>
5:17 am - Sunday August 1, 2021

አርብን በቂሊንጦ እስር ቤት [ኤሊያስ ገብሩ]

‹‹ኢህአዴግ ልጅነታችንን ቀምቶናል››
‹‹በሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ በእጅ የሚዳሰስ ኢ-ፍትሃዊነት ተፈጽሟል››
ጦማሪ አቤል ዋበላ
——
‹‹የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በደንብ መመርመር አለበት››
‹‹ማክሰኞ ሻይ እንጠጣለን (ፈገግታ ያጀበው ሳቅ)›› ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ
——
‹‹ለውጥ እንዲመጣ ፖለቲካችን መዘመን አለበት››
‹‹በመከራ እስር ቤት ውስጥ ተገኝተንም የፍረጃ ፖለቲካ ሥራውን ሲሰራ ስትመለከት በጣም ያሳዝናል››
ብርሃኑ ተ/ያሬድ

Abel Wabelaየአዕምሮ እረፍት ከሚሰጡ ነገሮች መካከል አንዱ የታሰረን ሰው መጠየቅ ነው፡፡ ከትናንት በስትያ አርብ ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም፣ ጠዋት ላይ ከወዳጆቼ አቤል ዓለማየሁ እና ኢዩኤል ፍስሐ ጋር ወደቂሊንጦ እስር ቤት አምርተን ነበር፡፡ እኔ እና አቤል ወደዞን ሶስት አመራን፣ ኢዩኤል ደግሞ ወደዞን ሶስት፡፡ መደበኛውን ምዝገባውን እና ፍተሻውን ቀድሜ እኔ ጨረስኩና ወደመጠየቂው ቦታ አመራሁ፡፡ አራት የሚሆኑ ፖሊሶች በጥበቃ ማማ ሥር ሆነው እየሳቁ እንጨት ላይ ስፖርት ይሰራሉ፡፡ እንደወታደር ስፖርታቸው አይማርክም፡፡

…ላስጠጣራቸው የነበሩት ልጆች በቤተሰቦቻቸው እየተጠየቁ ነበር፡፡ የዞን 9ኙ ጦማሪ አቤል ዋበላን ከጓደኛው ናትናኤል ፈለቀ ታናሽ እህት ጋር አገኘኋሁ፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ከናትናኤል እህት ጋር ‹‹ተዋዋቁ›› ሲለን፣ ‹‹ኧረ እንተዋወቃለን›› ብለን ፈገግ አልን፡፡ ናትናኤል ከርቀት ሰዎች እያናገረ ስላየሁት በዚሁ ዞን የሚገኘውን ብርሃኑ ተ/ያሬድን ጥራልኝ አልኩት አቤልን፤ እሱም ሊጠራልኝ ሄደ፡፡ ናቲ በቦታው ተተካ፡፡ ሞቅ ካለው ሰላምታ በኋላ ‹‹ሰኞ ከመውጣታችሁ በፊት እንያችሁ ብለን ነው፡፡›› ብዬ አሳኩት፡፡ ‹‹ብዙዎች እንዲህ እያሉ መጥተው እየጠየቁን ነው›› አለኝ – ፈገግ እያለ፡፡ ሳቁን ገታ አድርገን፣ ስለክሳቸው የፍርድ ሂደት ቁምነገሮችን ማውራት ቀጠልን፡፡ ‹‹አንዴ ሁላችንም ተሰብስበን፣ ‹የክሳችን ጉዳይ ምን ሊሆን ይችላል?› ብለን ተመካክረን ነበር፡፡ ግምታችን ትክክል ሆኖ አግኝተናዋል፡፡ የሚገርምህ ፣አምስት ሰው ይፈታሉ ብለን ጠብቀን ነበር፡፡ እንደጠበቅነውም ሆነ … ኢህአዴግ አስቦ ነው አንድን ድርጊት የሚያደርገው፡፡›› አለ ናትናኤል፡፡ እኔም ‹‹አንድን ነገር ትርፍ እና ኪሳራውን አስልቶ ነው የሚያደርገው›› ብዬ ጨመርኩለት፡፡ ብዙ ኢትዮጵያኖች ዋጋ እያስከፈለ ስለሚገኘው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅን በተመለከተ ትንሽ ሰፋ ያለ ሀሳብ በተመስጦ ለተዋወጥን፡፡ ናትናኤልም ‹‹የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በደንብ መመርመር አለበት›› አለበት ሲል አጽንኦቱን ሰጠ፡፡

ሁለቱ ጦማሪያንና ሶስቱ ጋዜጠኞች ከመፈታታቸው 26 ቀናት ቀደም ብሎ፣ በዚህ እስር ቤት ዞን 2 ሄጄ ተስፋለምን፣ በፍቃዱንና አጥናፍን ጠይቄያቸው ነበር፡፡ በወቅቱ በፍቃዱ ‹‹የተወሰናችንን ፈትቶ የተወሰናችንን ደግሞ ያስቀራል፡፡›› ሲል አጥናፍ በበኩሉ፣ ‹‹በእኛ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የእነሀብታሙን የፍርድ ጉዳይ ይወስናል፡፡ ከእኛ መካከል የሚፈታ ካላ ከእነሀብታሙም መካካል የሚፈታ ይኖራል›› ብሎኝ ነበር፡፡ እንዳለውም ሆነ፣ በእነሀብታሙ አያሌው ላይ ያልተተገበረ ነገር ቢኖርም! በአጠቃላይ የእነዚህ ወጣቶች ግምት ትክክል ነበር፡፡ የአገዛዙን አካሄድ እና ድርጊት በአንክሮ አስተውሎ ማሰላሰል ለዚህ ይጠቅማል፡፡ አስበውና አሰላስለው ለእውነተኛ ነገር የቀረበ ግምት ለሚሰጡ ሰዎች ትልቅ አክብሮት እሰጣለሁ፡፡ የቀድሞ የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ደኤታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ በዚህ ረገድ ያስደስቱኛል፡፡ ‹‹ከስርዓቱ ጋር 10 ዓመት ያህል አብረው ዘልቀው እንዴት አይገምቱ?›› የሚል ጥያቄ ከተነሳም ‹‹ሥንቱ አለ አይደለም ከሥርዓቱ ጋር አርጅቶ ምን እንደሚሰራበት የማያውቅ፣ ሥንቱ አለ አይደል የድል አጥቢያ አርበኛ ሆኖ ምን እንደሚከወን የማይረዳ …›› የሚል መልስ ሰጥቻለሁ፡፡

አቤል ዓለማየሁ ፍተሻውን ጨርሶ መጣና በሰላምታ ተቀላለቀን፡፡ ከጎናችን ዞር ስንል ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ አለ፡፡ ‹‹ተጠያቂው ጠያቂ ሆነ!›› ብዬ ስቄ ሰላም አልኩት፡፡ ወዲው ብርሃኑ ተ/ያሬድ መጣ፡፡ ብርሃኑን ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከጓደኞቹ ጋር ታስረው አራዳ ፍርድ ቤት ለተጨማሪ ምርመራ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ በጠየቀባቸው ወቅት በአካል ከተያየን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ያገኘሁት፡፡ ‹‹ኤሊ እንዴት ነህ? የግንቦት ሰባት ወታደር እስከአራት ሰዓት ድረስ ነው የሚተኛው›› ብሎ በመሳቅ አልጋው ላይ ጋደም ካለበት ተነስቶ መምጣቱን ተናገረ፡፡ …እሱ፣ እየሩሳሌም ተስፋውና ፍቅረማሪም አስማማው ወደኤርትራ ሄደው ግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባርን ለመቀላቀል ካቀዱበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባለፈው ሳምንት ስለተሰማባቸው የምስክርነት ቃልና በቀጣይ ስለሚኖራቸው የፍርድ ሂደት ጭምር ዝርዝር አድርጎ ለእኔ እና ለአቤል አጫወተን፡፡ ስለፓርቲ ፖለቲካም የራሱን አተያይ ሰነዘረ፡፡ ‹‹ለውጥ እንዲመጣ ፖለቲካችን መዘመን አለበት፡፡ ደካማ ቤተሰቦቻችንን ትተን፣ በመከራ እስር ቤት ውስጥ ተገኝተንም የፍረጃ ፖለቲካ ሥራውን ሲሰራ ስትመለከት በጣም ያሳዝናል፡፡ …ለሁላችንም አንድ ሀገር ነው ያለችን›› አለኝ፡፡ ‹‹ለውጥ እንዲመጣ ፖለቲካችን መዘመን አለበት፡፡›› የምትለዋ በውስጤ በደንብ የመዘገብኳት የብርሃኑ ቃል ነበረች – እኔም ስለማምንባት፡፡ ያለንበትን ጊዜ ባልዋጀ ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት መሽከርከራችን አይደለ የመከራ ዘመናችንን ያረዘመው? ፖለቲካችንን በቸከ የመጠፋፋት ባህል ስለታነጸም አይደል እርስ በእርስ በጠላትነት ተቧድነን ያለርህራሄ የምንመታታው? ኧረ ብዙ ማለት ይቻላል ….

ያው ሶስት ተጠያቂዎችና ከሶስት በላይ ጠያቂዎች በቆሙበት ቦታ እየተቀያየሩ ማውራት ተገቢ ነውና ወደ አቤል ዋበላ ዞርኩ፡፡ የክስ ሂደታቸውን እና ብይን ለመስጠት ተደጋጋሚ ቀጠሮ በተሰጣቸው ጉዳይ ላይ ሀሳቦችን ተለዋወጥን፡፡ ሕዳር ወር ላይ በዚህ ዞን ታስሬ ስለነበርኩ፤ ስለምናውቃቸው ሰዎች አንስተን አወጋን፡፡ ‹‹የቀድሞ የመኢአድ አመራር የነበረው አቶ ማሙሸት አማረ፣ ከሰሞኑ እስኪፈታ ድረስ አንተ ለአንድ ሳምንት ትተኛበት በነበረበት ቦታ ላይ ነበር መኝታው፡፡›› አለኝ፡፡ [በቂሊንጦ አልጋ ያላገኘ እስረኛ የሚተኛበት ቦታ ‹‹ደቦቃ›› የሚል መጠሪያ አለው፡፡ የቤቱ በር ሲዘጋ፣ አልጋ ያላገኙ እስረኞች ፍራሽ ደርድረው በር ሥር ያድራሉ፡፡ አቤል እና ዘላለም ክብረት ከማዕከላዊ ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ሲዘዋወሩ ከ15 ቀናት በላይ በዚህ ሁኔታ ለመተኛት ተገድደው እንደነበረ ነግረውኛል፡፡ እኔም እተኛ የነበረው አቤል ከሚተኛበት ተደራራቢ አልጋ ጎን ባለ ሌላ ተደራራቢ አልጋ መካከል፤ መሬት ላይ ነበር፡፡ እንግዲህ ማሙሸትም እዚሁ ነበር ይተኛ የነበረው]
‹‹ከማሙሸት ጋር ብዙ ሀገራዊ ቁምነገሮችን ተካፍለናል›› የሚለው አቤል፤ በቼዝ ጨዋታ ጎበዝ መሆኑንም ይመሰክርለታል፡፡ ባለፈው ወር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ከአቤል ጋር ዝዋይ እስር ቤት ስንጠይቀው መጽሐፎች ስለማይገቡለት ቼዝ በመጫወት ቀኑን እንደሚያሳልፍ አውግቶኛል፡፡

ጦማሪ አቤል ቀልድ ይችላል፤ ቁምነገር ሲናገርም የምሩን ነው፡፡ ወደቁምነገሩ ገባና እንዲህ አለኝ፡-
‹‹ኢህአዴግ ልጅነታችንን ቀምቶናል፡፡ ከአሁን በኋላ ልጅነት የለም፡፡ ከእስር ስንወጣም በጣም ከፍ ያለነገር ለሀገራችን በተግባር ማድረግ ይገባናል፤ ይጠበቅብናል፡፡ በእስር ቆይታችንም ብዙ የሀገራችንን ችግሮች ለማወቅ ችለናል፡፡››
ከአቤል ጋር፣ በዚህ በዚህ ዞን ታስረው ስለነበሩት ኡስታዝ አብበከር አሕመድ፣ አቡበከር ዓለሙ፣ ካሚል ሸምሱ ከሰዓት አኳያ ጥቂት ማወጋታችን አልቀረም፡፡ ‹‹ከአቡበከር ዓለሙ ጋር በአንድ ወቅት ስናወጋ፣ ስለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አጫውቶኝ ነበር፡፡›› የሚለው አቤል ፍርዳቸውን አስመለክቶ ቀጣዩን ተናገረ፡- ‹‹አቡበከር ዓለሙ በአንድ ወቅት ከእስክንድር ጋር በአንድ ዞን ታስረው በነበረበት ወቅት ጋዜጠኛው ጊዜ ምን ያህል ጨዋ፣ ሥነ-ምግባር ያለው፣ አስተዋይ፣ ለሀገር አርቆ አሳቢ እንደሆነ ጠቅሶልኝ ‹እስክንድር ላይ እንዴት 18 ዓመት ይፈረድበታል?› በማለት ሀዘኔታውን ነግሮኛል፡፡ ይኸው እሱም (አቡበከር) 18 ዓመት ተፈረደበት፡፡ ያሳዝናል፡፡ በሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ በእጅ የሚዳሰስ ኢ-ፍትሃዊነት ተፈጽሟል፡፡››
ያው የመለያያ ጊዜ ደረሰና ቻው ልንባባል ምዕራፉ ሆነ፡፡ ናትናኤልን ‹‹እንግዲህ ሰኞ በቀጠሯቸው መሰረት ፍርድ ቤት እንገናኝ›› አልኩት፡፡ ‹‹እሺ፣ ማክሰኞ ሻይ እንጠጣለን›› አለ እየሳቀ፡፡ ከእስር ተፈትተን ለማለት ነው፡፡ ብርሃኑም፣ የናቲን መልስ ሰማና በፈገግታ እየሳቀ ‹‹አንድ ቀን ማክሰኞ ድራፍት እንጠጣለን›› ካለኝ በኋላ ሰላም ሁኑ በመባባል ከእስር ቤቱ ግቢ ወጣን፡፡

ከእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጪም ኢዩኤል ቀድሞን ወጥቶ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሏል፡፡ ፀሐዩ በጣም ከበድ ያለ ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ወራት ገደማ ‹‹ክሳችሁ ተቋርጧል›› ተብለው ከእስር ከተፈቱት መካከል የሚገኙበት፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን እና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ ጓደኞቻቸውን (በፍቃዱ ሃይሉንና አጥናፍ ብርሃኔን) ጠይቀው ሲወጡ አገኘናቸውና ሰላም ተባባልን፡፡ እነተስፋለምን መጠበቅ ስለነበረባቸው ፀሐዩን ለመከላከል አንድ ጃኬት ነጥለው በጋራ ራሳቸው ላይ በማድረግ በቀስታ ጥላ ለመፈለግ ተንቀሳቀሱ፡፡ እኛም ወደመጣንበት ተመለስን፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት አራት የዞን 9 ጦማሪያንና ከሀገር ውጪ የምትገኘዋ ሶሊያና ሽመልስ፣ በሌለችበት በነገው ዕለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ብይን ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹መከላከል ሳስፈልጋችሁ በነጻ እንድትሰናበቱ›› የሚል ውሳኔ ተሰጥቷቸው ሁላችንም ደስ ይለን ዘንድ ከልቤ እሻለሁ!
ለዛሬ አበቃሁ፣ ሰናይ እሁድ ይሁንልን!!!

Filed in: Amharic