>
3:50 am - Friday February 3, 2023

ሰው በአሹቅ ብቻ አይኖርም ! [አሌክስ አብርሃም]

‹‹ጥጋብ ፍንቅል አድርጓችሁ ነው የተሰደዳችሁት እንጅ …አገራችሁ ማሩ ወተቱ …›› ማለት ‹‹ጠግባችሁ ሂዳችሁ ነው የታረዳችሁት እንኳን የእጃችሁን አገኛችሁ ›› ከማለት አይተናነስም !!አሁን ከትላንት ወዲያ ታዋቂው የማስታወቂያ ባለሙያ አርቲስት ሰዊት ፍቅሬserawit_fikre ጨርቆስ ሃዘን ቤቱ ንግግር እንዲያደርግ ተፈቅዶለት በሚያስገመግም ድምፁ እንዲህ አለ ‹‹ ከሰው አገር ወርቅና ብር እናታችን እቅፍ ውስጥ አሹቅ እየበላን ሙቆን ብንኖር ይሻላል›› ቆይ እውነቱን እናውራ እንጅ ! የታለ ጥጋቡ … የታለ ስራው … የታለ አሹቁ….እንዴዴ ….ምናይነት በሰው ህይዎት ላይ መቀለድ ነው ይሄ ! ሰው እኮ እንስሳ አይደለም …በልቶ ጠጥቶ ሆዱ ከሞላ መተኛት ብቻውን በቂ ነው ሊባል አይገባም !

እከሌ መቶ ሽ ብር ከፍሎ ተሰደደ ለምን እዚሁ አይሰራባትም የሚል የዋህ ሒሳብ የሚያሰሉ ሰዎች ገጥመውኛል ….እጁ ላይ አፈር ከድቤ በልቶ ያጠራቀማትን ገንዘብ እየበላ አጨብጭቦ ከሚቀር ….ስደት ላይ ኢንቨስት ሊያደርግ ወሰነ በቃ ….ለምን አገሩ ላይ ስራ አይሰራባትም ….አገራችን ላይ ስራ እድል በሆነበት በዚህ ጊዜ መቶ ሽ ብር ምን እንደሚሰራ ሁላችንም እናውቃለን ….ቤት ልከራይ ቢባል የስድስት ወር ኪራይ የአመት ኪራይ በአንዴ በሚጠየቅባት አገር ….መቶ ሽ ብር እና ከዛ ያነሰ ብርን እንደትልቅ ካፒታል የሚቆጥር ሰው …ምናልባት ነፍሱ ድሮ ላይ የቆመ ሰው ይሆናል !

እናቴ ያሳደገችኝ እኮ እሷ ስር ተወሽቄ አሹቅ እንድበላ አይደለም ! የተሻለ ኑሮ እሻለሁ …ለእናቴ ላሳልፍላት እፈልጋለሁ … ቤት እፈልጋለሁ የተሻለ ትምህርት እፈልጋለሁ ማግባት መውለድ ለቤተሰቤ አለኝታ መሆን እፈልጋለሁ ! ልጆቸ ጥሩ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ጥሩ እውቀት እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ ….አሹቅ እየበላሁ ነገ ይሄንኑም አሹቅ ያጡ ልጆችን መፍጠር አልሻም ! አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ህዝብ የሚሰደደው ደላላ ስለደለለው ወይም አገሩን ስለጠላና …አገሩ ላይ ((ሚሊየነር መሆን ስለደበረው)) አይደለም ! ከእለት ጉርስ ያለፈ ነገር ማግኘት ዘበት ስለሆነበት ለፍቶ ጠብ የሚል ነገር ስላጣ ነው !! ዛሬን ብቻ አይደለም ማሰብ …ዛሬ ለፍቶ ጉልበቱን ገብሮ ይኑር ነገስ እድሜው ሲገፋ ነገስ ልጆች ሲወልድ ….ነገስ ነው ጥያቄው ! እህት ወንድሞቹ ለእግራቸው ጫማ ሲያጡ እየተመለከተ አሹቁን እየቃመ ቁጭ የሚል ልብ ያለው ሰው የለም !

ተው እንጅ ባለቢላዎቹ ሲገርሙን የብሶት አንገታችንን በቃል ስለታችሁ አትረዱን ! በመጀመሪያ ድግሪ ሁለት ሽ ብር እንኳን በማትከፍል አገር … ጠግባችሁ ተሰደዳችሁ ይባላል እንዴ ….ስደት በባህሪው እኮ ተፈጥሯዊ ህግ አለው ….ካልተሸለ ቦታ ወደተሸለ ቦታ መሄድ ማለት ነው ! አገራችን የተሻለች ብትሆንማ እንኳን እኛ ልንሄድ ሌሎችም ወደኛ በተሰደዱ ነበር ! ጠላታችን ድህነት ነው ብለን አውጀናል እኮ … አቅም ያለው ድህነትን ይፋለመው አቅም ያጣ ደግሞ ከጥላት ቀጠና ማፈግፈጉ የጦርነት ህግም ነው ! ጦርነት እውነት ነው ጨካኝ ጠላት ነው ….በመፎክር ብቻ አይመለስም ! ስጋህን ብቻ ሳይሆን ነፍስህንም አጋድሞ ያርድሃል !
ድህነት ያባረረውን ህዝብ ስደተኛን ተቀባዮቹ ግፍ ዋሉበት ይሄ ነው እውነቱ ! እስቲ አሁን ዝቅ ብሎ መስራትን ከጨርቆስ ልጆች የበለጠ ማን ያውቃታል …. ዝቅ ተብሎም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ ሄዱ ! እና ስራ ንቀው እንል ዘንድ ተገቢ ነው እንዴ …. ለምን ወሬ እናሳምራለን …. አስር ጊዜ ‹‹ደላላ እያታለላቸው ›› ይላል ሚዲያው …ከኑሯችን የበለጠ ደላላ የለም ! እንደውም ለስደት የሚገፋፉ አንደኛ ደላሎች የማስታወቂያ ባለሙያዎች ናቸው !

Fetalaw artist Serawit-Fikreአሹቅ ብሉ ዳቦ ብሉ ….የተፈጠርኩት አሹቅ እየበላሁ ጮማ የሚቆርጡ ሰዎችን ምራቄን እየዋጥኩ እንድመለከት አይደለም ! ለዚህ ደግሞ ሰው ነኝና መጀመሪያ አገሬ ላይ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ለመስራት እሞክራለሁ …. አገሬ የልፋቴን ካልከፈለችኝ በተለይ ደግሞ ከእኔ በታች የሚደክሙትን እያነሳች አናቴ ላይ ካስቀመጠች … ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ከሌለ …ከሰውነቴ ይልቅ ባለኝ ገንዘብና ደረጃ የምመዘን ከሆነ ….እንደሰው የምቆጠርበት ተንቄም ቢሆን የተሸለ የገንዘብ አቅም የተሸለ ነገር የማገኝበት ቦታ ሁሉ ምርጫየ የማይሆንበት ምክንያት የለም !

‹‹እናትህ እቅፍ ውስጥ ሁነህ አሹቅም በልተህ ቢሆን መኖር ይሻላል ››ይሉት ቀልድ …አሹቅ እየበላህ የእኔን ማስታወቂያ እየተመለከትክ በአምሮት ኑር ከማለት ውጭ ምን ትርጉም ይኖረዋል ! እንዴ ራሳቸው የማስታወቂያ ባለሙያዎቹ አይደሉ እንዴ …‹‹ለበዓል ለእናትሽ ብር ላኪ በዚህ ባንክ መንዝሪ›› እያሉ የተሰደደው ሁሉ ሃብታም የተሰደደው ሁሉ ላኪ መንዛሪ መሆኑን እንቁልልጭ እያሉ ለስደት የሚገፉን …የምን ዞሮ ‹‹አሹቅ ቂጣ›› እያሉ በሰው ቁስል እንጨት መስደድ ነው ! እስቲ ሃቁን እናውራ በቴሌቪዥን ከሚሰራጩ ማስታወቂያዎች አንድ እንኳን ‹‹የአሹቅ በሊታዎች›› ማስታወቂያ አይታችሁ ታውቃላችሁ ?…. አሹቅ እየበላሁ ነው ኢንሹራንስ የምገባው? ….አሹቅ እየበላሁ ነው የተንፈላሰሰ ቪላ በሶስት ጊዜ ክፍያ የምገዛው ?…አሹቅ እየበላሁ ነው ….መኪና የማማርጠው? ….አሹቅ እየበላሁ ነው ዱባይ ያለ ምግብ ቤት የምዝናናው? …. አሹቅ እየበላሁ ነው ባለምናምን ኮከብ ሆቴል የምዝናናው ?… አሹቅ እየበላሁ ነው ለቴሌቶን ሚሊየን ብር የማዋጣው?

‹‹ፍሪጅ ከሌለዎት ምኑን ኖርኩት ይላሉ ›› የምባለው ፍሪጁን አሹቅ እንዳስቀምጥበት ነው ??…..ለምን ስራችን እና ስብከታችን ዬቅል ይሆናል ….በእርግጥ ስደት አስቀያሚ ነው ….ግን አገር ላይ በድህነት እንደመገፋት የባሰ አሰቃቂ ነገር የለም ! ሚሊየኖች በቤት ኪራይ ችግር በተንገሸገሹበት ሰዓት … እልፎች በስራ አጥነት ችግር ድግሪያቸውን እንደዣንጥላ እራሳቸው ላይ አድርገው በየማስታወቂያ ሰሌዳው ስር በሚንከራተቱባት ሰዓት ‹‹ጠግባችሁ ተሰደዳችሁ ›› ማለት …ሌላ እርድ ነው ! እንደው እነዚህ ወገኖቻችን በግላጭ በአደባባይ በግፍ ሲገደሉ አየን እንጅ በየጓዳው ስንቱ ነው የተራዘመ የችግር ሞት የሚሞተው ?! አሁንም ደላላ መርገም ስደተኛውን ተቀፅላ ስም እየለጠፉ ማሸማቀቅ መፍትሔ አይሆንም ….ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ….ለህዝቡ እንደልፋቱ የሚከፈልበት ስርዓት …. ሙስናን የሚፀየፍ አስተዳደር …. እናም ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና አፈፃፀም ያስፈልገናል ! ‹‹አህያውን ፈርተን ዳውላውን ››አይነት ከንቱ ልፈፋ የትም አያደርስም ! ህይዎት ብዙ መሻት ብዙ የማይገደብ ፍላጎት አላት …..ሰው በአሹቅ ብቻ አይኖርም !!

Filed in: Amharic