>
5:31 pm - Tuesday November 13, 7212

ይህ ልጅ ማን ነው [ ሄኖክ የሺጥላ ]

ትንሽ የስቃይ ታሪክ ( ምዕራፍ መጀመሪያ )

 Henok Yeshitlas brotherበዚህ ፎቶ ላይ የምታዩት ወንድሜ ነው ። ስለሺ መከተ ይባላል ። የምርጫ 1997ትን ተከትሎ የተፈጸመውን የንጹሃን ሰዎች ግድያ በመቃወም ፣ እኔና እሱ ወደ ጎንደር (አርማጮ) በ 1998 የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን ለመቀላቀል አምርተን ነበር ። በወቅቱ እንድ የኔ ቤተሰብ የሆነ ሰው ፣ ስለ ኮነሬል አለበል እና ጀነራል ታደሰ ሙሉነህ ያውቅ ነበርና ፣ ሃሳብችን ግቡን ሊመታ እንደሚችል አረጋገጠልኝ ። ወደ በርሃ የመግባቱን ነገር ግን ያቀነባበረችልን አንድ ሺ- ጉልትሽ የምትባል ሴት ነበረች ። ይህች ሴት የሶስት ልጆች እናት ስትሆን ፣ ባሏ ( እንደነገረችን ) በ 992 ምርጫ ፣ በሰበታ አካባቢ ለወያኔ የራስ ምታት ሆኖ ስለነበር ፣ አንድ ሌሊት የመኖሪያ ቤታቸውን ሰብረው እንደወሰዱት፣ በእስርቤትም ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት ህይወቱ እንዳለፈች እና አባት የሌላቸው ልጆች አሳዳጊ እንደሆነች፣ ይህን ተከትሎም የባሏን መከራ እና ሐዘን መቋቋም ስላልቻለች ፣ ልጆቹአንም ማሳደግ ስለዳገታት ፣ ወደፊትም እሷ ላይ አደጋ እንደሚደርስ ስለምታውቅ ፣ ይህንን ገዳይ ስርዓት ለመታገል እንደወሰነች እና በአዲስ አበባ የነበረው የዚያን ግዜው የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ሕቡዕ እንደመለመላት እና ወዘተ ለወንድሜ አጫወተችው ። ይህችን ሴት እንዴት እንዳገኘናት ፣ ከአዲስ አበባ ለመውጣትስ ምን ምን እንዳደረግን እና ሌሎቹን ጥልቅ ጉዳዮች እየጻፍኩ ባለው መጽሐፌ ውስጥ ስለምጠቅሰው ፣ እዚህ ጉዳይ ላይ አሁን ብዙ ማብራሪያ አልሰጥበትም ። ያለኝ መረጃ ምን ያህል ልክ እንደሆነ ባላውቅም ፣ አሁን ወያኔ እንደገደላት ሰምቻለሁ ። እውነቱ መታወቅ ስላለበት ፣ ማጣራቱን እቀጥላለሁ።

እኔና ወንድሜ በወቅቱ የዔሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ነበርን ። ይህንን ውሳኔ ስንወስን ፣ እንዲሁ በደመነብስም አልነበረም ። በይበልጥ እኔ አንድ ዩሐንስ አካባቢ ፣ በጥቅምት 1998 አመተ ምህረት በነበረው ሕዝባዊ አመጽ ፣ አስፓልት ላይ ጎማ ሲያቃጥል የተያዘ ወጣት ፣ የሚያቃጥለውን ጎማ በእጆቹ እንዲይዝ ፣ አለበለዚያ ግን በተነጣጠረበት ጥይት አናቱን እንደሚለው የነገረውን አንድ የአጋዚ ወታደር በመፍራት ፣ ከሚሞት የሚቀልጠውን ጎማ በእጆቼ ይዤ ሕይወቴን ላትርፍ በማለት ፣ እንደ እሳተ ገሞራ ፣ የቀላውን ጥቁር የቀለጠ የመኪና ጎማ በእጆቹ ሲይዝ የሆነውን በማየቴ ፣ (ልጁም ለአንድ ዓመት ተኩል ቁስሉ አልድን ብሎት እንደተሰቃየ ሗላ ላይ ሰምቻለሁ ) ፣ ሰላም በማጣቴ ፣ ይህንን ቁጭት እና እልህ ፣ ይህንን ግፉ ማስታገስ የሚቻለው ፣ እነሱ በሚመኩበት ፣ ደፋሪ ባጡበት ፣ ገፊ ባላዩበት መንገድ መሆኑን በማመኔ ( ዛሬም እምነቴ ያው ነው )፣ ወደ ጎንደር በመሄድ አርበኞች ግንባርን መቀላቀል የሚለው ሃሳብ ላይ ያለ ምንም ማቅማማት ፣ ፊርማዬን አኖርኩ ። እንደውም እውነቱን ለመናገር ፣ ለወንድሜ በመጀመሪያ ይህንን ሃሳብ የሰነዘርኩት እኔ ነበርኩ ። እንዴት እንሂድ የሚለው ጉዳይ ላይ ግን እሱ ከኔ የተሻለ ጥበብና ፣ አትኩሮት ሰጥቶ ሰራበት ። እቅዱ በሙሉ ክህሎት የተሞላበት ስለነበረ ፣ ተስማማን ።

ጉዞ ወደ ጎንደር

ከቀኑ ባንድኛው ፣ ከሆነ ቦታ ተንስተን ፣ በሆነ መንገድ ጎንደር ገባን ። መረጃውን መሸፈን አስፈላጊ ነው ። ምክንያቱም ፣ መጠቀም የሚፈልጉበት አካሎች ካሉ ፣ ምናልባት ስለሚጠቅማቸው ።
የሆነው ሆኖ ጎንደር ደረስን ፣ ለጊዜው ተራራ ሆቴል አረፍን ። ለ 22 ቀናትም በዚያ ሆቴል ውስጥ ተቀምጠናል ። በገሊላ ካፌ ቁርሳችንን እየተመገብን ፣ የጎንደር ተራራሮች ላይ ሰውነታችንን እያበሰልን ( እያጠነከርን )። ቀ 22 ቀናት ቆይታ በሗላ ፣ ወሳጃችን ከጎንደር ከተማ መጥቶ ወደ ትክል ድንጋይ ወሰደን ( እዛ ምን ተፈጠረ ፣ ምን ሆነ ፣ ምን ያህል ጊዜ ቆየን እና ወዘተ በመጥሐፌ ውስጥ ገልጬዋለሁ እና እዚህ ጋ አልገልጠውም )። ታዲያ በወቅቱ የነበረን መረጃ ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ፣ የራሱ ትንሽ መሬት ያለው ሲሆን ፣ አንዳንድ የትጥቅ እና የስንቅ ጉዳዮችን ፣ ከሱዳን መንግስት በእርዳታ መልክ እንደሚያገኝ ነበር ። አዲስ አበባ በነበርንበት ወቅት አንዳንድ መረጃዎች ለመሰብሰብ ሙከራ ብናደርግም ፣ በወቅቱ የህዝብ ኢንተርኔት በመጠቀም እንደዛ አይነት ድኅረ ገጾችን መጎብኘት አደጋ ይኖረዋል ብለን ስላሰብን ፣ የነገሩንን ብቻ አምነን ፣ ወደምንፈልገው ግንባር ለመቀላቀል አመራን ።

ታዲያ ጎንደር አብረሃ ጅራ እንደደርስን ፣ አንድ ሙስሊም ልጅ ( የሳንጃ ልጅ ነው ) ፣ በወቅቱ ኢትዮጵያ ለሱዳን ቆርሳ ልትሰጥ የወሰነችውን መሬት ፣ የቅየሳ ሥራ ላይ ተሰማሮ የሚሰራ ፣ ስለ ጉዳዩ ስንጠይቀው << አይ አርበኞች ያሉት ሱዳን ሳይሆን ዔርትራ ነው>> አለን። ትንሽም ቢሆን ስለ ዔርትራ የተጻፉ መጽሐፍት ፣ በይበልጥ ስለ ናቅፋ ጦርነት ፍንትው ያለ እውቀት ( ግንዛቤ ) ስልነበረን፣ ከምንም በላይ ደሞ ፣ የሻዕቢያ ባህሪ እጅግ የማይጨበጥ እና አሳሳች ነው ብዬ እኔ በግሌ አምን ስለነበር ለ ወንድሜ << ስሌ እኔ ተኩላ ሊበላኝ ነው ብዬ ለጅብ አላመለክትም >> አልኩት ። ይቺን ቃል ራሷን ነበር የተጠቀምኩት ። በእርግጥ እሱም እንደኔ አይነት አመለካከት ቢኖረውም ፣ ወያኔ እና ሻዕቢያ ተጣልተው ስለዚህ ምንም አንሆንም አለኝ ። << ተጣልተዋል ማለት ግን አይታረቁም ማለት አይደለም !>> አልኩት ። ትክ ብሎ ካየኝ በሗላ እሺ ምን እናድርግ አለኝ ። << በቃ እያወቅን እንሙት >> አልኩት ። ሳቅ አለና << ቢያንስ ብረት ይዘን እንሙት አለኝ !>> ። ያቺ ቃል በደም ስሬ ውስጥ ስትሰርግ ይሰማኛል ። ከዚያ ጉዳዩ ሁሉ ወያኔን ማሸነፍ ሳይሆን ፣ ታግሎ ፣ እምቢ ብሎ መሞት በሚለው ተካነው ። ሳስበው ዛሬም በዛ መንፈስ ከተዋጋን ብቻ ነው ለውጥ ልናመጣ የምንችለው ። አዲስ አበባ ለመድረስ ሳይሆን ፣ ጎንደር ላይ እምቢ ብሎ መዋጋት ፣ ጎጃም ላይ እምቢ ብሎ መዋጋት ፣ ድሬዳዋ ላይ እምቢ ብሎ መዋጋት ። ህልማችን በመልካ ምድር ተቀባ የተቀመጠች ዋና ከተማን መቆጣጠር ሳይሆን ፣ ፍርሃታችንን ድል መንሳት ነው ዛሬም አምናለሁ ። ሕዝባዊ አመጽ ያለ ሕዝባዊ መስእዋትነት የማይገኘውም ፣ ያልተገኘውም ሁሉም ታጋይ ዋና ከተማን ስለመቆጣጠር ስለሚያስብ ፣ ዋና ከተማው ሩቅ ሆኖ ነው ። ወያኔ ትግራይን ነጻ ለማውጣት ሲልም አልነበር የተዋጋው ፣ የተጋው ?

እርግጥ መሳሪያ የለንም ፣ ቀለብ የለንም ፣ ጫማ የለንም ፣ ግን ልብ አለን ። ስለዚህ ማድረግ የምንፈልገውን ( ሳይፈሩ መሞት ) ማድረግ እንችላለን ብለን ቃል ተጋባን ።

እዚህ ጋ በቢቢሲ ሰሞኑን ስለተተረከው የታሊባኖች ትግል ተከታትዬ ነበር ። እዛ ላይ ታሊባኖች በላያቸው ላይ የአማሪካን ድሮኖች እየጋለቡ ፣ እሩዝ ያመርታሉ ፣ ይጸልያሉ ፣ ያለ አንዳች ፍርሃት ፣ ያለ አንዳች መሸማቀቅ ማድረግ የሚገባቸውን ሁሉ ያደርጋሉ ። አንባቢ ሆይ ስለ አላማቸው ልክነት ወይ ልክ አለመሆን ሳይሆን መናገር የፈለኩት ፣ ስለ ቆራጥነታቸው እንደሆነ ይሰመርልኝ ። ተሰመረ ? እሺ
እና የሚፈልጉትን ነገር ለማድረግ ፣ ከሞት በላይ የቆሙ ሰለመሆናቸው ተረዳሁ ። አሜሪካንን የሚያህል ቤተክኖሎጂ ጫፍ ላይ የደረሰች ሀገር ለአመታት አልንበረከክልሽም ብለው መቆማቸው ፣ ይህ ሚዛናዊነት እና የጦርነት ኃያልነት የሚለውን ሃሳብ በዜሮ የሚያባዛ ግሩም ምሳሌ መሆኑንም ገባኝ ። ትግል ሚዛን የሚደፋው ሁሌም ወደ ቆረጡት ነው ። ምሳሌ ልጥቀስ ? ይህንንም በመጽሐፌ ላይ በስፋት ሄጀበታለሁ ፣ ስለዚህ እንደ ኪርየስ ጆርጅ ሃሳቡን ዘለልኩት !

ታዲያ ነገሮች እንዳሰባቸው አልሄዱም ። ይመጡና ይወስዷችሗል የተባሉት የአርበኞች ግንባርም ፣ በጊዜው መጥተው ሊወስዱን አልቻሉም ። ስለዚህ እዛው የቀን ሥራ እየሰራን ( ነቀላ የሚባል ፣ በመጥሐፌ ላይ ገልጨዋለሁ ) ፣ ( እጣን መፋቅ ) እና ወዘተ እየሰራን ለስምንት ወር ያህል ተቀመጥን ። ብዙ በቆየን ቁጥር ማንነታችን ሊታወቅ ሆነ ። ስለዚህ ከአብረሃ ጅራ ወደ አብደራፊ ሄድን ፣ እና እዛም እንደዚያው ።

የሆነው ሆኖ መለያየት እንዳለብን ተነገረን ( ሁለት ጸጉረ ልውጦች ) የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን ለመቀላቀል ጎንደር ገብተዋል ተባለ ።
እንደውም እርጎየዎች በነበርንበት ወቅት ፣ ከመያዝ ለጥቂት ነው የዳንነው ።

ስለዚህ ተለያየን ። ክረምት ነበር ፣ አንገረብ ም ወንዝ ሞላ ። ወንድሜ ከኔ ቀድሞ ወደ ጎንደር ( አርማጮ ) ሂዶ ነበር። በዚያን ወቅት በአርበኞች ግንባርና በወያኔ ሰራዊት መሃከል ከፍተኛ ውጊያ ተደረገ ። ከ 46 በላይ የወያኔ ሚሊሻ እና ሰራዊት ተገደለ ። ከአርበኞችም እንዲሁ ። ያን ቀን የኔን ወንድም ይዘውት ኤርትራ ገቡ ። እኔና እሱ ተላያየን ። ያን ውጊያ ተከትሎ ወያኔ ቁጥጥሩን አጠበቀ ። የኔ እና የሱ ጉዳይም ከሚስጥርነት ወደ ገሃድነት ተለወጠ ። ወደ ኤርትራ መግባት አልችልም ። አዲስ አበባም መመለስ አልችልም ። ስለዚህ መወሰን ነበረብኝ ።

ወንድሜ ኤርትራ ውስጥ ከአርበኞች ግንባር ጋ ሆኖ ለ ስድስት አመታት ከተዋጋ በሗላ ፣ ጭልጋ ላይ ሚሽን 1725 ተብሎ ( እሱ የሚሽን 17 መሪ ሆኖ እ ሲዋጋ በወያኔ ሰራዊት እንደተከበበ ሰምቻለሁ ። ይሙት ፣ ወይም ይዳን ግን ወያኔም ሊነግረን አልፈለገም ። ብዙ ጊዜ ወያኔ እንደምታደርገው ፣ በህዝባዊ ባዕሎች ላይ ፣ የተማረኩ የአርበኞች ታጋዮችን በሕዝብ ፊት ይቅርታ ሲያስጠየቁ እሱን አላየሁትም ( የኔ ግምት ይቅርታ ስለማይጠይቅ ነው ) የሚል ነው ። የሆነው ሆኖ ወንድሜን የበላው ስርዓት እኔን ሊበላ አልቻለም ። ይችል አይችል እንደሆነ ወደፊት የምናየው ጉዳይ ነው ። እንደ መረጃ እ እስከዚህ ድረስ ያለው ይበቃል ። መጽሐፉ ሲወጣ ብዙ ዝርዝር መረጃዎችን ፣ እና የተመሳከሩ ሴራዎችን እዘከዝካለሁ ።

ስለጉዳዩ በኢሳት ሬዲዮ ከመሳይ መኮንን ጋ ቃለ ምልልስ አድርገን ነበር ። ምክንያቱን ባላውቀውም ይህ ቃለ መጠይቅ ከኢሳት ላይ እንዲነሳ ተደርጏል ፣ ከኔ ልብ ውስጥ ግን ማንም ሊያነሳው ስላልቻለ ፣ ወደ መጽሐፍነት ተቀይሯል ። ጠብቁት ይወጣል !

እንደ መዝጊያ አንድ መንግስቱ የሚባል፣ በኢሳት ላይ ያደረኩትን ቃለ መጠይቅ ከሰማ/ ካደመጠ በሗላ ስልኬን ከሲሳይ አጌና ወስዶ ( ይህ ሰው አሁንም በኤርትራ ነው የሚኖረው ) ፣ ይህንን ነገር እንዳለ የኔ ወንድም ኤርትራ በነበረ ግዜ እንደነገረው ነግሮኛል ። እንደ እሱ አባባል << ስሌ አጠገቤ ሆና የምታወራኝ ነው የመሰለኝ ፣ እንደውም ሄኒን ገለዋታል ይል ነበር ለብዙ ጊዜ>> ብሎኛል ። እስካሁን አልሞትኩም ። ስሌም ራሱ ገለውት ቢሆን እንኳ አይሞትም !

ቸር እንሰንብት
ሄኖክ የሺጥላ

Filed in: Amharic