>
8:52 pm - Wednesday February 8, 2023

ከነካባው የተቀበረውን የፍትህ ሥርዓት ነፃ ለማውጣት ትግላችን አጠናክረን እንቀጥላለን! (ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

 
Blue partyኢትዮጵያ ውስጥ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ አዋጅና በሌሎችም የዜጎችን መብት የሚደነግጉ በርካታ መሰረቶች ቢኖሩም ለይስሙላ ህጋዊ ሥርዓት እንዳለ ከማስመሰልም አልፎ ለአገዛዙ ማጥቂያና መግዢያ ከመሆን ባለፈ የዜጎችን መብት እያስከበሩ አይደለም፡፡ ባለፉት 6 ወራት እንኳን ህግ እንደተቀበረች፣ በዚሁ አገዛዙ ውስጥ ተፅዕኖ ያለው የፍርድ ቤት አልፎ አልፎ የሚወስነው ውሳኔ በፖሊስ ቀጭን ትዕዛዝ ሲታጠፍ ታዝበናል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱትን ህገወጥ ተግባሮች በአንክሮ በመከታተል በየጊዜው ጩኸቱን ከማሰማቱም ባሻገር አባላቱም ጭምር የዚህ ህገ ወጥ ተግባር ተጠቂዎች በመሆናቸው በፍርድ ቤት በአጠቃላይ በህግ ላይ እየተደረገ ያለውን ጉዳይ ቀዳሚ ምስክር ነው፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ የሺዋስ አሰፋና ከእሱ ጋር በአንድ መዝገብ የተከሰሱ ፖለቲከኞችና ሌሎች ዜጎች ያለ ምንም መረጃ ቤታቸው ተበርብሮ ታስረው በማዕከላዊ፣ በቂሊንጦና በኋላም በቃሊቲ እስር ቤቶች ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት ደርሶባቸዋል፡፡ እነ የሺዋስ በእየ እስር ቤት የሚደርስባቸውን በደል ለፍርድ ቤቱ ቢያመለክቱም ሰሚ ከማጣትም ባሻገር ‹‹ችሎት ደፈራችሁ›› ተብለው ለተጨማሪ ቅጣት ተዳርገዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ያለ ምንም መረጃ የታሰሩትን ነፃ ናቸው ቢልም በካድሬ ትዕዛዝ የማረሚያ ቤቱ ፖሊስ ከእስር ቤት እንዳይወጡ በማገዱ፣ ይግባኝ ቢጠየቅ እንኳ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው መከታተል እየቻሉ በአስከፊው እስር ቤት እየማቀቁ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም መንግስት ራሱ በጠራው ሰልፍ ሰበብ ባልተገኙበት፣ የተገኙትንም በፈጠራ ክስ እየለቀመ ያሰራቸው የፓርቲያችን አባላትና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከ6 ወር በታች በማያሳስር ክስ እስከ አራት አመት ተወስኖባቸው፣ አብዛኛዎቹም አሁንም ድረስ ምንም አይነት ፍትህ ሳያገኙ በእስር ቤት እየተንገላቱ ይገኛሉ፡፡ በሰልፉ ሰበብ ከታሰሩት መካከል አባላችን ናትናኤል ያለምዘውድ 3 አመት ከ3 ወር ሲፈረድበት፣ ብሌን መስፍን፣ ማቲያስ መኩሪያ፣ ተዋቸው ዳምጤ ከ6 ወር በታች በሚያሳስር የፈጠራ ክስ ተከሰው አሁንም ድረስ ፍትህ ሳያገኙ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ እነ ብሌን በተደጋጋሚ በመከላከያ መረጃነት የሚያገለግላቸውንና አቃቤ ህግም አለኝ ያለውን የቪዲዮ ማስረጃ እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም ሊቀርብላቸው አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ ማረሚያ ቤቱ ‹‹መጓጓዧ መኪና ስለሌለን ነው›› በሚል ለምክንያትነት እንኳ መቅረብ በማይገባው ሰበብ በቀጠሯቸው እንዳይቀርቡ በማድረግ ለተጨማሪ ጊዜያት በእስር ላይ እንዲቆዩ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ አቶ አለነ ማህፀንቱ አንዱ ፍርድ ቤት በዋስ ሲለቀው በደህንነቶች እየተያዘ አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ሌሎችም የመኢአድና የአንድነት አባላት የነበሩ በተመሳሳይ የፍርድ ሂደታቸው ሆን ተብሎ እንዲጓተት እየተደረገ ይገኛል፡፡

አገዛዙ ሰማያዊን ለማዳከም በተለያዩ አካባቢዎች እየታደኑ የሚታሰሩት የፓርቲ አመራሮቻችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ህግ ተነፍጓቸው በእስር ቤት ይገኛሉ፡፡ ባህርዳር ላይ ታስረው የሚገኙ የፓርቲያችን 7 አመራሮች የ15 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ቢወስንም እንደተለመደው ካድሬዎች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሽረው በእስር ቤት እንዲቆዩ አድርገዋል፡፡ ሽዋሮቢትና ጎንደር ላይም በርካታ የፓርቲያችን አባላትና አመራሮች ለወራት የታሰሩበት ሳይታወቅ ከቆዩ በኋላ ወደ ማዕከላዊ ተዛውረው ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸው ተደርገዋል፡፡

ይህ ፓርቲውን የማዳከም የአገዛዙ ህገ ወጥ እርምጃ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ከሳምንት በፊት በአርባ ምንጭ የሰማያዊ ፓርቲ አደራጆችን፣ አባላትንና ቤተሰቦቻቸውን በሀሰተኛ ክስ እስከማሰር ደርሰዋል፡፡ ከታሳሪዎች መካከል የጋሞ ጎፋ ዞን አስተባባሪ የሆነው አቶ ሉሉ መሰለና ቤተሰቦቹ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ቤታቸው ተበርብሮ ሲታሰሩ፣ በእስር ላይ የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ የዞኑ አስተባባሪ አቶ በፍቃዱ አበበ የ65 አመት አዛውንት እናቱ እና እህቱም ታስረው፡፡ አብዛኛዎቹ የዜጎች ሰብአዊ መብት ወደሚገፈፍበትና ጭካኔ ወደሚፈፀምበት ማዕከላዊ እስር ቤት ተዛውረዋል፡፡

የፍትህ ስርዓቱ ለአገዛዙ መግዢያ፣ ፍርድ ቤትም በተራ ካድሬ የሚታዘዝ በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ በላይ ህግ ከእነ ካባዋ ተቀብራለች፡፡ ለይስሙላ የተቀመጠው ህግ እስረኞች በቤተሰቦቻቸው፣ በህግ አማካሪዎቻቸው፣ በእምነት አባቶቻቸውና በሌሎችም መጠየቅ እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ የሆኑትን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ጠቃቅሶ ቢያስቀምጥም በእውኑ ግን እነ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ተመስገን ደሳለኝ እና አሁንም በእስር ላይ የሚገኙት በርካታ አባላቶቻችንና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዳይጠየቁ ተከልክለዋል፡፡ ምግብ እንዳይገባላቸው ይደረጋል፡፡ እስር ቤቱ የሚያደርስባቸውን በደል ለፍርድ ቤት በሚያመለክቱበት ጊዜው ጨለማ ቤት ውስጥ እየታሰሩና እየተደበደቡ ነው፡፡

የፓርቲያችን አባላትና ሌሎች ዜጎች በተለያዩ ጊዜያት ያለ መረጃ ታስረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንደተያዘ አገዛዙና በስሩ የሚገኙት ሚዲያዎች ከፍርድ ቤቱ በፊት አጥፊዎች ተብለው ተፈርዶባቸዋል፡፡ ያለ መረጃ በመታሰራቸውና በመከሰሳቸው ይኼው ካድሬ የሚያዘው ፍርድ ቤት ነፃ ሲላቸውም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሶ እስር ቤት ውስጥ እያከረማቸው ይገኛል፡፡ አገዛዙ የሚደርስበትን ጫና በህግ ሥም ለማቃለልና ህግን ለመግዢያነት እንደሚጠቀምም ያለ ምንም መረጃ ታስረው መረጃ ስላልተገኘባቸው ከበርካታ ስቃይ በኋላ የተለቀቁትን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ለአብነት ከአንድ አመት ስድስት ወር በኋላ በስቃይ እስር ቤት የቆዩት የዞን ዘጠኝ አባላት እና አሁንም በፖሊስ ትዕዛዝ እስር ቤት እንዲቆዩ የተደረጉትን እነ የሺዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታና ዳንኤል ሺበሽ በታፈነው ፍርድ ቤት እንኳ ነፃ መባላቸው ለፀረ ሽብር ህጉና ሌሎች የመግዢያ ህጎችን ያጋለጠና ፍትህ እንደተቀበረች በግልፅ አሳይቷል፡፡

በአጠቃላይ ዜጎችን ያለ መረጃ አፍኖ ማሰር፣ በቀጠሯቸው አለማቅረብ፣ እንዳይጠየቁ እና ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዳይገቡላቸው መከልከል፣ በፍርድ ቤት ነፃ የተባሉ ይግባኝ ቢጠየቅባቸው እንኳ ከእስር ቤት ውጭ ሆነው መከራከር እየተገባቸው ከእስር እንዳይለቀቁ ማድረግና ሌሎችም በህገ መንግስቱና በአዋጆች አገዛዙ የደነገጋቸውን ሳይቀር መጣሱ በኢትዮጵያ ህግ ለፖለቲካው መሳሪያ እንጅ የበላይነት እንደሌለ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፡፡ አንድ ሀገር እንደ ሀገር ለመቀጠል፣ ዜጎችም ሀገር አለን ብለው ለመኖር ህግ ትልቅ ነገር እንደመሆኑ አገዛዙ ፍትህ ሥርዓቱን ለራሱ በሚመቸውና በሚጠቅመው መንገድ እየዘወረ ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ለባሰ አደጋና ስቃይ እየዳረገ እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ህጋዊ ሥርዓት እንዲመሰረትና የህግ የበላይነት እንዲከበር ሰማያዊ ፓርቲ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይህን ትግላችንን ከዳር ለማድረስ የሚመለከታቸው የፖለቲካ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ ህዝብና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ጥቅምት 24/2008 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic