>
6:13 pm - Tuesday May 17, 2022

ጀማል ማንስ ቢሆን!? [ በድሉ ዋቅጅራ ዶ/ር]

Islamic State shoots and beheads 30 Ethiopians Ruetersወንድሜ ዳንኤል ክብረት ስለጀማል ማንነት የጻፍከውን አነበብኩት፡፡ ሰማእቱ ጀማል ሳይሆን ኤፍሬም እንደሆነ ማስረጃ ያልከውን ገልጸህ የጻፍከውን ተከትሎ በሙስሊምና በክርስቲያን አንባቢዎችህ መካከል የተፈጠረውንም ሀሳብ ጉተታ እንዲሁ፡፡ ዳንኤል የዚህ ወጣት ሙስሊም ወይም ክርስቲያን መሆን ለምን ይህን ያህል እንዳሳሰበህ አልተገለጠልኝም፡፡ በዚህ ጊዜ የዚህ ወጣት ሙስሊም ወይም ክርስቲያን መሆን ብዙ አያስጨንቅም፡፡

እኔን እውነቱ የቀደመው ይሁን አንተ ያልከው ልቤን አያሞቀውም ወይም አያቀዘቅዘውም፡፡ ምናልባት አንተም ሆንክ ይህን ሀሳቤን የሚያነቡ የእምነቴን ጥንካሬ ሊያጠይቁ ይችላሉ፡፡ የሰማእቱ ጀማል ወይም ኤፍሬም መሆን የማያስጨንቀኝ ሰብአዊነት ከሀይማኖት ስለሚቀድምብኝ ነው፡፡ የሰብአዊነት ድንበር ከሀይማኖት ጥገግ ይሰፋል፡፡ ‹‹ጀማል የተባለ ወጣት የክርስቲያን ወገኖቹን ሞት ተቃውሞ አብሮ ሰማእት ሆነ›› ይሉን ስሰማ፣ ጀማል በሀይማኖቱ አስተምህሮት ተኮትኩቶ ያደገ ምጡቅ ሰብአዊነትን የታደለ ወጣት በመሆኑ እጅግ ኮርቼበታለሁ፡፡ እንግዲህ ዳንኤል ያንተ አውነት ይህንን ለሰብአዊነት የተከፈለ መስዋእትነት ዝቅ አድርጎ ለሀይማኖት የተከፈለ አድርጎ ስላቀረበብኝ ነው ይህን ሀሳቤን ልገልጥልህ መነሳቴ፡፡

እዚህ ላይ ዳንኤል ልብ እንድትልልኝ የምፈልገው፣ ‹‹አንተ የጻፍከው እውነት አይደለም›› ማለቴ እንዳልሆነ ነው፤ እኔ የምለው፣‹‹እኔ እውነት ብዬ የተቀበልኩት (አንተ ሀሰት ነው ያልከው) ሀሰት ቢሆን እንኳን፣ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከእውነቱ የበለጠ ዋጋ አለው›› ነው፡፡ ህጻናት ሆነን ምግብ አንበላም ስንል ‹‹አያ ጅቦ››፣ ስናጠፋ ‹‹ጭራቅ›› መጣ እየተባልን በልተን አድረናል፤ ከጥፋት ታርመናል፡፡ ነገር ግን አያጅቦ አንበለም ያልነውን ሊበላ፣ ጭራቁ ስላጠፋን ሊበላን ከጓሮ አልነበሩም፤ ውሸት ነው፡፡ ከአንዳንድ እውነት እንዲህ ያለው በጎ ውሸት (ፈረንጆቹ ‹‹ነጭ ውሸት›› የሚሉት) ይሻላል፡፡

እንደኢትዮጵያ ባለ ሙስሊም ከክርስቲያን በሚኖርበት ሀገር፣ እንደሰሞኑ ያለ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ሽብር ሲደርስ፣ ‹‹አንድ ሙስሊም በክርስቲያኖች መገደል የለባቸውም ብሎ፣ አብሮ ተሰዋ›› መባሉ፣ በዚህ ሽብር መሀከል እንኳን ሰብአዊ ፍጡርነታችንን የሚያስታውስ፣እንደአንድ ሀገር ዜጋም የሚያስተሳስር ፈውስ ነው፡፡ መቼም ዳንኤል ይህ ዜና በሙስሊሙም በክርስቲያኑም የፈጠረው ስሜትአይጠፋህም፡፡ እና ይህንን ስሜት በሳምንቱ መግደልና፣ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ሙግት (ይህንን በጽሁፍህ ስር የተሰጡትን አስተያየቶች በማንበብ ማረጋገጥ ትችላለህ) መፍጠር ጥቅሙ ምንድነው?በአንተ አስተያየት እውነት ያልከው ነገር ያመጣው በጎ ይበልጣል መጥፎው? ይህን ነገር የሀዘኑ ስሜት ከጠገገልን በኋላ መንፈቅ ቆይተህ ብትነግረን አይሆንም ነበር?

መቼም ዳንኤል ከአሸባራቹ ከራሳቸው በስተቀር እየተፈጸመ ያለው ሰብአዊ ፍጡራንን ሁሉ፣ አገርና ቀለም ሳይለይ አሳዝኗል፡፡ እኔና አንተን ደግሞ ይህ አደጋ በዜጎቻችን ላይ መድረሱ ሀዘናችንን እጥፍ ያደርገዋል፡፡ እና በዚህ ጊዜ በሀዘናችን መሀል ጽናት፣ በከበበን ጨለማ ውስጥ የብርሀን ጭላንጭል የሚሆኑ እንደ ጀማልና ኤፍሬም ያሉ እውነቶች ወይም በጎ ፈጠራዎች ናቸው፡፡ ሰማእቱ ኤፍሬም ቢሆን እንኳን፣ ‹‹አይ.ኤስ ሀይማኖትን መሰረት አድርጎ ገደለ፣ አንድ ክርስቲያን የክርስቲያኖች መገደል ተቃውሞ ሰማእት ሆነ››፣ ብሎ ከማሰብ፣ ‹‹አንድ ሙስሊም የክርሲቲያኖችን መገደል ተቃውሞ ለሀይማኖት ሳይሆን ለሰብአዊነት ሰማእት ሆነ››፣ ብሎ ማሰብ በምንኖርበት ማህበረሰብ፣ ሀገር ብሎም አለም የሚያጸና አብሮነት ተስፋ የላቀ ነው፡፡

ሰማእቱ ጀማል ከሆነ አላህ፣ ኤፍሬም ከሆነ ደግሞ እግዚአብሄር ጽናቱን ይስጣቸው፡፡

Filed in: Amharic