>
8:54 pm - Wednesday February 8, 2023

የዛሬ ቀትር - በጨርቆስ ሀዘን ቤት[ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ]

‹‹ልጆቼ፣ እኛ በታረድን››
በጨርቆስ የነበሩ አንድ እናት ለቅሶ
‹‹ወያኔ አታለለን … ወያኔ ሌባ …ይለያል ዘንድሮ …ወይኔ ወይኔ››
በጨርቆስ የነበሩ ወጣቶች ያሰሙት ተቃውሞ እና ሀዘን

ከሰሞኑ በአይሲስ በዘግንኝ ጭካኔ አንገታቸው በተቀሉት ሁለት ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ወገኖቼ ቤት ሀዘን ለመድረስ ወደጨርቆስ ረፋድ ላይ አምርቼ ነበር፡፡
ከሜክሲኮ ታክሲ ብይዝም ወደጨርቆስ የሚወስደው መንገድ በፌዴራል ፖሊሶች በመዘጋቱ በውስጥ ለውስጥ መንገድ ታክሲው ተጉዞ ጨርቆስ ቤተ/ክርስቲያን ጋር ተሳፋሪዎቹን አደረሰን፡፡ የታክሲ ፌርማታው አከባቢ በበርካታ ፌዴራል ፖሊሶች ተከብቧል፡፡ ገሚሶቹ ፖሊሶች ባዶ እጃቸውን ሲሆኑ ጥቁር ዱላ የያዙም ነበሩ፡፡ አንድ ፖሊስ ማይክራፎን ይዞም ተመልከቻለሁ፡፡
ብዛት ያላቸው ወንድና ሴት ሀዘንተኞች፣ ወደለቅሶ ቤቱ እያለቁሱና የተለያዩ የተቃውሞ ድምጾችን እያሰሙ በእርጋታ ነበር የሚሄዱት፡፡ በሰልፉ መሃል የነበሩ ወጣቶች የተቃውሞ ድምጽነ በቃላት ጮክ ብለው ከማሰማት ባለፈ ሁለት እጆቻቸውን በማቆላለፍ ወደላይ ሲያደርጉም ነበር፡፡ ‹‹ወያኔ አታለለን … ወያኔ ሌባ …ይለያል ዘንድሮ … ወይኔ ወይኔ›› የሚሉት ከሰማኋቸው የተቃውሞና የሀዘን ድምጾች መካከል ይገኛሉ፡፡ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙሮችም በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡
ወደለቅሶ ቤቱ ድንኳን ጋር ስንደርስ ሁሉም ባለበት ቆሞ እንባውን አውጥቶ የሚያለቅሰው እያለቀሰ እና በሀዘን ስሜት ተውጦም ‹‹ወይኔ ..ወይኔ›› የሚለውም ሀዘኑን ገለጸ፡፡ በርካታ ሰዎች በሞባይላቸው የሀዘን ድባቡን በቪዲዮ ካሜራም ሲቀርጹ ነበር፡፡
በዚህም ስፍራ በርካታ ፖሊሶች ከሀዘንተኛው በቅርብ ርቀት ሆነው ሁኔታውን ይከታተላሉ፡፡ አንዱ ፖሊስ ሞባይሉን አውጥቶ በሥርዓቱ ላይ የሚደመጠውን የተቃውሞ ድምጽ ሲቀርጽም አስተውያለሁ፡፡ እዚህ መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶችም ነበሩ፡፡ ፊታቸው ላይ ሀዘን የሚነበብባቸው ጥቂት ፖሊሶችን መኖራቸውንም ታዝቤያለሁ፡፡
አንዲት እናት ከጎኔ ቆመው ምርር ብለው እንዲህ ሲያለቅሱ ነበር፡- ‹‹ ልጆቼ ታረዳችሁ? እናንተ እኮ የእናት እና አባቶቻችሁ ብቻ አይደላችሁም፤ የእኛም ልጆች ናችሁ! ልጆቼ እኛ እንታረድ፣ እኛ ምን እናደርጋለን …››
በቦታው የነበርን ድጋሚ እንባችንን መቆጣጠር አልተቻለንም፡፡ …ብቻ እጅግ ያሳዝናል፡፡
ወዲያው አንድ ፒክአፕ የፌዴራል ፖሊስ መኪናም ፖሊሶችን ጭኖ በስፍራው ደረሰ፡፡ ዕድሜዋን ሙሉ የጨርቆስ ነዋሪ የሆነች አንድ አክስቴን ወንድ ልጇንና ባለቤቱንም አገኘኋቸው፡፡ ሁለቱንም ሟቾች ከነቤተሰቦቻቸው ያውቋቸዋል፡፡ አክስቴ ስለልጆቼ የሚያውቁትን እያለቀሰች ጥቂት አወጋችኝ፡፡
በርካታ ሰዎች ከተለያየ ቦታ በመምጣት በለቅሶ ቤቱ ሀዘናቸውን ገልጸዋል – እያለቀሱ ጭምር፡፡ የኢትዮጵያ ቡናን እግር ኳስ ቡድን ማሊያ የለበሱ በርካታ ሴት እህቶቻችን በለቅሶ ቤቱ ደርሰው ሲያለቅሱ በለቅሶ ቤቱ ድጋሚ የለቅሶ ጩኸትም ተደመጠ፡፡
የሁለቱ ሟች ወገኖቻችን ፎቶ ግራፍ፣ በትልቅ ተሰርቶ ወደድንኳን ከመገባቱ በፊት በሁለት ቦታዎች ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በድንኳኑ በር ላይ ‹‹ሉዓማዊነት በሁሉም ቦታ ያሉ ወገኖችን መብት ማስጠበቅ ነው›› የሚል ይዘት ያለው ባነር ተሰቅሎ ይነበባል፡፡ የለቅሶ ቤቱን አካባቢ ከቀኑ 08፡30 ሰዓት ላይ ለቅቄ ስሄድም በርካታ ፌዴራል ፖሊሶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ቆመው እና ተቀምጠው ነበር፡፡ በግፍ አንገታቸው ለተቀሉ ወገኖቻቸው እጅግ በማዘን፣ እርማቸውን ለማውጣት እና ሀዘን ለመድረስ የሚሄዱ ወገኖችን በፖሊስ በቅርብ ርቀት አስከብቦ ማስጨነቅ ግን ለምን?
ለማንኛውም የወገኖቻችንን ነፍስ ፈጣሪ በገነት ያኑርልን!

Filed in: Amharic