>
5:30 pm - Sunday November 2, 8769

ውይይታችን ኢሳያስ መልዓክ ነው ያድነናል አልያም ጭራቅ ነው ያጠፋናል አይነት ባይሆን?[አዜብ ጌታቸው]

Esat interview with Isayas Afewerkiበቅርቡ የኢሳት ጋዜጠኞች ወደ አስመራ ተጉዘው፤ የወያኔን አገዛዝ በትጥቅ ትግል ለመፋለም የተሰለፈው ወገን የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተመልክተውና እንደ ጋዜጠኛ ዘገባቸውን አጠናቅረው ተመልሰዋል። ይህም ተግባራቸው ኢሳት እንደ ህዝብ ሚዲያነቱም ሆነ የወያኔን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለመጣል የሚደረገውን ሁለንተናዊ ትግል በተግባር በማገዝ ረገድ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄዱን ያረጋገጠ ነው ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። ይህ ስሜት የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስሜት መሆኑንም በተለያዩ መንገዶች አረጋግጫለሁ።

የኢሳት ጋዜጠኞች ወደ አስመራ ተጉዘው ካጠናቀሩት ዘገባዎች ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ኢትዮጵያዊውን ወገን እያወያየ ያለው ከኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡

ለዚህም በቂ ምክንያት አለው። ኢሳያስ አፈወርቂ ወይንም ሻቢያ ሃገራችን አሁን ለምትገኝበት አጣብቂኝ ግዙፍ የሆነ ሚና የተጫወቱ መሆናቸው ነው፡፡

የኢሳት ጋዜጠኖች ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስን አስመልክቶ አቶ ክንፉ አሰፋ የጻፈውን አስተያየት አንብቢያለሁ።ልናስተውላችው የሚገቡ ነጥቦችን አንስቷል። ቀጥሎም የአዲስ ድምጽ ጋዜጠኛ አበበ በለው ክንፉ አሰፋንና ሌሎች ሁለት እንግዶችን በመጋበዝ በዚሁ በፕ/ት ኢሳያስ ቃለ መጠይቅ ዙሪያ ከሁለት ሰአት በላይ የዘለቀ ሰፊ ወይይት መድረክ አዘጋጅቶ አስደምጦናል።

አበበ ይህን ውይይት ያዘጋጀው በቃለ ምልልሱ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች እየተደመጡ ስለሆነ እንደ ጋዜጠኝነቱ ሽፋን ለመስጠት አስቦ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና አበበ የጋበዛቸው ሶስቱም እንግዶች አንድ አይነት አመለካከት ያላቸው መሆናቸው አድማጭ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው አላደረገም።

በርግጥ በአንድ ክስተት ዙሪያ ሁለትና አንዳንዴም ከሁለት በላይ የሚሆኑ ተቃራኒ አመለካከቶች ሲኖሩ ከተቻለ ልዩነቶቹን ለማጥበብ አልያም ለአድማጭ/አንባቢ ብዥታውን ለማጥራት ይህን መሰል ውይይት ማድረጉ ጠቃሚ ነው። ለዚህም እውን መሆን ጋዜጠኛው የተለያዩ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ጋብዞ ሁሉም በየበኩላቸው እውነቴ የሚሉትን እንዲገልጹ ያደርጋል። አድማጭም ግራ ቀኙን ሰምቶ ብዥታውን በጥያቄ አጥርቶ ያመነበትን ይቀበላል። ያላመነበትን ይጥላል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት ወገኖች ሁሉ አንድ አይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከሆኑ መድረኩ አንዱን አመለካከት ብቻ በአድማጭ ውስጥ ለማስረጽ ያለመ የፕሮፓጋንዳ መድረክ ይሆናል። እንደ ነጻ ጋዜጠኛ ይህን ማድረግ አይደገፍም።ትክክልም አይደለም።

አበበም በዚህ የውይይት መድረክ የጋበዛቸው ሰዎች አንድ አይነት አመለካከት ያላቸው በመሆናቸው ውይይቱን ሙሉ አላደረገውም። ጋዜጠኛ ክንፉን የጋበዘው በቅርቡ ለንባብ ያቀረበውን ጽሁፍ መሰረት አድርጎ እንደሆነ ነግሮናል። በቂ ምክንያት ነው። ሌሎቹ ሁለት እንግዶች የተጋበዙት ግን ቀደም ሲል በሻቢያ በደል ደርሶብናል የሚሉ ወገኖች ናቸው። ይህ ደግሞ ለምን የሚል ጥያቄ ያጭራል?

አዎ ለምን ለሚለው ጥያቄ አበበ በውይይቱ ላይ መልስ ለመስጠት ሞክሯል። በውይይት መድረኩ አንድ አይነት አመለካከት ያላቸውን ወገኖች የጋበዘበትን ሁለት ምክንያቶች ገልጿል፡፡

1ኛው ምክንያት በኢትዮጵያዊያን መካከል በተቃራኒ ሃሳቦች ዙሪያ በቀናነት የመወያየት ልምድ ስላልዳበረ ይህን ማድረግ አልቻልኩም የሚል ሲሆን

2ኛው ምክንያቱ ደግሞ፦ ሌላኛው አመለካከት በብዙ መድረኮች ሲንጸባረቅ ስለሰማሁ እድል ላላገኘውን አመለካከት እድል ለመስጠት ነው የሚል ነው።

በኔ አተያይ ሁለቱም ምክንያቶች በቂ ምክንያቶች አይደሉም። ለምን? በመጀመሪያ በኢትዮጵያዊያን መካከል የአመለካከት ልዩነቶችን ለማጥበብ በቀናነት መወያየት የተለመደ አይደለም ባለው ነጥብ እስማማለሁ። በርግጥም የአመለካከት ልዩነቶች ሲኖሩ በውይይት ወደ ስምምነት ከመድረስ ይልቅ እርስ በእርስ በመፈራረጅ ወደ አላስፈላጊ ቅራኔ ማደጋቸው የምናየው እውነት ነው። ይሁንና ይህን መጥፎ ልምድ ለማስወገድ ከማንም በላይ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ያለበት ጋዜጠኛ ነው። ነገር ግን አበበ ይህ በተቃራኒ ሃሳቦች ላይ በቀናነት መወያየት ያለመቻል መጥፎ ልምድ ሊወገድ እንደማይችል ሁሉ፤ አንድ አይነት አመለካከት ያላቸውን ወገኖች የጋበዝኩት የቀና ውይይት ልምድ ስለሌለን ነው ብሎ ማቅረቡ እንደ ጋዜጠኝነቱ ውኃ የሚቋጥር ምክንያት አይመስለኝም።

ሁለተኛው ምክንያቱ ደግሞ፦ ሌላኛው አመለካከት በብዙ መድረኮች ስለተገለጸ እድል ላላገኘው እድል ልስጥ ብዬ ነው የሚል ነው። ይህ ምክንያት ደግሞ በራሱ የአመለካከት ልዩነቶችን አስፍቶ ቡድናዊ ስሜት የሚፈጥር ነው። አበበ ማየት ያለበት የራሱ መድረክ ፌርና ባላንስ መሆኑን ብቻ እንጂ ከሱ ሬድዮ ውጭ ያሉ ሚዲዮችን ባላንስ ለማድረግ መሆን የለበትም። ይህም ምክንያት በቂ አይመስለኝም፡፡ ለኔ በቂ ምክንያት የምለው ሌላው ወገን ግብዣ ቀርቦለት ግብዣውን አልቀበልም ካለ ብቻ ነው።

በነገራችን ላይ አበበ በለው ላለፉት በርካታ አመታት የወያኔን መንግስት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ለማውረድ ሲደረግ በቆየውና እየተደረገ ባለው ትግል የግንባር ስጋ ሆነው አገዛዙን ከሚፈታተኑ ታጋዮች አንዱ በመሆኑ አክብሮቴን ልገልጽለት እወዳለሁ። የእርምት አስተያይቴንም እንደሱ ሁሉ በተቃዋሚው ወገን እንቅስቃሴ ዙሪያ በየግዜው የሚከሰቱ የአመለካከት ልዩነቶች ወደ ከፍተኛ ቅራኔዎችና የቡድን ስሜቶች እንዳያድጉ ካለኝ ስጋት የሚመነጭ እንደሆነ እንደሚረዳልኝም ተስፋ አለኝ።

ስለ ውይይት መድረኩ ይህን ያህል ካልኩ የውይይቱን ይዘት በተመለከተ ደግሞ ጥቂት ልበል። ሶስቱም ተወያዮች አስተያየታቸውን የሰነዘሩት ፍጹም ጨዋነት ባልተለየው ለሌላው እንቅስቃሴ አክብሮት ባልነፈገ መልኩ መሆኑ በጣም አስደስቶኛል። በተለይ ወደ አስመራ ለተጓዙት ጋዜጠኞችና ለኢሳት ያላቸው አድናቆትና ክብር በተደጋጋሚ ሲገለጥ መስማቴ፤ የለንም የምንለው የሰለጠነ የውይይት ልምድ ባለቤቶች ለመሆን መንገድ መጀመራችንን ያመላከተ ነው እላለሁ።

ማንም ወገን የሌላውን መብት ባልነካ መልክ የግሌ የሚለውን አመለካከት የመግለጽ መብት አለው። የወያኔን አገዛዝ የምንታገለውም ይህን መብት አሳጥቶ ከሃገር ስላስወጣን ነው። እኔ ያልኩትን ተከተሉ፤ የኔ እውነት ብቻ ይደመጥ አይነት አካሄዶች ፍጹም ተቀባይነት የላቸውም።

የአመለካከት ልዩነቶችን ወደ ግዙፍ ቅራኔ የሚያሳድጉ መጥፎ ልምዶች እንቁላል ጥለው የሚፈለፈሉት “ህይወትም መንገድም እኔ ነኝ” አይነት አመለካከት ባላቸው ወገኖች ጉያ ነው።

ይህን ደጋግሜ ያነሳሁት የሰለጠነ የውይይት ልምድ በማጣታችን ቀጫጭንና በውይይት ሊጠፉ የሚችሉ ልዩነቶች እያራራቁን በጋራ ልንሰራቸው የሚገቡ በርካታ ስራዎች ሳይሰሩ ቀርተው የመከራ ግዚያችንን አንድ ብለን ጀምረን እንሆ 24 አመታት በመድረሱ ነው።

የአበበ በለው ሬድዮም ሆነ ሌሎች መሰል መድረኮች ያለምንም ፍርሃት ፤ ማግለልና ወገንተኝነት በህዝቡ ውስጥ ያሉ የአመለካከት ልዩነቶችንና ብዥታዎችን በማጥራት ቢቻል ወደ አንድ አቅጣጫ ባይቻልም ልዩነትን ይዞ ተቻችሎና ተከባብሮ የመስራትን ልምድ ማበረታታት ይጠበቅባቸዋል።

ወደ ፕ/ር ኢሳያስ አፈወርቂ ወቅታዊ ቃለ ምልልስ ልመለስ፤

በመጀመሪያ ውይይቱ ኢሳያስ ጭራቅ ነው ይበላናል! ኢሳያስ መልዓክ ነው ያድነናል አይነት ግራና ቀኝ ጫፍ የረገጠ መሆን ያለበት አይመስለኝም።

ከላይ እንደገለጽኩት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፉት በርካታ አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ.. ውስጥ ትልቅ አሉታዊ ሚና የተጫወቱ ሰው መሆናቸው ግልጽ ነው። በመሆኑም ፕ/ት ኢሳያስ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀና ያስባሉ ብሎ ለመቀበል የ.. ዓመታቱ ጥቁር አሻራቸው ይጋርደናል። ይህ ደግሞ የማያከራክር ፤ያፈጠጠ! ያገጠጠ! እውነት ነው።

ለዚህም ነው ቃለ መጠይቃቸው ይህን ያህል አወያይ ሊሆን የቻለው። አዎ ኢሳያስ አፈወርቂ አመኑም አላመኑም ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት ምስቅልቅል …ከወያኔ ባላነሰ ሚና ተጫውተዋል። ቃለ መጠይቃቸውም ላይ ቢሆን ትናንትም ልክ ነበርኩ ዛሬም ልክ ነኝ አይነት አመለካከት እንጂ “የታሪክ መዛባት” ባሉት ላይ ሚና ነበረኝ ለማለት አልፈለጉም፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለ እድገትና ትውልዳቸው እንዲናገሩ ሲጠየቁ እንኳ “ኢትዮጵያ” የምትለውን ቃል ላለመጥቀስ ዙሪያ ጥምጥም መሄድ ግድ ብሏቸዋል። ስለዚህ በቃለ መጠይቃቸው ዙሪያ ኢትዮጵያዊው ወገን “ጠርጥር” አይነት ጥያቄ ማንሳቱ የሚጠበቅ ነው።

ይሁንና በፖለቲካው አለም ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የሚባል ነገር የለም ይባላልና ኢሳያስ አፈወርቂ በአሁኑ ወቅት ወያኔን ለመጣል የሚደረገውን ትግል ሊያግዙን አይገባም በሚል ጫፍ የያዘ የጥላቻና የተቃውሞ አመለካከት ማንሸራሸርም ፍጹም ተገቢ አይመስለኝም። ቢያንስ ቢያንስ በኢሳያስ አፈወርቂ ወይም በኤርትራ መንግስት ድጋፍ የወያኔን መንግስት ታግሎ መጣል ወቅቱ የጠየቀው ብቸኛው አማራጫችን ነው ብለው ያመኑ ወገኖች በኤርትራ ምድር እንደሚገኙ ልናስብ ይገባል። ላመነበት ህይወትን ያህል ዋጋ ለመክፈል የተሰለፈን ወገን የምንቃወመው በየትኛው የሞራል ማማ ላይ ቆመን ነው ብሎ ራስንም መጠይቅ ይገባ ይመስለኛል።

በሌላ አገላለጽ በኤርትራ በኩል የሚደረገውን ትግል የማይደግፉ ወገኖች ስጋታቸውን ከመግለጽ ባሻገር በተቃውሞ መልክ ዘመቻ መክፍት የለባቸውም ነው። ይህን ማድረግ ሊጠቅም የሚችለው ወያኔንና ወያኔን ብቻ ነውና።

ትናንት በኤርትራ ውስጥ ተንቀሳቅሰው ሻቢያ አላሰራ አለን የሚሉ ወገኖች ሻቢያ ያደረሰባቸውን በደልና ግፍ የመናገር መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ’ ነገር ግን ለነሱ የገጠማቸው እድል በአሁኑ ሰአት በኤርትራ ምድር ለሚገኘውም ወገን አይቀርለትም በሚል ድምዳሜ ከኛ በላይ ቀዳሽ አይነት ጭፍን የጥላቻ ዘመቻ ማድረግም አይገባቸውም። ቀደም ሲል በኤርትራ በነበሩ አርበኞች ላይ ሻቢያ ፈጸመ የተባለው ግፍና በደል እውነት ከሆነም በራሱ ግዜ የሚጋለጥ መሆኑን ሳንዘነጋ ማለቴ ነው።

በሌላው ወገን ደግሞ ከኢሳያስ አፈወርቂም ሆነ ከሻቢያ ጋር አብሮ መስራት ይቻላል ብለው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ፕ/ት ኢሳያስን ልዩና መልዓካዊ ስብዕና የሚያላብስ ዲስኩር በማሰማት የህዝቡን የአርባ አመታት ቁስል ባይቆሰቁሱ መልካም ነው ።

በኔ አመለካከት ፕ/ት ኢሳያስ ስለ ኢትዮጵያና ህዝቧ እንደሚጨነቁ ወይም እንደሚያስቡ ዛሬ ላይ ቆሜ መመስከር እችላለሁ የሚል ካለ እሱ ነብይ ካልሆነ ግብዝ ነው። በኔ በኩል ግን ኢሳያስ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ቀና ራዕይ ሊያረጋግጡልን የሚችሉት አሁን እየደገፉት ያለው አርበኛ ያለምንም ተጽእኖ ለውጤት እንዲበቃ ሲሆን ብቻ ነው። አልያ ዛሬ ላይ ቆመን በርግጠኝነት ልንናገር የምንችለው ስለትናንቱ እንጂ ስለነገው ባለመሆኑ ለግዜው ፕ/ት ኢሳያስን በኢሳያስ ወንበር ላይ እንጂ በኔሬሬ ወንበር ላይ ልናስቀምጣቸው አንችልም።

ባጠቃላይ ለኢትዮጵያና ሊትዮጵያዊያን ነጻነት የሚደረገው ትግል ባለቤት ኢትዮጵያዊውና ኢትዮጵያዊያን ብቻ በመሆናቸው ውይይታችን በራሳችን እንቅስቃሴ ዙሪያ መሆን ይገባዋል እላለሁ።

ኢሳያስ መልአክ ነው ያድነናል አልያም ጭራቅ ነው ያጠፋናል አይነት ሁለት ጫፍ የረገጠ አመለካት ይዞ መንቀሳቀስ ለዘመናት ከቆየንበት የባለህበት ሂድ … አያወጣንም።

ሁሉም ሳይጠላለፍ ተቻችሎ ባመነበት መንቀሳቀስ ይገባዋል። ካለፉት አራት አመታት ወዲህ በፖለቲካ ድርጅቶቻችን መካከል እየታየ ያለው መቻቻልና ተከባብሮ መንቀሳቀስ በእጅጉ የሚያስደስት ነው። ይህ አሁንም መቀጠል አለበት።

በተለይ ሚዲያዎች ይህን ጠንካራ የመቻቻልና ተከባብሮ የመስራት ልምድ ለማዳበር ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቅባቸዋል። እከሌ እከሌ ባልልም አንዳንድ ድህረ ገጾች የራሳቸውን ፍላጎት የሚያንጸባርቅን አመለካከት በብርሃን ፍጥነት ለንባብና ለጆሮ አብቅተው ሌላውን ሲያዘግሙበትና አንዳንዴም መጋረጃ ስር ሲደብቁት ይስተዋላሉና እርምት ሊያደርጉ ይገባል። የሰውን መብት እስካልቧጠጠና የወያኔን አገዛዝ በህዝብ ጫንቃ ላይ ለማቆየት ያለመ እስካልሆነ ድረስ የትኛውንም አመለካከት በማስተናገድ የቡድን ስሜትን ማጥፋት ይገባል እያልኩ የዛሬን ጽሁፌን ከመቋጨቴ በፊት ቀደም ባሉ ጽሁፌቼ ላይ ተመርኩዛችሁ አበረታችም/ነቃፊም አስተያየት ለላካችሁልኝ ወገኖቼ በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ።

ቸር ይግጠመን
አዜብ ጌታቸው
azebgeta@gmail.com

Filed in: Amharic