ ሃገሮች “ሓበሾች ነን” ነገር ግን “ከሓበሻ ቅኝ ግዛትነት” ነፃ አውጡን ብለው እርዳታ መጠየቁ አስቸጋሪ እንደምሆንባቸው አያጠያይቅም።ግራአጋቢነቱም ያቺ በነፃነት አከባባር ዕለት ላይ ላቧ የተንጠፈጠፈ ከበሮ እየደለቅች ፃሓፊ ተስፋዬ ገብረአብ አገኝቷቸው ያን የመሰለ ፍንደቃቸው ምክንያት ሲጠይቋቸው “ከኢትዮጵያ” ነፃ የወጣንባት ዕለት በመሆኑ ነው” ያሉት የአሥመራ ወይዝሮ ታሪክ ያስታውሰኛል።ጋዘጤኛው “እናቴ! ስሞዎትን ማን ልበል” ብሎ ላከታተለው ጥያቄ ግን ምንም ሳያንገራግሩ ፈርጠም ብሎ”ኢትዮጵያ! ነዋ” በማለት የሰጡት መልሳቸው ፈገግ ከማድረጉ በላይ ነው “ቁጥርጥር” ያለው የአካባቢው የማንነት ግራአጋቢነት ገላጭ ነው።

ይህ ዓይነቱ የማንነት ግብግብ ነው እንግዲህ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ከሲዳማ ነፃ አውጪ መሪ ከነበሩት ከሟቹ ወለደአማኔል ዱባሌ ጋር በኢትዮጵያ ታሪክና ዲሞክራሲ ጉዳይ በ 1986 በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ክፉኛ አፋጥጦ ግብግብ ያስገጠማቸው። ምስክርነቱን የሰጠው የኤርትራ ሕዝባዊ ሓርነት ግንባር (ኢ.ፒ.አል.አፍ) የቀድሞ ታጋይና የስለላ መረቡ የቀድሞ ተወካይ የነበረው የማነ ተክለጊዮርጊስ ነው። ባለታሪኩ በ 21 አውዲዮ-ካሴት በአሰና ራዲዩ በሰራጨው ረዥም የትግል ታሪኩና ስለ ፕረዝዳንት ኢሳያስ የሰጠው መግለጫ እምብዛም አውንታዊ ገፅታ የተላበሰ ባይሆንም ቅሉ “እኔ የምመለከተን የኢትዮጵያንና በሃገርቷ ዲሞክራሲ የማስፈን ጉዳያችን አይደለም ፣ የሲዳማ ነፃ ማውጣት እንጂ” የሚለውን የአቶ ወለደአማኔል ክርክር በብርቱ እንደመከቱ ይመሰክርላቸዋል።

አቶ ኢሳያስ “ግንባራችን ኢትዮጵያን የማበታተን ዓላማ የለውም” በማለት ፈርጠም በማለት ነገሯቸው ይላል አቶ የማነ። እንዲያውም ቃል በቃል “ኢሳያስ ሊያብድ ነበር” ይላል (10ኛው አውዲዮ ከደቂቃ 55፡16 ጀምሮ) የቀድሞ የስለላ ወኪልና የዚያን ጊዜ ግንባሩን ከኋላ የሚያሽከረክረው የሕቡዕ የኤርትራ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ አባል የምስክር ቃሉን ሲሰጥ። ስለዚህ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “የትግራይ ነፃ ሪብፕሊክ ምሥረታን አልተቀበልንም ” አባባላቸው፣ እኔም ለመቀበል አላንገራገርኩም። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ስብስቦች የራሳቸው መንግሥት ምሥረታ ውጥን የማይቀበሉበት ተጨማሪ ምክንያት እንደነበራቸው ልብ እንበል።ሁሉ ነፃ አውጪ ተብሎ ነፃ መንግሥታት ምሥረታ ትግል ካፋፋሙ የኤርትራ ጥያቄ ዋጋ ያሳጣዋል።ይራከሳል እንበል! ባልረቀቀ ቋንቋ። ያጉዳያቸው ልዩ ጥያቄና ከብሔራዊ ጥያቄዎች ጋር አለመመሳሳሉን አጠያያቂ ያደርግባቸው ነበር ፣በሌላ አባባል።ለወዲ አሥመራ የትግራዊ ሪብፓብሊክ ሆነ የሲዳማ መንግሥት ምሥረታ ፍላጎት ” ከኤርትራውያኑ ጋር የመወዳደር ከማን አንሼ ማንጠራራት” ተደርጎ ቢወሰድ አይገርመኝም።ለመቀበል የሚያስቸግሩን የአቶ ኢሳያስም ሆነ የአቶ የማነ ትርክቶች ግን በርካታ ናቸው። ለምሳሌ የ10 ዓመት የሽግግር ጊዜ ጠይቀን ነበር፤ ባንዱ ወይም በሌላው የመንግሥታዊ ቁርኚት እንጣምር ብለን ወያኔ እምቢ አለን ዓይነቱ አባባሎች ለማመን ያስቸግራሉ። የማንቀበለውና የማይዋጡን ለይተን በምክንያታዊነት እንጂ በጥላቻም ሆነ የሰሞነኛው ደርሶ የኤርትራ ትግልና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አቱንኩብን ባይ ጥብቅናም ሆነ የፕሮፌሰር ሙሴ ተገኝ አሥመራ ደርሶ-መልስ ተሞክሮ ምሬት ስሜታዊነት ቦታ ሊኖረው አይገባም። “አሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሃገር ልጅነት” መጽሓፌ ውስጥም አልፎ አልፎ እነዚህ የማንነት አወሳሳቢ ታሳቢዎችን በመጠኑ ተዳስሰዋል።ለመጽሓፌ ማስታወቂያ እያደረግኩ አለመሆኔን ይታወቅልኝ ሓረግ መጨመር ልያስፈልግ ነው መሰለኝ!።ከዚህ በተጨማሪ ዓለምሰገድ ዓባይና የኖርዌይ ተወላጅ የሆነው ሸቲል ቱሮንቮል በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ወቅት በሁለቱ ትግሪኛ ተናጋሪዎች ማለት ትግራዊ ኢትዮጵያውና ትግርኛ ስብስብ ነኝ ባዩ ኤርትራዊ ብሔረሰብ መካከል በተለያዩ የትግሉ ወቅቶች የታዩትን የማንነት መለዋወጦች አጥንተው የምርምራቸው ውጤት አቅርበዋል::የሁለቱም መጽሓፎቶች ርሶች በግርጌው ተመልክተዋል።

ገና ገና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከዓረቦች ጋር ሳይገናኙ ፣ ዛሬ በሚያስገርም ሁኔታ የሚያቀላጥፉት ዓረብኛም ሳይማሩ ገና ገና ድሮ ለወታደራዊ ትምህርት ከታላኩበት ቻይና ሳይመለሱ እነ ዑስማን ሣሊሕ ሳቤ አይገቡ ገብተው በኤርትራ ዓራባዊ ማንነት የዓረብ አሚሮችና ርእሳነ መንግሥታት ድጋፍና እርዳታ ይሸምቱ ነበር። የሻዕቢያ ወታደራዊ ክንድ የፈረጠመውም በዚሁ ማቴሪያልና የገንዘብ እርዳታ አማካኝነት ነው ቢባል እምብዛም ማጋነን የለበት።ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ 25 ዓመታት ከነፃነት እወጃ በኋላም ኤርትራ እንደ ሃገር የዓረብ ሊጉ (ራቢጣው) ተመልካች አባል እንጂ ሙሉ አባል አልሆነችም።ሌለኛው የኤርትራ የማንነት ለይታ ያወሳሰበው ወገንተኛነት አሰላለፍ እንበለው!

ቅኝ ተገዢዎች እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደለንም፣ ጥያቄያችንም ቅኝ ግዛታዊ ነው ብቻ ሳይሆን ከእኛ ጋር አብሮ ለመታገል ይህንን የጥያቄያችን ባሕርይ መቀበል የግድ ነው ባዮች ነበሩ፣ የሻዕቢያ መሪዎች በዚያን ጊዜ። መለስ ዜናዊና የትግል ጓዶች ይህንን ተቀብለው ነው ድጋፍና ትብብር የተለገሳቸው። ይህንን መቀበል አሻፈረን ያሉትማ ድጋፍና ትብብር ተነፈጋቸው።ይባስ ተብሎ ወያኔና ሻዕቢያ ባንድ ላይ በመሆን ተዋጓቸውና ከትግል ሜዳ ውጭ አደረጓቸው። በዚህ ድግግፎች ሁለቱም ዓላማቸው ለማሳካት ስለበቁ ሁለቱም ተጠቃሚዎች ነበሩ። win-win situation ነው የሚትሉት! ይህ ብቻ አልነበረም።ከነፃነት በኋላም ባንድ ላይ የሚያጣምራቸው የጋራ አንገብጋቢ ግቦች ነበሯቸው። ሻዕቢያ በዓለም መድረክ ለአዲስቷ ሃገር ነፃነት የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ማረጋገጥ ነበረበት።ሌላ ምክንያትም ነበረ።ከእነሱ ድርጅት ሌላ ማንም ኤርትራዊ ድርጅት እውቅና እንዳይሰጠው ፍላጎት ነበራቸው። 1991 ለአዲስ አበባው የሰኔ የሽግግር ኮንፊረንስ ኢሕአፓና የመኢሶን መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የኤ.አል፣ኤፍ አንጃዎች መሪዎችም ያልተጋበዙት እንበለ ምክንያት አልነበረም። ውያኔ/ ኢሓዴአግ በሚግባ መሬት ሳይቆናጠጥ ከቀድሞ የትግል አጋሩ አለመግባባት መፍጠር አይፈልግም ነበር። እነዚህ ታሳቢዎች ብዙ የሚያነታርኩ ጉዳዮች አይመስሉኝም።

እመለስበታለሁ ያልኩትን አደባባይ የማይወጡ የድርጅቶች መሪዎች ማንነት መገለጫዎች አልዘነጋሁም። ልከ እንደ ትናንቱ በአጼ ሃይለሥላሴ ዘመን የእናታቸው ስም (የሺእመቤት ዓሊ ጋንቾ ፈረዶ?) እንኳን በትክክል በይፋ ሊታወቅ ቀርቶ የሃገር ሕልውና -ነክ ምስጢር መስሎ ይታይ እንደ ነበረ የእናቱ ዘመዶች ሆኑ ፕረዝዳንት ኢሳያስ ራሳቸው ከትግራዊ ጋር የሚያቆራኛቸው የስጋ-ውልደት ዝምድና አሁንም የተጠቀሰ ነገር የለም።በተቃራኒው የሟቹ የመለስ ዜናዊ እናት ኤርትራዊነትና የሠራዬ አውርጃ ተወላጅነት ሃገር ያወቀው የአደባባይ ምስጢር ነው።አብራሃም ያየ የዛሬ ስንት ዓመት በፊት እሱ ከመረብ ሻገር ካለው ሠራዬ አውራጃ ብቻ ሳይሆን ከሦስቱ የኤርትራ ከበሳ ወይም ደጋ አውረጃዎች ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር ያላቸው ጥልፍልፍ ያለ ማን ማን ቢወልድ የስጋና የደም ውህደት በግራፍ መሰል አገላለጽ በትግርኛ ከሽኖ አስነብቦናል።አባይ ስብሓትም ኤርትራዊ ቁርኚታቸውን አለደበቁም ወይም አላፈሩበትም ሊበል።በተቃራኒው የኤርትራ ቁንጮ ባለሥልጣናት መረብ-ሸገር ትውልድ ሓረግ እንደ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆነ እንደ አንድ የሃገር ሕልውና ምስጢር ዛሬም በአሥመራ በሽኩሽኩታ ነው የምወሳው።አይገርምም! ይቺ ደግሞ ዓቢይ መነገገሪያ ጉዳይ ሆና ነው እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ።ግልፅነት የክፍት ሕብረተሰብ አንዱ መለያ መታወቂያ ነው። በዚህ አካባቢ የምንመለከተው የግራአጋቢው የማንነት ልውውጦች ማሳያም ጭምር ነው።

በመጨረሻ ይህንን የሁለቱን ሕዝቦች ፣ እደግመዋለሁ የሁለቱን ሕዝቦች የወደፊት ትስስርና የሁለቱ መንግሥታት የወደፊቱ አዘቦታዊ በይነ-መንግሥታዊ ግንኙነት ያሰናከለው የታሪክ “መዛባት” ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ በቃለ ምልልሱ እንደሚያረጋግጡት እውነት የሚገባ የተሰነደ ታሪክ ከሆነ እዳው ገብስ ነው። “መዛባቱን” የማጥራቱ ቀዳሚው ተግባር ለተመራማሪ ፈታሽነት ለባለሙያዎቹ ማቀረብ ብቻ ነው ። መቼም እስካሁን የሰንዶቹ የምስጢራዊነት ይርጋ ዘመን ይገባደዳል በሚል ተስፋ በመሰነቅ ነው። እነዚህ ሰነዶች ለታሪክ ተመራማሪዎች ክፍት ማድረግ ነው።በዚህ ምርምር መንግሥት አወዳሽ ምሁራን ጎን ለጎን በሂስነታቸው የሚታወቁትን ፕሮፌሰር ተከሰተ ነጋሽ፣ ተስፋፅዮን መንግሥቱ የመሳሰሉ ምሁራን መጨመር ሊያስፈግ ይችላል። ውጤቱ ታማኣንነት እንዲላበሰ ከተፈለገ ማለቴ ነው።

በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ትስስር አለ። በሥልጣን በተደላደሉ መንግሥታት መካከል ግን ለትስስሩ መንስኤና መነሻ እስተረተጂካዊ ጥቅማጥሞች ናቸው ።በሁለት ድርጅቶች መካከል የነበረው በጋራ ጠላቶች ላይ የጋራ ክንዳቸውን በማሳረፍ ውለታ የመዋዋል ግንኙነት ተክቲካዊ ነበረ።ግንባሮቹም አይክዱም። ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩበት።ይህ ሓቅም አይክዱም።ከ 1975 ጀመሮ እስከ አሥመራና አዲስ አባባ በድል መግባቱ ድረስና ከዚያም በኋላም።የዚህ ፅሑፍ ዓላማ የሁለት ነፃ አውጪ ድርጅቶች ፀረ ደርግ ቃልኪዳና “እኔ ነኝ ውለታ የዋልኩልህ ፣ እኔ ነኝ እንጂ የዋልኩልህ” ገራንጃና እሰጣ-አገባ ለዚያኑ ጊዜው የጦር ኮማንዶሮቻቸው መተው ሳይሻል አይቀርም። እነሱ ይወዛገቡበት። በቅርቡ ሜጀር ጀነራል ፃድቃን የሰጠው እንተርቪዩን ይመለከታል።እኛ ጉዳያችን የወደፊቱ የሁለት ሕዝቦች ትስስር “ሊያዛባ የሚችለውን የታሪክ መዛባት” ነቅሶ ማውጠት ነው ብለናል።

አሁንም የምናወሳው ስለ ሁለቱ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ማለት ወያኔና ሻዕቢያ የጋራ ትግል ታሪክ፣ ትስስርና ውዝግብ እንጂ ሰማኒያ በላይ ስለ ሆኑት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ዘጠኙ የኤርትራ ማሕበረሰቦች ግንኙነትና ታሪክዊ ትስስር እንዳለሆነ መዘንጋት የለበትም።ገፋ ቢል ስለ ሁለ መረብ ዳርቻ ስላሉት ሁለቱ የትግርኛ ተናጋሪዎች ታሪክ መዛባት ነው።ተወደደም ተጠላም ወሳኝ ሚና ያላቸውም አሁንም በመረብ ወንዝ ዳርቻ ያሉት ትግራዊና ትግርኛ ስብስብ ትስስር ብቻ መሆኑን መሰመር ያለበት ሓቅ ነው።ይህም ሌሎቻችን መቀበል ያለብን መራራ ሓቅ ይመስለኛል።የታሪኩን መዛባት ለማስተካከል ብቻ ሳይሆን ዘላቂው ሰላምና መልካም ጉርብትናም ሆነ ማለፊያ የወደፊት ቁርኚት ወሳኙ የሁለቱ ማለፊያ ግንኙነት መሆኑ ላንድ አፍታም መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም።

እነዚያ ኤርትራን ተራ በተራ በቅኝ ግዛትነት ተፈራረቁባት የተባሉት ቱርኮች፣ ግብፆች፣ ጣልያኖችና እንግሊዞች ጓዛቸውን ሸክፈው በመጡበት እግር ወደ ሃገሮቻቸው ተመልሰዋል። እድሜ “አልዛባ” ላለው ጆዮግራፊ “የመጨረሻ ቅኝ ገዢዎቹ″ ግን እንደ ጥንቱ በነበሩበት አሁንም እንደ ጎሮቤት አሉ።የትም አልሄዱም። የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ትስስር መሠረቱ እዚያ ላይ ነው። ባንዱ ወይም በሌላው የመንግሥታት ተጣማሪነት ባይገናኙም ቢያንስ ጎን ለጎን በጉርብትና መኖሩ እጣ ፋንታቸው ሆኖዋል።ከሁሉ በላይ ያለፈውን ታሪክ ብቻ ሳይሆን መጪው እጣ ፋንታቸው የተቆራኘው።መንግሥታትም ድርጅቶችም ጠፊዎች ናቸውና።ሃገሮችና ሕዝቦች ይኖራሉ።በጉርብትና ይኖራሉ።ጎን ለጎን ባንድ ሃገር ጥላ ሥር ወይም በሁለት ራሳቸውን በቻሉ ሃገራት ዜግነት።ኤርትራ በትግል ነፃነት መቀጀት ቻለች።ወያኔ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ቻለ።እንኳን በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መሓል ሰላም ሊያሰፍኑ ቀርተው በድርጅቶቻቸው ውስጥ መረጋጋት መፍጠር አልቻሉም። ሁለቱ ድርጅቶች ቢታረቁም ቢጠፋፉም የሕዝቦቻችን እጣ-ፋንታ ተጣማርነት ከእይታችን መራቅ የለበትም።ከጊዜያዊ ድሎች ባሻገር አሻግረን እንመልከት!

ጉዳዩን ጠለቅ ብላችሁ መመልከት ለምትሹት ተጨማሪ ንባብ፣

  • ዩሱፍ ያሲን ፣ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች- ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና፣ በሳን ሆዜ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት ኮንፊረንስ ማርች 2010
  • ዩሱፍ ያሲን ፣ አሰባሳቢ ማንነት ፣ ባንድ ሃገር ልጅነት ኤሶፕ አሳታሚ 2014
  • ሓሰን ዑመር ዓብደላ፣ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ያልተጠናቀቀ ፍቺ፣ ያልተቻለ ጉርብትና፣ ታህሣስ 1991 ጦቢያ መጽሔት
  • Hassan Umer Abdalla,Ethiopia & Eritrea: Let’s get the facts clear 2009 (http://www.ethiomedia.com/adroit/2560.html)
  • Abbay, Alemseged, Identity Jilted or Re-imagening Identity? The Different Paths of the Ertitrean and Tigrayan Nationalistic Struggles, Red Sea Press, 1998
  • Tronvoll, Kjetil, War & Politics of Identity in Ethiopia, Making of Enemies & Allies in the Horn of Africa, 2009

 

Filed in: Amharic