>

ሙሉጌታ ሉሌ......... [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

Ato Mulugeta Luleሰዎች ብዙ ስሞች አሉት ሲሉ እሰማለሁ፤ እኔ የማውቀው ሙሉጌታ ሉሌን ነው፤ ሙሉጌታ ሉሌንም የማውቀው በአጼ ኃይለ ሥላሴና በደርግ አገዛዞች ከማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ ከጋዜጦችና ከራድዮ ጋር አያይዤ ነው፤ በወያኔ ዘመን ደግሞ ጦቢያ በተባለውና እኔም ስጽፍበት በነበረው የሙሉጌታ ሉሌ መጽሔት ነው፤ ወያኔ በተለመደው አዳፍኔ ጠባዩ ባለሙያዎችን ከሥራ ወንበራቸው እያፈናቀለና እያባረረ የሱን መሀይሞች መትከል ሲጀምር ለሙሉጌታ ሉሌና ጓደኞቹ ባደጉበትና ባሳደጉት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቦታ አልተገኘላቸውም፤ የሥልጣኔ ሞረድ ያልነካቸውና ከጫካ የመጡ ወያኔዎች ከነሱ የሚበልጥ ሰው ሲያዩ ያማቸው ጀመረ፤ ቢቻላቸው መሥሪያ ቤቶችን ሁሉ በነሱ ስር ማድረጉ ብቻ አልበቃቸውም፤ የራሳቸው ልክ ጫጭቶ የሚያዩባቸውን ከነሱ የበለጡ ሰዎችን ሁሉ ማየትም ያቃጥላቸዋል፤ ስለዚህም ወደስደት ይገፏቸዋል፤ ሙሉጌታ ሉሌ በአሜሪካ የዚህ ዓይነት ግፍ ውጤት ነው፡፡
ሙሉጌታ በአገር ናፍቆት በጠና ታመመ፤ ሙሉጌታ በወገን ናፍቆት በጠና ታመመ፤ ሙሉጌታ ሉሌ በአሜሪካ ደህና ኑሮ እየኖረ ኢትዮጵያን መርሳት አቃተው፤ በአሜሪካ በነጻነት እየኖረ በጭቆናና በእስር ቤት የሚሰቃዩትን ወገኖቹን በአጠቃላይ፣ ጋዜጠኞችን በተለይ እያሰበ ይጨነቃል፤ በአሜሪካ ያገኘው ነጻነት በኢትዮጵያ ያጣውን ነጻነት ሊተካለት አልቻለም፤ ነፍሱ የተጠማችው የኢትዮጵያን ነጸነት ነው፤ የኢትዮጵያን ነጻነት እንደተጠማች እያለቀሰች ዐረገች፤ የኢትዮጵያ አምላክ ጩኸትዋን ይስማላት! የሌሎችንም ጩኸት ለአምላክ ታሰማ!

Filed in: Amharic