>

በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ የተፈፀመው ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ እስልምናን አይወክልም!! [አቡ ዳውድ ኡስማን]

በኢትዮጵያን ክርስቲያኖች ላይ በእስልምና ሽፋን የተፈፀመውን ጅምላ ጭፍጨፋ ሙስሊም በመሆኔ እቃወማለው ፡፡

Aba Dawid posterበእስልምና ውስጥ የዚህ አይነት እርኩስ ተግባር ተቀባይነት የለውም፡፡በእስልምና ሽፋን የዚህ መሰሉ ጭፍን አስተሳሰብ ባለቤቶች በሚፈፅሙት አሳዛኝ እና አሳፋሪ ተግባራት ኢስላም ሲሰደብ ማየት እንዴት ያሳምማል፡፤በኢስላም ውስጥ የበደለህን እና ድንበር ያለፈብህን አካል ለመበቀል ስትል ደካሞችን መጉዳት አበክሮ ያወግዛል፡፡

ከጠላት ጋር በሚኖርህ ፍልሚያ ላይ እራሱ ከጠላት ወገን በኩል ያሉ ንፁሃንን፣ ህፃናትን፣ ሴቶችን፣ አረጋውያንን፣ የማንኛውንም ሃይማኖት አባቶችን መግደል፣ቤተ አምልኮዎችን እና ገዳማትን መድፈር፣ዛፎችን ያለአግባብ መቁረጥን እና እንስሶችን መግደል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ላይ የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ ቡድኖች በሊቢያ የደረሰወን አይነት አሳፋሪ እና ዘግናኝ ጥፋት ሲፈፅሙ ይስተዋላሉ፡፡ ኢስላም ከነዚህ ሰዎች ተግባር የፀዳ ነው፡፤ ሌላውም ሙስሊም ማህበረሰብ ፅንፈኞቹ በፈፀሙት ተግባር በጅምላ አይወነጀልም፡፡

የአንዲትን ህያው ነፍስ ያለአግባብ ያጠፋ የአለምን ህዝቦች ሂወት እንዳጠፋ እንደሚቆጠርበት ቁርአን አስተምሮናል፡፡

مِنْ أَجْلِ ذَٰلِكَ كَتَبْنَا عَلَىٰ بَنِي إِسْرَائِيلَ أَنَّهُ مَن قَتَلَ نَفْسًا بِغَيْرِ نَفْسٍ أَوْ فَسَادٍ فِي الْأَرْضِ فَكَأَنَّمَا قَتَلَ النَّاسَ جَمِيعًا وَمَنْ أَحْيَاهَا فَكَأَنَّمَا أَحْيَا النَّاسَ جَمِيعًا ۚ وَلَقَدْ جَاءَتْهُمْ رُسُلُنَا بِالْبَيِّنَاتِ ثُمَّ إِنَّ كَثِيرًا مِّنْهُم بَعْدَ ذَٰلِكَ فِي الْأَرْضِ لَمُسْرِفُونَ

በዚህ ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ እነሆ ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው ማለትን ጻፍን፡፡ (ሱረቱል ማኢዳ 32)

በመሆኑም በሊቢያ በኢትዬጲያ ክርስቲያኖች ላይ በ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በቅድሚያ እምነቴ ኢስላም ስልሚያወግዘው አወግዘዋለው፡:ቀጥሎም የጠፋው የሰው ሂወት ነው እና እንደሰበአዊነቴ ድርጊቱ በማንም አካል ይሁን የትም ቦታ ይፈፀም አወግዘዋለው፡፡

ሃይማኖትን አስገድዶ ማስቀየር፣የኔን እምነት በግዳጅ ተቀበል ብሎ መግደል ፅንፈኞች የፈጠሩት እሳቤ እንጂ በእስልምና ውስጥ ፈፅሞ የለም፡፡ በሃይማኖት ማስገደድ እንደሌለ በቁርአንም ሆነ በሃዲስ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

لَا إِكْرَاهَ فِي الدِّينِ ۖ

በሃይማኖት ማስገደድ የለም(ሱረቱል በቀራ፡256)

እስልምና ሰዎችን በመግደል ትጸድቃላችሁ የሚል አስተምህሮ አላስቀመጠልንም፡፡ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑትን ሰዎች እስልምናን በግዳጅ ካልተቀበላችሁ በሚል መግደል ኢስላም ሊፈቅድ ይቅርና የትኛውም እምነት ተከታይ ይሁን የሚያመልከውን ፈጣሪ በክፉ መስደብ፣የሃይማኖት አባትን መግደል፣ገዳምን፣ቤተ አምልኮዎችን ማፈራረስ በእስልም በጥብቅ የተከለከሉ ወንጀሎች ናቸው፡፡

የሌሎችን እምነት መስደብ የከለከለ እምነት ዛሬ ላይ የሌላ እምነት ተከታዬችን በመግደል ይጸድቃል የሚል አስተምህሮ ሊኖረው አይችልም፡፡

በየትኛውም እምነት ተከታይ የሚፈጸምን ግድያ እና ኢ ሰብአዊ ድርጊት እንደ ሙስሊምነቴ አወግዛለው፡፡ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችም ሆኑ ሌላ እምነት ተከታዬች በሃገራችን ኢትዮጵያ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ተከባብረን ለብዙ አመታት ኖረናል፡፡ በሰላም እና በጋራ ስንኖር እስልምና ንፁሃን የሆኑ የሌላ እምነት ተከታዬችን መግደል የሚያፀድቅ ተግባር መሆኑን አስተምሮ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በመላው አለም አንድም የሌላ እምነት ተከታይ ባልኖረ ነበር፡፡ ምክንየቱን ሁሉም መፅደቅ እፈልጋለው በሚል ሰዎችን በገደለ ነበር፡፡ እውነተው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡

ከ 1400 አመታት በፊት ጀምሮ ሙስሊሞች በፍትህ ለሌላ እምነት ተከታዬች ጋር በጋራ ኖረዋል፡፡ የእምነት ልዩነት መኖር ጉርብትናን፣መልካም መዋዋልን፣ መከባበርን እና በችግር ጊዜ መረዳዳት አልከለከለንም፡፡ እስልምናም በጥብቅ ያዘዘን ይህን እንድንፈጽም ነው፡፡

አልሃምዱሊላህ የኢትዮጵያ ሙስሊም ህብረተሰብ ከዚህ መሰሉ ፅንፈኛ አስተሳሰብ የፀዳ ነው፡፡ በአላህ ፈቃድ ድሮም ፣አሁንም፣ ወደፊትም የኢትዬጲያ ሙስሊም ማህበረሰብ ከፅንፈኝነት የፀዳ ሆኖ ኢስላም ባስቀመጠው መልኩ ከሌሎች ዜጎች ጋር ተከባብሮ ይኖራል፡፡

ንፁሃንን ማረድ፣መግደል፣ በአጥፍቶ መጥፋት ንፁሃንን መጨረስ፣ሴቶችን ማገት፣ ንብረት መዝረፍ እና ማቃጠል፣ቤተ እምነቶችን ማቃጠል፣የየትኛውንም ሃይማኖት አባት መግደል፣ገዳማትን መድፈር፣ ቀሳውስትን መግደል እና ማጥቃት ወዘተ…. የእስልምና ጋር የሚያያይዛቸው አንዳችም ተግባር የለም፡፡

ንፁሃንን መጨፍጨፍ እምነት ቢኖረው ኖሮ በደቡብ አፍሪካ እየተፈፀመ የሚገኘው አሰቃቂ ወንጀል ባልተፈፀመ ነበር፣ በቡርማ፣በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ወ.ዘ.ተ…. የተፈፀሙት ኢ-ሰብአዊ ጭ ፍጨፋዎች ባልተፈፀሙ ነበር፡፡ እውነታው ግን ሽብርተኝነት እና ሰዎችን መጨፍጨፍን እምነት የሌለው የዘመናችን አሰቃቂ የጥፋት ተግባር ነው፡፡

ጉዳዩን ወደ ሃገራችን ልመልሰው እና የኢትዬጲያ ሙስሊሞችም ለ 3 አመታት ስናካሂደው የቆው ሰላማዊ የመብት ትግል መንግስታዊ የሃይማኖት ጣልቃ ገብነትን መቃወም እንጂ የሌሎች እምነት ተከታዬችን መብት የመጋፋት ሂደት አይደለም፡፡ የኢትዬጲያ ሙስሊም በሰላማዊ መንገድ እምነትን በግዳጅ የማስቀየርን መንግስታዊ ውንብድና እና ጣልቃ ገብነትን ነው የተቃወመው፡፡

በሊቢያ እስልምናን በግዳጅ ካልተቀበላችሁ በሚል እንደተገደሉት ኢትዬጲያውያኖች ሁሉ የኢትዬጲያ መንግስትም ሙስሊም ኢትዬጲያውያንን አህባሽ የተሰኘውን ጸረ ህዝብ አሰተሳሰብ በግዳጅ ካልተቀበላችሁ በሚል ሲያስር፣ ሲደበድብ፣ ደማችንን ሲያፈስ፣ ሲገድለን እና በርካቶችን ለበርሃ ስደት ሲዳርግ ቆይቷል፡፡

የሁለቱ ልዩነት በሊቢያ የተፈጸመው በሽብር በተፈረጀ ቡድን ሲሆን የኛ የሃገራችን ደግሞ ህጋዊ ሽፋን በተላበሰ የሃገር መንግስት ነው፡፡ ከዛ በተረፈ ሁለቱም በግዳጅ እምነት ለማስቀየር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህንን መንግስታዊ እምነት የማስቀየር ዘመቻ በሰላማዊ መንገድ ስንቃወም ግን የሌላ እምነት ተከታዬችን መብትም ሆነ ክብር አልተዳፈርንም አልነካንምም ፡፡

በመሆኑም የኢትዬጲ ሙስሊሞችን እምነታቸውን ከበካይ አስተሳሰብ ለመጠበቅ ሲያደርጉት የቆየው ሰላማዊ ትግልን ከየትኛውም የሽብር ቡድንም ሆነ አካል ጋር ለማያያዝ መሞከር ህዝብን ከህዝብ በሃይማኖት ከፋፍሎ ለማፋጀት ለሚፈልገው የሃገራችን መንግስት ግብዓት ከመሆን የዘለለ ጥቅም አይኖረውም፡፡

በመጨረሻም በየጊዜው እስልምናን ሽፋን በማድረግ እየተፈፀመ ለሚገኝ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፍትሄው የሌላ እምነት ተከታዬች በእስልምና ተከታዬች ላይ ጥርጣሬ እና ፍርሃት እንዲያድርባቸው በፕሮፖጋንዳ ጭንቅላታቸውን ማዞር፣ ንፁሃን ሙስሊሞችን በየቦታው እያሰቃዩ ማሰር፣ መግደል እና መፍጀት ሳይሆን ሁሉንም ወገኖች በፍትሃዊነት በማስተዳደር ሁሉም የችግሩ ሰለባ በመሆኑ እምነት ሳይለዩ በጋራ በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ እንዲቀሳቀሱ መስራት ነው፡፡

ለሀጋራችን ህዝብ አላህ ሰላሙን ያውርድልን!

በየቦታው በስደት ያሉ ዜጎቻችንን አላህ እየተሰማ ከሚገኘው ፈተና ሁሉ ይጠበቃቸው

በየቦታው በግፍ እየተገደሉ ለሚገኙ ኢትዬጲያውያን ወላጆችም አላህ ሰብሩን እና መፅናናቱን ይስጣቸው!

አሚን!!

Filed in: Amharic