>
4:53 pm - Wednesday May 25, 3566

የችሎቱ ድራማ ተጠናቋል! በኢትዮጵያዊው ሙስሊም ላይ ከ7 እስከ 22 ዓመት እስራት ተፈርዷል! [ድምፃችን ይሰማ]

የወኪሎቻችን ፍርድ ተጨማሪ የትግል ተነሳሽነት ምንጫችን ሆኖ ይቀጥላል!

ሰኞ ሐምሌ 27/2007

በወኪሎቻችን ላይ ሲካሄድ የነበረው ለዓመታት የቆየ የችሎት ድራማ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል!

መንግስት በወኪሎቻችን ላይ ፖለቲካዊ የቅጣት ፍርድ ያስተላለፈ ሲሆን በ18ቱም ተከሳሾች ላይ 7 እስከ 22 ዓመታት የሚደርስ እስራት በይኗል፡፡ በዚህም መሠረት አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ እና ካሚል ሸምሱ የ22 ዓመት፣ በድሩ ሑሴን፣ ሷቢር ይርጉ፣ ሙሀመድ አባተ፣ አቡበከር ዓለሙ እና ሙኒር ሑሴን የ18 ዓመት፣ ሸኽ መከተ፣ አህመድ ሙጠፋ፣ ሰዒድ ዓሊ፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም 15 ዓመት፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ባሕሩ ዑመር፣ ዩሱፍ ጌታቸው እና ሙራድ ሽኩር 7 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ የቅጣት ፍርዱ ሲነበብ ሁሉም ጀግኖቻችን ተክቢራ ይሉ ነበር!

Ye chilotu dirama....ይህ አሳዛኝ ፍርድ ያገጠጠ ኢ-ፍትሐዊነት መሆኑን ውሳኔውን ያስተላለፉት የመንግስት ባለስልጣናት እና ድራማውን የተወኑት አቃቤ ሕግጋት እና ዳኞች እንኳን ሳይቀር ያውቁታል፡፡ ለዓመታት ሰላማዊ ትግሉን ቀጥሎ ያለው ሕዝበ ሙስሊም እና አጋርነቱን የገለጸው መላው ኢትዮጵያዊም ያውቀዋል፡፡ የበለጠ እንታገል ዘንድ የሚያነሳሳ ምክንያት እንጂ ከትግል የሚያርቅ ሰበብ አለመሆኑም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ሰላማዊ ትግልን በግፍ የእስር ፍርድ ማስቆም ቢቻል ኖሮ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ባልተገረሠሠ ነበር! ማንዴላ የትግል መሪ እንጂ ትግሉ ራሱ ባለመሆናቸው ‹‹አሸባሪ›› ተብለው ቢታሰሩም ትግሉን ከስኬት ደጃፍ ከመድረስ አላገደውም፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የሚያስተምረን አንድን የማይቋረጥ ዑደት ነው፤ አምባገነኖች ይጨቁናሉ…. ሕዝብ ጭቆናውን ይቃወማል…. ሕዝብ ጭቆናውን ይታገላል… ሕዝብ ትግሉን ያቆም ዘንድ አምባገነኖች ያስራሉ፣ ይገድላሉ፣ ይገርፋሉ… በመጨረሻም ሕዝብ ድል ያገኛል! ሌላ ዑደት የለም! ወኪሎቻችን ላይ የተሰጠው ፍርድ ሁሉም የጠበቀው እንደመሆኑ ትግላችንን እንደምንቀጥል ከመግለጽ ያለፈ አዲስ መግለጫ አይኖረንም! ከፊታችን ያለው ረዥም ትግል ነው! ለዚህ ትግል ሊኖረን የሚገባው ዝግጁነት በዒድ እለት በተላለፈው መግለጫ ውስጥ በሰፈሩት የሚከተሉት 6 ነጥቦች ተጠቃሏል፡፡ ነጥቦቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
*************************
ሕዝባዊ ፕሮጀክቶች ይኖሩናል – ኢንሻአላህ!
ሰላማዊ ትግሉ ህዝባዊ መሰረት ያለው እንደመሆኑ የወደፊቱ ሂደታችን ህዝቡን በስፋት የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡ አካሄዱም እስከዛሬ ስንሰራ ከነበረው በተጨማሪ ማንኛውም ሙስሊም በነፍስ ወከፍም ይሁን በቡድን የራሱን ድርሻ የሚያበረክትበት መድረክ የሚመቻችበት ይሆናል – ኢንሻአላህ! ትግላችን በተመረጡ ‹‹መርሃ ግብሮች›› ዙሪያ ብቻ የታጠረ አይሆንም፡፡ ሁሉም ሙስሊም የተለያየ ችሎታ፣ ዝንባሌና ኢስላምን ሊያገለግልበትና ትግሉን ሊደግፍበት የሚችልበት አጋጣሚ አለው፡፡ ይህንን ችሎታ፣ አቅምና አጋጣሚ ሁሉ ደግሞ ለሃይማኖቱ ነፃነት ትግል የሚያውልበትን መንገድ ማቀድና በተሳለጠ መልኩ ማስሄድ ያስፈልጋል፡፡
የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች እንኳን የሚታወቁባቸው የተለያዩ ችሎቻዎች አሉ፡፡ ከፊሉ ቁርአንን በመፃፍ፣ ከፊሉ የቁርአን ትንታኔ (ተፍሲር) በመስጠት፣ ከፊሉ በሐዲስ እውቀት፣ ከፊሉ ገንዘቡን በመለገስ፣ ከፊሉ የተላት መከላከል ስልት በማወቅና በጀግንነት፣ ከፊሉ በዙህድ (የመጪውን ዓለም በማስታወስና ዱንያን በመናቅ)፣ ከፊሉ ሐሳብ በማፍለቅና ምክር በመለገስ ተሳትፈዋል፡፡ ሌሎችም በርካታ ሚናዎች ነበሯቸው፡፡ ይህ የሚያመላክተን እያንዳንዱ ግለሰብ አላህ የሰጠው ችሎታና አቅም መኖሩንና የሚኖረውም ችሎታ፣ አቅምና አጋጣሚ ስራ ላይ መዋል እንዳለበት ነው፡፡
በእስልምናችን የሚናቅ መልካም ተግባር የለም! የነፍስ ወከፍ ተነሳሽነትም የሚበረታታ ነው!
ለብዙዎች ቀላል የሚመስሉ አንዳንድ ስራዎች ትልቅ ተግባር መሆናቸውን መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) አመላክተውናል፡፡ ነሳኢና ኢብኑ ማጀህ በዘገቡት ሐዲስ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በአንድ ወቅት አንድ በቂብላ አቅጣጫ የተተፋን ቆሻሻ አይተው ቅር ሲሰኙ አንዲት የአንሷር ሴት (ረ.ዓ) ከቦታው ፍቃ አንስታ በቦታው ላይ ሽቶ አርከፈከፈች፡፡ በዚህም መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ተደስተው ‹‹ምንኛ ያማረ ስራ ነው!›› ሲሉ አወደሱ፡፡ ይህች የአንሷር ሴት (ረ.ዓ) በግሏ ያደረገችው ነበር፤ ይህንን ለመፈፀም ልዩ ትእዛዝ መጠበቅም አላስፈለጋትም፡፡ ይህን የመሳሰሉ ምሳሌዎች በርካታ እንደመሆናቸው ማናችንም ብንሆን ‹‹እኔ አቅም የለኝም፡፡ የማበረክተው ስራ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም›› የሚል አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም፡፡ ሁሉም የሚጠየቀው አላህ በሰጠው ችሎታ፣ ዱንያዊ እና ዲናዊ እውቀት፣ ጊዜ፣ ጉልበት፣ ገንዘብ ነውና፡፡ ሁሉም ሙስሊም ለሃይማኖት ነፃነቱ ‹‹ተጨማሪ ምን ላበረክት እችላለሁ?›› ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡ ‹‹እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ! ምን ለውጥ ላመጣ እችላለሁ?›› የሚሉ አስተሳሰቦች ፈፅሞውኑ ሊኖሩን አይገባም፡፡
ግላዊ አቅምን ከማየት ቀጥሎ ደግሞ በቡድን የሚሰሩ ስራዎችን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በየአካባቢያችን በቡድን (ጀመዓ) ሆነን በመደራጀት ልንሰራቸው የምንችላቸው ስራዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ሰፊ ውይይት ልናደርግ ይገባል፡፡
የወደፊት አቅጣጫችን ሁሉም ተሳታፊነቱን የሚያጎለብትበትን ህዝባዊ መሰረት ለማጠናከር የምንሰራበትን መንገድ የሚከተል ይሆናል፡፡ በመሆኑም የትግላችንን ረጅምነት ተገንዝበን፣ ህዝባዊ መሰረቱንም አጠናክረን ለመቀጠል የሚከተሉትን 6 ተግባራት እንፈፅም፡-
1. ለረጅም ጊዜ ለመታገልና ድልን ለመጎናፀፍ ዱዓ እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ በትግል ሜዳ ላይ የነበሩ ሙስሊሞችን አላህ በቁርአኑ በሚከተለው መልኩ አውስቷቸዋል፡-
‹‹በንግግራቸውም ‹ጌታችን ሆይ! ኃጢአቶቻችንንና በነገራችን ሁሉ ወሰን ማለፋችንን ለእኛ ማር፤ ይዞታችንንም አደላድል፤ በከሃዲዎችም ሕዝቦች ላይ እርዳን› ማለታቸው እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡›› (ሱራ አሊ ዒምራን 3፡147)
እነዚያን ታጋዮችና አላህን የጠየቁትን ጥያቄያቸውን እስከዓለም ፍፃሜ ድረስ ለመጪው ትውልድ አርዓያ እንዲሆኑ በቁርአኑ አውስቷቸዋል፡፡ ዱዓቸው ደግሞ አላህን ምህረት መጠየቅን (ኢስቲግፋርን)፣ በቦታቸው ላይ ሆነው ፅናትን እና ድል ማግኘትን (ነስርን) ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህ በዱዓችን በርትተን መቀጠል ይኖርብናል፡፡
2. ህዝቡ በነፍስ ወከፍ ራስን መፈተሽና በጀመዓ ሆኖ ምን መስራት እንደሚችል መወያየት አለበት፡፡ ያለውንም ሐሳብ መልእክት በገጻችን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ካለው ትምህርት፣ እውቀት፣ የዲን ዒልም፣ አካባቢያዊ ተፅእኖ የመፍጠር ችሎታ፣ የማስተባበር ችሎታ፣ መረጃ የማግኘት አጋጣሚና አቅም፣ በገንዘብ የመደገፍ አቅም፣ ሐሳብና ስልት የመቀየስ ችሎታና የመሳሰሉትን ግብዓቶች መጠቀም ትግላችንን አጠናክረን እንድንሄድ ይጠቅመናል፡፡ ስለዚህም በዚህ ዒድና በሚቀጥሉት ተከታታይ 15 ቀናት በግላችን እያሰብን፣ በቡድን እየተወያየን፣ ያለንበትን አካባቢ እያገናዘብን ሐሳብ የምንሰጥበት ጊዜ ይሆናል፤ ኢንሻ አላህ!
3. ለአንድ ትግል መደራጀት እጅግ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ በተለይም የሃይማኖት ጭቆናን በሰፊው ሊያሰፍን አስቦና አቅዶ ከሚንቀሳቀስ መንግስት ጋር ለሚደረግ የረጅም ጊዜ ሰላማዊ ትግል ከመደራጀት ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖርም፡፡ ስራ በጀመዓ ሲሰራም የአላህ እርዳታ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ይህን ወሳኝ ሰላማዊ ትግል በሚያግዝ መልኩ በስፋት መደራጀት ይጠበቅብናል፡፡
4. መረጃ ለትግል ወሳኝ የሆነ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች መንግስት የሚያደርግብንን ደባ ለማወቅ መጣርና ለትግላችን ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎችን ማቀበል ይኖርብናል፡፡ በአንፃሩም ለትግሉ የሚሆኑ መረጃዎችንም እንዲሁ ላልደረሰው የማዳረስ ስራ ይጠበቅብናል፡፡
5. የህዝባዊ ትብብር መንፈግ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ የትብብር መንፈግ ስልቶችን በስፋትም በዓይነትም ተግብሮ በአላህ ፈቃድ ውጤት ለማምጣት የሁሉም ተሳትፎ አስፈላጊ ነው፡፡ ‹‹እኔ ምን ለውጥ ላመጣ እችላለሁ?›› የሚሉ የነፍስ ወከፍ ሚናን የሚያሳንሱ አስተሳሰቦች በአስቸኳይ መቀረፍ አለባቸው፡፡ የዚህን ሰላማዊ ትግል ስልት አድማስ ለማስፋት መረጃን ከማዳረስ ባሻገር ከዚህ በፊት ስለ ህዝባዊ ትብብር መንፈግ ስልት ጠቀሜታዎች የተሰጡ ማብራሪያዎችን ግንዛቤው ላልደረሳቸው ሁሉ ማስተላለፍ ይኖርብናል፡፡
6. በዚህ ትግል ሂደት መስዋእት ለሆኑና በግፍ ለታሰሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በዘላቂነት ድጋፍ ለመስጠት ህዝቡ እያደረገ ያለው ጥረት በጣም አበረታች ነው፡፡ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ሰላማዊ ትግል የራሳቸውን አስጸዋፅኦ ለማድረግ መልእክት እየላካችሁልን ትገኛላችሁ፡፡ ይህ ድጋፋችሁ በበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ አላህ ስራችሁን ይቀበላችሁ እንላለን፡፡
*******************************
እንግዲህ ቀጣይ ሰላማዊ ትግላችን ለመቀጠል እነዚህን 6 ነጥቦች ከልብ እናጢን፡፡ እነዚህን ነጥቦች እንደመንደርደሪያ በማድረግ አሁን በመላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ውስጥ የተፈጠረውን ቁጭት ትግሉን ይበልጥ በሚያጎለብትበት መስመር እንዲፈስ እናድርግ። ሁላችንም ፊታችንን ወደትግሉ እናዙር፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
የወኪሎቻችን ፍርድ ተጨማሪ የትግል ተነሳሽነት ምንጫችን ሆኖ ይቀጥላል!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!

Filed in: Amharic