>
5:41 pm - Sunday December 5, 2021

መንግሥት ለምን ጩኸት ይወዳል? [ኤሊያስ ገብሩ]

Photo Elias Gebiruየየትኛውም ሀገር መንግሥት፣ ለሚመራው ህዝብ፣ እየሰራ ስለሚገኛቸው ሥራዎች የማሳወቅ ኃላፊነት እና ግዴታ ስላለበት ይናገራል፡፡ የአገላላጽ ደረጃ እና መጠኑ እንደየመንሥታቶቹ ባህሪ የሚወሰን ነው፡፡ መንግሥታት ሥለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ለህዝቡ በግልጽ ዕውነቱን ሊናገሩ እንደሚችሉ ሁሉ፣ ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ ቀናንሰው እና ውሸትን አቀላቅለው ሊገልጹም ይችላሉ፡፡
ይሄም ብቻ አይደለም፣ ከተሰራው በላይ በማጋነን፣ የፕሮፖጋንዳ ሥራን በፈጆታነት ይጠቀማሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል ብዬ የማስበው ገዥው መንግሥት ኢህአዴግ ነው፡፡ መንግሥታችን ትልቅም ሆነ ትንሽ ሥራ ሲሳራ በግንነት መግለጽ አንዱ መለያው ማድረጉን ምርጫው ያደረገ ይመስላል፡፡
ከወራቶች በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት የሙያ ዘርፍ ተመራቂ ተማሪዎች እኔን እና ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪን ሀሳብን ከመግለጽ ነጻነት አኳያ እንግዳ አድርገው ከተማሪዎች ጋር በጥያቄ እና መልስ አወያይተውን ነበር፡፡ በዚህ ደስ የሚል ፕሮግራም ላይ ልማታዊ ጋዜጠኝነትን በተመለከተ በነበረው ገለጻ ላይ አናንያ የሚያስቅ ነገር ግን ቁም ነገር አዘል አስተያየቱን ሰንዝሮም ነበር፡፡ ‹‹ኢህአዴግ ለአባይ ግድብ ግንባታም ሆነ ሰፈር ውስጥ የቦኖ ውሃ እንዲወጣ አድርጎ ኅብረተሰቡን እኩል ድቤ ያስመታል›› ነበር ያለው አናንያ፡፡ ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ለትንሹም ሆነ ለትልቁ ‹‹ልማት›› ጩኸት ከመፈለጉም ባሻገር ውዳሴም መሻቱን ነው፡፡
ካነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡-
ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም አመሻሽ ላይ የፌዴራል የጸረ ሙስና እና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ከብሔራዊ የመረጃ ደኅንነት ተቋም ጋር በመተባበር የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን መ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ እና ምክትላቸው አቶ ገብረህዋድ ገ/ጊዮርጊስን ጨምሮ 13 ሰዎችን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰር በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የአገሪቱ ከተሞች ሰበር ዜና ሆኖ የመረጃ ቅብብሎሹ በፍጥነት ተዛምቶ ነበር፡፡ በተጨማሪም በሂደት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ50 በላይ ደረሱ፡፡
ይህንንም እስር ተንተርሶ ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትልቅ ሥራ እንደሰሩ ተደርጎ ‹‹በርቱ ተበራቱ፣ በዚሁ ቀጥሉበት፣ አሁን ሥራ መስራት ጀመሩ!›› ተብለው ሲመሰገኑ እና ሲወደሱ ነበር፡፡
በዚያ ሰሞን በሀገሪቱ ላይ ትልቅ ተዓምር የተፈጠረ ይመስል፣ የመንግሥት እና የተወሰኑ የግሉ ሚዲያዎች ጉዳዩን ከልክ በላይ ዘገቡት፡፡ የኅብረተሰቡም ዋነኛ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ይሄ ሆነ፡፡

ነገር ግን፣ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማስተዋል ቢቻል ጉዳዩ ይን ያህል አስገራሚ አልነበረም፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሥራ ኃላፊዎችና ታዋቂ ባለሃብቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥራ መዋላቸውና መከሰሳቸው አይደለም፡፡ ከዚያ ቀደም የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ታምራት ላይኔ እና የመከለከያ ሚኒስትሩ አቶ ስዬ አብርሃም በመሰል ወንጀል ተጠርጥረው ከተከሰሱ በኋላ ተፈርዶባቸው ከእስር ወጥተዋል፡፡ ግን ሥርዓቱ ከእንደዚህ ዓይነት ተጠንተው በታቀዱ ክስተቶች ጩኸትን ይሻል፡፡ ለምን ለሚለው በጽሑፌ መደምደሚያ ላይ እመለስበታለሁ፡፡

የአባይ ግድብን የወሰድን እንደሆነም፣ መሰል ነገር እናስተውላለን፡፡ የአባይን መገደብ የደገፉት ብዙዎች እንዳሉ ሁሉ በምክንያታዊነት የፕሮጀክቱን ዓላማ የሚተቹ ወገኖችም መኖራቸው እሙን ነው፡፡ …የግድቡን ሥራ በቅንነት ካየነው፣ የዐባይ መገደብ አንድ ትልቅ ሀገራዊ የልማት ተግባር አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሆኖም በዐባይ ግድብ ስም ያለማቋረጥ እየተሰራ ያለው ፕሮፖጋንዳ ቀላል አይደለም፡፡ ስለፕሮጅክቱ ዝርዝር ነገር በመንግሥት ኃላፊዎች፣ በመንግሥት፣ በግሉና በውጭ ሀገራት ሚዲያዎች ለረዥም ጊዜ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ በዚህ መሰረት፣ ሰፊው ሕዝብ ሥለግድቡ ጥሩ ግንዛቤ አግኝቷል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ግን በሳምንት ለሰባት ቀናት እና 24 ሠዓታት ሙሉ በሚያስብል መልኩ ‹‹አባይ …አባይ›› ማለት ግድቡን ለፖለቲካ ፍጆታነት መጠቀም መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኩል አባይ በሶስት ብር እንደሚገደብ አድርጎ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን እስኪሰለቹ ድረስ ማቅረብም ጩኸትን መሻት አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ እንዲሁም ህዝብ ለግድቡ በግሉ ማድረግ ያለበትን ድጋፍ ከልቡ ፈቀዶ እንጂ በማስታወቂያ ጋጋታ ተሰላችቶ መሆን የለበትም፡፡

ሌላኛው ጩኸት የበዛበት ነገር፣ የህወሃት 40ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ነው፡፡ ክብር ለሚገባቸው ታጋዮች ክብር መስጠት ተገቢ ሆኖ ሳላ፣ በዓሉን አስመልክቶ፣ ለረዥም ቀናት፣ እጅግ በተጋነነ መልኩ ጉዳዩን ማስጮህ አግባብ አይደለም፡፡ ለኦህዴድ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓልም ሌላ ግነት የበዛበት ጩኸት እየሰማን ነው፡፡
የርዕሰ ጉዳዬ ሀሳብ፣ ‹‹መንግሥት ለምን ጩኸት ይወዳል?›› የሚል ነው፡፡ በተለያዩ የልማት ሥራዎች እና መንግሥታዊ እርምጃች ውስጥ ጩኸትን መፈለግ እና መሻት ተገቢነት አለው ብዬ አላምንም፡፡ ለምን? ሥራውን በአግባቡ የሚሰራ መንግሥት ጩኸት አይፈልግም፤ አያሻውምም፡፡ ብዙ አያወራም፤ እንዲወራለትም አይፈልግም፡፡ ሥራው በራሱ ታሪካዊ ምስክሩ ነውና፡፡

ነገር ግን ኢህአዴግ የመንግሥት፣ የግሉን ሚዲያ የኅብረተሰቡን የሀሳብ በአቅጣጫ በተለያዩ ጊዜያት የማስቀየር የማስጮህ ልምድ አለው፡፡ በዚህ ረገድ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ አቶ መለስ ወቅት እየጠበቁ የሚዲያውን እና የኅብረተሰቡን ሀሳብ ለተወሰኑ ጊዜያቶች በ‹‹አዳዲስ›› የተቀመሩ አጀንዳዎች (አነጋጋሪ ንግግሮችንና ቃላትን ይጨምራል) መስረቅ እና መጥለፍ የተካኑ ነበሩ ብል ያጋነንኩ አይለመስለኝም፡፡ ሚዲያው (አጠቃላይ ለማለት አይቻልም) እና ኅብረተሰቡ ‹‹አዲሱ››ን ርዕሰ ጉዳይ በመዘገብ፣ ትንታኔ በመስጠትና የመነጋገሪያ አጀንዳ እና ወሬ በማድረግ ለተወሰነ ጊዜ ሌላ ሐሳቡን በመጠኑ እንዲረሳ እና እንዲዘነጋ የቤት ሥራ ይሰጡት ነበር፡፡ ከዚያም ቀን እና ጊዜ ጠብቆ ሌሎች አጀንዳዎች እና የጩኸት ዜማዎች ይመጣሉ፡፡
በዚህ ቀመራዊ አካሄድ ሥርዓቱ ህዝብን ግራ እና ቀኝ እያወዛወዘ ‹‹ህዝብ የተሰጠን …ኮንትራት›› በሚል 24 ዓመታትን ሲገዛ ኖራል፡፡ ተጨማሪ ዓመታትንም ይፈልጋል፡፡ በዋነኝነት ጩኸት መውደዱም ለዚሁ ነው – ለሥልጣኑ!!!

Filed in: Amharic