>
6:45 am - Saturday July 31, 2021

ወያኔነት ለኔ ጥፋት ነው - መልስ ለዶ/ር ቴድሮስ [ግርማ ካሳ]

Girma Kasa to  Tedros Adhhanomዶር ቴድሮስ አዳኖም በሶሻል ሜዲያ ከፍተኛ ትችት እየቀረበባቸው ነው። «ሰዎች ወያኔ ይሉኛል» ብለው በወያኔነታቸው እንደሚኮሩ ጽፈዋል። ሁኔታውን ለተከታተለ ሕዝቡ በርሳቸው ላይ ቅሬታና ትችት ያቀረበው፣ ወያኔ ስለሆኑ ሳይሆን እንደ መንግስት ህዝብ ማገልገል ባለመቻላቸው ነው ። ሌሎች አገሮች ካደረጉት ጋር ሲነጻጸር፣ ወያኔ ግድ የሚሰጠው ሆኖ ስላልታየ ነው። አብዛኞቻችን እኮ፣ ወያኔ መቶ አመት ቢገዛ ችግር የለንም። እኔ በግሌ ማንም ይግዛ ማንም ግድ አይሰጠኝም። እኛ የምንጠየቀው ግን፣ « አራት ኪሎ ማን ነው ያለው ?» የሚለውን ጥያቄ ሳይሆን፣ «አራት ኪሎ ያለው ህዝብን ያገለግልላል ወይንስ ሕዝብን ያሸበራል ?» የሚለውን ነው። በአሁኑ ወቅት ወያኔ ሕዝብ እያገለገለ ሳይሆን ሕዝብን እያሸበረ ነው። እንደ አይሰስ፣ አልካያዳ ያሉ እውነተኛ ሽብርተኞችን ሳይሆን ፣ ሰላማዊዉን ኢትዮጵያዊ ነው ሽብርተኛ እያል እያሰራና እያሰቃየ ያለው። ወያኔ ጉልበቱ ሴቶችን፣ አሮጊቶች፣ ብ እር ያነሱ ሰላማዊ ዜጎችን ላይ ነው። «ወያኔ መንግስታዊ የወንበዴ ቡድን ስለሆነ፣ ከሽብር ተግባሩ ይቆጠብ» ነው እያልን የምንጮኸው።

ዶክተሩ ስሜታዊ ሆነው፣ የዉይይቱን አቅጣጫ ቀይረው፣ በዚህ ወቅት ስለወያኔነት ሊሰስብኩን ከወደዱ፣ እኛም ምላሽ አለንና መልስ ሰጥተናቸዋል። ለዶር ቴዶርስ የሰጠሁት ምላሽ እንሆ፡

የተከበሩ ዶር ቴድሮስ፣ እዚህ የሚጻፈዉን ላያነቡ ይችላሉ። ሆኖም ከሚጻፉት ጠንካራ ትችቶች መቼም ትንሽም ቢሆን ራስዎትን ይመረምራሉ ብዬ አስብለሁ።

«ደቡብ አፍሪካ እየተጎዱ ላሉ ወገኖች ሳስረዳ ስሞክር ወያኔ አሉኝ» ብለዋል። ስለወያኔነትም ትንሽም ቢሆን ሊሰብኩን ሞክረዋል። በነገራችን ላይ ወያኔነትዎን አክብራለሁ። መብትዎት ነው። በዚህም ምክንያት ሊሰደቡም ሆነ ሊወቀሱ አይገባም።

ሆኖም እርስዎ ወያኔነትዎትን ሌላው እንዲያክብርልዎት እንደሚፈልጉት፣ ሌላውን ደግሞ የወያኔ ተቃዋሚ የመሆን መብቱን፣ እርስዎና ጓዶችዋ አለማክበርዎ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው። ይኸው ለ24 አመት ገንዘቡን፣ ሜዲያዉን፣ ፍርድ ቤቱን፣ ፖሊሱን፣ ወታደሩን ተቆጣጥራችሁ፣ ከናንተ ፍቃድ ውጭ የሚንቀሳቀሰዉን ሰው ሁሉ ሽብርተኛ እያላችሁ፣ ህዝቡን ጨፍልቃችሁ በኃይል እየገዛችሁት ነው። ሁሉም ሰው ከፋብሪካ እንደወጣ፣ የናንተን አስተሳሰብ፣ የናንተን ፖለቲካ፣ የናንተን አቅጣጫ ብቻ እንዲከተል ነው የምትፈልጉት። ሁሉም ወያኔ እንዲሆን ነው የምትፈልጉት።

ለዚህ ማስረጃ ከፈለጉ በጆንያ አምጥቼ ልበትንልዎት እችላለሁ። የርስዎ ወዳጅ፣ የአባይ ቦንድ ሰው እንዲገዛ ሲቀሰቅስ የነበረው፣ ኢሕአዴግ የሚያደርጋቸውን የልማት እንቅስቃሴዎች መደገፍ አለበት ሲል የነበረው፣ በሶሻል ሜዲያ መስማት ከምትፈልጉት አስተያየት ትንሽ የወጣ አስተያየቱን ስለሰጠ ብቻ፣ ብሎግ ማድረግ ወንጀል ሆኖ፣ ሽብርተኛ ተብሎ፣ ከሌሎች የዞን ዘጠኝ ልጆች ጋር ይኸው ወህኒ ከተጣለ አንድ አመት ሆነው። መቼም ናትናኤል ፈለቀን አላውቀዉም አይሉኝም። የጆን ኬሪም ወዳጅ ነበር። እርግጠኛ ነኝ እርስዎ የዜጎችን መታሰር አይፈልጉም የሚባል ነገር አለ። ከሌሎቹ ይሻላሉ ሲባል ሰምቻለሁ። ሆኖም ደካማና የማይረቡ ሰው ስለሆኑ፣ ከርስዎ ጋር ያሉ ማጅራት መቺ፣ ጋደኞችዎትን ምንም ለማለት አልደፈሩም። ለስሙ ተምረዋል። የተማረ ነገሮችን ማገናዘብ ይገባው ነበር። ሆኖም የእርስዎ አይምሮ ግን አርቆ ከማሰብ ታጠረ። ጋዜጠኞች፣ የሰላማዊ ፓርቲ መሪዎች ( እነ ሃብታሙ፣ አብርሃ ደስታ …) እናንተ መስማት የማትፈልጉትን ስለጻፉ ብቻ ሽብርተኛ ተብለዋል እየሰቃዩ ነው። አንዱ ይሄ ነው እንግዲህ ከናንተ ጋር የሚያጋጨኝ።

ሌላው ነጥቤ ለወገኖቻችን ተደረገ የሚባለውን እርዳታ በተመለከተ ነው። እርስዎ፣ ኢትዮጵያዊያን በደቡብ አፍሪካ የሚሰልሉ የኤምባሲ ካድሬ ሰራተኞችን እያነጋገሩ የሰሙትን ነው ሊነግሩን የሚሞክሩት። ሆኖም በኢሳት ( እሺ ኢሳት ይቅር) ፣ በአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ፣ በጀርመን ድምጽ ራዲዮ እየተከታተልን የምንሰማው ግን ሌላ ነው። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያዊንን ድምጽ እየሰማን ነው። «ሌሎች መንግስቶቻቸው እየረዷቸው ነው። እኛ ግን መንግስት የለንም» ሲሉ ነው የሰማነው። ከተሳሳትን፣ እንታረም ዘንድ፣ እባክዎት እንደው በይፋ ወጥተው ከጻፉ አይቀር፣ በምን መልኩ ወገኖቻችን ድጋፍ እንደተደረገላቸው ያሳዉቁን። መናገር ቀላል ነው። መጻፍ ቀላል ነው። የኤምባሲ ሰራተኞችን ደዉሎ ማነጋገር ቀላል ነው። ግን ለወገን በተግባር መድረስ ሌላ ነገር ነው። ይሄ ሁለተኛ ነጥቤ ነው።

በመጨረሻ ወያኔነት ልማት ማለት ነው ስላሉት አንድ ሁለት ብዬ ላቁም። ወያኔነት አዎ ከፈረንጅና ከቻይና በልመና በተገኘ ገንዘብ የሚደረግ የፎቅ፣ የመንገድ፣ የድልድይ ግንባታ ነው። ግሩም ለማኞች በመሆናችሁ ልትኮሩበት ትችላላችሁ። ግን እኔ እናንተን ብሆን ብዙ አፌን አልከፍትም። ቻይና በሰራዉ ባቡር ተሳፍራችሁ፣ ገነባን ማለት ያስተዛዝባል። ገንዝቡ ከቻያና፣ እቃዉ ከቻያና፣ ሰራተኞቹ ከቻያና ሁሉም ከቻያና ,…..እናንተ ምን አደረጋችሁ ? ? ?

ዉድ የተከበሩ ዶር ቴድሮስ፣ ለኔ ወያኔነት ዘረኝነት ነው። ወያኔነት አገርን ባህር አልባ ማድረግ ነው። ወያኔነት ዜጎችን ሽብርተኛ እያሉ ማሸበር ነው። ወያኔነት የኑሮ ዉድነት ነው። ወያኔነት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ነው። ወያኔነት ኢትዮጵያዉያንን በዘር መከፋፈልና የዘር ግጭት ነው። ወያኔነት ከዚህ ዘር ናችሁ፣ ይሄን ቋንቋ ትናገራላችሁ ተብሎ መባረር ነው። ወያኔነነት ባለስልጣን ስለፈለጉት ብቻ ዜጎች ከእርሻና ከመኖሩያ ቤታቸው አፈናቅሎ መሬትን መንጠቅ ነው። ወያኔነት በኢትዮጵያዊያን መካከል መግባባት፣ እርቅ እንዲመጣ አለመፈለግ ነው። ወያኔነት አሁን በደቡብ አፍሪካ በወገኖቻችን ላይ የተፈጠረው እንዲፈጠር፣ ዜጎች በአገራቸው መኖር አማሯቸው እንዲሰደዱ ማድረግ ነው። ወያኔነት ብዙዉን አስረቦ ጥቂቶችን ሚሊየነር ማድረግ ነው።

ይልቅ እንዲሁ ከመመጻደቅ፣ ድክመቶቻችን ተረድተን፣ አገራችን በአሁኑ ወቅት ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታን ከግምት በማስገባት፣ ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሮ ሁላችንም ተከባብረን፣ እንደ ሕዝብ ተያይዘን፣ ከነጮችና ከቻያናዎች ጥገኝነት ወጥተውን፣ ለልጆቻችን የተከረበረችና የበልጸገች አገር በፍቅርና በአንድነት መገንባቱ ይሻለናል። ጥጋብ የትም አያደርስም።

Filed in: Amharic