>

ትንታግ ብዕር ነጠፈ!! [አስፋ ጫቦ Corpus Christi, Texas, USA]

Page 1 of 4

ትንታግ ብዕር ነጠፈ!!
አስፋ ጫቦ Corpus Christi, Texas, USA
ESAT Special Documentary about Mulugeta Lule Oct 07, 2015ወንድሜ፤ጓደኛዬ ፤ሙሉጌታ ሉሌ ተለየን! የቀበሩ ስነስርአት መስከረም 27,2008 (October 8,2015) እስክንድሪያ ፤ቨርጂኒያ፤አሜሪካ(Alexandria,Verginia,USA) ተፈጽሟል። የግዴን በሰዉ አገር ሟቾች ሙሾ አዉራጅ ሆንኩኝ።ሌላው ወንድሜ፤ሻለቃ ፍስሀ ገዳ ከጥቂት ወራቶች በፊት አርፎ ሙሾ አውርጀ ነበር። ይኸኛው የሙሉ ሙሾ መሆኑ ነው።የሙሉጌታ ነገር እንዲያ የኢትዮጵያን ፍቅር በግጥም ጭመር ሲዘምርላት ኖሮ “እንደወጣ ቀረ!” የሆነውን ሰአሊውን ገብረ ክርስቶስ ደስታንና ሌሎችንም አስታወሰኝ
ሙሉ ማረፉን ወንድሜ ሻለቃ ግርማ ይልማ ከሲያትል፤ዋሽንግቶን(Seattle,Washington) ደውሎ አረዳኝ።አለም ፀሐይ ወዳጆ ከዋሺንግቶን ዲሲ (Washington,D.C)ደውላ እንዳረዳችው ነገረኝ።ግርማ ፤ሙሉጌታን፤እንደጋዜጠኝነቱ ብቻ ሳይሆን የማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበረ ጊዜ አለቃዉ፣ እዚህም በስልክ ጭምር የገኘው ነበር። አለም ፀሐይንም በሌላው ዝናዋ ብቻ ሳይሆን ባህል ሚኒስቴር የነበር ጊዜ አለቃዋ የነበረ ይመስለኛናል። የአለምን ስልክ ሰጥቶጦኝ ደውልኩላት።
Page 2 of 4
አለም ፀሐይ ገና ስላምታ ሳንለዋወጥ እሪታዋን ለቀቀችው። ያለፈ ስንትስ አመታት ዲ፤ሲአካባቢ ኗሪ ብቻ ሳይሆን ጓደኞች እንደሆኑ ለማወቅ እድል ገጥሞኝ ነበር።ለካስ እዚያ ሙሉጌታ ቤት ነበረች።አንድ አምስት ደቂቃ ያክል እንደተላቀስን የለችበትን ቤት እሪታ፤ኡኡታ እንደወረሰው፤እንደተረከበው ስልኩ ነገርኝ። አለምም ስልኩን ጣጥላ ተቀላቀለችበት።በስንት አመት የኢትዮጵያን ለቅሱ በድምጽም በመንፈስም ተካፈልኩ።ለአንድ አስራ አም ስት ደቂቃ ያክል ተካፋይ ከሆንኩ በኋላ፤አለምም ወደስልኩ ስለአለተመለሰች ዘግቼ ው ወደየግል ሐዘኔ ወረድኩ።
ሙሉን የማውቀው ድሮ-ድሮ ሳይሆን የጥንት-ጥንት መስሎ ይታየኛል።ያ የጥንት-ጥንት ደግሞ በመንፈሴ ትላንትናና ዛሬን መስሎ ይታየኛል። መሀል 1950ዎቹ ነበር የተዋወቅነዉ።ሙሉጌታ ያኔ የሚሰራው የምሥራች ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ ነበር።ለግኑኝነታችን ዋናው ሰበቡ ሁለታችንም ለአማርኛ ጋዘዜጦች በተለይም ለአዲስ ዘመን እንጽፍ ስለነበረ ነው።አራት ኪሎ፤ወይ ጳውሎስ ኞኞ ወይም ብርሐኑ ዘሪይሁን፤የአዲስ ዘመን ምክትልና ዋና አዝጋጆች ቢሮ ይመስለኛል።”ለምን የምስራች ራዲዮ ጣቢያ መጥተህ ስራ አትጠይቅም?” አለኝና ሔጄ አንድ ፈረንጅ ቃለ መጠይቅ አድሮጎ አልጣምኩትም መስለኝ ሳይሆን ቀረ። የሙሉጌታ ወንድምነት፤ጓደኝነት ጸንቶ እስከ እለት ሞቱ ኖረ። ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ ያነጋገርኩት ከመጨረሻው ቀን አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ነበር። የስልክ ወሬያችን የሚቋረጠው ወይ ባትሪው ሲሞት ወይ ሌላ አጣዳፊ ጉዳይ ሲመጣ ነበር።
አቶ ብርሐኑ ዘሪሁንና ጳውሎስ ኞኞ ሁለታችንም ወደማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዛውረን እንድንስራ ሀሳብ አቀርቡ። ተስማማንበትና ለየመስሪያ ቤቶቻችን ደብዳቤ ተጻፈ።እኔ የምሰራው ሲቪል አቪየሸን ነበር። በጥያቄውና ደባዳቤው መሠረት ሙሉጌታ ወደማስታወቂያ ሚኒስቴር፤አዲስ ዘመን፣ ተዛዉሮ ስራውን ቀጠለ። እኔ፤በዚያው አመት ዩኒቨርስቲው ስለተቀበለኝና መማርም የምፈልገው ማታ ማታ እየሰረሁ ስለነበር ጋዜጠኝነቱ አመለጠኝ።ከሙሉጌታ ጋር ግን ወዳጅነታችን ቀጠለ።
አድሮ ዉሉ ጓደኝነታችን አዲስ ዘርፍም ከፈተ።ሲመሻሽ ባንኮኒ ላይ ቢያንስ በሳምንት አንድ ሁለቴ መገናኘት የተለመደ ሆነ።በወቅቱ ከሙሉጌታ ሌላ የባንኮኒ ላይ ጓደኛችን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ መርስኤ ሐዘን አበበ ነበር።ከመርስኤን ሙሉጌታና ጋር ባንኮኒ ላይ ማምሸት ለኔ ትምህርት ቤት ነበር።ሁለቱ እየተቀባበሉ የሚፈጥሩት ራሱን የቻለ ሌላ አለም ነበር።
መርስኤ ከሁለታችንም የላቀ፣ ጠለቅና ዘለቅ ያለ የቤተ ክህነት ትምህርት የነበረው ሰው ነበር። ጫወታም አዋቂ ነበር።ይህ የቤተ ክህነት እወቀት፤ዘመናይ ትምህርትና ጫወታ አዋቂነት ባንድ ሰው ላይ ሠምረው አምረው ሲገኙ የሚፈጥረውን ለዛ ሊያዉቁ የሚችሉ አጋጣሚውን ያገኙኑና የሚያውቁ ብቻ ይመስለኛል። አንድምታ፣ ሰምንና ወርቅ፤ቅኔም ጣል ጣል ይደርግበታል።
ሙሉጌታ ከሁለታችንም፤ምናልባትም እኔ ከማውቃቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ለየት ያለ የአጨዋወት ዘይቤ ነበረው።ባንኮኒ ላይ ሆነ ከዚያ ባሻገር! ሌላው ባሕርዩ፤ሙሉጌታ የተዋጣለት አንባቢ ነበር። ራሴን አንባቢ ነኝ እያልኩ አኩራራለሁ። ከሙሉጌታ ሉሌ ጋር ግን በምኑም የሚመጥን አይመስለኝም።ሙሉጌታ ከንባቡ ያካበተው ግና የራሱ ንብረት(Internalize) ያደርገውን ጣል ጣል ሲደርገው ለጫወታው ጌጥና ፍርጥ ይሆናሉ።ይህም የሚጎንጩትን ወደ አናት ሳይሆን መዝናናኛና ጫወታ አድማቂ ያደርገዋል።ሌላው የባንኮኒ ተደርዳሪም የራሱን ጫወታ ይተውና ቀስ በቀስ ወደኛው ይጠጋል።ባለቡና ቤቶቹም ይወዱናል ይመስለኛል። ገበያቸውን ያደራለና!!ክፋቱ ጊዜ ይሮጣል!ስይታወቅ ወደእኩለ ሌሊትነት ይቀየራል!!
ሁለተኛው የሙሉጌታ ባህርይ አንዴ ማእከላዊ ወዳጄ ዘገየ አስፋው የነገረኝን አስታወሰኝ። ዘገየን፤የመሬት ይዞታ ሚኒስቴር የነበሩ አለቃው ስለዘመናይ ምሁራን ያሉትን ነበር የነገረኝ። “እናነተ የዘመኑ ወጣቶች የኢትዮጵያ እውቀታችህ ከመጽሐፍ ብቻ የተጠና ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያን በሙሉ
Page 3 of 4
አታውቋትም። ስለኢትዮጵያ ለማወቅ በየለቅሶው፤በየእድሩ፤በየተዝካሩና ክርስትናው፤ በየሰርጉ መገኘት አስፈላጊ ነው። የውስጥ ታሪኳ የሚወራው፤ማን ማንን አገባ፤ፈታ? ለምን አገባ፣ ፈታ? የሚለው ያለው እዚያ ነው” ብለዋል ነው ያለኝ። ሙሉጌታ ያለተጻፈውን ፤ወይም ተጽፎ፤ተንቆ ያልተነበበውን የኢትዮጵያ ታሪክ ያውቃል።
ራሱ ከነገረኝ በመነሳት ለማስርዳት ልሞክር። ለምሳሌ የንጉሱን ዘመን ራስ መስፍን ስለሺን ፊድዋል፣ የመሬት ከበርቴ ብቻ ብለን ነው የምናወቀው።ነበሩ!! ሙሉጌታ ግን ራስ መስፍን ኦሮሞ መሆናቸውን፤ የልጃቸው ስም ጃራ መሆኑ የአያታቸው ይሁን የቅድመ አያታቸው ስም መሆኑን፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ የሽእመቤት ጉማ ኦሮሞ በመሆናቸው ልጆቻቸው ኦሮሞ መሆናቸውን ይነገረኛል። የነገርን አጥንቱን ብቻ ሳይሆን ጉልጥምቱንም ፤የሚያይዘውን ቅባቱንም ጭምር ያውቃል።
ሌላ ምሳሌ ለመጥቀስ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ይመስለኛል ስለኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጀት (ኦነግ))በስልክ ስንወያይ የራስ ጎበና ዳጨን ነገር አነሳብኝ።። ራስ ጎበና ምንሊክ ከተዎድሮስ እስር ቤት አምልጠው ሸዋ ሲገቦ ጦር አስለፎ የተቀበሉ መሆናቸውን፤ምንሊክ ንጉስ ሲሆኑ የመጀመሪያው ራስ ሁነው የተሾሙት ጎበና መሆናቸውን፤ ያም ከምንሊክ አጎት፤ከራስ ዳርጌ የሚቀድም መሆኑን ነገረኝ። ያታሪክን፤ወይም የወጉን ሙሉ ስእል(Big Picture) የመቅረጽ ባሕይርይ ነበረው።
ሙሉጌታ ሉሌ ከሶስት ይሁን አራት ምሁራን ጋር ሆኖ ደርግ ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያና በሱማሌ መካከል ያለውንና የነበረውን ግኑኝነት ያጠና ነበር። እኔም ቢሮዬ እዚያ ስለነበር አልፎ አልፎ አዲስዋ ካፌ አብረን ቡና እንጠጣ ነበር። የዛሬ ሶስት ወርረ ገደማ ፤እኔ የረሳሁትን፤እዚያው ካፌ ከደርጉ ምክትል ሊቀ መንበር ከነበሩት ከኮሎኔል አጥናፉ አባተት ጋር የተለዋወጥነውን ነገረኝ።” ጓድ ኮሎኔል፤ እገሌ (የደርግ አባል ስም ጠርቼ) ለመሆኑ ንጉሱ የዛሬ ስንት አመት ከስልጣናቸው መውርዳቸውን ስምቷል? አልኩኝ።ምነው ቢሉ “ይኸው ዛሬም ኃይለ ሥላሴ ይሙት!!” ይላል አልኩ። ሙሉጌታ እንደሚነገርኝ ነው።ይህንን ማለቴን አስታውሳለሁ። ለአጥናፉ መሆኑን እሱ እስከሚነገርኝ ድረስ ረስቸው ነበር። “አንተ የት ነበርክ “ስለዉ “አላየኸኝምእንጅ እዚያዉ ነበርኩ”አለኝ።ሙሉጌታ የሰማውን ቋጥሮ አስቀምጦ ወቅቱን እንዲጠብቅ የሚያደርግ ታላቅ መዝገብ ቤት ነበር ።ይህንኑ፤ “ የደርግ ጓደኝኞች ነበሩት “ ብሎ እንደክስና ውቅስ Ethio American News አቀረበበት።” የአዋጁን በጆር!” እንደማለት ይመስለኛል። አብሮ ይስራ ነበርኮ!!በዚህም ላይ የንጉሱም ይሁን የደርግ የሙሉጌታ ሉሌ ወዳጅ የነበሩ ብዙ ባለስልጣናት አውቃለሁ። ሙሉጌታ ሉሌ አድማሱም ግኑኝነቱም ሰፋ ያለ ነበር።
ይህን “ሙሉጌታ ሉሌ በበዓሉ ግዳይ ውስጥ እጁ አለበት” የሚለውን የፈጠራ (Conspiracy Theory)ወሬ መስማት ብቻ ሳይሆን በድህረ ገጾች ላይ ተጽፎ አንብቤ “ምነው መልስ ብትሰጥ?” ብየው መልስም ሰጥቶጦ ነበር። መልሱ፤ አንድ ጎንደሬ ደጃዝማች ብለዋል የሚባል ጠቅሶ “ለመሆኑ ማነው የላከህ? ከአለቃው ጋር እንጅ ከተላላኪው ጋር አፍ አልካፍትም “የሚል ነበር። እንደጠበኩትም የሙሉጌታ አመላለስ ነበር!! ያም ሁኖ አይጋና Ethio American News የሚባሉ ድሕረገጾች የሙሉጌታን እረፍት ምክንያት በማድረግ ያንኑ (Recycle ) የደጋግሙታል።”ለመሆኑ ማነው የላከህ?” የሚለውን የሙሉጌታ ሉሌን መልስና የወዳጄን የፍስሐ ደስታን መጽሐፍ ቢያነቡ መዝገባቸውን ይዘጉት ነበር።
ፍስሀ ደስታ (ሌ/ ኮሎኔል)የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክርሳዊ ሪፑብሊክ ም/ፕሬዚዳንት “አብዮቱና ትዝታዬ” በሚለው መጽሐፉ ገጽ 442 ስለበዓሉ ግርማ አማሟት እስር ቤት የድህንነት ሚንስቴር ከነበረው ከኮሎኔል ተስፋዬ ጋር ያደረገውን ውይይት እንደሚከተለው አስፍሮታል፤
ከደርግ ውድቀት በኋላ በእስር ላይ እያለን ፤”በዓሉ ለምን እርምጃ ተወሰደበት?” በማለት ተስፋዬን ጠየቅኩት።እሱም” መጽሐፉ ከወጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ሻአቢያ በራዲዮ
Page 4 of 4
ጣቢያው በማስተላለፍ በሠራዊቱ ላይ ለከፍተኛ ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ይጠቀምበት ጀመር።በዚህ ምክንያትም የፖለቲካ፤የደህንነት ሠራተኞችና አዛዦች ከፍተኛ እሮሮና ተቃውሞ ስለ አስሙ በተለይ በ አመራሩ ላይ ቅሬታቸውን ስለገለጹ ነው”የሚልና መገደሉን የሚያረጋግጥ መልስ ሰጠኝ።
ሙሉጌታ ሉሌን በአይነ ስጋ አግንቸው የተጨዋወትነው ከአስር አማታት በፊት ዋሺንግቶን ዲሲን ለመጎብኘት የሔድኩ ጊዜ ነበር። አለም ፀሐይ ወዳጆ፤ሙሉጌታና ካሳ ከበደ ራት ጋበዙኝ።ግሩም ራት ነበር። ከራቱ ይልቅ እኒህን ሶስቱን ባንድነት ማግኘት ለኔ ባለዞሆኑን ሎቶሪ እጣ እንደማገኘት ነበር። አለም ፀሐይን፤መላኩ አሻግሬ ማእከላዊ ይነገረኝ ከነበረው በስተቀር ይህንን ያክል አላውቃትም ነበር።መላኩ አንስቷት አይጠግብም ነበር። ካሳ ከበደ ከሙሉጌታ ጋር የሚጋራው የነገሮች አጥምት ጉልጥምት የማወቅ ስጦትም አለው። የተዘናና ፣የሚያረካ ምሽት ነበር። “በሩን ልንዘጋ ነውና ውጡለን!” ብለውን የወጣን ይመስለኛል።አድማጭ እንጅ እምብዛም ተናጋሪ እንዳልነበርኩ ይታወሰኛል።
ሙሉጌታ ሉሌ የተዋጣለት ጽሐፊ፤ተቺ፤ገምጋሚ ነበር። በስራው ባህርይ የተነሳ ኢትዮጵያን በአብዛኛው ዞሮ ያየ ሰው ነበር። የሚጽፈው የሚያውቀውን የሚያምነውን ነበር። እምነቱ ደግሞ መሠረት ፤ጥልቀት ካለው ባህር የሚቀዳ እንጅ ከድስት የሚጨለፍ አልነበርም። የእምነቱን፤ የጽሁፎችን ምንጮች ደግሞ “ዘከመ ይቤ እገሌና እግሌ!” ብሎ ማስረጃ ምንጭ ይጠቅሳል። ከሁሉም በላይ፤ሙሉ ሰው፤ዘመናይ ሰው፣ ዘመናይ ስልጡን (Cosmopolitan)ኢትዮጵያዊ ነበር። አጣናው!!
“የማይሞት ሰው ሞተ!!” ይባላል። አባባል ነው! ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት ሁሉ ይሞታል። የተካልክም!ተተኪው ዋንኛውን ላያክልም ሊበልጥም ይችላል። ሁላችንም ተፈጥሮ ያዘጋጅልን ባቡር ተስፋሪዎች ነን። መዉረጃ ጣቢያችንን ነው የማናውቀው። በስደት ባይሆን ጥሩ ነበር!!ያ ደግሞ የአገራችን አካልና አምሳል ፣ገላጭ ባህር ሆኗል! ዋናው ነገር እንዴት ሞተ መሆን ያለበት አይመስለኝም። “እንዴት ኖሮ ነበር!” ነው። ሙሉጌታ አንገቱ ቀና አድርጎ፤ያመነበትን በግልም በአደባባይም ተናግሮም ጽፎ ያለፈ ጀገና ነው። ። እኔ ብርቱ ወንድሜን፣ ወዳጀን አጣሁ! ኢትዮጵያ አንድ ተሟጋች ልጅዋን አጣች!ጥናቱን ይስጠን!
ለልጆቹ፤ለቤተሰቡ፤ዘመድ አዝማዱ ብርቱ መጽናናትን እመኛለሁ!!

Filed in: Amharic