>

የሳምንቱ ማስታወሻ [ኤርሚያስ ለገሰ]

ከትላንት ወዲያ ( እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2007)
” እናት ሬስቶራንት” አሌክሳንድሪያ
እሁድ ምሳ ሰአት ላይ አትላንታ የሚገኘው ማህደር ሬዲዬ አዘጋጅ የሆነው አቶ ሰይፋ ደወለልኝ። በቀጥታ እየተላለፈ ባለው ፕሮግራማቸው ላይ አጫጭር ጥያቄዎች ስላሉት ሊጠይቀኝ እንደሚፈልግ ገለፀ። አጭር ከሆነ ለመመለስ ፍቃደኛ መሆኔን ነገርኩት።
” በዛሬው ምርጫ የወያኔ መንግስት ለተቃዋሚዎች ስንት ወንበር የሚለቅላቸው ይመስልሀል?” በማለት ጠየቀኝ።
ብዙም ማሰብ ሳይጠይቀኝ፣ ” ምንም ወንበር አይሰጣቸውም!” አልኩት። መልሴ ብዥታ የፈጠረበት ስለመሰለኝ ምክንያት ያልኩትንም ጨምሬ ለማስረዳት ሞከርኩ። ከማህደር ሬዲዬ ጋር የነበረን ቃለምልልስ ሲጠናቀቅ “በእናት ሬስቶራንት” ምሳ የጋበዘኝ ጋዜጠኛ ወዳጄ በአስተያየቴ አለመስማማቱን ነገረኝ። አገርቤትን የሚያስታውስ ክትፎ መመገብ ትቶ ይሞግተኝ ጀመር። በስስት የሚቀርበውን ቆጮ የምሻማበት ጊዜ በማግኘቴ ወጉን እንዲቀጥል አደረኩ። እንዲህ በማለት ጀመረ፣
” ለማየት ያብቃህ እስከ ሀያ ወንበር ይፀድቁባቸዋል። ለሰማያዊ 2፣ ለመራራ ፓርቲ እስከ 15፣ ለበየነ እስከ 3 ወንበር ይሰጧቸዋል። ከጀርባቸው ቢታረዱ ሰባራ ወንበር የማይሰጡት ለገብሩ አስራት ፓርቲ ነው” አለኝ።
” ሌሎቹም ፓርቲዎች ከአረና ፓርቲ የተለየ እጣ ፋንታ አይደርሳቸውም” አልኩት።
” እንዴት?፣ ለምን? መነሻህ ምንድነው?” በጥያቄ አጣደፈኝ። ድሮም የጋዜጠኛ ነገር!
” የህውሀትን ባህሪ በደንብ መረዳት ያስፈልጋል። የህውሀት ባለስልጣናትና ካድሬዎች አስተሳሰብ፣ ባህሪ፣ እምነትና ተግባር ጠንቅቆ ማወቅ የስርአቱን ምንነት ለመረዳት እድል ይሰጣል። ሲጀምር ህውሀት የበታችነት ስሜት የተጠናወተው ድርጅት ነው። በዚህ ምክንያት ቀንና ለሊት የፍርሀት ማእበል የሚንጠው ነው። በሁለተኛ ደረጃ ህውሀት እወክለዋለው ብሎ የሚያስበው ህዝብ ከኢትዬጲያ ህዝብ ከ7% በታች ስለሆነ የስልጣኑ ምንጭ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሚካሄድ ምርጫ አይደለም። ይልቁንስ ህዝብን የመግዛት ሌጅትመሲው የሚመነጨው በዘረጋው የፀጥታ መዋቅርና የጠመንጃ አፈሙዝ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ሁሉን የጠቀለለ ስልጣን ፍላጐት የሚመነጭ ነውር የማያውቁ ስግብግቦች ናቸው። አንዲትም ቀዳዳ መክፈት አይፈልጉም። በዛ ላይ ልባቸው አይገኝም” አልኩት።
” ልባቸው አይገኝም ስትል ምን እንዳስታወስከኝ ታውቃለህ? አስመራ የሄድኩ ጊዜ አንድ እጅግ ጠመዝማዛ ፣ በጣም ረጅምና የሚያስፈራ መንገድ ጐብኝቼ ነበር። ”
ንግግሩን አቋርጬው ፣
” ከሊማሊሞ ይብሳል?” አልኩት። በአንድ ወቅት አቶ መለስ ተቃዋሚዎችን ሲያስፈራራ የሊማሊሞን መንገድ ማንሳቱ ትዝ ብሎኝ።
” ሊማሊሞን አላውቀውም። ኤርትራ እንዳየሁት ጠመዝማዛ መንገድ ከሆነ ግን በጣም ያስፈራል። …እናም የገረመኝ ምኑ መሰለህ? የመንገዱ ስያሜ!”
” ምንድነው የሚባለው?”
አንገቱን አየነቀነቀ ” ልበ-ትግራይ ” አለኝ።
” አውቃለሁ አልኩት ” ርግጥም አውቅ ነበር። አስከትዬም “ታዲያ ጃንሆይ በዚህ መንገድ ላይ ከኤርትራውና ከትግራዩ ገዥ ጋር ሲሄዱ የተበሻሸቁትን አልነገሩህም?” አልኩት።
” አልነገሩኝም!” አለ ጆሮውን አቁሞ።
” እንዳትናደድ ብለው ነው። ለማንኛውም ሌላ ጊዜ አጫውትሀለሁ። አሁን ቅድም ወደ ጀመርነው የምርጫ አጀንዳ እንመለስ። …ህውሀቶችን እስከማውቃቸው ድረስ ሁሉን ካልጠቀለሉ እንደ ውርደት የሚቆጥሩ ናቸው። በዛ ላይ ተቃዋሚዎችን ” ጠላቶች”፣ ” እንቅፋቶች”፣ ” የጥፋት ግንባሮች” በሚል የማጭበርበሪያ ስትራቴጂ የሚፈርጁ ናቸው። እንደዚህ አይነት አመለካከት ኖሯቸው ወንበር ይለቃሉ ማለት ከእባብ እንቁላል እርግብ የመጠበቅ ያህል ነው” አልኩት።
” እኔ እኮ ይሄ አዳፋና እኩይ ባህሪያቸው ጠፍቶኝ አይደለም። ግን ቢያንስ ምእራባውያንን ለማስደሰትና እርዳታና ብድር ለማግኘት የተወሰነ ወንበር ሊለቁ ይችላሉ ከሚል ምልከታ ተነስቼ ነው።”
” የኢሳቱ ብእረኛ ገብረጳዲቅም እንደዛ አይነት ሀሳብ ያለው ጵሁፋን አዳምጫለሁ። እነዚህ ሰዎች የለከፋቸው የጠባብነት ደዌ ወደ ካንሰር ከተቀየረ ቆይቷል። ከድሮ አስተሳሰባቸው መላቀቅ አይችሉም። እንደውም የመራራን ቃል ልዋስና ‘ ጫካው ከእነሱ ወጣ እንጂ፣ ‘እነሱ ከጫካው አልወጡም ‘ … ከተጣባቸው የዜሮ ድምር ፓለቲካ መላቀቅ አይችሉም” በማለት ምላሽ ሰጠሁት።
” አንተ ያልከው ከሆነ አሜሪካንን ጉድ አደረጓት። በተለይ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤቱና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ብላ የተናገረችው ሴትዬ ምን ይውጣታል? እውነቴን ነው የምልህ! ስቴት ዲፓርትመንቱ አመታዊ ሪፓርቱን ሲያወጣ ምን ብሎ ሊጀምር ነው? ” በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው የኢትዬጲያ መንግስት…” ብሎ ሊጀምር ነው?” በማያቋርጥ ሳቅ ውስጥ ሆኖ ተናገረ።
” አየህ! አሜሪካኖቹ ብዙ የገባቸው የማይመስለኝ ህውሀት አሜሪካንን ማዋረድ እንደ አንድ ዋነኛ ስራው ከወሰደ መቆየቱን ነው። ለዚህ የተለያየ ምክንያት አላቸው። ሲጀመር አሜሪካኖች ስታዋርዳቸውና ፊትህን ስታዞርባቸው ይቀርቡሀል የሚል አመለካከት አላቸው። ሲቀጥል በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካን ፍላጐት ወታደራዊ ድጋፍ ማግኘት ነው። ይህን ፍላጐት ያለማቅማማት ማሟላት የሚችሉት እነሱ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለዚህም ነው በብዙ ኢትዬጲያውያን ዘንድ የሱማሊያ ጦርነት ” ለአሜሪካን ቀብድ ማስያዣ የተደረገ የውክልና ጦርነት” የሚል ስያሜ የተሰጠው። በነገራችን ላይ ከኢትዬጲያ አንጳር የአሜሪካ ወታደራዊ አታሼዎቹ ከውጭ ጉዳይ መስሪያቤቱ በላይ ስልጣን እንዳላቸው ህውሀቶች ያምናሉ። ሌላው ቀርቶ በቅርቡ የሳሞራ የኑስ ወደ አሜሪካ መምጣት ለምን እንደሆነ መገመት ትችላለህ” አልኩት።
” እና አሜሪካን የምርጫ ውጤቱን ትቀበለዋለች ብለህ ታስባለህ?”
” ብትቀበለውም/ ባትቀበለውም ለራሷ ጥቅም ስትል ከህውሀት መራሹ መንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆና ለተወሰነ ጊዜ ትቀጥላለች።”
” እስከመቼ?”
” የሐይል ሚዛኑ እስኪያጋድል ድረስ!”
***
ግንቦት 18 ቀን 2007, ክሪስታል ሲቲ
አሜሪካኖቹ የነጳነት ቀናቸውን እያከበሩ ነው። ስራ ተዘግቷል። ዋሽንግተን ዲሲ ከየግዛቱ በመጡ ሞተረኞች ተጨናንቃለች። አንዳንድ የቀለበት መንገዶች ተዘግተዋል። መዝናኛዎች እስከ አፍጢማቸው ሞልተው ህዝቡ እደጅ ፈሷል። እኛም ወጉ አይቅርብን ብለን የአሜሪካኖቹን የነጳነት ቀን ለማክበር ከጋዜጠኛው ጓደኛዬ ጋር ወደ ክሪስታል ሲቲ ተያይዘን ሄደናል። አላማችን የአሳዳሪዎቻችንን የነጳነት ቀን ለመዘከር ቢሆንም ወጋችን በሙሉ በብዙ ሺህ ማይሎች ተጉዞ የሀገራችን ሁኔታ ላይ አርፋል። ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቀው ምርጫ!! እውነት ለመናገር ለምርጫው ሂደት ትኩረት ያልሰጠው የኢትዬጲያ ህዝብ በየቦታው በሚሰማው የሰማይና የምድር ልዩነት ያለው ውጤት እጅግ መገረሞች ታይተዋል። የህውሀት ንቀት መረን ማጣቱ ብዙ ኢትዬጲያውያንን አስቆጭቷል። በማህበራዊ ድረገጶችም መወያያ የሆነው ይህ ለከት ያለፈው የህውሀት ነውረኝነት መሆኑ አልቀረም።
ቀኑን ሙሉ መረጃ ሲሰበስብ የዋለው ጋዜጠኛ ወዳጄ የነበረው ፊት መገረሙን የሚያሳብቅ ነበር። ንግግሩንም የጀመረው እሱ ነበር፣
” የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ያለውን ሰማህ?” በማለት ጠየቀኝ።
” ለምንድነው የምንሰማው?… መጀመሪያውኑ የሟሸሸና ለይስሙላ የመጣ ነው። በሀገሪቱ ኢህአዴግ ያዘጋጃቸው ምርጫ ጣቢያዎች ከ45,000 በላይ ናቸው። የአፍሪካ ታዛቢዎች ማዳረስ የቻሉት 356 ጣቢያዎች ብቻ ነው። ይህ ማለት በአጠቃላይ ማዳረስ የቻሉት ከአንድ ፐርሰንት በታች (0•8% ) ብቻ ነው። መሰረታዊ የስታስቲክስ ናሙና ጥናትን ገደል የከተተና ተቀባይነት የሌለው ነው። በዛ ላይ እንደ አፋር ያሉ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ኮሮጆ የሚጠቀጠቅባቸው ቦታዎች ታዛቢ አላኩም” በማለት ምላሽ ሰጠሁት።
” ቢሆንም ባልተለመደ ሁኔታ ከተመለከቷቸው ቦታዎች 21% ኮሮጆዎች ቀድመው ህጉ ከሚፈቅደው በፊት ተከፍተው አይተናል ማለታቸው ትልቅ ጅምር ነው። በዛ ላይ ምርጫው ፍትሀዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጳ የሚሉ ቃላትን ከመጠቀም ተቆጥበዋል። ይህ ለህውሀት መጥፎ ምልክት ነው” በማለት ከሰበሰበው መረጃ በመነሳት ተናገረ። አስከትሎም፣
” ይልቁንስ አስገራሚ ውጤቶች ልንገርህ። ሀይለማሪያም ደሳለኝ በተወዳደረበት በሎሶ በምትባል ምርጫ ክልል 100% ሲያገኝ፣ የሰማያዊና ኢራፓ ፓርቲ እጩዎች 0% አግኝተዋል። ” በማለት እፍረት አፋን ሞልቶት ተናገረ። እኔም ከአፋ ተቀብዬ፣
” ባይሆን ነበር የሚገርመኝ። ጋሽ ሀይሌ እኮ በልቡ አቶ መለስን አስቀምጦ ነው የሚንቀሳቀሰው። እሱ ያደረገውን ማድረግ አለበት። እሱ የተናገረውን መናገር አለበት። ቀድሞ አቶ መለስ እንደሚያገኘው አህያ የማይሸከመው ድምጵ ማግኘት አለበት። በአካባቢው ያለውን ተቀባይነት በመቶ ፐርሰንት ካላሳደገ ሌላው ጋር ያለው ክብር ወደ ታች ይወርዳል ብሎ ማሰቡ አይቀርም። ጋሽ ሀይሌ ለህዝብ በሚታይ ችሎታው ተፈትኖ ሰለወደቀ ያለችው ብቸኛ አማራጭ ይህቺ ብቻ ናት። አማኑኤልና ጋዜጠኛ ወንድሙ ይህን ተልእኮ የፈፀሙ ይመስለኛል” አልኩት።
” ሆዳሙ በሬ?”
“በነገራችን ላይ ከማን አንሼ በሚመስል መንገድ አማኑኤል አብርሀ ( ኢህአዴግ ቢሮ) በወላይታ አንድ ምርጫ ክልል 1182 ሲያገኝ ተቀናቃኙ አንድ ድምጵ ብቻ እንዲያገኝ አድርጓል። የሚገርምህ በምርጫ 97 አማኑኤል የወላይታ ህዝብ ይጠላዋል ብሎ በረከት በመጨረሻው ሰአት ጋሽ ሀይሌን ትእዛዝ ሰጥቶት እንዲሰረዝ ተደርጓል።
” ታዲያ ዛሬ ለውድድር ሲቀርብ ህዝቡ ተሳስቶ ነበር ማለት ነው? ወይንስ በረከት ተደቆሰ?”
” እሱ ጊዜ ይፈታዋል። ከዛ ይልቅ ህዝቡ ተሳስቶ ነበር የሚለውን እንቀበል! አይመስልህም?” አልኩት።
” ህዝብማ መሳሳቱን እማ በፕሮፌሰር በየነ ድምጵ አሳዩን። እስቲ እግዜር ያሳይህ የሾኔ ህዝብ ” በየነ ክብራችን” የሚል ዘፈን ያለው ህዝብ ነው። ሾኔ ስለበየነ ክብርና ዝና አውርታ የምትጠግብ አይደለችም። በእሱ መማል ብቻ ነው የሚቀራቸው። በነገራችን ላይ ብዙ ልጆች ስማቸው በየነ ነው። እንደዚህ በምታከብረው ወረዳ ዬሴፍ ዳይሞ የሚባል ማንም የማያውቀው የኢህአዴግ ተወካይ 10,961 ሲያገኝ በየነ 252 አገኘ ብሎ ማወጅ አሳፋሪ ነው። ቢገባው ለሀይለማርያም ራሱ ውርደት ነበር? ”
” ሀይሌ ከተዋረደ ቆየ እኮ!” የለበጣ ሳቁን ለቀቀው።
” ለነገሩ ጋሽ ሀይሌ መቼ እንደበቃኝ ታውቃለህ? አንድ ጊዜ በድሬደዋ የሀገር ሽማግሌዎችን ለማነጋገር ወደ ድሬ ያቀናል። ሽማግሌዎቹ አርብቶ አደሮች ስለነበሩ በርካታ ግመሎች አላቸው። በጥያቄና መልስ ጊዜ በድሬደዋ የተሰራው ድልድይ አጭር ስለሆነ ግመሎቻቸውን ማሳለፍ እንደቸገራቸው ይነግሩታል። ምን ብሎ ምላሽ የሰጠ ይመስልሀል?”
” ምን አለ በእናትህ?”
” ፕላኑን የሰሩት ቻይናዎች ስለሆኑ የግመል ቁመት ስንት እንደሆነ አያውቁም። ኢትዬጲያዊ መሀንዲሶቹም ከደጋ አካባቢ ስለመጡ የግመል ቁመት አያውቁም።”

Filed in: Amharic